ግርማ ካሳ

ሰሞኑን በሰሜኑ የሀገራችን ግዛት ጦርነት ተቀስቅሷል። አስመራም፣ አዲስ አበባም ያሉ ገዢዎች ጦርነት መደረጉን ማመን ብቻ ሳይሆን “ይሄን ደመሰስን፣ ይሄን ያህል ገደልን” እያሉ በመማጸደቅ ላይ ናቸው። ዓለም የትናየት ደርሳለች፣ ትላንናት እኛ እየረዳናቸው ነጻ የወጡ የአፍሪካ ሀገራት እንኳን የትናየት ደርሰዋል፣ እኛ አሁንም መግደልን እንደ ጀብዱ አድርገን እናወራለን።

አንዳንድ የኢህአዴግ ደጋፊዎች ከሻዕቢያ ጋር የሚደረግን ጦርነት ከአንድ የውጭ ሀገር ወራሪ ጋር እንደሚደረግ ጦርነት አድርገው ነው የሚያዩት። በኔ ዕይታ ይህ የተሳሳተ አመለካከት ነው። በሻዕቢያ እና በኢህአዴግ መካከል የሚደረገው ጦርነት ከኢትዮጵያ ህዝብ እና ከኤርትራ ህዝብ ጥቅም ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም። ጦርነቱ ፣ በዜጎች ደም የሰከሩ፣ የሁለት አምባገነን ቡድኖች ጦርነት ነው። የነርሱ ጣጣ ነው። ለጥቅማቸው፣ ለሥልጣናቸው ሲሉ የሚያደርጉት።

ምንም እንኳን ላለፉት 25 ዓመታት ኤርትራ በፖለቲካ አስተዳደር፣ በሻዕቢያ እና በህወሓት ሴራ፣ ከኢትዮጵያ ብትለይም፣ የኢትዮጵያ ህዝብ እና የኤርትራ ህዝብ ግን በመንፈስ የተለየ ህዝብ አይደለም። በታሪክ፣ በባህል፣ በስጋ፣ በኃይማኖት እርስ በርሱ የተሳሰረና የተዋለደ ወንድማማች ህዝብ ነው። እግዚአብሔር ፈቅዶና ህዝቡ በትግሉ በርትቶ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንግሥታት በአስመራና በአዲስ አበባ ቢመጡ እንደገና ተስማምቶ ሊዋሃድ የሚችል ህዝብ ነው።

ብዙዎቻችን ላለፉት 25 ዓመታት ከነበረው ፖለቲካ የተነሳ፣ ሻዕቢያን ከህዝቡ መነጠል አቅቶን፣ ሻዕቢያ ላይ ችግር ስላለብን፣ ኤርትራውያን ላይ በጅምላ እንፈርዳለን። ይህ ሌላ ትልቅ ስህተት ነው። እስቲ ስለ ኤርትራ ህዝብ ትንሽ ላካፍላችሁ። የሰማሁትንና ያነበብኩትን ሳይሆን ያየሁትንና እና ያለፍኩበትን። የአስመራ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የነበሩኩኝ ጊዜ የማስታወሰውን። (ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል ሆና የመጨረሻዎቹ የአስመራ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎች ነበርን)

ኤርትራ፣ አስመራ ሲባል ብዙ ጊዜ ወደ አይምሯችን ከሚመጡት ነገሮች ጥቂቶቹ፣ ግፈኛው ሻዕቢያ ሲሆን ሌላው ደግሞ ብዙ ጊዜ በፖስት ካርድ ላይ የምናየው፣ ዘንባባዎች በዳርና በዳር ያሉበት መንገድ በመሃከሉ የሚያልፈው፣ ፒያሳ ወይንም ኮምፖሽታቶ የሚባለውን ሰፈር ነው። በዚያ መንገድ ብዙ ኬክ ቤቶችና ቡና ቤቶች ነበሩ። ትዝ ይለኛል በአምሳ ሳንቲም አንድ ኬክና ምን የመሰለ ካፑቺኖ እናዝ ነበር። በተለይም ሲመሽ ከመብራቶቿ ጋር ከተማዋ በጣም ታምር ነበር። (በነገራችን ላይ አሁን አስመራ ያኔ የነበራት ውበት የላትም። የተንኮታኮተችና ያረጀች ከተማ ሆናለች። የቀድሞው የክፍለ ሃገር አወቃቀር ብንመለከት የትግራይ ክፍለ ሃገር ቢያንስ አራት ፣ ጎንደር ሁለት፣ ጎጃም ሁለት፣ ወሎ ሁለት ዩኒቨርሲቲዎች እያንዳንዳችው ሲኖራቸው፣ ኤርትራ የነበራት፣ እኛ የተማርንባት አንዱ ዩኒቨርሲቲ ተዘግቷል። ከከተማው ውበት ባሻገር የማልረሳውና በውስጤ የተተከለ አንድ ሌላ ነገር ቢኖር የሕዝቡ ፈሪሃ እግዚአብሔርነትና ደግነት ነበር። እስቲ አንዳንድ ያጋጠሙኝን ላጫውታቹህ።

አንድ ቀን በዮኒቨርሲቲ ውስጥ ወዳለው ካፍቴሪያ እራቴን ለመብላት እየሄድክ ሳለ ጓደኞቼ አገኙኝና «አትሄድም እንዴ?» አሉኝ። «የት?» አልኳቸው። «ንግደት» አሉኝ። ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር ያንን ቃል የሰማሁት። ጓደኞቼ ነገሩን ያውቁ ነበርና ምን እንደሆነ በኋላ አስረዱኝ። ያን ቀን በአስመራ በሰሜን ምዕራብ በኩል ቪላጆ የሚባል ሰፈር፣ የሚካኤል ይሁን የገብርዔል ቤተ ክርስቲያን አለ። (የቱ እንደሆነ አሁን አላስታወስም)። የዚያ ቤተ ክርስቲያን ታቦት የሚወጣበት ቀን ነበር። ታዲያ ቤተ ክርስቲያኗ አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎች ታቦቱ በነገሰበት ቀን ግብዣ አድርገው በአካባባው ያሉትን ሁሉ ይጋብዙ ነበር። ይሄ ሥርዓት ነው እንግዲህ ንግደት የሚባለው።

ያኔ መኪና የለንም። በእግራችን ከአንድ ሰላሳ ደቂቃ በኋላ በቪላጆ ደረሰን። አራት ተማሪዎች ነበርን። በሰፈሩ ስንሽከረከር «ኑ ግቡ» ብሎ የሚጠራን ሰው አጣን። ለካ ኑሮ በጣም ስለተወደደ እንደድሮ በየመንገዱ እየቆሙ «ብሉልን ጠጡልን» ማለት ቆሟል። «መቼም የዩኒቨርሲቲ ካፍቴሪያ ምግባችንን ትተን ባዶ ሆዳችንን አንመለስም» ብለን ወደ አንዱ ቤት አመራንና አንኳኳን። «እንኳን አደረሳቹህ?» ስንል፣ አንዲት ያኔ ወደ አርባ ዓመት የሚጠጋት እናት፣ በእጇ አንድ ሕጻን ልጅ ታቅፋ ወጣችና «ግቡ፣ ግቡ» አለችን በፈገግታ። የቤቱ በር ጠባብ ነበር። ጎንበስ ብለን ገባን። የነበረችዋን ጠረጴዛ ከበብናት። በትልቅ ትሪ እንጀራ ቀረበልን። ሴትየዋ ድስቱን አመጣችና ወጡን እንዳለ እንጀራው ላይ ደፋችው። ብዙ ጊዜም አልፈጀብንም ትሪውን ጠረግነው። ከዚያም በትላልቅ ጣሳዎች ጠላ አመጣች። ለኔ ውሃ ተሰጠኝ። ምን ልበላቹህ ምን የመሰለ መስተንግዶ ተደረገልን።

አስመራን ሳስብ፣ የአስመራ ነዋሪዎችን ሳስብ፣ ያቺን ሴት አስባለሁ። ለእግዚአብሔር ፍቅር ስትል፣ እንግዳን በደስታ የምትቀበል! ችግረኛ ናት፣ ነገር ግን ከፊቷ ውስጣዊ ሰላም ያላትና ሰውን የምትወድ ትልቅ ሴት ነበረች!! ያኔ በትግሪኛ አልነበረም ያናገርናት። «የኔ ዘር ናቸው» ብላ አልነበረም ያስተናገደችን። ነገር ግን ትልቅ ሴት በመሆኗ እንጂ።

የማያልፍ ነገር የለምና የዩኒቨርሲቲ ትምህርታችንን አጠናቀን የምረቃታችን ቀን ደረሰ። ባጽእ (ምጽዋ) በህዝባዊ ሓርነት ኤርትራ ግንባር ሥር ከወደቀ በኋላ በምጽዋና በአስመራ መሃከል ከሚገኝ አንድ የከፍታ ቦታ፣ «ግራፒ» እንለው የነበረ ከሩቅ የሚተኮስ መድፍ በየጊዜው አስመራ ከተማ ላይ ያርፍ ነበር። በዚህ ምክንያት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አስመራ መብረሩን አቁሞ ነበር። የጦር አይሮፕላን ግን ማረፉን አላቆመም። በወቅቱ ደግሞ ህወሓት በትግራይ ጥቃቶች ያደረግ ስለነበረ ከአስመራ አዲስ አበባ ያለው መንገድ ሙሉ ለሙሉ ተዘግቶ ነበር። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስለማይበርም ቤተሰቦቻችን ለምረቃችን ከአዲስ አበባ ሊመጡ አልቻሉም። ስለዚህ የምረቃ ሥነሥርዓታችን ብዙ አልጓጓንለትም ነበር። የምረቃችን ሥነሥርዓት ቀን በወንዶች ሽንት ቤት ውስጥ ትልቅ ፈንጂ ፈነዳ። ያን ሰዓት ትልቅ ድንጋጤ በዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ ለጥቂት ደቂቃዎች ተፈጠረ። ወዲያው ሻዕቢያ የደስታ መግለጫ መልዕክት ማስተላለፉ ነው ብለን ቀልደን አለፍን። ከሩቅ በሚተኮስ መድፍ በግራፒ ተምሮ በፈንጂ መመረቅ ይሉታል ይሄ ነው።

ያ ቀን ከፈንጂ ፍንዳታው ሌላ የማልረሳው፣ በጣም ልቤን የነካና ከኤርትራ ህዝብ ጋር ዘላቂ ፍቅር እንዲኖረኝ ያደረገ አስደናቂ ነገር ሆነ። ቤተሰቦቼ ከአዲስ አበባ ስላልመጡ የምረቃ ልብሴን አውልቄ ወደ ዶርሚተሪ ለማምራት እየተዘጋጀሁ ሳለ ድንገት፣ አንዲት ሴትዮ አበባ ይዘው ብቅ አሉ። ትዬ ዘይዳ ነበሩ። ትንሽ እንደቆየው ደግሞ አንዲት አሮጊት ሴትዩ ሌላ እቅፍ አበባ ይዘው መጡ። አደይ ፀሐይቱ ነበሩ። ሁለቱም አይተዋወቁም። በአራት ዓመት የአስመራ ቆይታዬ የተወዳጀኋቸው እናቶች ናቸው። ያኔ ብቻዬን የሆንኩኝ መስሎኝ ነበር። ግን ከአንድም ሁለት እናቶች እንደ እናቴ ሆነው አበባ ይዘው በምረቃዬ ተገኙ። እነዚህ ሁለት እናቶች ዶሮ አርደው ቤታቸው ድግስ አዘጋጅተው ነበር። ሁለቱም ወደ ቤታቸው እንድመጣ ፈለጉ። ግራ ገባኝ። በኋላ አንዳቸው ጋር ምሳ ሰዓት፤ ሌላኛዋ ጋር ደግሞ ሲመሽ ለእራት ሂጄ ከጓደኞቼ ጋር የተዘጋጀልኝን ድግስ ተካፈልኩ።

አስመራን ሳስብ፣ የአስመራን ህዝብ ሳስብ ትዬ ዘይዳና አደይ ፀሐይቱን አስባለሁ። እነዚህ እናቶች በስጋ እናቶቼ አይደሉም። እንደነርሱ ትግሬ አይደለሁም። እንደነርሱ የኤርትራ ተወላጅ አይደለሁም። ነገር ግን የእነዚህን እናቶች የዋህነት፣ ፍቅርና ያላቸውን ፈሪሃ እግዚአብሔር የሞላባቸው ትልቅ ሴቶች ናቸው። ደጎችና ለዘር ቦታ የማይሰጡ። እግዚአብሔር ባሉበት ቦታ ይባርካቸው።

የመጨረሻ ዓመት ተማሪ እያለን በአንድ ሃይስኩል፣ ለሦስት ወር ማስተማር ነበረብን። ባርካ ተብሎ በሚታወቅ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመደብኩኝ። የተመደብኩበት ክፍል አስተማሪ ክፍሉ በጣም ረባሽ ክፍል እንደሆነ አስጠነቀቀኝ። በጣም ፈራሁ። ነገር ግን ማስተማሩን ስጀምር አስተማሪው ከነገረኝ የተቃረነ ሁኔታ ነው ያየሁት። ተማሪዎቹ በጣም የሚያዳምጡ፣ በአክብሮት ከተያዙ ብዙ ሊሠሩ የሚችሉ ሆነው ነበር ያገኘኋቸው። አስተማሪያቸውም ብሆን ጓደኞቼም ሆነው ነበር የተለያየነው። ያኔ ከተማዋ ችግር ላይ ነበረች። እንደዚያም ሆኖ ግን ከፊታቸው፣ ከሁኔታቸው ያየሁት ፍቅርንና ደስታን ነበር።

አስመራን ሳስበ፣ የአስመራን ህዝብ ሳስብ፣ ያኔ ወርቃማ ዩኒፎርም ለብሰው የማስተምራቸውን፣ ያዳምጡኝና ሳስረዳቸው ፊቴን ያዩ የነበሩትን የባርካ ተማሪዎችን አስታወሳለሁ። እርግጥ ነው ብዙ የሚያሳዝኑ ነገሮች በአስመራ አይቻለሁ። እርግጥ ነው ከተማዋ ያኔ መለስተኛ ጦር ግንባር ነበረች። እርግጥ ነው በየጊዜው ሳይታሰብ በሻዕቢያ የሚተኮስ መድፍ ባልተጠበቀ ቦታ ያርፍ ስለነበረ ብዙ ሰዎች አልቀዋል። እርግጥ ነው በደርግ ወታደሮች የተሰሩ ብዙ ግፎች ነበሩ። ነገር ግን እንደዚያም ሆኖ፣ የህዝቡ ፍቅር አሸንፎኝ ነው የጦር መሣሪያ በተሸከመ የጦር አይሮፕላን፣ መሣሪያ ላይ ተቀምጬ ከተማዋን የለቀኩት።

አሁንም ለአስመራ ትልቅ ፍቅር አለኝ። አሁንም አስመራን ከአዲስ አበባ ቀጥሎ እንደከተማዬ ነው የማያት። አሁንም ያንን ህዝብ እንደ ህዝቤ ነው የማየው። አሁንም ኤርትራውያንን ከተቀረው ኢትዮጵያዊ እንደተለዩ ተደርጎ ሲታይ አያስደስተኝም። በዚህም ምክንያት ነው የኤርትራን መገንጠል አጥብቄ የተቃወምኩት። አሁንም የምቃወመው። ለዚህም ነው ከመረብ ደቡብ ይኖሩ የነበሩ ወደ ኤርትራ፣ ከመረብ ሰሜን ይኖሩ የነበሩ ደግሞ ከኤርትራ በግፍ እንዲባረሩ መደረጉ ትልቅ ታሪካዊ ስህተት ነው የምለው። ለዚህ ነው የባድመ ጦርነት የወንድማማቾች የርስ በርስ ጦርነት እንጂ ከውጭ ኃይላት ጋር የሚደረግ ጦርነት አይደለም የምለው።

የኢትዮጵያ ህዝብ መንቃት አለበት። የኢህአዴግ መንግሥት በባድመ ጦርነት እንዳደረገው አሁንም ኢትዮጵያውያንን ለመገበር እየተዘጋጀ ያለ ይመስላል። በኦሮሚያ፣ በጎንደር በመሳሰሉት ቦታዎች እንዳየነው፣ ህዝባችን በኢህአዴግ ታጣቂዎች የሚታረደውና የሚገደለው አንሶ፣ እንደገና ከሻዕቢያ ጋር በሚደረግ ጦርነት የሚማገድበት ምንም ምክንያት የለም። በመሆኑም ለኢህአዴግ የጦርነት ጡሩምባ ጆሮውን ይደፍን ዘንድ እመክራለሁ። ህወሓት/ኢህአዴግ ለሀገርና ለህዝብ አስባለሁ፣ ለሀገርና ለህዝብ ደህንነት እቆማለሁ የሚል ከሆነ፣ ሀገር ማለት መሬቱ ሳይሆን ህዝቡ ነውና ህዝብን መጀመሪያ ያክብር።

በሌላ በኩል ለዴሞክራሲ ቆመናል እያሉ፣ አለም በወንጀለኛነት የሚፈለገው የአረመኔው የኢሳያስ አፈወርቂን አገዛዝ መደገፍና ዕድሜውንም ለማራዘም ደፋ ቀና ለሚሉ ተቃዋሚ ነን ባይዮችም፣ መልዕክት አለኝ። የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን የሚቃወም፣ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሚነቀፍና በሻዕቢያ የተዘጋጀ ፔቲሽኖችን ኢትዮጵያውያን እንዲፈርሙ እንዳንድ እንደ ግንቦት ሰባት ያሉ ደርጅቶች የቅስቀሳ ዘመቻ መጀመራቸው በጣም የሚያሳፍር ነው። የሻዕቢያ መንፈስ በአሁኑ ወቅት የኤርትራ ህዝብ ጠላት ነው። የሻዕቢያ መንፈስ የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላት ነው። የሰብዓዊነት ጠላት ነው። ከሻዕቢያ ጎን በቆምን ቁጥር በሻዕቢያ እጅ ለሚፈሱ ደሞች ሁሉ ተጠያቂ ነው የምንሆነው። በመሆኑም ከሻዕቢያ ጋር የምናደረገውን ዳንኪራ በአስቸኳይ ማቆም አለብን።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ