የሺሀሳብ አበራ (አማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት)

Dr. Abera Molla
ዶ/ር አበራ ሞላ

መስከረም ጠብቶ አደዩ ሲፈነዳ፣ ከሚመጡ የመስከረም ትዝታዎች አንዱ ወደ ተማሪ ቤት ማዝገም ነው። ለምን መስከረም ግን ሁሌ እንደ ወር ህፃን ይጠባል? ጡት አይተውም እንዴ ብሎ የሞገተ ማን ነበር? መስከረምማ ገና እንቡጥ ነው።

ህፃን መስከረም እንጂ አሮጌ መስከረም የለም። መስከረም ተስፋን፣ ምኞትን፣ ሀሳብን ጠብቶ ያድጋል። የሀሳብ እንገር ይመገባል። የአማርኛ ቋንቋ በቅኔ የተዘነቀ በመሆኑ መጥባት ለመስከረም መንጋት ነው። ሌሎች ወራቶች ጨለማ ነበሩ ባይ አይጠፋም። ጥርጣሬ፣ ተጠራጥሮም መጠየቅ የፍልስፍና መጀመሪያው ምዕራፍ ነው ብለዋል አንደበተ ርዕቱው ፈላስፋ የኛው ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ። አማርኛ ቃላት አማራጭ አላቸው። ባማራጭ ውስጥ ፍልስፍና ይፈሳል። የኛ ፍልስፍና ቅኔ ነው።

አማርኛን በኮኒቲከት ዩኒቨርሲቲ አሜሪካ ማስተማር ጀምራለች። በአሜሪካ የአማርኛ ቋንቋ ፕሮጀክት አስተባባሪው ፕሮፊሰር አማኑኤል አናግስቶ አማርኛን ለማስተማር 4.3 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር እንደተመደበ የዩኒቨርሲቲው ድረገፅ አስነብቧል። አሜሪካ በምድሯ ከ 500 ሺ በላይ ተናጋሪ ላለው ቋንቋ ለተጨማሪ የስራ ቋንቋነት ታጫለች። አማርኛ ከ 10 ዓመት በፊት ታጭቶ በተለያዩ ግዛቶች የስራ ቋንቋ ከሆነ ቆይቷል። ዕድሜ ለዲያስፖራዎቻችን አያ!!! እስራኤልም አማርኛን በስራ ቋንቋነት ልትጠቀምበት ጥናቷን ጨርሳለች።

መስከረም ሊጠባ አካባቢ ከአደይ አበባው እኩል የተስፋ ገብረሥላሴ የፊደል ሠራዊት ከተማውን በቁጥጥር ስር ያውለዋል። በተለያዩ ከተሞች እንደቃኘሁት የመስከረምን መባት አስመልክቶ ፊደላት ለልጆች እንደ ታጠበ ሸማ ተሰጥተዋል። ተስፋ ገብረሥላሴ ዘብሔረ ቡልጋ … ቆይ እዚህ ፍሬም እንጨብጥማ። ቡልጋ የዛኔ ብሔር ነበረች? አፈወርቅ ገብረእየሱስ ዘብሔረ ዘጌ ከጣና ተሻርካ የተቀመጠችው ዘጌም በወቅቱ ብሔር ነበረች? ብሔር፣ ብሔረሰብ እና ሕዝብ ምነው ልዩነቱ? ትርጉሙ ላይ ብዙ ስምምነት የለም። በነዚህ ጉዳዮች ዙሪያ ከርሞ እልል ያለች ሀሳብ ይዠ እመጣለሁ። ከርሞ ስላችሁ ከሰዓታት በኋላ ማለቴ ነው። አሁን የምፅፍበት ሰዓት አምና፣ አሮጌው ዓመት ሊባል እኮ ነው። ሁሉም ያልፋል፣ ለሁሉም ጊዜ አለው ይላል ጠቢቡ ሰለሞን። ግን የኛው ከበደ ሚካኤል ጠቢቡ ሰለሞንን ሁሉም ካለፈ፣ ለሁሉም ጊዜ ካለው ሞት ራሱ መቸ ያልፋል? ሞት የሚሞትበት ጊዜ መቼ ነው? ሲል ይጠይቃል። ሰለሞኑን አንደበቱን ሞት ስለያዘው ለከበደ ሚካኤል ምላሹን አላቀረበም።

ተስፋ ገብረሥላሴ ፊደላትን በወረቀት ላይ በመሰደር የሚታከላቸው የለም። ከሸዋ መንደር ሳልወጣ ዶክተር አበራ ሞላን ሳልጠቅስ ባልፍ የምኒልክ መንፈስ ይወቅሰኛል። ዶክተር አበራ ሞላ የተስፋ ገብረሥላሴ የፊደል ሠራዊት ወደ ኮምፒውተር ያዘመቱ የፊደል ጀኔራል ናቸው። ዶክተሩ፣ የዘመን መቁጠሪያችንን እና ሌሎች እንግዳ ጉዳዮቻችንን ወደ ኮምፒውተር መንደር ያለምንም መሸራረፍ
አስፍረውልናል።

ዶክተር አበራ ሞላ የግዕዝ ፊደላት በኢትዮጵያ ይመዝገቡ ሲሉም 30 ዓመታት አልፈዋል። አሜሪካ ምኗ ሞኝ ሆነና!! የፊደላትን የኮምፒውተር አጠቃቀም በተመለከተ ለዶክተር አበራ የፈጠራ ባለቤትነት መብት ሰጠች። ድሮም አሜሪካ ለዶክተር አክሊሉ ለማም የእንዶድን የቢልሃርዚያ ቁጥጥርን በተመለከተ የፈጠራ ባለቤትነት መብት የሰጠች አሜሪካ ናት። የጤፍ እንጀራ አዘገጃጀት በተመለከተ የፈጠራ ባለቤትነቱ መብት ሰጭ አሜሪካ ናት።

ዩኒቨርስቲዎቻችን እንኳን ቢያንስ የክብር ዶክትሬት መስጠት ነበረባቸው። ለማንም እያፈሱ ከሚሰጡ ለሕክምናው ዓለም ፈርጥ እና የፊደል የኮምፒውተር ቴክኖሎጂ አስተዋዋቂ ለሆኑት ለዶክተር አበራ የክብር ዶክትሬት ቢቸሯቸው ስራቸውን ለመረከብ መንገድ ይጠርጋል።

አዲሱ ዓመት የአሮጌው ዓመት ባለዕዳ እንደሆነ ውስጤ ቢረዳም፣ ለአባባል ያህል ግን አዲሱ ዓመት አዲስ ይሁንልን!!!

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ