እስክንድር ነጋ (አዲስ አበባ)

ዘንድሮ ዲሽ በየደሃው ቤት እንኳን ዘልቆ ገብቷል። ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን መደበቂያ መሆኑ ነው እንጂ፣ ብዙሃኑ ህዝብ እንግሊዝኛውንም ሆነ አረብኛውን አይሰማም። አበው፣ «የቸገረው እርጉዝ ያገባል» እንዲሉ፣ በኢቲቪ ከመጨቅጨቅ ከአረብ ሳት ምስሎች ጋር መፋጠጡን መርጧል። የሚባለው ለምናባዊ ጨዋታ (imaginative conversation) የሚተው ነው። አስቂኝም አሳዛኝም ነው። ህዝብ የሀገሩ ባለቤት ሳይሆን እንዲህ ነው። ትራጂ ኮሜዲ ይሉታል ፈረንጆች። እየሳቁ ማልቀስ ማለታቸው ነው። ይህን ይመስላል የኢትዮጵያዊያን ኑሮ፤ በዘመነ ኢሕአዴግ።

 

እድሜ ለደጓ እናቴ (ነፍሷን ይማረውና)፣ እኔ እንግሊዝኛ በመጠኑ ከሚያወቁት መካከል አንዱ ነኝ። ዲሽ ማሳደድ የጀመርኹት ገና ድሮ ነው፤ ሲ.ኤን.ኤን ብቻ በነበረበት ዘመን። መጀመሪያ የገባው ሂልተን እንደነበር አስታውሳለኹ። በጣም ብርቅ ነበር። በኋላ ላይ ትላልቅ የመንግሥት ሆቴሎችም እየተንጠባጠቡ አስገቡ። እፎይ አልን። ሂልተንን ትተን የሸበሌ ደንበኛ ሆንን። የሂልተን ዋጋ በእጅጉ አማሮን ነበር።

 

ሸበሌ በፍንዳታ እንደተመታ የሰማኹ ግዜ ክው ነበር ያልኹት። በርሬ ሄድኹኝ፡፡ እንደጠረጠርኹት ነበር። የተመታው ቡና ቤቱ ነበር፤ ቁጭ ብለን ዲሽ የምናይበት። የእግዜር ፍቃድ ነበረና፣ ከሞት ለትንሽ አመለጥን። አንድ የማውቀው ሰው በፍንጣሪ መመታቱን ሰማኹ። ልጆች አሉት። ደግነቱ ሳይሞት ቀረ። ሌሎች የማላውቃቸው ሰዎች ግን ያቺን ቀን አላለፏትም፤ ተቀሰፉ። እነሱ አንደኛውን አረፉት፣ ለቤተሰቦቻቸው ግን ለማይረግብ ሀዘን የመጀመሪያ ቀን ሆነች።

 

ያን ቀን በጊዮን ሆቴልም ተመሳሳይ ፍንዳታ ተከስቷል። ከዚያ በኋላ፣ ፒያሳ የነበረውን ትግራይ ሆቴል አስታውሳለኹ። ከምርጫ 97 በኋላ ደግሞ፣ ታክሲዎችና አውቶብሶች ላይ የተጠመዱ ፈንጂዎች የንፁሃንን ህይወት ቀጥፈዋል።

 

የጭካኔ ድርጊቶች እንደነበሩ አያነጋግረንም፡፡ ዒላማቸው ሰላማዊው ህዝብ ነበር። እንደ እኔ አይነቱን። ይሄ ነው ሽብርተኝነት ማለት። አስረጅ አይፈልግም፡፡ ምሁርነትን አይጠይቅም። ትንታኔ አያስፈልገውም። ለህፃኑም ለትልቁም፤ ለመሃይሙም ለምህሩም፤ ለከተሜውም ለገጠሬውም፤ ለሴቱም ለወንዱም ቁልጭ ብሎ የተቀመጠ ነው።

 

ሰላማዊውን ህዝብ ቀጥተኛ ዒላማ አድርገው የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች አሉ። ዋነኛው የቢንላዴኑ አልቃይዳ ነው። ፖለቲካዊም ኃይማኖታዊም ምክንያት ያቀርባል። ከፖለቲካው አኳያ፣ አሜሪካዊያን በፈቃዳቸው ያቆሙት መንግሥት የሙስሊሙን ዓለም እስከጨቆነ ድረስ፣ እያንዳንዱ የአሜሪካ ዜጋ ተጠያቂ ነው የሚል አቋም አለው። ስለዚህም፣ የታጠቀውም ያልታጠቀውም አሜሪካዊ ዒላማ ነው። በኃይማኖት በኩል፣ በጅሃድ ጊዜ ሙስሊም ያልሆኑትን መግደል ይቻላል ብሎ ያምናል። አልቃይዳ ደግሞ ጀሃድ ላይ ነው። የዚህ ሁሉ ድምር የኒዮርክ መንትዬ ሕንፃዎችን ጥቃት አስከትሏል። 3000 ንፁሀን ረገፉ።

 

ኢትዮጵያ፣ አልቃይዳን በሕግ በሽብርተኝነት ለመፈረጅ 10 ዓመታት ፈጅተውባታል። በመጀመሪያዎቹ 8 ዓመታት የፀረ ሽብርተኝነት ሕግ አልነበራትም፡፡ በ2001 ዓ.ም በቁጥር 652 የፀረ ሽብርተኝነት ሕግ አፅድቃለች። ከሁለት ዓመታት በኋላ፣ ባለፈው ሳምንት፣ በአዋጁ ምዕራፍ 2፣ ንዑስ ቁጥር 4 መሠረት አልቃይዳ በሽብርተኝነት በይፋ ተሰይሟል።

 

ማናቸውም ሰው የዚህ ድርጅት አባል ሆኖ ከተገኘ፣ ከ5 እስከ 10 ዓመታት በሚደርስ ፅኑ እስራት ይቀጣል። በአመራርነት ለሚሳተፉት ቅጣቱ ከበድ ይላል፤ መነሻውን 20 ጣራውን እድሜ ልክ አድርጎታል።

 

አልቃይዳ ግን ኢትዮጵያ መጥቶ አያውቅም። የመምጣትም ፍላጎት የለውም። እልሁ በዋናነት ከአሜሪካዊያን ጋር ነው። ወረድ ሲልም በደፈናው ምዕራባዊያንን በጅምላ ይጠላል። ኢትዮጵያ የግርጌ ማስታወሻው ነች። ለዚህም ያበቃት ሱማሌ ውስጥ የአሜሪካ ጉዳይ አስፈፃሚ ናት ተብላ ነው።

 

ለግዜው፣ አልቃይዳ ለግርጌ ማስታወሻዎቹ ትኩረት መስጠት የሚችልበት ወቅት ላይ አይደለም። ከአሜሪካ ጋር የሞትና የሽረት ትንቅንቅ ላይ ነው። ባለፈው ሰሞን፣ በቢላደን ሞት አናቱ ተቆርጧል። በሞትና በሽረት መካከል እየተላተመ ነው ማለት ይቻላል። ድርጅቱን ይሄኔ በአሸባሪነት መፈረጅ፣ «ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ» እንደሚሉት ያደርገዋል፡፡ ፋይዳው የት ላይ እንደሆነ ግልፅ አይደለም።

 

ከአልቃይዳ ሌላ፣ 4 ድርጅቶች የአሸባሪነት ካባ ደርበዋል።

 

አንዱ፣ የአልቃይዳን ያህል ባይርቅም፣ ኢትዮጵያዊ ድርጅት አይደለም። የጎረቤት ሀገር ሱማሊያ አልሸባብ ነው። ብሔርተኝነትና ኃይማኖትን አደበላልቆ የሚንቀሳቀስ የታጠቀ ኃይል ነው። ጥንስሱም፣ ውልደቱም፣ እድገቱም ለ1998ቱ የኢሕአዴግ ወረራ ሀገር በቀል ምላሽ ሆኖ ነው። ወረራው ባይኖር አልሸባብ ባልተፈጠረ ኖሮ። የኦባማ አስተዳደር ወረራውን ስህተት ነበር የሚለው ለዚህ ነው። መዘዙ ለአሜሪካን ተርፏታል።

 

ለአልሸባብ፣ ከኃይማኖት ይልቅ ፖለቲካ (ሀገርን ከወረራ መከላከል) ዋነኛው መገለጫው ነው። ሆኖም፣ የኢትዮጵያ ጦር ከወጣ በኋላ ኃይማኖታዊ ገፅታውን ለማጉላት ታግሏል። አዲስ ሀገራዊ አጀንዳ ፍለጋ መሆኑ ነው። እንደ ኢሕአዴግ ወረራ ግን፣ ሕዝብን ሊያሰባስብለት አልቻለም። አልሸባብም እንደ አልቃይዳ እየተንገዳገደ ነው። ኢትዮጵያን ለማጥቃት የሚያስብበት ጊዜ ላይ አይደለም ያለው። በዚህ አጋጣሚ፣ በሽብርተኝነት መፈረጁ ጥቅሙ የጎላ አይደለም። እንዲያውም፣ በተቃራኒው፣ ተስፋ እየቆረጡ ያሉትን አባላቱን ማነቃቂያ ሊሆነው ይችላል።

 

በሶስተኛነት፣ ኦነግ በሽብርተኝነት ተፈርጇል። እንደ ኢሕአዴግ ከሆነ፣ ከ1987 እስከ 2000 ዓ.ም ድረስ 106 የሽብር ጥቃቶችን ፈፅሞ፣ 56 ዜጎች ሞተዋል። 284 ደግሞ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ከ2000 በኋላ ስላለው ጊዜ ምንም የተባለ ነገር የለም።

 

ኦነግ የተቋቋመው በ1967 ዓ.ም ነበር፡፡ ዘንድሮ 36 ዓመታትን አስቆጠሯል። 16ቱ በደርግ ዘመን መሆኑ ነው። ጦርነት ላይ ነበር። ወደ መጨረሻው፣ በብርጌድ ደረጃ እስከመዋጋት ደርሶ ነበር። አንድም ጊዜ ግን፣ ከተማ ውስጥ ፈንጂ በማፈንዳት ተወንጅሎም ታምቶም አያውቅም።

 

በ1984 የሽግግር መንግሥቱን ጥሎ ከወጣ በኋላ በለስ አልቀናውም። ነፃ መሬቶቹን አጥቷል። ሰራዊቱ ተመናምኗል። ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴውም ቀዝቅዟል። አመራሩም ተከፋፍሏል። ከዋናው አካል የተገነጠሉ አንድ ሁለት አንጃዎችም ተፈጥረዋል። እነዚህ አንጃዎች ሰላማዊ ሰዎችን ኢላማ እስከማድረግ እንደደረሱ ይታማሉ። የሽብርተኝነቱ ፍረጃ፣ ይህንን እውነታ ሆን ብሎ ግምት ውስጥ ያላስገባ ነው።

 

የኦነግ ድርጅታዊ መዳከም እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ፖለቲካ ተቀባይነቱ አሁንም ድረስ የገዘፈ ነው። ኦነግን ያገለለ የተሟላ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ሊኖር አይችልም። የኦነግን ችግር መፍታት የሚቻለው በፖለቲካ ነው። ለፖሊስም ሆነ ለሠራዊቱ የሚተው አይደለም። በሽብርተኝነት በመፈረጅ በሚሊዮኖች እንደሚቆጠሩ ከሚገመቱት ደጋፊዎቹ ልብ ውስጥ ፈንቅሎ ማውጣት አይቻልም። ትርፉ፣ በሰላማዊው በር ላይ በርን መዝጋት ብቻ ነው የሚሆነው፡፡

 

በአራተኛነት የተፈረጀውን ኦብነግንም በአዋጅ ማጥፋት አይቻልም፡፡ እዚህም ያለው የፖለቲካ ችግር ነው፡፡ መፍትሄውም ፖለቲካዊ ብቻ ነው፡፡ ፍረጃው ሀገሪቷን ወደዚያ አያቀርባትም፡፡ ደርግ፣ በኤርትራ የሰራውን ስህተት ኢሕአዴግ በኦጋዴን ሊደግመው አይገባም፡፡ የኢትዮጵያ አንድነት ታላቁ ፈተና በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ውስጥ ተቀብሮ ይገኛል። መፍትሔው፣ ጥበብን፣ ብልሃትን፣ ብስለትን ይጠይቃል። ኃይል ቦታ የለውም። በኤርትራ ተረጋግጧል።

 

በአምስተኝነት የተፈረጀው ግንቦት 7 ድርጅት ነው። እነ ዶ/ር ብርሃኑን የኢሕአዴግ መሪዎች በደንብ ያውቋቸዋል። በየቡናቤቱ ፈንጂ ያጠምዳሉ ብለው እንደማይጠረጥሯቸው መገመት አያስቸግርም። በምዕራብ ሀገራት ለረዥም ግዜ የኖሩት የግንቦት 7 መሪዎች፣ ለሰብአዊ መብት ደንታ የሌላቸው ሽብርተኞች ሆነው መቀመጣቸው ተዓማኒነቱ እምብዛም ነው። ከዚያ ይልቅ፣ እውነታው ያለው እነዚህ ሰዎች ወደ ሀገራቸው ተመልሰው የፖለቲካው አካል መሆን ለእውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እውን መሆን አስፈላጊ መሆኑ ላይ ነው። የኢሕአዴግ መሪዎች፣ እየመረራቸውም ቢሆን ከዚህ እውነታ ጋር የመጋፈጥ ኃላፊነት አለባቸው። አሁን የተያዘው መንገድ አያዋጣም፣ አያዛልቅም።

 

ፖሊስና ወታደር የፖለቲካ ችግር ፈቺዎች አይደሉም። የሀገሪቱን የዲሞክራሲ ፈተና የእነሱ ዕዳ አድርጎ ማስቀመጥ ከደርግ ስህተት አለመማር ነው። ችግሩን ከምንጩ ማድረቅ ያስፈልጋል፡፡ ምንጩ ደግሞ ፖለቲካ ነው።

 

የኢሕአዴግ መሪዎች ሆይ! ውንጀላውን ትታችሁ ተደራደሩ። ለሀገር የሚበጀው ብቸኛው መንገድ ድርድርና እርቅ ነውና።

ፀሐፊውን ለማግኘት፤ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!