20210302 adwa

PM Abiy Ahmed

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ

አብርሃም አየለ

እንዳልካቸውን የሚሰማቸው አላገኙም። የተቃውሞው አድማስ እየሰፋ በተለያዩ የሕብረተሰቡ ክፍሎች ቀጠለ። ለዚህም ተቃውሞ ኢሕአፓ፣ መኢሶንና ሌሎችም የተቃዋሚ ቡድኖች በተቀጣጠለው ተቃውሞ ላይ ቤንዚን በመጨመር አጋጋሉት። ነገሩ ያላማረውና አመጣጡም ሆነ አመላካች ግቡ መልካም ሆኖ ያልታየው እውቁ ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ ዋና አዘጋጅ በሆነበት አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ “ማንም እየተነሳ ቱግ ማለቱን ትቶ አርፎ ሥራውን ይሥራ” የሚል አስተያየት ሰነዘረ። ከዚህ ሐሳብ በተፃራሪ የቆሙት የወቅቱ ‘ተራማጆች’ ጋዜጠኛው የሰጠውን ምክር አዘል አስተያየት በማጣጣል “እርስዎንና መሰሎችዎን ያስደንግጥ እንጂ …” በሚል ሐተታ የተያዘው የለውጥ ሂደት የዘመናት የትግል ውጤት እንደመሆኑ እየተጋጋለ እንደሚቀጥል በተለመደው በራሪ ወረቀት ይገልጻሉ። ፋታ የጠየቁት ጠቅላይ ሚንስትር ጥያቄያቸው ሰሚ ባለማግኘቱ ‘የዘመናት የትግል ውጤት’ የሆነው መንፈስ አሸንፎ እሳቸውም እስር ቤት ይገባሉ። ከዚያም የምናውቀው ሆነ።

ነገሩን ለማሳጠር የዚሁ እንቅስቃሴ ድምር ‘ደርግ’ የሚባለውን ዲያቢሎሳዊ ስብስብ ለሥልጣን አበቃ። በዚሁ ስብስብ የተገደሉትን የሁለቱን ሊቀ መናብርት ማለትም የሌ/ጀነራል አማንና የብ/ጄነራል ተፈሪ ባንቲን የሥልጣን ዘመን በመቀነስ ቀሪውን የደርገ ቆይታ ሌ/ኰሎኔል መንግሥቱ ኃ/ማሪያም ደርግ ወደ መቃብር እስከተሸኘበት ድረስ ፈነጩበት። ኢትዮጵያ በታሪኳ አይታ የማታውቀውን የእርስ በእርስ እልቂትን በመሪ ተዋናይነትም አስተናገዱ። ጨካኙ መንግሥቱ በጭፍጨፋቸው የቀራቸው የሕብረተሰብ አካል አልነበረም። ሕፃኑ፣ ወጣቱ፣ ጎረምሳው፣ ተማሪው፣ ወታደሩ ሠራተኛው ፆታና ዕድሜ ሳይለዩ ፈጁት። ለሥልጣናቸው ማብቃትና ለሳቸውም አገር ጥሎ መፈርጠጥ ዋናውና አንኳር ምክንያት ይሄው ገደብ የለሽ ግድያቸው እንደሆነ ምንም አያጠራጥርም።

‘ፋታ’ ወደተነፈጉት ጠቅላይ ሚ/ር እንዳልካቸው መኰንን እንመለስ። በወቅቱ እኝህ ሰው በነበራቸው የትምህርትና የሥራ ተሞክሮ ሁኔታዎች ተመቻችቶላቸው ሥራቸውን ቀጥለው ቢሆን ኖሮ - የነጭና ቀይ ሽብር ተብሎ ስም የወጣለት እልቂት ይካሄድ ነበር? ከኤርትራ ጋር የተካሄደውና ለብዙ ወገኖች (ኢትዮጵያም ኤርትራም) እልቂትና ለአገራቱም መድኅን ሊሆን ይችል የነበረው የኤኮኖሚ ውድመት ይፈፀም ነበር? ለዚች ድሀ አገር በተለያየ መልኩ ቤዛ ሊሆኑ ይችሉ የነበሩት የጦርና የሲቪል ባለሥልጣናት እንዲሁም ወጣቶች በአሰቃቂ ሁኔታ ይገደሉ ነበር? በአጠቃላይ ለማስቀመጥ በሌ/ኰሎኔል መንግሥቱ ዘመነ መንግሥት የተካሄዱት ሌሎች ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመቶች ተግባራዊ የማይሆኑበት እድል የሰፋ እንደነበር መገመት ይቻላል።

አገራችን ወደ አለችበት ወቅታዊ ሁኔታ ስንመለስ፤ ወጣቱና አንደበተ ርቱዕ ጠቅላይ ሚንስትር ጅማሯቸው መልካም ነው። በሂደት ሊያሻሽሏቸው የሚገቡ ጉዳዮች እንዳሉ ይታመናል። ሆኖም፤ በአጭሩ የሥልጣን ዘመናቸው ብዙ አመርቂና አስደናቂ ተግባራትን አከናውነዋል። ይህንኑ በአጭር ለመግለጽ፤ በሕይወት እናገኛቸዋለን ብለን ያላሰብነውን የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ፣ በጦርነት ፍጥጫ የነበሩትን ኤርትራንና ኢትዮጵያን ሰላም እንዲያሰፍኑ፣ በተለያዩ የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ሰብአዊ መብታቸው ተጥሶ በአሰቃቂ ሁኔታ ይገኙ የነበሩ ወገኖቻችንን ከራሳቸው ጋር ይዞ በመምጣትና ከዚያም ሕጋዊ በሆነ መልኩ መብታቸው እንዲጠበቅ ማድረግ፣ ሌሎች ሌሎችንም አድርገዋል። እኝህን መሪ ከማደንቅበት እንዱ ምናልባትም ዋናው ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊያን የሰጡትን ክብር ነው። ባለፉት አርባ ያህል ዓመታት የኖርንበት ድባብ፤ ቀይ ሽብር፣ ነጻ እርምጃ፣ እጅ ይቆረጣል፣ አስፈላጊው እርምጃ ይወሰዳል፣ ወዘተ እየተባልን የኖርን ዜጎች ዛሬ አገራችንና ሕዝቧን ከፍ ከፍ የሚያደርግ መሪ ስናገኝ የፈጣሪ ፀጋ ነው ከማለት ውጭ ሌላ ምን ማለት ይቻላል? አገራችን ሰላም የሰፈነባት ሆና ለዘመናት በማኅበራዊ ኑሯችን፣ በኤኮኖሚና በፖለቲካውም ምኅዳር የተረጋጋች እንድትሆን ይህንን እድል በአግባቡና በሰከነ ሁኔታ ልንንከባከበው ይገባል። ይህንንም ስናደርግ አግባብ በሆነና በሠለጠነ መንገድ አስተያየት በመስጠት መሆን እንዳለበት በማመን ነው።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ወደ ሥልጣን ሲመጡ የተረከቧት አገር፤ በሚያሳዝን ሙስና የተዘረፈች፣ በሚያሰቅቅ ሁኔታ የሕዝቡ ሰብአዊ መብት የተጣሰበት፣ ስልታዊ በሆነ መንገድ ሕዝቡ በዘርና በጎሣ እንዲከፋፈል የተደረገበት፣ የውጭ ምንዛሪም ሆነ የአገሪቱ የፋይናንስ አቋም የተመናመነበት፤ ምናልባትም የተሟጠጠበት እንደሆነ ግልጽ ነው። በሜቴክ፣ በሕዳሴው ግድብ፣ በልማት ባንክ፣ ባልተገለፀው ኤፈርትና በሌሎችም የደረሰውን ዝርፊያ ስንመለከት አገሪቱ አገር ሆና መቀጠሏም የሚገርም ሆኖ እናገኘዋለን። ይህን በመሰለ አቋም የምትገኝን አገር እንኳን በአንድ ዓመት ከዚህ በኋላ በሚገኙ ብዙ ጊዜያትም እንኳን ማስተካከል ከተቻለ የሚደነቅ ይሆናል።

በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች የመፈናቀልና የጦርነት ችግሮች አሉ። ይህም ለሃያ ሰባት ዓመታት የተዘራው የተንኮል አዝመራ ውጤት ለመሆኑ እማኝ መቁጠር አስፈላጊ አይሆንም። ይህን ከመሰለው እኩይ ሰቆቃ ለመታደግ የምንወስዳቸው ርምጃዎችና የምንሰጣቸው አስተያየቶች እንዲሁም ምክር የሰከነና በጥበብ የታጀበ መሆን ይኖርበታል።

የሶሻል ሚዲያውን ለጊዜው ወደ ጎን በማለት (በዚህ መድረክ ላይ የሚሳተፉት በአብዛኛው የአገራችንን ሰላም የማይፈልጉ ምንደኞች በመሆናቸው)፤ አንዳንድ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችና የግል ጋዜጦች/መጽሔቶች ላይ ወቅታዊ ሁኔታችን ባላገናዘበ መልኩ በጠቅላይ ሚኒስትሩና በአስተዳደራቸው ላይ የሚሰነዝሩት አንዳንድ አስተያየትቶች ከመስመር የወጡ ሆነው አግኝቼቻዋለሁ። የኢሳት የተወሰኑ ጋዜጠኞች የሚወረውሯቸው ቃላትና አስተያየቶች - ምን ነካቸው? ያሰኛል። አሁን አሁንማ ብዙ የኢሳት ወዳጆች የነበሩ ወዳጆቼ ‘አይ ኢሳት በቃኝ’ ማለት ከጀመሩ ሰነባብተዋል። የጣቢያው አስተዳደርም በዚህ ጉዳይ ላይ ለሕልውናው መቀጠል ሊያስብበት ይገባል። አቶ ኤርምያስ ለገሰ ጠቅላይ ሚንስትሩ የኢንሳ ባልደረባ በነበሩበት ወቅት ይህን አደረጉ፣ ይህን ፈጸሙ እያለ ብዙ ለመናገር ያደረገው ሙከራ አግራሞት ጭሮብኛል። የግለሰቡ አነጋገርና የሰውነት እንቅስቃሴ ሐሳብ የሚሰነዝር ብቻ ሳይሆን የተለየ ተልእኮ ያለው ያስመስላል። እንዲያው ነገርን ነገር ያነሳዋልና፤ ያገለገለውን ኢሕአዴግን ከመክዳቱ በፊት ራሱ በጻፈው ‘የመለስ ትሩፋት’ ገጽ I ላይ፤ “በኢሕአዴግ የፖለቲካ ጎዳና በአባልነት፣ በመካከለኛና ከፍተኛ ካድሬነት ከ12 ዓመታት በላይ አገልግሏል” በሚል ተገልጿል። እንግዲህ ኢሕአዴግን ስናውቀው ካድሬ ማለት ምን ማለት እንደሆና የአርባ ዓመታት ተሞክሯችን እንደሚነግረን አቶ ኤርምያስ በእነዚህ ጊዜያት ለኢትዮጵያ ሕዝብ እርጥብ ቄጤማ እንዳላነጠፈለት የምንገነዘብ ይመስለኛል። ‘በሌላው ዓይን ውስጥ ያለውን ጉድፍ …’ እንዲል መጽሐፉ፤ መጀመሪያ ራስንም መመርመር ጠቃሚ ይሆናል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ያሉበት ሁኔታ፤ የገናውን ዳቦ ያስታውሰኛል። የታወቁት ጠላቶቻቸው የማይሸርቡት ተንኮልና ሴራ የለም። ሊደግፏቸው የሚገቡት ደግሞ እንዲሁ የሆነውንም ያልሆነውንም እያነሱ ችግር አብቃዮች ሆነዋል። ለእኝህ ሰው በተቻለ መጠን ድጋፋችንን ሳናቋርጥ፤ አስፈላጊና ጠቃሚ በሆኑ ጉዳዮች ላይ አስተያየት/ምክር እየሰጠን ወደቀናው መንገድ በጋራ ብንጓዝ አገራችንንም ወገናችንንም እንጠቅማለን። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሥልጣን በተረከቡበት ዕለት ከአደረጉት ንግግር የሚከተለውን በመጥቀስ ልሰናበት፤

በታሪካችን በተለያዩ አጋጣሚዎች አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ የመጀመር እድሎችን አግኝተን ብዙዎቹን በወጉ ሳንጠቀምባቸው አምልጠውናል። አሁንም፣ ይህ የሥልጣን ሽግግር አዲስ ምዕራፍ የምንጀምርበት ሌላ ታሪካዊ እድል ነው። በመሆኑም በከፍተኛ ስሜት ልንጠቀምበት ይገባል …ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!