እማማ አለብላቢት - የዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ነቀርሳ
ሸንቁጥ አየለ
በገጠሪቱ ኢትዮጵያ በአንድ ሰፈር ይኖሩ የነበሩ፣ እማማ አለብላቢት የሚባሉ ሴትዮ አጭር ታሪክ እና የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ሥነልቦናን ትስስር ሁሌም ይገርመኛል። የሰፈሩ ልጅ ሁሉ እማማ አለብላቢት ብሎ ይጠራቸው ስለነበረ ታሪካቸውን በዚሁ ስማቸው እንተርከዋለን።
እማማ አለብላቢት በሰፈራቸው ውስጥ የሚደረግ ማንኛውም ነገር አይጥማቸውም። አንድ ሰው አዲስ ልብስ ለብሶ ቢወጣ "ኤዲያ" ብለው ያጣጥሉበታል። አንድ ሰው በሬ ቢገዛም ያጣጥላሉ። ሌላው ሚስት ቢያገባ ወይም ልጅ ቢወልድ ያጣጥሉበታል። ሠርግ እንኳን ተጠርተው እንዲበሉ እንዲጠጡ ተጋብዘው ሳለ የርሳቸው ዋና ሥራ ሠርጉን ማጣጣል ነው። "ኡ ኡ እቴ ...!" ብለው ጀምረው ሁሉንም አሉታዊ ቃላት ያዘንቧቸዋል።
እማማ አለብላቢት እግዚአብሔር ውብ አድርጎ የፈጠረው የሰው ልጅ ውበት አይማርካቸውም። ያንድም ሰው ውበት ሲያደንቁ ተሰምተው አያውቁም። ሴትም ሆነ ወንድ ወይም ህጻን ልጅ ሲያደንቁ አይታወቁም። ከዚያ ይልቅ ሲያጣጥሉ ብቻ ነው የሚታወቁት። በጣም ሰውን ሁሉ የሚያናድደው እና የሚያስገርመው ታዲያ፤ እማማ አለብላቢት ለራሳቸው ውበት እና ለራሳቸው ነገሮች ያላቸው ክብር እና ፍቅር ነው። እሳቸው የሚፈልጉት መወደስ እና መወደድ ብሎም መከበር ብቻ ነው። የሚደንቀው ታዲያ፤ አንዳንድ ፈሪ እና ሰነፍ የሰፈር ሰዎች እማማ አለብላቢትን ስለሚፈሯቸው እሳቸው የሚፈልጉትን ሁሉ አድናቆት እና ሙገሳ ሁሉ ይሰጧቸዋል።
እማማ አለብላቢት ልጅ የላቸውም። ልጅ ያለውም ሰው አይወዱም። እናም አንድ ጊዜ እንዲህ ሆነ። አንዲት አይነስውር ሴት በልመና እየተዳደረች ልጅ ወለደች። እማማ አለብላቢትም በአደባባይ ሴትዮዋን ሰደቡ። ተራገሙ። ዲቃላ ከመንገድ አርግዛ በልመና እየተዳደረች ልጅ ወለደች ሲሉ ለያዥ ለገራዥ አስቸግረው ድሃይቱን ሲሳደቡ ኖሩ። የሆነ ሆኖ በመጨረሻው የዕድሜ ዘመናቸው እማማ አለብላቢት ወደ ጎዳና ወጡ። ልመናም ጀመሩ።
የዚያች የአይነስውር ልጅ ግን አድጎ ሀብታም ገበሬ ሆኖ ነበር እና አዝኖ ሊጦራቸው ከናቱ ጋር አንድ ቤት እንዲኖሩ አደረጋቸው። እማማ አለብላቢት ግን የለመደባቸው ባህሪ አለቃቸው ብሎ ጠዋት እና ማታ ብድግ እያሉ ጎበዙን ገበሬ እና አይነስውር እናቱን በስድብ ማጥረግረጋቸውን ቀጠሉ። "እናንተ ለማኞች ደግሞ እናንተ ብሎ ሰው አስጠጊ" ብለው ጀምረው ሁሉንም የስድብ ከረጢታቸውን ፈትተው በእናት እና በልጅ ላይ ይደነፉባቸዋል። እማማ አለብላቢት ክፉ፣ ሸፍጠኛ፣ ምቀኛ፣ ሐሰትን በእውነት ለመለወጥ ወደኋላ የማይሉ እና ቡድነኛ ናቸው። ከሁሉም በላይ መለያቸው ግን እኔ ብቻ የሚለው መርኀቸው ነው።
እናም ብዙ ጊዜ ወደ ፖለቲካው ጠጋ የሚሉ ቀላል ቁጥር የሌላቸው ሰዎቻችን ዓላማ ግራ ያጋባል። ቀላል ቁጥር የሌለው ፖለቲከኛ ለመሪነት ካለው ጉጉት የተነሳ ልክ እንደ እማማ አለብላቢት አብሮት ሊታገል የተነሳውን ወንድሙን አፈር አቅሞ ያጣጥለዋል። አገራዊ መቻቻል፣ አገራዊ እውነት፣ አገራዊ ዲሞክራሲ እና አገራዊ የጋራ ብልጽግና ገደል ይገቡ። ሸፍጥ፣ ጥላቻ፣ ማግለል እና ሌላውን ማኮስመን ይቀጥላል ብሎ የተነሳ የሚመስለው የፖለቲከኞቻችን ቁጥር ብዙ ነው። አንዱ አንዱን የለህም ብሎ ይጀምር እና እንደውም ሕዝብ እውቅና አልሰጠህም፣ በሕዝብ የምታወቅ እኔ ብቻ ነኝ ሲል እርሱ እውቅና ሰጭ እና ነሽ ይሆናል።
ከሁሉም የከፋ ደግሞ በየቡድኑ ውስጥ አንድ ነን ሲሉ የነበሩ ሰዎች እርስ በርስ ይበላሉ እና ሁሉም እኔ ብቻ ሲሉ እራሳቸውን አንግሠው ቁጭ ይላሉ። የሚያሳፍረው ደግሞ እማማ አለብላቢት ሰፈር ውስጥ ያሉ ፈሪ እና ሰነፍ ሰዎች ለእማማ አለብላቢት እውቅና እና ሙገሳ ይሰጡ እንደነበሩት ሁሉ ከሕዝቡ መሃልም አንዳንድ ሰነፎች ድምጻቸውን ከፍ አድርገው የእማማ አለብላቢት ሥነልቦና ለተላበሱ ፖለቲከኞች አስገራሚ እና አሳፋሪ ውዳሴ ያቀርቡላቸዋል። ፖለቲከኞቹም ያኔ ልባቸው እንደ እማማ አለብላቢት ያብጣል።
የኢትዮጵያ ትግል ትናንትም ሆነ ዛሬ አንድ አይነት ባህሪ አለው። በኢህአፓ ዘመን ከደርጎች ጋር የተደረገው ትግል፣ በደርጎቹም ከንጉሡ ጋር የተደረገው ትግል፣ በወያኔ ከደርግ ጋር የተደረገው ትግል እንዲሁም አሁን ባሉት ተቃዋሚዎች ሁሉ ከወያኔ ጋር የሚደረገው ትግል አንዱ እና ብቸኛው የጋራ መገለጫው እፖለቲከኞቻችን ውስጥ የተወሸቀው የእማማ አለብላቢት ሥነልቦና ነው። ”እኔ ብቻ!” ሌላው ባዶ እና ዜሮ። ሌላው የለም። ሌላው መኖር የለበትም። እኛ ያላደራጀነው እና ያልመራነው፣ እኛ ያልነካነው ሁሉ ከንቱ የሚለው ሥነልቦና ነው።
በዚህ ሥነልቦና ላይ የብሔረተኝነት ሥነልቦና ሲደረብበት በዚህ የብሔረተኝነት ሥነልቦና ላይ ደግሞ የድህነት እና የፍርሃት ሥነልቦና ሲጣፋበት ሁሉ ነገር ባዶ እና ዜሮ ይሆናል። ይባስ ብሎም ቡድን ቡድንን ማግለሉ ይቀርና በየቡድኑ ውስጥ ደግሞ እኔ ብቻ የሚል በሽታ ይነግሣል። ትናንትና አብረን እንሞታለን ያሉ ሰዎች በብርሃን ፍጥነት ተገለባብጠው ከሌላ ጋር ወግነው ይገኛሉ። በማግስቱ ግን በወገኑበት ቡድን ውስጥ እንደገና እኔ ብቻ ብለው አዋጅ እንደ እማማ አለብላቢት ያስነግራሉ። ሌላውንም ያለ ምንም ይሉኝታ ይደመስሱታል። ይሄን ለተወሰኑ ኃይሎች ብቻ ማሸከም አይቻልም። እውነታው አስፈሪ ነው። በርካታ ቡድኖች ውስጥ የእማማ አለብላቢት ሥነልቦና ተሸንቅሯል።
እንግዲህ በፖለቲከኞቻችን ውስጥ የተሸነቀረው የእማማ አለብላቢት ሥነልቦና ሳይታከም እና ሳይድን፤ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ማለም ተረት ተረት ነው። ያልተፈታው እንቆቅልሽ ግን ይሄን ሥነልቦና እንዴት ማከም እና ማዳን ይቻላል የሚለው ነው። ይሄን ሥነልቦና ማከምም ሆነ ማዳን የሚችል አቅም እና ጉልበት ግን እሕዝቡ ውስጥ አለ። እንቆቅልሽነቱ ግን ሕዝብ እምቅ ኃይል እመሆኑ ላይ ነው። ምንም ያህል ተግዳሮታማ ቢሆንም ግን እማማ አለብላቢት የዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ነቀርሳ ናቸው እና ከፖለቲከኞቻችን ሥነልቦና ውስጥ በሕዝብ ተነቀው መጣል አለባቸው።



