TPLF. ህወሓት/ወያኔይገረም አለሙ
ከውልደቱ የተበላሸ በዕድገቱ ያልተቃና፤
እንዴት ይታረቃል አሁን በስተርጅና፤

“ይታረቃል” የሚለው ቃል ሁለት ፍቺ አለው፤ በአጭሩ አንዱ እርቅ ሲሆን፣ ሁለተኛው የጎበጠን ማቅናት፣ መስመር የሳተን ማስተካከል ወዘተ ነው። ይህ ጽሁፍ የሚያተኩረው በሁለተኛው ትርጉሙ ላይ ነው። ወያኔ ሊለወጥም ሊስተካከልም ሊታረቅም የሚችል አለመሆኑን ለማሳየት።

ወንበሩን የሚነቀንቅ እንቅስቅሴ ባጋጠመው ቁጥር ተሃድሶ የሚለው ወያኔ፤ የመጨረሻ ደረጃ የደረሰውን የህዝብ እንቢተኝነት ለመቀልበስ ያስችለኛል ብሎ ተሃድሶ ተቀምጧል።የማያዳግም ርምጃ እንወስዳለን የሚለው ማስፈራሪያም ሆነ ይቅርታ እንጠይቃለን የሚለው መለማመጥ የህዝቡን ተቃውሞ ማለዘብ ባለመቻሉ፤ ግድያውም ሆነ ማስፈራራቱ ተቃወሞውን ከማርገብ ይልቅ ይበልጥ በማባባሱ፣ ከመትረየስ ፊት ደረታቸውን ሰጥተው ሞትን የሚጋፈጡ ነጻነት የሚሉ ወጣቶች በመፈጠራቸው … ወዘተ የጨነቃቸው ወያኔዎች በጥልቀት እንታደሳለን አሉ። በ1993 ዓ.ም. በስብሰናል ካሉን በኋላ፤ እስከ ዛሬ ያቆያቸው ተሃድሶ ማድረጋቸው እንደሆነ ስለሚያምኑ ነው ዛሬም እንደትናትናው ይህን ወቅት በማስቀየሻ ስልት ሊያልፉት የህዝቡን ተቃውሞ በመደለያ ሊሸነግሉት በማሰብ እንታደሳለን ማለታቸው።

መታደስ አይከፋም፤ ነገር ግን መታደስ በሂደት የተፈጠረ መበላሸትን ለማስተካከል፣ መስመር የሳተን ለመመለስ፣ ከዓላማ ያፈነገጠን አካሄድ ለማረቅ፣ በእርጅና የመጣን ጉዳይ ለመጠገን እንጂ፤ በተፈጥሮ የሆነን ነገር ለመለወጥ አያስችልም። ወያኔ ግን ከውልደቱ የተበላሸ፣ በእድገት ዘመኑም ሊቃና ያልቻለ፤ ችግሩ ከመሰረቱ፣ ከተፈጥሮው ነውና በጥልቀትም ይሁን በምጥቀት ቢታደስ ሄዶ ሄዶ የሚቆመው የደደቢት ውልደቱ ላይ ነውና የሚያስገኘው ፋይዳ አይኖርም።

የደደቢቱ ወያኔ ስለኢትዮጵያ ያለው እምነትና አመለካከት አይደለም እኛ ኢትዮጵያውን ዓለም ስለኢትዮጵያ ከሚያውቀው ፍጹም የተቃረነ ነው። ኢትዮጵያን የመቶ ዓመት ታሪክ ያላት ሀገር አድርጎ፣ በቅኝ ገዢነት ኮንኖ፣ ህዝቡን በገዢና ተገዢ ፈርጆ፣ ራሱን ነጻ አውጪ ብሎ ወዘተ የተፈጠረ ድርጅት እንደመሆኑ፤ ቁመቱም ሆነ ወርዱ፣ አስተሳሰቡም ሆነ ድርጊቱ፣ ዓላማውም ሆነ ግቡ ለኢትዮጵያ የማይመጥን መሆኑ ነው ስረ ችግሩ። ለዚህ ደግሞ ከደደቢትም ሆነ ከቤተ መንግሥት የተጻፉና የተነገሩ ዓላማዎቹን መመርመር ሳያስፈልገን ህወሓት የሚለው መጠሪያው ብቻ በቂ ማስረጃ ይሆናል። አንድን የኢትዮጵያ ክፍል ነጻ እናወጣለን ብለው እንጂ፤ የኢትዮጵያን መንበረ ሥልጣን ጨብጠው በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለማምጣት የተወለዱ ባለመሆናቸው ነው ሃያ አምስት ዓመት ሙሉ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ተቀምጠው የደደቢት ሕልማቸውን መተው አይደለም ነጻ አውጪ የሚለውን ስማቸውን መቀየር ያልቻሉት።

ከውልደቱ የተበላሸ በዕድገቱ ወቅት ከብዙ ነገር በመማር ሊስተካከል የሚችልበት፤ አልፎ ተርፎም ሙሉ ለሙሉ የሚለወጥበት አጋጣሚ ቢኖርም ወያኔዎች ግን ለዚህ ሊበቁ አልቻሉም። የኢትዮጵያ መንግሥት መባላቸውም ሆነ ከውስጥም ከውጪም የሚገጥማቸው ተቃውሞምና የሚሰነዘርላቸው ምክር ከደደቢት ሕልማቸው ሊያለያያቸው አልቻለም። በተዓምር ያገኙትን የምኒልክ ቤተ መንግሥት በተዓምር ሊያጡት እንደሚችሉ ስለሚስያቡ አንድ ቀን ወደዛው መመለሳችን አይቀርም በሚል ይመስላል ከደደቢት ዓላማቸው የማይላቀቁት። ታዲያ በዚህ ሁኔታ ያለ ድርጅት ሲታደስ ውሎ ሲታደስ ቢያድር ምን ለውጥ ሊያመጣ ይችላል?

ወያኔዎች ሰዎች ናቸውና ሰው ደግሞ ከሕይወት ይማራልና፤ ሃያ አምስት ዓመት ሙሉ በመታደስ ያመጡት ለውጥ አለመኖሩን ተረድተው፤ የህዝቡም ተቃውሞ የማይቀለበስ ደረጃ ላይ መድረሱን ተገንዝበው አገዛዙ ባይሆንላቸውም ከሥልጣን አወራረዳቸውን ለማሳመር የሚያበቃቸው ተግባር ሊከውኑ ይችሉ ይሆናል ብሎ ለማሰብ ደግሞ፤ የምናይ የምንሰማቸው ነገሮች ለዚህ የሚያበቁ አይደሉም።

ገዳይ ሠራዊት በማሰማራት ሊጨፈልቁት ባልተቻላቸው ህዝባዊ እምቢተኝነት ተደነጋግጠው መፍትሔ ብለው ላቀዱት ድንገተኛ ውይይት ያዘጋጁዋቸው ጽሁፎች የሚያሳዩት፤ ወያኔ በራሱ ላይ መሰረታዊ ለውጥ ሊያመጣ ቀርቶ በጥልቀት ለመታደስ እንኳን ያልተዘጋጀ መሆኑን ነው። በየስብሰባቸውም ሆነ በራዲዮ፣ ቴሌቭዥንና ጋዜጦቻቸው ህዝቡ በተግባር እየኖረው ካለው ሕይወቱ በተቃራኒ የሆነ ነገር ሲነግሩት ትንሽም አያፍሩም። ከዓይንህ ይልቅ ጆሮህን፣ ከምትኖረው ኑሮ በላይ እኛ የምንነግርህን እመን ብለው ሲያዳርቁት ለከት የላቸውም። በርግጥ በየመድረኩ የሚታዩት ሰዎች የተነገራቸውን የሚናገሩ፣ ለራሳቸው ነጻነት የሌላቸው በመሆናቸው ሀፍረትም ለከትም ከእነርሱ አይጠበቅም፣ ቢታዘንላቸው እንጂ።

ወያኔ ከኢትዮጵያውያን ጋር ሊያስታርቀው የሚችል ከተፈጥሯዊ ችግሩ የሚያላቅቀው መሰረታዊ ለውጥ ሊያደርግ አለመቻሉ አከራካሪ አይደለም። ለመለወጥ መጀመሪያ ከሥልጣን ለመሰናበት መዘጋጀትና መወሰን ይኖርበታል። ይህ ደግሞ አይታሰብም፤ ሥልጣን ለወያኔ የነብር ጅራት ነውና። በመሆኑም ወያኔ መሰረታዊ ለውጥ ማድረግ ቀርቶ ተሃድሶ የሚለውንም በወጉ አያደርገውም። የወያኔ ተሃድሶ ከዴሞክራሲ ጋር ሆድና ጀርባ እንደሆነ፣ በሕግ የበላይነት እንዳላጋጠ፣ ሰብዓዊ መብቶችን እንደረገጠ … ወዘተ መቀጠል ያስችለኛል የሚለውን ጡንቻ ለማፈርጠምና ምን አልባትም የአንዳንድ የዋሆችን ልብ ለማማለል የሚያስችል ትግል ማዘናጊያና አቅጣጫ ማስቀየሻ ርምጃ ለመውሰድ ነው።

ችግሩ ከመሰረቱ፣ በሽታው ከውልደቱ ዋንኛዎቹ የበሽታው ተጠቂዎችና የችግሩ ፈጣሪዎችም የደደቢቶቹ ሆነው ሳለ፤ አዲስ አበባ ከደረሱ በኋላ የተቀላቀሉትንና በእምነታቸው ሳይሆን በአገልጋይነታቸው ተመርጠው ለሹመት የበቁትን በተሃድሶ ስም የጭዳ ዶሮ በማድረግ መፍትሔ እንደማይገኝ ደጋግመው ያዩት ቢሆንም፤ ዛሬም ያንኑ ለማድረግ እንደተዘጋጁ ነው የሚያሳዩን። ድርጅቱ መሰረታዊ ለውጥ ማድረግ እስካልቻና ዋናዎቹ የችግሩ ስረ መሰረቶች እስካልተነኩ ድረስ፤ አዲስ መጤዎችን በመለዋወጥ ለውጥ አይመጣም። አዲስ ተሹዋሚዎቹ ወደ ታመመ ቤት ነውና የሚገቡት ሹመት ያዳብር ተብለው ሳያበቁ ነው በበሽታው የሚጠቁት። አስተማማኙ መፍትሔ ቤቱን በሚገባ ማጽዳት ቢሆንም ይህ መሰረታዊ ለውጥ ስለሚጠይቅ አይታሰቤ ነው።

ከወያኔ ተሃድሶ ለሀገርና ለህዝብ የሚበጅ ጠብ የሚል ነገር የለም ስንል ትናንት የተፈጸሙትን በማስታወስ ብቻ አይደለም። ዛሬም እየሆነ ያለው ለመታደስ መዘጋጀትን የሚያሳይ ባለመሆኑ እንጂ። ወያኔ መሰረታዊ ለውጥ ማድረጉ ቀርቶ፤ ከምር ለመታደስ የተዘጋጀ ቢሆን፤ ከደደቢት ዓላማው ጋር የማይጣረሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ የራስ ዳሽንን ተራራ በትግራይ ክልል እንደሚገኝ አድርጎ የሚያሳየውን መጽሐፍ ከመሰረዝና ይቅርታ ከመጠየቅ ዘለል ያለ የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችል ዝግጁነትም ድፍረትም በኖረው ነበር። ነገር ግን ተሃድሶው ጡንቻውን ለማጠናከር እንጂ ለህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ ለማስገኘት ባለመሆኑ ስለ ተሃድሶ እያወራም ከጥፋት ተግባሮቹ አልተቆጠበም። እንደውም የሚፈጽመው ከነበረው የባሰ ከቀደመው የከፋ ነው።

የቂሊንጦ እስር ቤት ቃጠሎ በራሱ ብዙ የሚያስብል ሆኖ፤ ልጃችሁ በቃጠሎ ሞተ ያሉትን አስክሬን ለቤተሰብ ሰጥተው ሳጥን ከፍታችሁ እንዳታዩ ብለው መከልከላቸውን፣ ከዛም አልፎ የአስክሬኑ ግብአተ መሬት እስኪፈጸም ድረስ በወታደር አስጠብቀው ማስቀበራቸውን፣ ነቀምት ላይ ልጃውን ገለው አስክሬኑ ላይ አንበርክከው የደበደቡዋቸው እናትን ድምጽ እንባችንን እየታገልን የሰማነው በጥልቀት መታደስ እንደሚያስፈልገን ተረድተናል ካሉን በኋላ ነው። እነዚህና ሌሎችም ያልተቋረጡት ኢሰብዓዊ የሆኑ አረመኔ ድርጊቶች ስህተቴ ገብቶኛል ጥፋቴን አውቄአለሁ፤ ስለሆነም በጥልቅ ተሃድሶ ራሴን አርማለሁ በሚል ኃይል ሳይሆን፤ በጠብ-መንጃው የሚተማመን ምን ታመጣላችሁ ብሎ ህዝብን የናቀ መንግሥት የሚለው መጠሪያ የማይገባው በጉልበቱ አዳሪ የሚፈጽሙ ናቸው። ታዲያ ከእንዲህ አይነቱ ኃይል ምን የተሃድሶ ውጤት ይጠበቃል፤ እነዚህ ሰዎች ከሚያዘጋጁት የውይይት መድረክስ ምን ለሀገርና ለወገን የሚበጅ ነገር ይገኛል?

በህዝብ እንዳልተወደደና እንዳልተፈለገ ያወቀና በሥልጣን መቆያ ብቸኛ መንገዱን ኃይል ያደረገ ማናቸውም አንባገነን የሚያደርገውን ነውና ወያኔዎች የሚያደርጉት፤ ሊደንቅም ሊገርምም አይችልም። የሚገርመው የወያኔዎችን ውልደትና እድገት፣ በተለይም የሃያ አምስት ዓመታት የመንግሥትነት ቆይታ የማያውቁ ይመስል ተሃድሶ ሲባል ወያኔ የሚለወጥ፣ ውይይት ሲባል የሚነገረውን ሰምቶ የሚያርም ይመስል፤ ልባቸው የሚንጠለጠል ሰዎች ያውም ከተቃውሞው ጎራ መኖራቸው ነው።

የኀዘንም ሆነ የደስታ፣ የብሶትም ሆነ የቁጭት … ወዘተ ስሜቱን በዘፈንም ሆነ በቀረርቶ የሚገልጸው የሀገሬ አርሶ አደር “ይሄ የቆላ ሰው ዛቢያ መቁረጥ ያውቃል፤ ካልተለበለበ መቼ ይታረቃል” ይላል። በመግቢያው ላይ እንደተገለጸው ይታረቃል የሚለው ቃል ሰምና ወርቅ ነው።

ሰሙም ሆነ ወርቁ አልያም ከሁለት አንዱ ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው ህዝባዊ እምቢተኝነቱ ተጠናክሮ ሲቀጥል፤ ፖለቲከኞቻችንና ምሁራኖቻችን የየግል ፍላጎታቸውን ገትተው፣ የርስ በርስ ንቁሪያቸውን ከልተው፤ ከራስ በላይ ሀገርና ህዝብ በማለት የቀደማቸውን ህዝብ በመከተል ለትግሉ መጠንከር፣ ለድሉም የሰመረ መሆን መሥራት ሲችሉ ነው። ከወያኔ ተሃድሶ ቁም ነገር መጠበቅ ግን የወያኔን ውልደትና እድገት መዘንጋትና ከእባብ እንቁላል ርግብ መጠበቅ የሚሉት መሆን ብሎም እስካሁን ከሆነው ለሚከፋው አገዛዝ ራስን ማዘጋጀት ነው።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ