Dr. Fekadu Bekeleፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር)

መግቢያ

ይህንን ጥያቄ አንድ ስሙን ልጠቅሰው የማልፈልገው ምሁር በኢሜይል ለብዙ ጓደኞቹ በጥያቄ መልክ ሲያስተላልፍ ለእኔም ስላስተላለፈልኝ ይህንን በሚመለከት ቀደም ብዬ በትንተና መልክ ያቀረብኩ ቢሆንም እንደገና ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ ይህችን አጭር ትንተና ለመስጠት ቃጣሁ።

በወያኔና በወጭ ኃይሎች፣ በተለይም በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና በግብረአበሮቹ መሀከል ያለውን የእከክልኝ ልከክልህ ግኑኝነት በሚመለከት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃነትና፣ ዲሞክራሲያዊ መብቶች መጠበቅ ጠበቃ ቆሜያለሁ ብሎ ድምጹን እዚህና እዚያ በሚያሰማው ተቃዋሚ ነኝ በሚለው ኢትዮጵያዊና፣ በተለይም ምሁር ነኝ በሚለው ዘንድ የተምታታ አቋም አለ። በፕሮፌሽናል ደረጃ ሳይሆን በትርፍ ጊዜውና ደስ ሲለው የሚጮኸውን ሰፊውን ተቃዋሚ ነኝ የሚለውን ኢትዮጵያዊ ትተን ምሁር ነኝ ወደ ሚለውና ”ካለኔ በሰተቀር የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠበቃ የለም“ ብሎ ድምጹን የሚያሰማውንና በአብዛኛው የዋሁ ኢትዮጵያዊ ዘንድ ተቀባይነትን ያገኘውን በአጠቃላይ ኤሊት ነኝ የሚባለውን አቋም በምንመረምርበት ጊዜ በጣም የተምታታና ከሳይንስና ከሎጂክ ጋር የማይጣጣም ሀታታ እናነባለን።

በዚህ ተቀባይነትን ባገኘው ግን ደግሞ ከሳይንስና ከሎጂክ ጋር እንዲሁም ከተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር ምንም ግኑኝነት የሌለውን አስተሳሰብ ስንመረምር፣ ለሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠበቃ ባይ ነኝ በሚለው በኤሊቱ ዘንድ የወያኔ አገዛዝ በአለፉ 25 ዓመታት በአገራችን ምድር የሚያካሂደው የከፋፍለህ ግዛ ፖለቲካ፣ አንድን ሕዝብ በብሔረ-ሰብ ከልሎ ጠቅላላው ሕዝብ የመንፈስ አንድነት እንዳይኖረው ማድረግና፣ እየተፈራራና እየተጠራጠረ እንዲኖር ማድረግ፣ የአንድን አገር የተፈጥሮ ሀብትና የሰው ኃይል ሥርዓት ባለው መልክና በሳይንሳዊ ዘዴ ቀስ በቀስ ተግባራዊ ለማድረግ የማያስችለውን፣ በአጠቃላይ አነጋገር የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመባል የሚታወቀውን ተግባራዊ ማድረግና፣ አንድን አገር በጠንካራ መሰረት ላይ እንዳትገነባ ማድረግ፣ በተጨማሪም ከውስጥም ሆነ በአካባቢው አገሮች መረጋጋት እንዳይኖር አሸባሪዎችን መዋጋት ነው የዘመኑ ዋና ፖለቲካ ብሎ አገዛዙ በእዚህ ላይ አትኩሮ እንዲያደርግ አስፈላጊ በሆኑ የጦርና የስለላ መሳሪያዎች ማስታጠቅና ማሠልጠን፣ እነዚህና ሌሎች አገራችንን ከፍተኛ አደጋ ላይ የጣሏት ነገሮች በሙሉ አገዛዙ ብቻውን እንደሚያደርግ ተደርጎ ነው የሚቀርበው። በአንዳንዶች ድርጅቶችና ምሁሮች አነጋገር የውጭ ኃይሎች ለወያኔ ዕርዳታ የሚሰጡት በጣም ስለሚያፈቅሩትና ስለሚሳሱለት እንጂ ሕዝባችንና አገራችንን ለመጉዳትና ለመበታተን አይደለም የሚል ነው። እንዲያውም አንዳንዶች ለማሳመን እንደሚሞክሩት የውጭ ኃይሎች አገራችን እንዳትበታተንና እንደ ዩጎዝላቪያ እንዳትሆን ስጋት አለባቸው ይሉናል። በዚህ ዐይነቱ ”የጨዋዎች ትንተና“ እኛንና ሰፊውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ለማሳመን የሚሞክሩት ደግሞ ከዚህ ቀደም በፀረ-ኢምፔሪያሊስትነት የማይታወቀውና ኢትዮጵያ ዛሬ ላለችበት ደረጃ እንድትደረስ አምርሮ ይታገል የነበረው ኢትዮጵያዊ ቢሮክራሲያዊና የቴክኖክራት ኃይል ብቻ ሳይሆን አፄ ኃይለሥላሴ ሥልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት የኢትዮጵያ ሕዝብ ዋና ጠላት ፊዩዳላዊው ሥርዓት ብቻ ሳይሆን ኢምፔሪያሊዝም፣ በተለይም ደግሞ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ነው ብሎ የትግል አርማ አንስቶ ይታገል የነበረው ኃይል ነው።

ይህ ዐይነቱ የተምታታ ሁኔታና የሃሳብ ጥራት አለመኖር አገራችንን ዛሬ አፍኖ ከያዛት የወያኔ አገዛዝና ፀረ-ዕድገትና ፀረ-ሥልጣኔ ፖሊሲው አላቆ የተረጋጋችና ሰላም የሰፈነባት፣ እንዲሁም ሕዝቦቿ በሳይንስና በጥበብ እየተመሩ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመፍጠርና ሰፋ ያለ የውስጥ ገበያ፣ ጠንካራ ሕብረተሰብና ለፈጠራና ለትችት የሚያመችት አገር ገንበተው እንደ አንድ ሕዝብ ሊኖሩ እንዳይችሉ እንቅፋት የሚሆን አደገኛ አካሄድና አጉል የሪያል ፖለቲካ (Real Politics) ስሌት ነው። እንደሚታወቀው በተለይም እንደ ኢትዮጵያ የመሰሉ በብዙ የተወሳሰቡ ችግሩች የተወጠሩ አገሮች እንደዚህ ዐይነቱን የተምታታና ሳይንሳይዊ መሰረት የሌለው ፖለቲካ በመከተል አይደለም በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ በመገንባት እንደ አንድ ሕዝብ ሊተሳሰሩና ድህነትን ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ በማስወገድ በውጭው ዓለም ደግሞ ተከብረው ለመኖር የበቁት።

ስለዚህም ይህንን ዐይነቱን እጅግ አደገኛ አቋምና የድህነቱን ዘመን በማራዘም መበታተናችንን የሚያፋጥነውን አጉል ፖለቲካ፣ ግን ደግሞ ከሳይንስና ከፍልስፍና ጋር የማይገናኘውን አቋምና ትንተና የግዴታ መጋፈጠና ማጋለጥ ያስፈልጋል። አንዳንድ ድርጅቶችና ምሁር ነን ባዮች ሁሉንም ነገር ከሕዝብ ዕውነተኛ ነፃነትና ብልጽግና ጋር ሳይሆን ከራሳቸው ውስጣዊ ፍላጎትና ሥልጣን ላይ ወጥቶ ከመታወቅ ጋር ስለሚያገናኙት ይህ አጉል የፖለቲካ ቫይረስ ተባዝቶ ሰፊውን ወጣት ትውልድ ከማዳረሱና የትግሉን አቅጣጫ ከማዛነፉ በፊት በተቻለ መጠን በሳይንስና በሎጂኩ መንገድ መታገሉ የጊዜው አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። በእንደዚህ ዐይነቱ ጥራትነት በሌለው መንገድ ነው ሕዝባችን እስከዛሬ ድረስ የሚሰቃየውና በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ ወጣት ልጆቹ የሚገደሉትና አገርን ጥለው በመሄድ በየበረሃው ሕይወታቸውን እንዲያጡ የሚደረገው። ስለሆነም እንደዚህ ዐይነቱን አዘናጊና ፀረ-ሳይንስ የትግል ፈሊጥ መጋፈጡና ማጋለጡ የታሪክና የባህል ግዴታ ነው። አንድ ሕዝብና አገር በመቅለስለስና በፍርሃት፣ እንዲሁም በዩልኝታ ዕውነተኛ ነፃነትን የተቀዳጀበት ጊዜ የለም። የካፒታሊስት አገሮች እዚህ ደረጃ ላይ ሊደርሱ የቻሉት ከውስጥ ሆነው እንደነቀዝ የሚበሏቸውን ዕድገትን የሚቀናቀኑ ኃይሎችን በሳይንሱ ዘዴ በመታገል ነው ወደ ውስጥ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ኢኮኖሚና ሕብረተሰብ መገንባት የቻሉት። በተጨማሪም የቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት፣ የዛሬዋ ሩሲያ፣ ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያና ቻይና እዚህ ደረጃ ላይ ሊደርሱ የቻሉት በቆራጥነትና በአገር ወዳድ ስሜት በመነሳት እንጂ ከሌሎች አገሮች ፈቃድ በመጠየቅና በመለማመጥ አይደለም።

አንዳንድ ትዝታዎች ከታሪክ ማህደር!

የድሮ ታጋዮች ዛሬ የሚያፍሩበትና፣ በአንድ ወቅት ደግሞ ከግራም የበለጠ ግራ በመሆን ደረታቸው ላይ የማጭድና የመዶሻ አርማ ካነቴራ ለብሰው የሚሄዱ እኛ ገና የፖለቲካን ሀሁ ባልሰማንበት ዘመን፣ ፊዩዳሊዝም፣ ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝምና ኤምፔሪያሊዝም እንዲሁም የብሔረሰብ ምናምን የሚባሉትን ነገሮች ምን እንደሆኑ በማናውቅበት ጊዜ- ካለምንም ውሽት እነዚህን ጽንሰ-ሃሳቦች በሙሉ የሰማሁትና የኋላ ኋላ ጉጉት አድሮብኝ በጥብቅ ለመከታተል የቻልኩት አውሮፓ ከመጣሁና ጥቂት ዓመታት ካሳለፍኩኝ በኋላ ነው- ያስተጋቡ የነበረው እነዚህ ሦስት ጠላቶች የኢትዮጵያ ሕዝብ የዕድገት ዋና ጠላቶች ወይንም የጭቆናና የኋላ-ቀር ዋናዎቹ ምክንያቶች ናቸው የሚል ነበር። በመሰረቱ በጊዜው በተማሪው እንቅስቃሴ የተነሱት ጥያቄዎች በዘመኑ በዓለም አቀፈ ደረጃ የሚናፈሰው ነፋስ አካልና ተፅዕኖም በመሆናቸው የኋላ ኋላ ምርምር ለማድረግ ዕድል ላጋጠመን ግለሰቦች የእነዚህ ጽንሰ-ሃሳቦች አነሳስና የፖለቲካ መታገያ መሳሪያዎች ሆነው መቅረባቸው ትክክል አይደሉም ብሎ መናገር በጣም ስህተት ነው። ምክንያቱም በጊዜው በአገራችን ምድር በገሃድ ይታዩ የነበሩት እንደ ድህነት የመሳሰሉትና፣ በአጠቃላይ ሲታይ ኋላ-ቀርነትና ከዚህ ጋር ተያይዞ አገራችን በረሃብ መታወቋና ከግማሽ ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ሕይወቱን እንዲያጣ መደረጉ እነዚህ ነገሮች ሊያያዙ የሚችሉት ከሥርዓቱ ጋር ብቻ ነው። እንደሚታወቀው አንድ ነገር ካለአንድ ምክንያት በፍጹም ሊከሰት አይችልም። ስለዚህም በጊዜው በግልጽ ይታዩ የነበሩት የኋላ-ቀርነት ምልክቶች በሙሉ የሥርዓቱ ገጽታዎች እንደሆኑ ከአገራችን ታሪክ ብቻ ሳይሆን፣ እዚህ አውሮፓ መጥተን ከአውሮፓው የፊዩዳል ዘመን ሥርዓትና የአሪስቶክራሲው መደብና የካቶሊክ ሃይማኖት ጭፍን ዕምነትና አገዛዝ ጋር ከአወዳደርንና፣ በ16ኛው ክፍለ-ዘመን በአንዳንድ የተገለጸላቸው ቀሳውስት ከገበሬው ጋር በመተባበር የሚያደርጉትን ትግል ስናጠና በጊዜው በአገራችን ምድር በተማሪው እንቅስቃሴ መሪዎች የተነሱት ጥያቄዎችና በአገራችን ምድር ለተከሰቱት ችግሮች ተጠያቂዎቹ እነማን እንደሆኑ መነሳቱና፣ በዚህም ዙሪያ ጥናትና ትግል መካሄዱ ትክክል አይደለም የሚል ወይም ይህ ዐይነቱ አካሄድ የዕብዶች የትግል ዘዴ ነው የሚል ካለ ባለፉት ሁለት ሺህ ዓመታት ዘመናዊነትን ለማምጣትና የአንድን ሕዝብ ኑሮ ለማሻሻል የተደረገውን ምሁራዊ ትግል አይ ለማንቋሸሽ የሚፈልግ፣ አሊያም ያልገባው፣ ወይም ደግሞ የአንድ ሕዝብ ዕጣ በድሮው መልኩ መቀጠል አለበት፣ አንድ ሕዝብ ዕድገትና መሻሻል አያስፈልገውም ብሎ የኋላ-ቀርነት ጠበቃ ሆኖ ለመታገል የሚፈልግ ብቻ ነው። ስለሆነም በእኔ ዕምነት በማያጠራጥር መልኩ አፄ ኃይለሥላሴና አገዛዛቸው የኋላ-ቀርነት ቁንጮና ዋናው አራማጅ በመሆናቸው የግዴታ ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና ከግብረአበሮቹ ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ግኑኝነት ነበራቸው። በመሰረቱ የአፄ ኃይለሥላሴ አገዛዝ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ነፃነት የሚጠብቅና ጠበቃ ሳይሆን- በማወቅም ሆነ ባለማወቅ- የውጭ ኃይሎችን ጥቅም የሚያስጠብቅ ነበር። ስለሆነም አገራችንን እንደ አገር ሊያሰጠራትና ሕዝባችንንም እንደ ሰው ተከብሮ እንዲኖር የሚያስችለውን የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ፖሊሲ ለመከተል አልቻለም። ውብ ውብ ከተማዎችንና መንደሮችን በመገንባትና የሕዝቡን መሰረታዊ ፍላጎቶች በሟሟላት ሕዝባችን አገሩን አገሬ ነው ብሎ እንዲጠራና እንዲኮራባት ማድረግ አልቻለም።

አብዛኛው ተቃዋሚ ነኝ የሚለውና በጥሩ የሶይሶሎጂ ትምህርት ያልሰለጠነና የካፒታሊዝምን ዕድገት በየደረጃው ያላጠና፣ ይህንን ከእኛ አገር የኋላ-ቀርነት ሁኔታ ጋር ለማወዳደር ዕድል ያላገኘው፣ ወይም በስንፍና ምክንያት የተነሳ በጥብቅ ጠለቅ ብሎ ለማጥናትና ለማወዳደር ለማይፈልግ እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ሦስት መሰረታዊ ጽንሰ-ሃሳቦች፣ ፊዩዳሊዝም፣ ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝምና ኢምፔሪያሊዝም እንዴት ለዕድገት እንቅፋት ሊሆኑ ይችላሉ? ብሎ ይጠይቅ ይሆናል። ፀሐዩ ንጉሣችን እየተባሉ የሚሞገሱትና ኢትዮጵያን ከዘመናዊነት ጋር አስተዋውቀዋታል ተብለው የሚታሙት አፄ ኃይለሥላሴስ እንዴት ዕድገትን ይጠላሉ ወይም የዕድገት እንቅፋት ሊሆኑ ቻሉ ? ብሎም ሊጠይቅ ይችል ይሆናል። በዚህች አጭር ጽሁፍ ውስጥ ነገሩን በዝርዝር ለማስረዳት ባይቻልም እንኳ ማንኛውም ሰው እንዲገባው ቀለል ባለ መልክ ለማሳየት እሞክራለሁ።

በመሰረቱ ፊዩዳሊዝም የሚለው ሥርዓት ሰፋፊ መሬትን በሚቆጣጠሩ የመሬት ባላባቶች በአንድ በኩልና በሌላ ወገን ደግሞ ጭሰኛ በመሆን ካመረተው ምርት አብዛኛውን ለባላባቱ በመስጠት ራሱ የምርቱ ባለቤት እንዳይሆን የተደነገገበት መግለጫ ነው። ባጭሩ ፊዩዳሊዝም ማለት መሬትንና ሌሎች ለማምረት የሚያገለግሉ የማምረቻ መሳሪያዎችን በሚቆጣጠሩና፣ በሌላ ወገን ደግሞ በማረስና በመገበር የሚኖር ጭሰኛ የሚባል የሕብረተሰብ ክፍል የሚገለጽ ሲሆን፣ ይህ ዐይነቱ ግኑኘነት የፖለቲካ አወቃቀርንና የኃይል አሰላለፍን እንዲሁም የሕብረተሰቡን አስተሳሰብንም ያጠቃልላል። እንደሁኔታው ጭሰኛው ሙሉ በሙሉ የገበሬው ታዛዥ በመሆን ለማድረግ የሚፈልጋቸውን ነገሮች ሁሉ በመጀመሪያ ከባላባቱ መደብ ፈቃድ ማግኘት ያለበት ነፃነትን የሚገፍ ሥርዓት ነው። ይህ ዐይነቱ ጠበቅ ያለ ሥርዓት በአውሮፓ ውስጥ የተለመደ ሲሆን በአገራችን ምድር ግን በባላባቱ መደብና በጭሰኛው መሀከል የነበረው ግኑኝነት የላላ ነበር። በዚህም ምክንያት የተነሳ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ በባላባቱና በገባሩ የሕብረተሰብ ክፍል ብዝበዛን አስመልክቶ የሚካሄድ ወደ ጦርነት የሚያመራ ግጭት አልነበረም። የሥርዓቱን የዕድገት ጠንቅነትና የሰፊውን ሕዝብ አስተሳሰብ አቆርቋዥነት ሊያሳይና ሊያስተምር የሚችል የሕብረተሰብ ክፍልም ባለመኖሩ ሥርዓቱ እንደተፈጥሮአዊና፣ ሊለወጥና ሊሻሻል የማይችል ሆኖ የታመነበት ሥርዓት ነው። ከዚህም በላይ መሬትን የሚቆጣጠሩና የገበሬውን የእርሻ ውጤት አብዛኛውን የሚጋሩት የመሬታቸውን ምርታማነት ለማሳደግና የገበሬውን አድካሚ ስራ ለማቃለል የሚወስዱት ምንም ዐይነት እርምጃ ስላልነበረ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ውስጥ የኑሮ መሻሻል በፍጹም አይታይም ነበር። ራሳቸው ባላባቶችም የፍጆታ አጠቃቀማቸውና አኗኗራቸው በጣም ውስን በመሆኑ ለካፒታሊዝም ዕድገት እንቅፋት ነበሩ ማለት ይቻላል። ይህም ሊሆን የቻለበት ምክንያት በንግድና በዕደ-ጥበብ የሚገለጽ የምርት ግኑኝነትና እንቅስቃሴ ስላለነበረ የባላባቱ መደብ በራሱ ተነሳሽነት ለውጥ ሊያመጣ አልቻለም። በዚህ መልክ የጠቅላላው አገሪቱ ሁኔታ እዚያው በዚያው የሚንደፋደፍና ውስጣዊ-ኃይል በማግኘት ወደ ተሻለ የአመራረትና የአኗኗር ሁኔታ ለመሸጋገር ያልቻለ ነበር። በዚህ ላይ የንጉሣዊ አገዛዝና በላይነት እንደ ዕምነት በመወሰዱ አገዛዙን መቃወም እንደ ትልቅ ወንጀል የሚቆጠር ነበር። ”ንጉሥ አይከሰስ ሰማይ አይታረስ“ የሚባለው አባባል የንጉሣዊ አገዛዝን ፍጹማዊነት ለማሳየት የሚሰበክና በሕዝቡ ጭንቅላት ውስጥ እንደ ዕምነት እንዲያዝ የሚደረግ ቅስቀሳ ነበር። በአጭሩ የፊዩዳሉ ሥርዓትና የንጉሣዊ አገዛዝ የተፈጥሮንና የሕብረተሰብን ዕድገት ህጎች የሚቀናቀኑ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ጠንቆች ነበሩ ብሎ መናገር ይቻላል። ድርጊታቸውም በከተማና በመንደር ግንባታዎች የሚገለጹ ሳይሆኑ በቀጨጨ የአኗኗር ዘዴ የሚገለጹና የሰፊውን ሕዝብ አስተሳሰብ አፍነው የያዙ በመሆናቸው ለአገሪቱ ሁለ-ገብ ዕድገት ምንም ዐይነት ለውጥ ሊያመጡ አልቻሉም። ይህ ዐይነቱ ባህል አንድ ሰው ፍላጎቱንና ምኞቱን እንዳይገልጽ የሚያደርግ፣ ጥያቄ ለማቅረብ ዕድል የማይሰጥ፣ አስተሳሰብን ውስን በማድረግ አንድ ሰው ተፈጥሮ የለገሰችውን ልዩ ልዩ የጭንቅላት ባህርዮች በመጠቀምና ራሱን በማግኘት አዲስ አስተሳሰብ በማዳበርና አዲስ ነገር በመፍጠር ሕይወቱን እንዲያሻሻል ዕድል የማይሰጥ፣ በረቀቀ መልክ በመመራመር የተፈጥሮን ውበት በመቃኝትና ተፈጥሮን በመኮረጅ ከአንድ የኑሮ ደረጃ ወደ ተሻለ እንዲሸጋገር የማያደርግ ጭንቅላትን ቆልፎ የሚይዝ ሥርዓት ነበር። በቴክኖሎጂ ዕድገት የሚገለጽ ሕብረተሰብዓዊ ግኑኝነት ባለመኖሩ ግለሰብዓዊ ድርጊትና ነፃነት፣ እንዲሁም ትችትን መሰንዘርና መቀበል የተለመደ አልነበረም። ስለሆነም ለአዲስ ሃሳብ ጭንቅላትን ክፍት ለማድረግ አለመቻል፣ ችክ ብሎ ማምረርና ወዲያው ማኩረፍ፣ ልዩነትን በውይይትና በክርክር ለመፍታት አለመቻል፣ ቶሎ ብሎ ወደ ጠብ ማምራትና አልበገርም ማለት... ወዘተ.፣ የሥርዓቱ መግለጫዎች ናቸው። ይህ ዐይነቱ ባህርያችን እስካሁንም ድረስ በአስተሳሰባችንና በድርጊታችን የሚንጸባረቅ ሲሆን በተወሰነ ሃሳብ ዙሪያ ተሰባስበን በጋራ ለአንድ ዓላማ እንዳንሰራ እንቅፋት የሆነ ከፊዩዳሉ ባህል የወረስነውና እስከዛሬ ድረስ የሚከታተለን መጥፎ ባህል ነው። ስለሆነም ይህ ሥርዓት የዕድገትና የሥልጣኔ ፀር ነው መባሉ ትክክል ነበር።

ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝምና ኢምፔሪያሊዝም በጥብቅ የተያያዙና፣ ዘመናዊ የሚባለው ቢሮክራሲም ከኢምፔሪያሊዝም ወደ አገራችን መግባት ጋር ብቅ ሊል የቻለ የዕድገት እንቅፋት እንደሆነ ማየቱ ዛሬ ላለብን የአስተሳሰብ ችግር መነሻ ሊሆነን ይችላል። በመጀመሪያ ደረጃ ማንኛውም ሰው ሊገነዘበው የሚገባው ነገር አለ። አንድ ጽንሰ-ሃሳብ ዝም ብሎ የሚሰጥ ወይም አንዳንድ ሰዎች የተዘበራረቀ አስተሳሰብ ስላላቸው ዝም ብለው የሚወረውሩት ቃል ሳይሆን የአንድ ነገር መግለጫ ስለሆነ ነው። አንድን ነገር በስሙ የምንጠራው የተሰጠው ስም የነገሩን ምንነትና ተግባሩን እንዲሁም አመጣጡን ስለሚገልጽ ብቻ ነው። ለምሳሌ ጠረጴዛን ጠረጴዛ ብለን የምንጠራው አንድ የተወሰነ ተቅዋም ስላለውና ምግብ የምንበላበት ወይም ለመጻፍ ስለሚያመቸን ነው። በተጨማሪም ከዚህ ፍጆታዊ ጠቀሜታ ባሻገር እንደ ጠረጴዛው አሰራር ለቤታችን ውበት ወይም መልክ ይሰጠዋል። ይህም ማለት በህሊናችን ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል ማለት ነው። ስለዚህም ጠረጴዛን ጠረጴዛ ብለን እንጠራዋለን። ወደ ኢምፔሪያሊዝም የሚለው ጽንሰ-ሃሳብ ስንመጣም በአበዱ ሰዎች የተሰጠ ሳይሆን ከፍተኛ ዕውቀት ባላቸው ሰዎች የተሰጠ ብዙ ነገሮችን በማጠቃለል የሚገለጽ ነው። በመሰረቱ ጽንሰ-ሃሳቡ አሉታዊ ሚና ያለው ነው።፡ኢምፔሪያሊዝም የሚባለው ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት የሚታወቅ ጽንሰ-ሃሳብ ቢሆንም ትርጉሙ አንድ አገር በሌላ ደካማ ላይ የሚያደርገው ጣልቃ-ገብነትና ወረራ ጋር በጥብቅ የተያያዘ ነው። በ20ኛው ክፍለ-ዘመን ሆብሶንና ሌኒን ያዳበሩት የኢምፔሪያሊዝም ጽንሰ-ሃሳብ ደግሞ በቀጥታ ከካፒታሊዝም ዕድገት ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ የካፒታሊዝም የመጨረሻው የዕድገት መግለጫ ነው። ጽንሰ-ሃሳቡ በወረራ ብቻ የሚገለጽ ሳይሆን በዓለም-አቀፍ ደረጃ ከምርት ክንዋኔና ዓለም አቀፋዊ ባህርይ መያዝ ጋር፣ እንዲሁም ከፋይናንስ ካፒታሊዝም ዕድገት ጋር መቆላለፍ የሚገለጽ ነው። በተጨማሪም በታወቁት የይሁዲዋ ፈላስፋ ወይዘሮ ሃና አሬንድት አገላለጽ ኢምፔሪያሊዝም ለመስፋፋት ብሎ የሚስፋፋ በቀጥታ ከካፒታሊዝም የምርት ክንውን፣ የሸቀጥ ማራገፍ፣ የጥሬ-ሀብት ፍለጋና ሀብትን ለመዝረፍ የሚያመች የመዋዕለ-ነዋይ ክንዋኔ ጋር የተያያዘ ሂደት የሚገለጽ ሲሆን፣ በሳቸው አባባል ኢምፔሪያሊዝም የአምባገነን አገዛዝ ወይም ቶታሊታሪያን ዋናው ምንጭ እንደሆነ በደንብ ያብራራሉ።

ለምሳሌ ፋሺዝም የካፒታሊዝምና የኢምፔሪያሊዝም ውጤት ሲሆን፣ በሌሎች ቀድሞ በነበሩ ቅድመ-የካፒታሊስት ሥርዓቶች ውስጥ ሊወለድ በፍጹም አይችልም። ይህ ዐይነቱ ሥርዓት በተለይም ከሚሊታሪው የኢንዱስትሪ ውስብስብ (Military Industrial Complex) የምርት ክንዋኔ ጋር በመቆላለፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ በመስፋፋት ዕድገትንና ዲሞክራሲን አጋዥ ሳይሆን አፋኝና ሕብረተሰቦችን የሚያዘበራርቅ ነው። ዋናው ዓላማው በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥሬ-ሀብትን በመቆጣጠርና ወደ ካፒታሊስት አገሮች በቀጥታ እንዲመጡ በማድረግ የተወሳሰበና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የሀብት ክምችት (Capital Accumulation) በጥሬ-ሀብት አምራች አገሮች ውስጥ እንዳይዳብርና ጠንካራ ሕብረተሰብ እንዳይመሰርቱ የሚያግድ ነው። ይህ ዐይነቱ በቀጥታ በመዋዕለ-ነዋይ (Direct Investment) ሂደት የሚገለጽ ሲሆን ከመሬቱ ውስጥ የሚወጣው የጥሬ-ሀብት ወደ ውጭ መውጣቱ ብቻ ሳይሆን ጥሬ-ሀብቱ በሚወጣበት አካባቢ ከፍተኛ የሆነ የማኅበራዊና የአካባቢ ቀውስ ይፈጠራል። በተለይም ጠንካራ ኢንስቲቱሽንና የወዝ አደር የሙያ ማህበርና መንግሥታዊ ንቃተ-ህሊና በሌለበት በአብዛኛው የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ዓለም አቀፋዊ ኩባንያዎች እንደልባቸው ሀብትን በመዝረፍና መንግሥታትን በማባለግ ከፍተኛ የሆነ ባህላዊ፣ ማኅበራዊና የአካባቢ ቀውስ እንዲፈጠር ያደርጋሉ። ስለሆነም የዘመኑ ኢምፔሪያሊዝም በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በሚሊተሪ፣ በርዕዮተ-ዓለምና በባህል ወረራ የሚገለጽ እጅግ የረቀቀና የተስተካከለ ዕድገትን፣ ነፃነትንና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን የሚቀናቀንና እንዳይፈጠሩም አጥብቆ የሚዋጋ ነው። የካፒታሊስት አገሮች መንግሥታትም በዚህ ዐይነቱ ዓለም አቀፋዊ የሀብት ክምችት ገለልተኛ ሆነው እጃቸውን አጣጥፈው የሚቀመጡ ሳይሆኑ የጥሬ-ሀብት አምራች አገሮችን በተለያዩ የንግድና የኢንቬስትሜንት ስምምነቶች በማሰር ሁኔታዎችን የሚያመቻቹና በእነዚህ አገሮች ውስጥ ጤናማ ማህበረሰብና ሕብረተሰብ እንዳይገነባ የሚያደርጉ ናቸው። በካፒታሊስት አገሮች የተለያዩ ፓርቲዎች ቢኖሩም፣ ይህንን ወይንም ያንን ስም የያዙ በምርጫ ጊዜ አሸነፍው ሥልጣን ሲረከቡ ሶሻል ዴሞክራቲክ ወይም ሶሻሊስት ፓርቲ ነኝ የሚለው ከዚህ በፊት ሥልጣንን ይዞ ይገዛ የነበረውን ፓርቲ በተለይም የውጭ ፖለቲካውን ገልብጦ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ የሆነ የውጭ ፖለቲካ በፍጹም አያካሄድም። በውስጥ ያለውም ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ የኃይል አሰላለፍ አንድ ፓርቲ እንደፈለገ የካፒታሊስቶችን ጥቅም የሚጻረር የውጭም ሆነ የውስጥ ፖለቲካ እንዲከተል አይፈቅድለትም። ከዚህ ባሻገር ደግሞ በአብዛኛዎቹ የካፒታሊስት አገሮች ህጎችን የሚያረቁት በሕዝብ የተመረጡ የሕዝብ ተወካዮች ሳይሆኑ በየምኒስትሪዎቹ ውስጥ ሎብይስቶችን በመሰግሰግና ፓርሊያሜንት አካባቢ ቢሮዎችን በመክፈት የየመንግሥታት ህጎችን በቅጥታ የሚያረቁትና ተግባራዊ እንዲሆኑም ግፊ የሚያድርጉት፣ ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች፣ ባንኮችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች እንዲሁም በማህበር ደረጃ የተደራጁ የንግድ ሙያተኞች ናቸው ። ብረሰልስ ብቻ ወደ ስድስት ሺህ የሚጠጉ ሎቢይስቶች ቢሮዎች ከፍተው ተጠሪዎችን ያባልጋሉ። ስለዚህም ነው በዘመኑ አጠራር በአብዛኛው የካፒታሊስት አገሮች የውክልና ዲሞክራሲ ሳይሆን ፖስት-ዲሞክራሲ ስፍኗል የሚባለው። ከፓርሊሜንታሪ ዴሞክራሲ ተላቀናል ለማለት ያህል ነው።

ይህንን አልፈን ወደ ሦስተኛው ዓለም መንግሥታት ደግሞ ስንመጣ አብዛኛዎቹ መንግሥታት ራሳቸውን ችለው በራሳቸው ፍልስፍናና ህሊና የሚንቀሳቀሱ አይደሉም። ስለሆነም በየመንገስታት ቢሮክራሲ ውስጥ የካፒታሊስት አገሮችን፣ በተለይም የአሜሪካንን ኢምፔሪያሊዝም ጥቅም የሚያስጠብቁ ሰዎች ቀድሞውኑ ተኮትኩተው ከፍተኛ ሥልጣንን ስለሚይዙ እነዚህ ኃይሎች በቀጥታ የየአገራቸውን ጥቅም ሳይሆን የካፒታሊስት አገሮችን ጥቅም ነው የሚያስጠብቁት። ስለሆነም የካፒታሊስት አገሮች የራሳቸውን ሰዎች በመንግሥት መኪና ውስጥ አሰልጥነው በማስገባት በገዢው መደብ ዘንድ መተማመን እንዳይፈጠር ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ ዕውነተኛ ሕብረተሰብዓዊ ሀብት እንዳይፈጠርና ሕዝቡ ተጠቃሚ እንዳይሆን ያደርጋሉ። በዚህ መልክ የሦስተኛው ዓለም መንግሥታት በቀጥታ የካፒታሊስት አገሮች ታዛዥና አፈ-ቀላጤ በመሆን ወደ ውስጥ ማንኛውንም የማኅበራዊና የምሁራዊ እንቅስቃሴ አፍነው ይይዛሉ። ነገሩ ገፍቶ የሚሄድ ከሆነ ደግሞ በማሰርና በመግደል የተቀሰቀሰውን ትግል ለማብረድ ይሞክራሉ። በዚህ ድርጊታቸው የበለጠውን አምባገነናዊ በመሆንና ለዕድገት የሚያመቹ ማንኛውንም ምሁራዊ እንቅስቃሴዎችን በማፈን የካፒታሊስት አገሮች ተጠሪነታቸውን ያረጋግጣሉ። ሕብረተሰብዓዊና ማኅበራዊ ንቃተ-ህሊና እንዳይዳብርና ሕዝቡ በራሱ ተነሳሽነት አገሩን እንዳይገነባ በሚሆን በማይሆን ነገር ጠምደው በመያዝ አስተሳሰቡን ያዘበራርቁበታል። ከዚህ ስንነሳ በካፒታሊስት አገሮችና በጥሬ-ሀብት አምራች አገሮች መሀከል ያለው ግኑኝነት የጌታና የሎሌ ዐይነት ግኑኝነት ነው ማለት ይቻላል። ስለሆነም ዛሬ በብዙ የአፍሪካ አገሮችና በአገራችንም ያለው አምባገነናዊና ፋሺሽታዊ ሥርዓት ከዚህ ዐይነቱ ግኑኝነት ውጭ አይደለም። ዋናው ዓላማውም ድህነትን ማስፋፋትና የሕዝቡን አስተሳሰብ አዳክሞና አዘበራርቆ አቅመ-ቢስ ማድረግ ነው። ጠቅላላው ሕዝብ አገርና ሕብረተሰብ የሚለውን አስተሳሰብ ከጭንቅላቱ ሰርዞ በማውጣት እንደ አንድ ነፃ ሕዝብ እንዳይኖርና ታሪክን እንዳይሰራ ማድረግ ነው። የካፒታሊስት አገሮችም ዋናው ፍላጎት ይህ ሲሆን እንደዚህ ዐይነቱን አገዛዝ በማንኛውም ነገር መደገፍና በድርጊቱ እንዲገፋበት ማድረግ ነው።

ይህ ዐይነቱ ሥርዓት ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ መልኩን በመቀየር በውስብስብ ነገሮች በመገለጽ የብዙ አገሮችን ዕድል ወሳኝና ጦርነት ቀስቃሽ ለመሆን ቻለ። በተለይም ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የበላይነትን በመቀዳጀትና በሱ ቁጥጥር ስር ሊውሉ የሚችሉ የተለያዩ ዓለም አቀፋዊ ኢንስቲቱሽኖችን በመፍጠርና በእነዚህ ኢንስቲቱሽኖች አማካይነት የገበያ ኢኮኖሚ የሚባለውን፣ በመሰረቱ በቴክኖሎጂና በሳይንስ የሚደገፍን ዕድገት ሳይሆን በርዕዮተ-ዓለም የተሸፈነን (Neo-Liberal and Neo-Classical Economy Policy) ፖሊሲ ተግባራዊ እንዲሆን በማድረግ በየአገሮች ውስጥ ያለ የጥሬ-ሀብትና በመዋዕለ-ነዋይ ስም የሚካሄድ ትርፍ ወደ ውጭ እንዲወጣ በማድረግ በየአገሮች ውስጥ ያልተስተካከለ ዕድገት እንዲስፋፋ ለማድረግ በቃ። ከአንድ አገር ሕዝብ ፍላጎት ጋር የማይጣጣሙና የዕድገት አጋዥ ሊሆኑ የማይችሉ እንደ ኮካኮላ፣ የሲጋራ ፋብሪካ፣ የብስኩት፣ የቢራ ፋብሪካና ቀላል የጨርቃ ጨርቅ ማምረቻ ፋብሪካዎች የዚህ ዐይነቱ የተዘበራረቀ የዕድገት መግለጫዎች ሲሆኑ፣ የፍጆታ ዕቃዎቹ ለተወሰነው የሕብረተሰብ ክፍል ብቻ የታቀዱና ይህንን የተወሰነ የሕብረተሰብ ክፍል ከጠቅላላው የሕብረተሰብ ክፍል በመነጠል በአሜሪካን የአስተሳሰብ ክልል ውስጥ እንዲሽከረከር በማድረግ ብሔራዊ ስሜት እንዳይኖረው ማድረግ ነው። ይህ ዓይነቱ የፍጆታ አጠቃቀም (Consumption Pattern) ከ1950ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ የተስፋፋና እዚያው በዚያው ኢንፎርማል ኢኮኖሚ (Informal Sector) ከሚባለው መስክና ከእጅ ወደ አፍ ከሚመረተው (Subsistence Economy) የምርት ክንዋኔ ጋር በመጣመር በካፒታሊዝም ሎጂክ ላይ የተመሰረተ የምርት ክንዋኔ እንዳይካሄድ ያገደ ጣልቃ-ገብነትና የኢምፔሪያሊዝም መስፋፋት መግለጫ ነው። ይህ ዐይነቱ ሂደት በተለይም ወደ ውስጥ የተወሰነውን የሕብረተሰብ ክፍል በንግድና በአልባሌ መስኮች ላይ ብቻ እንዲሰማራ በማድረግ ከውስጥ ብሄራዊ ከበርቴ እንዳያድግ ያገደና የሚያግድ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ነው። በአንዳንድ የአሜሪካን የዘመናዊነት ተመራማሪዎች (Modernization theortecian) ዕምነትና፣ ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብ ከሦስተኛው ዓለም አገሮች የሚመጡ ተማሪዎች ጭንቅላት ውስጥ ተቋጥሮ እንዲያዝ በሚሰብኩት ፍላጎት መሰረት የአፍሪካ አገሮችና የተቀሩት የሦስተኛው ዓለም አገሮች ሁለ-ገብ የሆነ በመጀመሪያ ደረጃ ባህላዊ ዘመናዊነትንና ጭንቅላትን ያስቀደመ ዕድገት ሳይሆን የሚያስፈልጋቸው አንድ የተወሰነ ኤሊት ብቻ በመኮትኮት በዚህ አማካይነት ቀስ በቀስ ዕድገት ሊመጣ ይችላል ብለው ያስተምራሉ። ይህም አካሄድ ዕውነተኛው የዕድገት መንገድ ተደርጎ በመወሰዱና ይህንንም የተዛባና ከሳይንስ ጋር በፍጹም ሊጣጣም የማይችል አስተሳሰብ ሊዋጋ የሚችል ኃይል ብቅ ማለት ስላልቻለ እስከዛሬ ድረስ አገራችንና አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች በድህነት እንዲማቅቁ ተፈረደባቸው።

ወደ አገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ስንመጣና በተለይም በመንግሥት መኪና ላይ ያለውን ተፅዕኖ ስንመለከት የሲቪልና የሚሊታሪ ቢሮክራሲውን በማሰልጠንና የአገዛዙ መሰረት በማድረግ፣ በአንድ በኩል ወደ ውስጥ ብዝበዛን ሲያጠናክርና የተስተካከለ ዕድገት እንዳይመጣ ሕብረተሰቡን ቆልፎ ሲይዝ፣ በሌላ ወገን ደግሞ በሚያስፈልግበት ጊዜ የመንግሥት ግልበጣ በማድረግ አንድ መንግሥት መፈጸም ያለበትን ተግባር እንዳያከናውን ያደረገና የሚያደርግ ሥርዓት ነው። እንደሚታወቀው እንደተቀሩት የሦስተኛው ዓለም አገሮችም የኛም አገር ዘመናዊ የመንግሥት መኪና አወቃቀር ከታች ወደ ላይ ከኢኮኖሚው ዕድገትና ከምሁራዊ እንቅስቃሴ ጋር አብሮ እያደገ የመጣና የጠቅላላውን የአገሪቱን ዕድገት ሁኔታ የሚያንፀባርቅ ሳይሆን ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና ከተቀረው የምዕራቡ ካፒታሊዝም ጋር በሺህ ድሮች በመቆላለፉ የዕድገት አጋዥና ሰፋ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ እንዲዳብር የሚያግዝ አልነበረም። ስለዚህም ነው በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን የተዋቀረው የመንግሥት መኪና ከኢትዮጵያ ሕዝቦች ፍላጎትና ብሔራዊ ዕድገት ጋር የተያያዘ ሳይሆን የወጭው አካል ነበር ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር የሚቻለው። ስለዚህም ነው የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም አብዮቱ ሲፈነዳ አሜን ብሎ ያልተቀበለውና በጠቅላላው ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትና ነፃ ኢኮኖሚ ሊያስገነቡ የሚችሉ የአብዮቱ ድሎች እንዲጨናገፉ አብዮቱን የሚቀናቀኑ ኃይሎችን ሁሉ በማስታጠቅ አጠቃላይ ጦርነት ያወጀብን።

በአብዮቱ ወቅት ወደ ውስጥ በተለያዩ ኃይሎች የተከሰቱትን የማያስፈልጉ ሽኩቻዎችንና ምስቅልቅል ሁኔታዎችን ወደ ኋላ በመተው፣ አብዮቱ ከፈነዳ በኋላ ሕዝቡ የተቀዳጃቸው እንደ መሬት ላራሹ የመሳሰሉት ድሎችና ዲሞክራሲያዊ ጥያቄዎች ሙሉ በሙሉ ወደ ተግባርነት ተመንዝረው ሕዝባችን ያለ የሌለውን ኃይሉን በአገር ግንባታ ላይ እንዳያውል የታገደው በውጭ ኃይሎች፣ በተለይም በአሜሪካንና በእንግሊዝ እንዲሁም በተቀሩት የሰሜን አትላንቲክ የጦር አባል አገሮች በሕዝባችን ላይ ጦርነት ስለታወጅብን ነው። እነዚህ የውጭ ኃይሎች ሕዝባችን ብሔራዊ ስሜቱ አድጎ አገሩን በጸና መሰረት ላይ እንዳይገነባ ለማድረግ በቀጥታ ሳይሆን በተዘዋዋሪ የነፃ አውጭ ኃይሎች ነን የሚባሉትን የብሔረሰብ እንቅስቃሴዎች በሙሉ በማስታጠቅና የገንዘብ ዕርዳታ በማድረግ የወታደራዊዉን አገዛዝ ከውስጥም ከውጭም ወጥረው እንደያዙት በግልጽ የሚታወቅ ጉዳይ ነው። በአገራችን ምድር በጊዜው በቀይ ሽብርና በነጭ ሽብር የተካሄዱት የወንድማማች ሕዝብ ርስ በርስ መተላለቅ በስተጀርባ ሲአይኤና ሌሎች የስለላ ድርጅቶች እንደነበሩበት ይታወቃል። እንደሚባለው የውጭው ርዕዮተ-ዓለም ወደ አገራችን በመግባቱ ሳይሆን የርስ በርስ መተላለቅ ሊፈጠር የቻለው፣ ወደ ውስጥ የአብዮቱ ድሎች በተለይም በሚሊቴሪውና በሲቪል ቢሮክራሲው ዘንድ ግንዛቤን ባለማግኘታቸውና፣ ይህም የሕብረተሰብ ክፍል ገና ብሔራዊ ስሜቱ ያደገ ባለመሆኑ በአንድ በኩል፣ በሌላ ወገን ደግሞ ተራማጅ ነኝ በሚለው ዘንድ አብዮቱ ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲያገኝ በጥንቃቄ ባለመካሄዱና የፊዩዳሉን መደብ የሚያስቆጣ ስር-ነቀል የመሬት ላራሹ ተግባራዊ መሆን እነዚህ ሁሉ አንድ ላይ በመደመር በጊዜው ለተከሰተው አስከፊ ሁኔታ ተደራራቢ ምክንያቶች ሊሆኑ ቻሉ። በተጨማሪም የተወሰነው የተማሪው ንቅናቄ አካል የነበረው አርቆ የማሰብ ኃይል በጣም ደካማ ስለነበር ድርጊቱን በቅጡ ለመመርመርና ከአደገኛ ተግባሩ ሊቆጠብ አልቻለም። በዚህም ምክንያት የተነሳ መሰባሰብና አብሮ መታገል የሚገባው ተራማጅ ነኝ ይል የነበረው ኃይል በዚህ ጨቅላ አስተሳሰቡና ድርጊቱ ጠቅላላውን የሕዝብ ኃይል መበተን ቻለ። በአጠቃላይ ሲታይ ተራማጅ ወይም የለውጥ ፈላጊ ኃይል በሚባለው ዘንድ ሕብረተሰብዓዊና ፓለቲካዊ ንቃተ-ህሊና ስር የሰደደ ባለመሆኑ፣ ድርጊቱን ከራሱ የሥልጣን ፍላጎት ውጭ ማየት አልቻለም። ይህ ዐይነቱ የኃይል መከፋፈል ለውጡን ለሚጠሉ የውስጥና የውጭ ኃይሎች አመቺ ሁኔታ ፈጠራላቸው። እንደሚታወቀው አገራችን የረዥም ጊዜ አገር ታሪክ አላት ቢባልም ምሁራዊ እንቅስቃሴ የሚባለው ከ1950ዎች ዓ.ም. ጀምሮ ብቅ ያለ በመሆኑና ይህም ቢሆን በሰፊ መሰረት ላይ የተገነባ ባለመሆኑና አመለካከቱም በጣም ውስን በመሆኑ አብዛኛውን ምሁር ተብሎ የሚጠራውን ያቀፈ አልነበረም። በአገራችን ምድር በሁሉም መልክ የሚገለጽና አገሪቱን ሊያዳርስ የሚችል ምሁራዊና ሕብረተሰብዓዊ እንቅስቃሴ ባለመኖሩ አብዮቱን ለማዳከመና ዲሞክራሲያዊ ኃይሎችን ለመምታት በጣም የሚያመች ነበር። አብዛኛው ዘመናዊ የሚባሉት ነገሮች አዲስ አበባ ብቻ ይካሄዱ ስለነበር ከ90% በላይ የሚሆነው ሕዝባችን ንቃተ-ህሊናውን ለማሳደግ የሚያስችለው የትምህርት፣ የቲያትርና ልዩ ልዩ ጭንቅላትን የሚያዳብሩ ትምህርታዊ ነገሮችን የማግኘት ዕድል አልነበረውም።

ከዚህ ሀተታ ስንነሳ የተቀረውን ትተን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ጀምሮ አሜሪካንና ግብረ አበሮች ደካማ አገሮች ራሳቸውን እንዳይችሉ የተከተሉትንና የሚከተሉትን በግልጽና ግልጽ በአልሆነ መልክ የሚካሄደውን ፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የሚሊታሪ ፖሊሲያቸውን በጥብቅ ለተከታተለ አሜሪካንና ግብረአበሮቿ በምንም ዐይነት የዕድገትና የሰላም አራማጆች ሆነው አያውቁም። ነበሩም፣ ናችውም ብሎ ሽንጡን ገትሮ የሚከራከር ካለ በዓለም አቀፍ ደረጃ ምን እንደተካሄደና እንደሚካሄድ የማያውቅ ብቻ ነው። ከኢራን እስከ ጓቴማላ፣ ከብራዚልና እስከቺሌ ድረሰ የተደረጉት የመንግሥት ግልበጣዎችና የአምባገነን መንግሥታት አነሳሶች፣ እንዲሁም የቬትናም ጦርነት በአጭሩ የሚያረጋግጡት የአሜሪካንን ኢምፔሪያሊዝም ዐይን ያወጣ ተግባር እንጂ ዲሞክራሲያዊ ባህርዩን አይደለም። ይህንን በሚመለከት በዐይናችንን ከምናየው በሻገር ሺህ በሺህ የሚቆጠሩ የድሮና አሁን በየጊዜው የሚወጡት ሊትረቸሮች በሚገባ ያረጋግጣሉ። ዛሬ በተለይም በአፍሪካ ምድር አምባገነን በመባል የሚታወቁት አገዛዞች በሙሉ አነሳሳቸውና የውስጥ ፖሊሲያቸው ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና ከግብረ-አበሮቻቸው ጋር በጥብቅ የተያያዙ እንደሆነ አያሌ ጥናቶች ያረጋግጣሉ። የአፍሪካን አምባገነን አገዛዞች በአፈጣጠራቸው ጭራቆችና የዕድገት ተቀናቃኝ ኃይሎች ናቸው ተብሎ በተናጠል የሚቀርበውጥ ጥናትና የሚሰጠው የቃለ-ምልልስ ገለጻ በመሰረቱ ሳይንሳዊ አይደለም። ይህንን ካልኩኝ በኋላ ወደ ዛሬው በአገራችን ምድር ወደ ሰፈነው አምባገነናዊና ፋሺስታዊ አገዛዝ ልምጣ። ወያኔ ብቻውን የሚገዛ ኃይል ወይስ የውጭ ኃይሎችን ጥቅም የሚያስጠብቅ አገዛዝ ? ይህንን በደንብ ጠጋ ብለን እንመልከት።

ወያኔ ለማን ነው ጠበቃ የቆመው? የትኞቹ ኃይሎችስ ናቸው ከበስተጀርባው የቆሙት?

አብዮቱ ከመፈንዳቱ በፊት ለዕድገት ጠንቅና ለዲሞክራሲያዊ ነፃነት አለመኖር ዋናው ጠላቶች ፊዩዳሊዝም፣ ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝምና ኢምፔርያሊዝም ናቸው ብለናል። እዚህ ላይ ከሞላ ጎደል ስምምነት ያለ ይመስለኛል። አብዮቱ ከፈነዳና ከተቀለበሰ በኋላ ግን እነዚህን ከላይ የተጠቀሱትን ነገሮች እንደዋና ጠላቶች አድርጎ መውሰድ በፍጹም አይቻልም። የፊዩዳሊዝም የማቴሪያል መሰረቱ ሙሉ በሙሉ ስለተደመሰሰ እንዲሁም ፖለቲካዊ መዋቅሩ ተገርስሷል። ስለዚህ ይህንን እንደምክንያት ወስደን የኋሊት ጉዞ በመጓዝ በአረጀ የትግል መሳሪያ ልንታገል አንችልም። ስለሆነም ለዛሬው ችግራችን ዋናው ምክንያት የሆነውን ቆፍሮ በማውጣት ላይ የሚያተኩር መሆን አለበት። እንደሚባለውና እንደሚታመንበት ለአንድ ሕመም ሆነ ሕብረተሰብዓዊ ችግር በቂ ምክንያት አለ። የችግሩን ዋና ምንጭ ሲታወቅ ብቻ ነው መፍትሄ መስጠት የሚቻለው። ይህንን በሚመለከት አዲስ ባወጣሁት መጽሐፌ ላይ በሰፊው ስላተትኩ አልመለስበትም።

ያም ሆነ ይህ በመጀመሪያ መታወቅ ያለበት አንድ ጉዳይ አለ። ይኸውም አንድ የውጭ ኃይል ለአገራችን ዕድገትንና ነፃነትን የሚመኝ ከሆነ መስራት ያለበት ከተገለጸላቸውና ዕውነተኛ ነፃነትንና ዕድገትን ከሚያመጡ ብሔራዊ ኃይሎች ጋር እንጂ ሥልጣንን ዋና ዓላማው አድርጎ የጦር ትግል ከሚያካሂድና አንድ ወንድማማች ሕዝብ ወደ ርስ በርስ ጦርነት እንዲያመራ ከሚያደርግ አሸባሪ ኃይል ጋር አይደለም። በዚህ ረገድ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና ግብረአበሮቹ አገራችንን ለማዳከም ፀረ-ዲሞክራሲያዊና ተገንጣይ ኃይሎችን በሃሳብና በማቴሪያል እንዲሁም በገንዘብ ሲደግፉ ኖረዋል። ስለሆነም ትላንትናም ሆነ ዛሬ አገራችን እንድታድግ፣ እንድትረጋጋና፣ ሕዝባችንም ዕውነተኛ ነፃነትን እንዲቀዳጅ በፍጹም አይፈልጉም። ይህንን ማድረግ ማለት በራስ ላይ ዘመቻ እንደማካሄድ ይቆጠራል። ከሄጄሞኒ (Hegemony) ቲዎሪ አንፃር ስንነሳ፣ ለአንድ የሦስተኛው ዓለም በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመረኮዘን ሁለ-ገብ ዕድገት መደገፍ ማለት ቀስ በቀስ የራስን የበላይነት እንደማጣት ይቆጠራል ማለት ነው። አንድ አገር የጠነከረ ብሔራዊ ኢኮኖሚና በሁሉም መስክ የተማረ ኃይልና የአገሩን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠብቅ የሕብረተሰብ ኃይል ካላት ከውጭው ኃይል ጋር የመደራደር ኃይሏ ይጨምራል። አገሩንም የሚወክለው ኃይል በድፍረት የሚፈልገውንና የማይፈልገውን፣ ለአገሩ ዕድገት የሚያዋጣውንና የማያዋጣውን በግልጽ ስለሚናገርና ስለሚደራደር ይህንን ዐይነቱ የሕብረተሰብ ክፍልና መንግሥት እንዲፈጠርና እንዲጠነክር መፍቀድ ማለት የራስን መቃብር እንደመቆፈር ይቆጠራል። ስለሆነም በውጭው ኃይልና እንደኛ ባለው አገር ጋር ያለውን ግኑኝነት ከዚህ አንፃር በመነሳት ነው መገምገምና መረዳት ያለብን። እንዲያው በአጉል ጥላቻ ላይ የተመረኮዘ ቅስቀሳ የትም አያደርሰንም። በሌላ ወገን ደግሞ በውጭው ኃይል ላይ የሚሰጠውን ክሪቲካል ትንተናና ገለፃ የአክራሪዎችና የግራ-ቀደሞች አስተሳሰብ ነው እያሉ ለማንቋሸሽና ስም ለማጥፋት መሞከር በተጨባጭ ሲታይ ዕውነተኛ ሥልጣኔና ዲሞክራሲያዊ ነፃነት እንዳይመጣ አጥብቆ እንደመታገል ይቆጠራል። በተለይም በአንድ ወቅት ግራ ነን ብለው ያዙኝ ልቀቁኝ በሚሉት ዘንድ ይህ ዐይነቱ የፀረ-ዕድገትና የፀረ-ዲሞክራሲ ዘመቻ እየተስፋፋ መጥቷል። በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለጤናማ ትንተናና ውይይት እንቅፋት ለመሆን በቅቷል ማለት ይቻላል።

ያም ሆነ ይህ ወያኔ እዚህ ደረጃ ላይ ሊደርስ የቻለው በእንግሊዝ፣ በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና በተቀሩት የካፒታሊስት አገሮች ድጋፍ እንደሆነ የታወቀ ነው። አፀነሳሱና አነሳሱ ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ አወቃቀር ድክመት ጋር የተያያዘና የአገራችን ኋላ-ቀር ዕድገት ውጤት ቢሆንም፣ በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ይደገፍ የነበረው ሻቢያ፣ የኋላ ኋላ ደግሞ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ሥልጣን ላይ ቁጥጥ ብሎ የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲውን ተግባራዊ እንዲያደርግ እንደረዳው ግልጽ ነው። በሌላ አነጋገር ለወያኔ መፀነስ፣ መወለድና ማደግ የውስጥ ተጨባጭና ህሊናዊ ነገሮች ዋናው ምክንያት ቢሆኑም፣ ሊጠናከር የቻለውና የዲሞክራሲና የነፃነት ጠላት ሊሆን የበቃው በአካባቢው በሚገኙና በውጭ ኃይሎች አማካይነት ነው። ከዚህ ስንነሳ ወያኔ ሥልጣን ሲይዝ እንደ ዋና ቅድመ-ሁኔታ ከቀረቡለት ነገሮች የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትንና (IMF) የዓለም ባንክን የተቅዋም ፖሊሲ ማስተካከያ (Structural Adjustment Program) ተግባራዊ ማድረግ እንዳለበት ነው። የዚህ ፖሊሲ ዋና ዓላማ ደግሞ የገበያ ኢኮኖሚን ማስፋፋት በሚል ስም በፖሊሲው አማካይነት የሕዝብ ሀብቶች በግለሶብች ቁጥጥር ስር ውለው የተወሰኑ ድርጅቶችና ግለሰቦች ሀብታም ሊሆኑ የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው። በተጨማሪም የመንግሥቱ ሚና በሞኔተሪ ፖሊሲ ላይ ብቻ በማትኮር ወደ ውስጥ ሰፋ ያለ የአገርን የውስጥ ገበያ ሊያሳድግና ሊያስፋፋ በሚችልና የሰውን ኃይልና የአገርን የተፈጥሮ ሀብት ለማንቀሳቀስ በሚችለው ሂደት ላይ በምንም መንገድ አለመሳተፍ ነው። ከዚህም ባሻገር ሰፊውን ህብዝ ለማድኸየት ሲባል ሀብትን ከደሀው ወደ ሀብታሙ የሕብረተሰብ ክፍል ለማሸጋሸግ የግዴታ ለማኅበራዊ መስክ የሚወጡ ድጎማዎችን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ነው። በዚህ መልክ የውስጥ ሀብት በፍጹም ሊዳብር አይችልም። አገርም ልታድግና ሕዝብም ሊሰባሰብና ብሔራዊ ስሜት ሊያድርበት አይችልም። እንደሚታወቀው ለአንድ አገር ዋናው የዕድገት መሰረት ወደ ውስጥ ያተኮረ ሳይንሳዊና ሁለ-ገብ የኢኮኖሚ ፖሊሲ መከተል ሲሆን፣ አንድ አገዛዝ በውጭ ኃይልና በኢንስቲቱሽኖቹ እየተመከረና እየታገዘ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚያወጣና ተግባራዊ የሚያደርግ ከሆነ በመሰረቱ የአገሩን ጥቅም የሚያስጠብቅ አይደለም። ከዚህም በላይ በአንድ አገር ውስጥ አንድ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት በውስጥ የሕብረተሰብ ኃይሎች መጠናትና ለክርክር መቅረብ የሚችል መሆን አለበት። ይህንን አስመልክቶ ወያኔ ሥልጣን ከያዘ በኋላ በውስጥ ኃይሎች የተደረገ ክርክርና ወያኔም በራሱ ተነሳሽነት ምሁሩን ጋብዞ እንወያይ ያለበት ጊዜ የለም። ስለሆነም ወያኔ ተግባራዊ ያደረገው የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንደ አሽከር በመሆን በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና በኢንስቲቱሽኖቹ የቀረበለትን ፖሊሲ ነው። ይህም ማለት ፖሊሲው ሙሉ በሙሉ የኢትዮጵያን ሕዝብ ጥቅም የሚፃረርና የዕድገትና የሥልጣኔ ተቀናቃኝ ነው። በብዙ አገሮች ተሞክሮ በጥናት እንደተረጋገጠውና በዐይናችንም እንደምናየው በውጭ ኃይሎችና አማካሪ ኩባንያዎች የሚረቀውና የሚደገፍ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ድህነትን ፈልፋይ ነው። በከተማዎች ብቻ ሳይሆን፣ በጠቅላላው በአንድ አገር ውስጥ ያልተስተካከለ ዕድገትን በማምጣት ለሕብረተሰብ መወዛገብና ለሌሎች እንደ ጎሳና ሃይማኖት ለመሳሰሉት ነገሮች ያለመግባባትና የግጭት ምክንያት ሊሆን ይችላል። ሰፋ ያለ አንድን አገር የሚያዳርስ የስራ-ክፍፍል ለመዳበር ስለማይችልም፣ አብዛኛው ሕዝብ ሀብትን በማይፈጥር ጥቃቅን የምርትና የአገልግሎት መስኮች ላይ በመረባረብ ኑሮውን ለማሻሻል አይችልም። ለመኖር የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ነገሮችን (Basic Needs) የማግኘት ዕድሉም በጣም እየጠበበ ይመጣል። ስለዚህም ነው ዛሬ በአገራችን ምድር ድህነትና ረሃብ ሊስፋፉ የቻሉት። በፖሊሲውም አማካይነት ነው ከተማዎች ካለ ዕቅድ የሚሰሩትና ሕዝባችንም የተዝረከረከ ኑሮ እንዲኖር የተገደደው። በአንፃሩ ግን ፖሊሲውም በቀጥታ ወያኔና ግብረአበሮቹን የረዳና በሀብት እንዲናጥጡ ያደረገ ነው።

የወያኔ አገዘዛ በአጠቃላይ ሲታይ ከአንድ ብሔረሰብ የተውጣጣ በመሆኑ ስትራቴጂክ የሚባሉ መስኮችን ገንዘብ በርካሽ ወለድ ከባንክ በመበደር ከዚህ ቀደም በመንግሥት ቁጥጥር ስር የነበሩ ሀብቶችን በራሱ ቁጥጥር ስር ለማድረግ በቃ። በዚያው መጠንም እያደገ ሲመጣ ይቀናቀኑኛል የሚላቸውን ታታሪ ግለሰቦች ከገበያው ተስፈናጥረው እንዲወጡ በማድረግ ወደ ውስጥ በግለሰብ ታታሪነትና ፈጠራ ላይ የተመሰረተ የካፒታሊዝም እንቅስቃሴ እንዳይካሄድ አገደ። የተቀሩትን የኢኮኖሚ ክንዋኔዎች ስንመረምር ደግሞ ወደ ውስጥ ሀብት ሊያፈሩ የሚችሉ ሳይሆኑ ወደ ውጭ የጥሬ ምንዛሪ ለማግኘት ሲባል የሚካሄዱ የምርት ክንዋኔዎች ናቸው። የአበባ ተከላ፣ የስኳር አገዳ ተከላና ምርት፣ የሰሊጥና የኑግ ምርት እንዲሁም ቡናና ሌሎች በጥሬ ሀብት ላይ የተመረኮዙት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች የሚባሉት በሙሉ የስራ መስክ ፈጣሪዎችና የአገር ውስጥ ሀብት (National Wealth) እንዲዳብር የሚያደርጉ ሳይሆኑ አገሪቱ ራሷን እንዳትችልና ሰፋ ያለ ብሔራዊ ኢኮኖሚ እንዳይገነባ የሚያደርጉ እንቅስቃሴዎች ናቸው። በአገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚካፈሉት የውጭ አገር ሀብታሞች የሚባሉት በሙሉ በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የምርት ክንዋኔ የሚያካሄዱ ሳይሆኑ በአበባ ተከላና በፍራፍሬ ምርት ላይ የተሰማሩ ናቸው። እንደነዚህ ዐይነት የምርት ክንዋኔዎች ደግሞ ምንም ዐይነት የኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋፅዖ የላቸውም። በአንፃሩ የውስጥ ገበያና የአገር ውስጥ ከበርቴ እንዳያድጉ የሚያደርጉ ናቸው። በመሰረቱ እነዚህ የውጭ መዋዕለ-ነዋዮች የሚባሉት፣

1ኛ) የምርት ክንዋኔዎቹ ከተቀሩት የኢኮኖሚ መስኮች ጋር የተያያዙ አይደሉም። ይህም ማለት የሚመረቱት የጥሬ-ሀብቶች ሳይፈበረኩ (Unprocessed) እንዳሉ ወደ ውጭ የሚላኩ ወይም የሚወጡ ናቸው። በዚህ መልክ በአጠቃላይ ሲታይ የተሳሰረና የተደጋገፈ የምርት ክንዋኔ ወይም ሂደት (Value-added Chain) ይበጠሳል። ወይም ርስ በርሱ የተያያዘ የኢኮኖሚ ክንዋኔ አይኖርም ማለት ነው።

2ኛ) የስራ መስክ የመክፈት ኃይላቸው በጣም ደካማ ነው። ተቀጥሮ የሚሰራው ደግሞ አነስተኛ ደሞዝ ስለሚከፈለው ከኢኮኖሚ ዕድገት አንፃር ሚናው በጣም ውስን ነው ማለት ነው። በሚያገኘው ደሞዝ ደግሞ ፋብሪካ ውስጥ የሚመረቱትን ወይም ራሱ የሚያመርታቸውን ሳይሆን ገዝቶ የሚጠቀመው ከሌሎች ዘመናዊ ኢኮኖሚ ከሚባለው ዘርፍ ጋር ባልተያያዙ መስኮች የሚመረቱ ምርቶችን ነው።

3ኛ) እንደዚህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ክንዋኔ የፕላንቴሽን ኢኮኖሚን በማስፋፋት ከውስጥ ቴክኖሎጂያዊ ዕድገት እንዳይመጣ ያግዳል። ስለሆነም በካፒታሊስት አገሮች በከፍተኛ ደረጃ እያደገ የመጣውን የፍጆታ አጠቃቀምና የሀብት ክምችት ዘዴ የሚያግዝ ሲሆን፣ ወደ ውስጥ ደግሞ ለምለም መሬቶች የሕዝቡን ፍላጎት ሊያሟሉ የሚችሉ ሰብሎች እንዳይዘራባቸውና እንዳይመረትባቸው ይደረጋሉ። በዚህም ምክንያት አገር ቤት ውስጥ የእህል እጥረት ሲከስት፣ በቁጥር እየጨመረ ከሚሄደው ሕዝብ ጋር የሚመጣጠን በቂ ምግብ ገበያ ላይ እንዳይቀርብ ያግዳል።

4ኛ) ይህ ዐይነቱ ፖሊሲ የምግብ እጥረትን ማስከተሉ ብቻ ሳይሆን ኢንዱስትሪዎች የጥሬ-ሀብት እንዳያገኙ ይደረጋሉ። በዚህም ምክንያት የተነሳ የተወሳሰበ የአገር ውስጥ ገበያ(Home Market) እንዳያድግ ያግዳል።

5ኛ) አገዛዙ ከእንደዚህ ዐይነት የውጭ ከበርቴዎች ጋር በመቆላለፍ በአገር ውስጥ ብሔራዊ ባህርይ ሊኖረውና በኢኮኖሚው መስክ ሊሰማራ የሚችል የአገር ውስጥ ከበርቴ እንዳይዳብር ያግዳል።

6ኛ) ይህ ዐይነቱ የውጭ መዋዕለ-ነዋይ ያለውን ድህነትና ዝርክርክነት የባሰውኑ ያጠናክረዋል። በተጨማሪም ጥበባዊ የሆኑ ከተማዎችና መንደሮች እንዳይገነቡ ያግዳል።

7ኛ) የተወሰነው የሕብረተሰብ ክፍል አትኩሮው እንዲቀየር በማድረግ ብሔራዊ ስሜቱ እንዳይዳብር ያደራግል። በዚህ መልክ ጠቅላላው አገሪቱ ከውስጥ ስትዳከም ለውጭ ወረራ አመቺ ትሆናለች ማለት ነው። ስለሆነም በውጭውና በአገር ውስጥ ያለውን የኢኮኖሚ ትስስርና የድህነትን መጠናከርና ጥገኝነት መግለጽ የሚቻለው በዚህ መልክ ነው። የኢምፔሪያሊስት ኃይሎችም ዋና ተግባር አገዛዙ በዚህ ዐይነቱ ድህነትን ፈልፋይ ፖሊሲው እንዲቀጥል መገፋፋት ነው። ጭቆናውን እንዲያጠናክር ማንኛውንም ነፃነት አፋኝ የሆኑ ሕዝቡን መቆጣጠሪያ መሳሪያዎች በሙሉ ያቀርቡለታል። በሁሉም መልክ የሚገለጽ ኋላ-ቀርነት በሰፈነበት አገር ደግሞ ይህ ዐይነቱ በአገዛዙና በውጭ ኃይሎች መሀከል ያለው የእከክልኝ ልከክልህ መደጋገፍ እንደትክክለኛ ድርጊትና ዕርዳታ ተደርጎ ይቆጠራል። ስለሆነም የወጭ ኢንቬስተሮች የሚባሉትን ሚና ትርፍን ወደ ውጭ በማውጣት ብቻ በገምገም መረዳት የሚቻል ሳይሆን፣ ለአንድ አገር ብሔራዊ ኢኮኖሚ ዕድገት፣ የቴክኖሎጂና የሳይንስ ምጥቀት፣ የባህል ዕምርታና የሕብረተሰብ መተሳሰርና መጠናከር ሊያበረክቱ የሚችሉትን አስተዋፅዖች ከስሌት ውስጥ የከተትንና መተንተን የቻልን እንደሆን ብቻ ነው። በራሱ የሚንቀሳቀስና ከሌላው የኢኮኖሚ መስክ ጋር የማይተሳሰር የኢኮኖሚ ዘርፍ ለዘረፋና ለአምባገነን አገዛዞች የሚያመች ነው። ማንኛውም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ከጠቅላላው የኢኮኖሚ ፕላኒንግ ሲይሰተም ጋር ሲዋሃድ ብቻ ነው ኢኮኖሚያዊ ትርጉምነቱን መረዳት የሚቻለው። ያም ሆነ ይህ የውጭ ዕርዳታና መዋዕለ-ነዋይ አገራችንን ከድህነትና ከጥገኝነት ሊያላቅቁ በፍጹም አልቻሉም።

ይህ ዐይነቱን የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ለማድረግና ዘረፋን ለማጠናከር ደግሞ አገዛዙን በሚሊታሪ ቴክኖሎጂዎች ማስታጠቅ ዋናው የኢምፔሪያሊስት ኃይሎች ተግባር ነው። የፀጥታው መስክ ውስጥ ስርጎ በመግባትና በማማከር አምባገነናዊ ባህርዩን ማጠናከርና በሕዝባችን ላይ ግልጽ ጦርነት ማካሄድ፣ ዕድገትን ማጨናገፍ፣ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር ማድረግ፣ በአገሪቱ ውስጥ የርስ በርስ ጦርነት በመነሳት ሕዝባችን አቅመ-ቢስ እንዲሆን ማድረግ፣ ከውጭ ኃይሎች ጣልቃ-ገብነት ተነጥሎ በፍጹም የሚታይ ጉዳይ አይደለም። ስለዚህም ነው የውጭ ኃይሎች ቢያንስ የግንቦቱ 97 ዓ.ም ምርጫ ውጤት ከከሸፈ በኋላ ባለፉት 12 ዓመታት አገዛዙ የበለጠ ፀረ-ዲሞክራሲና ፀረ-ሕዝብ፣ እንዲሁም ፀረ-ዕድገት እየሆነ ሲመጣ ዝም ብለው የሚመለከቱት። ከአንድ ዓመት ጀምሮ የሚካሄደውን ሕዝባዊ ተቃውሞና አገዛዙ በሕዝባችን ላይ የሚያካሂደውን ፋሺሽታዊ ጭፍጨፋ ካለምንም ተቃውሞ ዝም ብለው የሚመለከቱት ወያኔ እነሱ የሚፈልጉትን ስራ ስለሚሰራላቸው ነው። ከዚህ ስነሳ የውጭ ኃይሎችን ሚና በሚመለከት በአገር ቤት ውስጥም ሆነ በውጭ አገር በሚንቀሳቀሰው ተቃዋሚ ነኝ በሚባለው ኃይል ዘንድ ከፍተኛ የግንዛቤ ጉድለት አለ። ጩኸትና ስለማዊ ሰልፍ ስለተደረገ፣ የመንግሥታትን ተጠሪዎች ወይም ፓርሊሜንቴርያኖችን ማነጋገር ስለተቻለና ግብዣም ተደርጎ ገለጻ ስለተሰጠ የውጭ ኃይሎች በአገዛዙ ላይ የፖለቲካዊና የዲፕሎማሲ ጫና ማድረግ የሚፈልጉና፣ ይህ አላዋጣ ሲል ደግሞ የኢኮኖሚ ማዕቀብ በማድረግ በአገዛዙ ላይ ግፊት ለማድረግ የሚችሉ የሚመስላቸው ብዙ የዋህ ኢትዮጵያውያን አሉ። ይህም የሚያረጋግጠው በአጠቃላይ ሲታይ ተቃዋሚ ነኝ የሚለው ኃይል በዓለም አቀፍ ደረጃ የተጨናገፉትን ዲሞክራሲያዊ እንቅስቃሴዎችና ለብሔራዊ ነፃነት የተደረጉትን ትግሎች በቅጡ እንዳልከታተለና ጉዳዩም እንዳልሆነ ነው። ስለሆነም በአገራችን የሰፈነውን ፀረ-ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትና ጭፍጨፋ ሌሎች የሦስተኛው ዓለም አገሮች ከሰፉኑ አምባገነናዊ አገዛዞችና የብዝበዛ ሥርዓቶች ጋር ማያያዝ ከተቻለና፣ ወደ ኋላ ተጉዞ ለዲሞክራሲና ለነፃነት የተደረጉትን ትግሎች መመርመር ከቻለ ምናልባት የተሻለ ስዕልና ግንዛቤ ማግኘት ይቻል ይሆናል።

ያም ሆነ ይህ ከላይ የተጠቀሰው በወያኔና በውጭ ኃይሎች መሀከል ያለው ግኑኝነት የኢምፔሪያሊዝም መግለጫዎች ሲሆኑ፣ ግኑኝንቱና በአገራችን የሰፈነው ጭቆናዊ አገዛዝ ከአሜሪካንና ከተቀረው የኢምፔርያሊስት ኃይሎች ትስስር ውጭ በፍጹም ሊታዩ አይችልም። ስለሆነም የአገራችንን በፓለቲካና በኢኮኖሚ እንዲሁም በባህልና በማህበረሰብ መዳከም ከውጭው ዓለም ጣልቃ-ገብነት ውጭ አውጥቶ ማየት ከፍተኛ የስትራቴጂ ስህተት ነው። እንደ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና የአውሮፓው አንድነት የመሳሰሉት የሦስተኛው ዓለም አገሮች በጥሬ-ሀብት አምራችነት ብቻ ተወስነው እንዲቀሩ የሚሰብኩና የሚደግፉ ድርጅቶች በመሆናቸው እነዚህን የመሳሰሉት ድርጅቶች የዲሞክራሲና የነፃነት አራማጆች ሊሆኑ በፍጹም አይችሉም። የተቃዋሚ ኃይሎች መሪዎች ነን የሚሉት ተጠሪዎች እዚህ አውሮፓ እየመጡ ለአውሮፓው አንዳንድ የፓርሊያሜንት ተጠሪዎች ገለጻ ሲያደርጉ የማይረዱት ነገር የአውሮፓው አንድነት አዲስ አበባ ውስጥ ትልቅ ቢሮ እንደሌለውና አገር ቤት ውስጥ ምን ነገር እንደሚካሄድ እንደማያውቁ አድርገው በመቁጠር ነው። እንደሚታወቀው የአውሮፓው አንድነት አዲስ አበባ ትልቅ ቢሮ ሲኖረው፣ ተጠሪዎቹም ከወያኔ ጋር ሽር ጉድ የሚሉና ከዚህ አንዳንድ ልዑካን በሚሄዱበት ጊዜ ልዩ ዐይነት መስተንግዶ ከሴት-ልጃገረዶች ጭምር የሚቀርብላቸው ናቸው። በዚህ መልክ ነው ወያኔ የውጭ ኃይሎችን የያዘውና በሕዝባቸን ላይ የሚቀልደው። ይህንን ጉዳይ በጥብቅ ለመከታተል የማይፈልገው ተቃዋሚ ነኝ የሚባለው ኃይል እዚህ እየመጣ እሮሮ ሲያሰማ በእርግጥም የአውሮፓውን አንድነት የዲሞክራሲና የብልጽግና አራማጅ አድርጎ በመቁጠርና የዋሁን ታዳጊ ወጣትና ሕዝባችንን በማታለል ነው።

ከዚህ ስንነሳ፣ ይህ ጸሀፊ በአሜሪካንና በተቀረው የካፒታሊስት አገሮች ላይ ግልጽ የሆነ ዘመቻ እንዲካሄድ ቅስቀሳ እንዲደረግ ባይፈልግም፣ መታሰብ ያለበት ጉዳይ የግዴታ ብሔራዊ ስሜት ያላቸውና የዕውነተኛ ዕድገት አጋዥ ኢትዮጵያውያን ራሳቸውን ማደራጀትና ማጠናከር አለባቸው ብሎ ያምናል። ይህ ካልተቻለ ደግሞ ምሁር ነኝ፣ የግዴታ የኢትዮጵያ ነገር ያገባኛል በሚለው ኃይል ዘንድ ግልጽ ክርክር መካሄድ አለበት። ሜዳው ዝም ተብሎ ለአሳሳች ኃይሎች መለቀቅ የለበትም። ይህንን ማድረግ ፀረ-ዲሞክራሲያዊ ድርጊትንና ኃይሎችን ማገዝ ብቻ ሳይሆን የድህነቱንም ዘመን እንዲራዘም አስተዋፅዖ ማበርከት ነው። አንድ አገር በግልጽና በድፍረት የሚታገልላት ምሁራዊ ኃይል ከሌላትና፣ የተወሰነው ኃይል የግንባር ቀደምትነቱን ቦታ ይዞ እዚህና እዚያ በመንቀሳቀስ ወጣቱን የሚያሳስት ከሆነ በቀጥታ ይህ ዐይነቱ ኃይል ጥቅሙ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር የተያያዘ አይደለም ማለት ነው። ስለዚህ መስመር መለየትና ግልጽ ውይይት ማድረግ የጊዜው አንገብጋቢ ጥያቄዎች ናቸው። ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ መሰረት የሌለው፣ ግልጽ ውይይ የማይደረግበትና፣ ሀቀኝነት የጎደለው ትግል የመጨረሻ መጨረሻ አንድን ሕዝብ ነፃ ሊያወጣውና ዲምክራሲያዊ ሥርዓት መስርቶ ዕውነተኛ ዕድገትን ሊያጎናጽፍ አያስችለውምና።

ፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር) This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ታህሳስ 26፣ 2016

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ