ይገረም አለሙ

Jawar Mohammed

መንደርደሪያ

ጃዋር የኦሮምያን ቻርተር እያዘጋጀን ነው በማለት የተናገረው ዋንኛ የመነጋገሪያ ብቻ ሳይሆን፤ የመነታረኪያም ርዕሰ ጉዳይ ሆኗል። ከሚያግባባን ይልቅ በሚያለያየን ላይ ጎራ ለይቶ የመነታረካችን አንዱና ዋናው ጉዳይ ወይ ከዚህ ወይ ከዛ የሚለው መሃል ላይ ቦታ የሌለው ወይንም የማይሰጠው ፖለቲካችን ነው። ሁለተኛው ችግራችን ደግሞ ድጋፋችን ነፋስ አይንካህ የሚል ነቀፌታችን መልካም ጎኖችን የማይመለከት መሆኑ ነው። ይሄ በፍጹም አይበጅም የምንወደውንና የምናደንቀውን ልንተቸውም ሆነ ልንመክረው፤ የማንወደውንና የማንደግፈውን ደግሞ ብዙ ስንነቅፈው ለበጎ ሥራው በትንሹም ቢሆን ጎሽ ልንለው ይገባል። ነቀፌታም ሆነ ትችታችን ወደ መሃል የሚጎትት እንጂ ወደ ዳር የሚገፋ መሆን የለበትም፤ ከስህተት ለመማር ከጥፋትም ለመቆጠብ የሚያበረታታ እንጂ፤ ጥላቻን የሚያስፋፋና እልህ ውስጥ የሚያገባ መሆን አይኖርበትም።

ትንሽ ምክር ለጃዋር፤

ብዙ ተከታይ፣ ብዙም አድማጭ አለኝ ብሎ የሚያምንና የህዝብን ትግል እየመራሁ ነኝ የሚል ሰው ቀርቶ፤ ማናቸውም በመገናኛ ብዙኃን ብዙ የሚናገርና የሚጽፍ ሰው፤ ረጋ፣ ሰከን ብሎ በስሜት ሳይሆን በእምነት ላይ ተመስርቶ፤ በሞቅታ ሳይሆን በአስተውሎት ሊሆን ይገባል። ደጋፊን ለማስደሰት ተብሎ ተቃራኒን ይበልጥ ማስቆጣት በአንጻሩ ተቃዋሚን ላለማስከፋት ተብሎ ደጋፊን ማስኮረፍ እንዳይመጣ ጥንቃቄ ያስፈልጋል። መሰረቱ እምነት የሚነገረውም እውነት ከሆነ ደግሞ እንዲህ ያለው ችግር ብዙም አይገጥምም።

ስለሆነም ጃዋር በየንግግሮችህ ወጣትነት ሲደመር የደጋፊ ጭብጨባና ሙገሳ የሚፈጥረው ስሜት ይንጸባረቅብሀል። አንተም የምትመኘው ደጋፊዎችህም በስስት የሚያዩህና የሚጠብቁህ ለትልቅ ደረጃ መድረስን ነውና፤ ለዛ ትበቃ ዘንድ ወጣትነቱንም የደጋፊ ጭብጨባ የሚፈጥረውንም ስሜት በመቋቋም ሰከን በል። በዙሪያህ ካሉ የዕድሜም የእውቀትም ታላላቆችህ ተማር ተመከር። ስትናገርም አትፍጠን። በፍጥነት መናገር የእምነት ሳይሆን የስሜት ቃላቶች እንዲያፈተልኩ በር ይከፍታል።

ለጃዋር ደጋፊዎች፤

ትናንትም ያየነው ሆነ፤ ዛሬ የምናየው አንድን ሰው ወደውና አድንቀው የሚደግፉ ሰዎች ነፋስ አይንካው ባዮች ይሆናሉ። ስህተቱም ሆነ ጥፋቱ አይታያቸውም። በሌሎች ሲነገርና ሲጠቆምም ለመቀበል አይደለም ለመስማት ፈቃደኛ አይደሉም። እንደውም የቃላት አረራቸውን ታጥቀው፤ የስድብ ጎራዴያቸውን መዘው በተከላካይነት ይሰለፋሉ። በዚህም ስህተቱን እያረመ ጉድለቱን እያሟላ ቀስ ብሎ አድጎ ለቁም ነገር ሊበቃ ይችል የነበረውን ሰው በአጉል ጭብጨባና ውዳሴ መሬት ይለቅና መጨረሻው “ልቤ አደገና አለ ቁመቴ፤ አላስገባ አለኝ የገዛ ቤቴ” እንደሚባለው ይሆንና አዬ! የት ይደርሳል የተባለው ሰው ለመባል ይበቃል። በዚህ ሁኔታ ብዙ ሰዎችን አጥተናል፤ ጃዋርንም እንዳናጣው፤ አድናቂው ነን ደጋፊው ነን የምትሉ ድጋፋችሁ እየኮተኮተ የሚያሳድገው፣ እያረመ ለቁም ነገር የሚያበቃው እንጂ በአጭር የሚያስቀረው እንዳይሆን ብታስቡበት መልካም ይመስለኛል።

ለጃዋር ነቃፊዎች፤

የትችትና የነቀፋ ባህላችንም፣ ልምዳችንም በአብዛኛው ከድጋፍ አሰጣጣችን ጋር ተመሳሳይ ነው። ስንደግፍ ስህተት ድክመት እንደማይታየን ሁሉ፤ ስንነቅፍም መልካም ጎኖች አይታዩንም። ስለሆነም ነቀፌታችንም ሆነ ትችታችን፣ ተቃውሞአችንም ሆነ ምክራችን ወደ ዳር የሚገፋ እንጂ ወደ መሃል የሚጎትት፤ የሚያራራቅ እንጂ የሚያቀራርብ፣ ይበልጥ እልህ የሚያስገባ እንጂ የሚያለዝብ አይደለም። ስለሆነም ይህ ነገረ ሥራችን እስካሁን እንዳልበጀን ሁሉ፤ ለወደፊቱም አይበጀንምና ትችታችንም ሆነ ነቀፌታችን እስከ ዛሬ ከመጣንበት መንገድ ወጣ ቢል መልካም ነው። የትናንቱ ካልበጀን ዛሬም በዛው መቀጠሉ ለምን!?

ወደ ጃዋር ስንመጣ፤ ወጣትነቱ፣ ብሔረተኝነቱ፣ የደጋፊዎች ጭብጨባና ሙገሳው (የማናውቃቸው ሌሎች ምክንያችም ካሉ) ተደማምረው ሃሳቡ ተለዋዋጭ ቃላቶቹ ሸንቋጭ ቢያደርጉትም፤ አትኩሮቱ ኦሮሞና ኦሮምያ ላይ ቢሆንም፤ በማይታበል ሁኔታ እየሠራ ነው። ለዚህ ልጅ የሚሰነዘሩ ትችቶችና ነቀፌታዎች፤ ድክመቱን እያረመ ጥንካሬውን እንዲያጎለብት የሚያግዙት ቢሆኑ፤ ኦሮሞነቱ ላይ ይበልጥ እንዲጣበቅ የሚያደርጉት ሳይሆን ወደ ኢትዮጵያዊነት እልፍኝ የሚስቡት ቢሆኑ፤ ለመሸናነፍ ሳይሆን ለመተቃቀፍ የሚያበቁ ቢሆኑ፤ ለጃዋር ብቻ ሳይሆን ነገ ልናያት ለምንሻው ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ግንባታ ይበጃል።

ጃዋርን በልኩ አለማየት፤

ጃዋር የፖለቲካ ድርጅት መሪ አይደለም፤ እሱም ነኝ ብሎ አያውቅም። የፖለቲካ ድርጅት መሪ ባልሆነበት ቀርቶ ቢሆን እንኳን አንድ ብቻውን በኦሮሞ ጉዳይ ወሳኝ ሊሆን አይችልም። ታዲያ እንዴት ነው ከእሱ ንግግር ቃላት እየመዘዝን የኦሮሞዎች አቋም ፍላጎትና አምነት ይሄ ነው ብለን በድፍረት የምንጽፍ፣ የምንናገረው። ይህ ሁኔታም ጃዋር ራሱ ሳያውቀውና ሳይዘጋጅበት ራሱን ብቸኛ የኦሮሞ ፊት አውራሪ አድርጎ ራሱን እንዲያስብ እያደረገው ይመስላል። የሌሎቹ የኦሮሞ ምሁራን፣ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችና አዛውንቶች መልካም ሃሳብና ሀገራዊ ራዕይ ትኩረት ሳያገኝ፤ የአንድ ጃዋር ንግግር ገኖ ይወጣል፤ የኦሮሞ ሁሉ ሃሳብና እምነት እንደሆነ ተደርጎ ይስተጋባል። ለምን?

ብዕር ከማንሳት ጠይቆ መረዳት፤ መረዳዳት ቢቀድም፣

ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነውን ንትርክ የፈጠረው የኦሮምያ ቻርተር መዘጋጀት በጃዋር በተነገረበት ሰሞን፤ ሳዲቅ አህመድ በራዲዮ ጣቢያው ጃዋርን ከፕ/ር ህዝቅኤል ገቢሳ ጋር ጋብዞ ቃለ ምልልስ አድርጓል። ፕ/ሩ የኦሮሞ ቻርተር የሚባል ነገር አልሰማሁም አላውቅም ነው ያሉት። ከዛ በኋለም የሰጡት ገለጻም በየትኛውም ወገን በተሰለፉ ሰዎች ሊነቀፍ የማይችል፤ በጥቅሉ ዕጹብ ድንቅ የሚባል ነው። ነገር ግን ጥሩ አይደለም ያልነው ላይ መረባረብ እንጂ፤ ጥሩውን ማድነቅና ማበረታት አልታደልንምና የፕ/ሩን ንግግር እንደዋዛ ሰምተን አልፍነው፤ የጅዋርን ንግግር እንወቅጣለን። ለምን? የሚያለያዩ ነገሮችን እያነፈነፉ ከማሳበጥና ከመለጠጥ ጃዋርንም ከሚገባው ቦታ በላይ አልቆ ከማስቀመጥ በሚያስማሙ ነገሮች ላይ ማተኮሩ አይበጅምን።

ስለ ጃዋር ቻርተር ከፕ/ር ህዝቅኤል ገቢሳ ከተረዳሁት በመነሳት ሁለት ጥያቄዎች ላንሳ። የመጀመሪያው አንድ አክቲቪስት ጃዋር የኦሮምያ ቻርተር እያዘጋጀን ነው ሲል ተጣድፎ ይሄው ኦሮሞዎች እንዲህ ናቸው ብሎ ከመናገርና ከመጻፍ፤ በርግጥ የተባለው እውነት ነው ወይ? ከሆነስ ዓላማና ይዘቱ ምንድን ነው? ብሎ ሌሎች የኦሮሞ ፖለቲከኞችንና ምሁራን መጠየቅ አይሻልም ነበርን?

ሁለተኛው ጥያቄየ እንደ ፕ/ር ህዝቅኤል ገለጻም ሆነ እንደ ራሱ ማስተባበያ ሌሎች በተረዱት ደረጃ የተዘጋጀም ሆነ የሚዘጋጅ ቻርተር የለም። ይህ በሆነበት ሁኔታ ከጃዋር ንግግር ብቻ በመነሳት፤ እሱን የኦሮሞ ብቸኛ ወኪል አድርጎ መውሰዱና ከግራ ቀኝ ሳያጣሩ የኦሮሞዎች ፍላጎት ይሄ ነው ብሎ፤ የአንድ ጃዋርን የስሜት ንግግር የመላው ኦሮምያ ሃሳብና እምነት እንደሆነ አድርጎ ማቅረብና ክርክር መክፈት፤ ለምንፈልገው ኢትዮጵያዊነት መጎልበት የሚበጅ ነው ወይ? ማናቸውም የምንሠራውም ሆነ የምንጽፈውና የምንናገረው ነገር ሁሉ አሁን ህዝቡ በተግባር ለተያያዘውና መስዋዕትነት እየከፈለበት ላለው የነጻነት ትግል መጠናከር የሚረዳ ቢሆን ነው የሚሻለው፤ በጥላቻ፣ በስሜት፣ በፉክክር፣ ወዘተ የምንሠራው ሥራ የነጻነት ትግሉን ይጎዳል፤ በድል ማግስት የሚታሰበውን ለሁሉም ልጆቿ እኩል እናት የሆነች ኢትዮጵን የማየት ምኞታችንን ያጨናግፋል። እናም ከራስ በላይ ሀገር ብለን አናስብ።

ሁሉም የየራሱን የቤት ሥራ ቢሠራ

ከፕ/ር ህዝቅኤል እንደሰማሁትና እንደተረዳሁት፤ የተዘጋጀው የኦሮሞ ኮንፈረንስ ዋና ዓላማ የተለያየ ዓላማ የሚያራምዱ ግን በኦሮሞ ስም የተደራጁ ፓርቲዎች፤ ከወያኔ በኋላ ምን አይነት ኢትዮጵያ በሚለው ላይ ተነጋግረው አንድ ስምምነት ላይ በመድረስ፤ ከሌሎች ጋር ለመነጋገር የሚያስችላቸውን አቋም ለመያዝ ነው። ይህ ለእኔ ተገቢ እንደውም የዘገየ ተግባር ነው። ሌሎችም በአንድ ብሔር ስም ከአንድ በላይ ሆነው የተደራጁ ይህን መሰል ተግባር በአፋጥኝ ሊጀምሩ ይገባል። እስቲ ይታያችሁ ሁሉም የቤት ሥራውን ሳይሠራ ሀገራዊ ጉባዔ ላይ ቢገናኝ ምንድን ነው የሚሆነው። በብሔር የተደራጁ ፓርቲዎችን ልዩነት ለማስታረቅ ይመክራል ወይንስ ለሀገራዊው ችግር መፍትሔ ፍለጋ ላይ። በአንድ ብሔረሰብ ስም ተደራጅተው ግን የተለያየ ዓላማ ያላቸውን ኃይሎች ወደ አንድ መስመር ሳያመጡ በሀገራዊ ጉዳይ ላይ ለመምከርስ ቀና ይሆናል። እኔ አይመስለኝም።

ስለሆነም ከምር ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ማየት የምትናፍቁ ከሆነ ከወያኔ በኋላ ምን አይነት ኢትዮጵያ ለሚለው በግልም በጋራም የቤት ሥራችሁን ሥሩ። ሠርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ አይጠቅምም። ስለሆነም፤

1. በአንድ ብሔር ስም ከአንድ በላይ የተደራጃችሁ እንወክለዋለን የምትሉት ብሔር በነገዋ ኢትዮጵያ ምን ይፈልጋል፣ ምን አይነት ኢትዮጵያን ማየት ይሻል፣ ያ እንዴትና በምን ሁኔታ ተግባራዊ ይሆናል፣ … ወዘተ የሚል የጋራ ስምምነት ላይ መድረስ አንድ ሰነድ ማዘጋጀት፤

2. በብሔር የተደራጃችሁ በሙሉ በዓላማ ብትለያዩም ከምትመሳሰሉበት ብሔረተኝነት አንጻር ስለ ነገዋ ኢትዮጵያ እንዴትነትና ምንነት መክራችሁ ዘክራችሁ ስምምነት ላይ መድረስ የጋራ ሰነድ ማዘጋጀት፤

3. ሀገራዊ አደረጃጀት ያላችሁም እንዲሁ የትግል ስልታችሁም ቢለያይም በአላችሁ ኢትዮጵያዊ ዓላማ ተጠራርታችሁ ሸንጎ በመቀመጥ ከወያኔ በኋላ ኢትዮጵያን ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማብቃት በሚያስችሉ መንገዶች ላይ ተነጋግራችሁ አንድ ሰነድ ማዘጋጀት፤

4. የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ በፖለቲከኞች ብቻ እንዲወሰን መተው አይገባምና (ጉዳቱን አይተነዋል) ምሁራንም በየፈርጁ በመጠራራት ኢትዮጵያን ለዴሞክራሲያዊ ሽግግር በሚያበቁ ጉዳዮች ላይ በስፋት በመምከር አንድ ሰነድ ማዘጋጀት።

በእንዲህ ሁኔታ አስቀድሞ ሥራው ቢከናወን ከድል በኋላ ያለውን መንገድ ጨርቅ ያደርገዋል ብቻም ሳይሆን፤ እስከ ዛሬ በየለውጡ እንደገጠመን የአንድ ወይንም የጥቂት ድርጅቶች የፖለቲካ ፕሮግራም የሽግግር ቻርተር የመሆን ዕድል አይኖረውም። ስለሆነም ሽግግሩ የሰመረ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው በጠንካራ መሰረት ላይ የቆመ ይሆናል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!