ይገረም አለሙ

የአቶ አሰፋን ነፍስ ይማር! በጥላቻ ለምንኖር የይቅርታ ልብ ይስጠን!

Assefa Chabo
አቶ አሰፋ ጫቦ

የት አባቱ ሞትም ይሙት!
እባካችሁ ዘመዶቼ ስሞት ሞትም አብሮኝ ይሙት
በሳቅ በደስታ ግደሉት
በሀሴት በእልልታ ውገሩት
ከአጥንት በታች ቅበሩት
እባካችሁ ለሞት የልብ ልብ አትስጡት
ናቁት አጥላሉት አውግዙት
በሙሾ ግነን አትበሉት
በሞቴ አታስደስቱት፣
(ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን)

የሰው መጨረሻው ሞት እንደመሆኑ ሞት በራሱ አያሳዝንም፣ አሟሟቱ እንጂ፤ ያለ ግዜው መቀጨት፣ በአሳቃቂ ሁኔታ መሞት፣ እውቀቱን፣ ልምዱን ችሎታውን ለአገር ጥቅም ሳያውል ወይንም ጀምሮ ሳይጨርስ መሞት ወዘተ ያሳዝናል። ያስቆጫል። ሟች በሕይወት በነበረበት ግዜ ለቤተሰቡ ምሰሶ ከሆነ ቤተሰቡ ለአንድ ሰሞንም ቢሆን ያዝናል። ለአገር ለወገን ጠቃሚ የነበረ ከሆነ ሕዝብ ያዝናል። በእኛ ባህል ደግሞ ሰው ሲሞት ክፉው ደግ፣ ጨካኙ ሩህሩህ፣ ንፉጉ ቸር፣ ፈሪው ጀግና ተደርጎ ይነገርለታል የሕይወት ታሪክ ተብሎ ይነበብለታል። ምን መጥፎ ቢሆን ሙት አይወቀስም። ሙት ወቃሽ አታርገኝ ይላሉ አበው።

የአቶ አሰፋ ጫቦ ሞት መርዶ የደረሰን ሕመማቸውን ሳንሰማ መሆኑ አስደንጋጭ ነበር፣ ገለጥለጥ በሚል ርዕስ January 12, 2017 በጻፉት ጽሁፍ “ያጋራ ቤታችንን” ጨርሼ በ10 ቀን ውስጥ አደባባይ አዋጣለሁ። አማራና ኦሮሞ የሚመለከት ነው የሚል Facebook ላይና ሌላም ቦታ ጠቃቀስኩ። ይህ እርግማንና ዘለፋ የተጀመረው ገና ባልታየ፤ ባልተነበበ ጹሁፍና አስተያየት ላይ ነበር። ያ ነው ይበልጥ የገረመኝ። ከማንውቀው ይሰውረን ማለት ይሆን? ከምናውቀው ግን ከሸሸነው እውነት ሰውረን ነው? አውቀን የካንደነውን እውነት አታስታውሰን ማለት ይሆን? ይህንን ደህና ያጧጧፍነውን ሥራና ገበያ ይሻማብናል ማለት ይሆን? ሥራ ያሰኘኝ በተለየ አንዳንድ ዲያስፖራው ኗዋሪዎች መተደዳደሪያም ወደ መሆን የተቃረበ የሚያስመስል ፍንጭ ስለሚታይ ነው። በተፈጠረው የሕዝብ አመጽ ሳቢያ ታዋቂ ሆነን፤ አገር አውቆን፣ ፀሐይ ሞቆን፤  አንቱ የተባልንበትን ልታፈርስብን ነው የሚል ስጋት ፈጥሮ ይሆን? የሚል መላ ምት ይፈጥራል።” ብለውን ስለነበር 10 ቀኑ አልፎ ወራቶች በመቆጠራቸው አቶ አሰፋ የነገሩንን ምነው አዘገዩት የሚል ጥያቄ ለመሰነዝር ዛሬ ነገ እያልኩ ባለሁበት ሰአት ነበርና ሞታቸውን የሰማሁት በጣም ነው የደነገጥኩት።

ከአቶ አሰፋ ጋር ያስተዋወቀችን ጦቢይ መጽሄት ከአስር አመት በፊት ሞተች፣ እነሆ ዛሬ ደግሞ በጦቢያ ያወኩት ያለፈበትን በድፍረት ይነግረን በጽሁፉ እንደ የፊልምና የትያትር ያህል ነገሮች በአይነ ህሊናችን ለማየት ያስችለን የነበረው ሰው የብእሩ ቀለም ሳያልቅ ሳይነጥፍ ብእር የሚጨብጠው እጁ በሞት ተሸነፈ። ቋሚ የእርሱም ወር ተራ እስኪደርስ ሟችን ሸኝቶ ነብስ ይማር፣ ቤተሰብና ወዳጅ ዘመድን አግዚአብሄር ያጥናችሁ ማለት ነውና ወግ ልማዱ ነብስ ይማር!

የአቶ አሰፋ ጫቦ ሞት ዜና ከናኘ በኋላ ኢሳት ያነጋገራቸው አቶ ያሬድ ጥበቡ የተናገሩት ደግሞ በሁለት መንገድ በጣሙን የሚያሳዝንና በኢትዮጵያዊነት የሚያሳፍር ሆኖ ተሰማኝ። አንደኛው አቶ አሰፋ ታመው ሆስፒታል ተኝተው የሚጠይቃቸው ቀርቶ ታመው መተኛታቸውን ለወዳጅ ዘመድ የሚነግር ሰው መጥፋቱ ሲሆን፣ ሁለተኛውና ይበልጥ አሳዛኝና አሳፋሪው ነገር ለዚህ ምክንያት የሆነው እንደ አቶ ያሬድ ጥበቡ አገላለጽ የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት መሆኑ ነው። አንደኛ የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት የአንድ አገር ልጆችን እዚህ ደረጃ ማደረሱ ሁለተኛ ደግሞ ከአርባ አመት በላይ ቆይቶ አለማርጀቱ ያ ትውልድን የሚያስወቅስ መድረኩ ቢገኝም የሚያጠያቅ ይመስለኛል።

አቶ ያሬድ እንደነገሩ አቶ አሰፋ የተኙበት ሆስፒታል በሚገኝበት ከተማ የሚኖሩት በአብዛኛው ኢህአፓ የነበሩ ሰዎች ናቸው፣ እግዜር ይማርህ ባይሉዋቸውም የሞታቸው ዜና የተነገረው በእነዚሁ ኢህአፓዎች ነው። አቶ አሰፋ ኢጭአት እንደነበሩ ነው የሚታወቀው። ሁለቱም በግዜው ሥልጣን ላይ የነበረው ደርግ ተቀዋሚዎች ነበሩ። ዛሬ ሲቃወሙት የነበረውም ደርግ እነርሱ የተሰለፉባቸው ፓርቲዎችም (ኢህአፓም፣ ኢጭአትም፣ መኢሶንም፣ ወዝ ሊግም፣ ማልሬድም) የለሙ፣ ነገር ግን ሰዎቹ ቢያረጁም የጥላቻ ስሜታቸው አላራጅ ብሎ እስከ ሞት አብሮአቸው ይኖራል። በሁለት የተቀዋሚ ፓርቲ አባላት መካከል እዚህ ደረጃ የደረሰ እድሜ የማይሽረው ጥላቻ ከተፈጠረ በወያኔና በተቀዋሚዎች መካከል ያለው ሁኔታ ሊደንቀንም ሊያስገርመንም አይችልም። ግን የሳዝናል ያሳፍራል። ለመሆኑ ይህ መጠላላት ፋይዳው ምንድን ነው? ለማነውስ የሚጠቅመው? ምንድስ ነው ጥቅሙ? መስዋዕትነት ከፍለንለታል ለሚሉት በነበር ለሚያስታውሱት ዓላማቸውም ሆነ ምን አልባት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ይመኙ ያስቡ ከሆነ ለዛ የሚያበረክተው አስተዋጽኦስ አለ?

ከወያኔ ጋር እርቅ እያሉ ከማላዘን ይህን እንደ መልካም ነገር ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ ያለ እርጅና የማያስረጀው ስደት የማያስቀረው የአንድ አገር ልጆችን ለክፎ መድኃኒት ያልተገኘለት መጥፎ በሽታ ጸብና ቁርሾ ማስወገዱ ነበር ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ የሚሻለውም። ከእነ ጥላቻችሁ ወደ ሞት ከምትሄዱ በመጨረሻው ሰዓትም ቢሆን ይቅር ተባባሉ።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ