ኦነግ

መንግሥት ኦነግን እሽሩሩ የሚልበት አንቀልባ እስኪበጠስ በትዕግሥት ስንጠብቅ አገራችንን እናጣታለን

አንተነህ መርዕድ

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ለኦሮሞ ሕዝብ መብት የተነሳሁ ነኝ ቢልም፤ ባለፉ አርባ ዓመታት ለምን እንደቆመ ተግባሩ እያሳየን ነው። በተለይም በዚህ የለውጥ ጊዜ ኢትዮጵያን ወደየት ይዟት ሊሄድ እንደፈለገ በተግባር ያሳየን ስለሆነ፤ ዛሬ ሁሉም በሚገባ ያውቀዋል። ሁሉን አካታች የሆነው የኦሮሞ ሕዝብ በስሙ በሚካሄድ ወንጀል የአገሩ ሕልውና አደጋ ላይ እየወደቀ ከሌላው ወገኑ ጋርም በፍቅር የሚኖርበትን ሁኔታ እየተበላሸ ነው።

ከሁሉም በላይ ሥልጣን ላይ ያለው የለውጥ ኃይል ኦነግን እሽሩሩ የሚልበት ሁኔታ አሳሳቢ ነው። አምስት መቶ የማይሞላ ታጣቂ አለኝ ባለ በወሩ በአስር ሺዎች ታጣቂ አለኝ ሲልና ትጥቅ አልፈታም ብሎ ለያዥ ለገራዥ ሲያስቸግር ዝም ተባለ። ኦነግ ሲያልማት የኖራትን የተገነጠለች ኦሮምያ ሪፐብሊክ ለመመሥረት ሁሉንም ለመዋጥ ሲያዛጋ እያየን ነው። አሁን ግን ከማዛጋት አልፎ እየነከሰም እያደማም ነው። ሶማልያ ለተፈፀመው እልቂትና ስደት ከአብዲ ኢሌ የበለጠ እንጂ ያነሰ ሚና አልነበረውም። ሐረርንና ድሬዳዋን ለመሰልቀጥ በሚያደርገው ሩጫ የአካባቢው ነዋሪዎች ስቃይ ላይ ናቸው። በመቶ ሺህ የሚቆጠር የጌድዮ ሕዝብ ላይ የተፈፅመው ዘግንኝ ግፍ፤ አይደለም በድርጊቱ የተሳተፉትን ሥልጣን ላይ ሆነው በቸልታ የተመለከቱትን ነገ ማስጠየቁ የማይቀር ነው። ኦነግ በደቡብ ለሚገኙ ሌሎችም ማኅበረሰቦች የስጋት ምንጭ ነው። ቡራዩ የተካሄደው ዘግኛኝ ጭፍጨፋ በግልጽ ለመናገር የዘር ማጥፋት ወንጀል በሚገባ በመረጃ ተደግፎ የተቀመጠ ወንጀል ስለሆነ ነገ የሚወጣ እውነት ነው። አዲስ አበባን በመዳፉ ለማድረግና ነዋሪዋን ቅኝ ለመግዛት የተሄደበት ግልጽና ስውር ደባ የሚሳካ ባይሆንም፤ ብዙ የሚያስከፍለን ነው። ሞያሌ እንዲሁም ምዕራብ ወለጋ በዜጎች ላይ የተደረገው ግድያ፣ ዘረፋና የንብረት ማውደም፤ ለሌላው ብቻ ሳይሆን ቆሜለታለሁ ለሚለው ለኦሮሞው ሕዝብም የማይመለስ አረመኔያዊ ድርጊት መሆኑን በአደባባይ አስመስክሯል። አስራ ስምንት የሕዝብ ባንክ ሲዘርፍ፣ የሕዝብ መጠቀምያ የሆኑ ትምህርት ቤቶች፣ ክሊኒኮችና መሥሪያ ቤቶች ሲያወድም፤ የአካባቢ ተወላጁን ኢንቨስተር ከውጭ ባለሙያዎቹ ጋር ገድሎ ሲያቃጥል፤ ኦነግ ለኦሮሞ ሕዝብ ቆሟል የሚል ካለ ጤነኛ አይደለም።

የቤንሻንጉል ባለሥልጣናትን በመግደል በኦሮሞዎች ጉሮሮ ላይ ቆሞ በመቶ ሺዎች እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሲሆን፤ አሁን ደግሞ ወደ አማራው ሰሜን ሸዋና ወሎ ዘልቆ የመንግሥት የውስጥ ደጋፊዎቹ ባስታጠቁት ከባድ መሣሪያ ንጹኅ ኢትዮጵያውያንን ሲገድል፤ ኦሮሞው ከሌላው ወገኑ ጋር በሰላም እንዳይኖር እያዘጋጀው ያለው አደጋ የማይታየው ካለ የሞተ ብቻ ነው።

ባለፉት ሦስት የትንቅንቅ ዓመታት፤ በወያኔ ስናይፐር ሺ ወጣቶች በአደባባይ ሲረፈረፉ አንዲት ጥይት መተኮስ ሳይችል በኢሳያስ ጉያ የነበረ ልፍስፍስ ድርጅት፤ ዛሬ ሺ ንጹኀንን የሚገድልበት ጉልበትና ችሎታ ከየት አገኘ? መልሱ ቀላል ነው። ኦሕዴድ/ኦዴፓ ውስጥ ተጠልለው የኖሩ ዘራፊና ፈሪ ዘረኞች መሣሪያውን፣ ገንዘቡን፣ መንግሥታዊ ተቋሙንም ከፍተው አቅም ሰጥተውታል። ዴሞክራሲያዊ ለውጥ እነሱንም እንዳይጠራርግ ሕወሓት ትቶት የሄደውን ሥልጣንና የሀብት ምንጭ ተቆጣጥረው ተረኛ አምባገነን ለመሆን ያለሙ ናቸው። በእያንዳንዷ ክፍት ቦታ ራሳቸውን ሲሞሉ እያየን ነው።

ትናንት የአገር ጠላት ሕወሓት መራሹ ጨካኝና ዘራፊ ቡድን ነበረ። በሕዝብ ትግል ተወግዷል። ዛሬ ደግሞ ጎልቶ ያልወጣ ቢመስልም በኦነግ ዓላማ ዙርያ ኢትዮጵያን ቀፍዶ የሚይዝ ሌላ ዘረኛና ዘራፊ አምባገነን ሥርዓት ለመትከል ቅርፅ እየያዘ የመጣ ኃይል በተረኛነት በኢትዮጵያ አድማስ ላይ ይታያል። ከዓመት በፊት የተለኮሰውን ተስፋ ሊያደበዝዝ ጥላውን እያጠላ ያለው አስፈሪ ዘረኝነት በጠቅላይ ሚንስትሩ የመደመርና የፍቅር እንዲሁም የለማ መገርሳ ኢትዮጵያ ሱሴ አማላይ ሰበካ የሚወገድ አይደለም። ያዘናጋን እንደሆነ እንጂ።

መፍትሔው በሕዝቡ እጅ ነው። መንግሥት የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ እየተሳነውና የተደራጀ ዘረኛ ቡድን ተስፋፊ ፍላጎቱን በመላ ኢትዮጵያውያን ላይ ለመጫን እድል እየሰጠው ስለሆነ፤ ራሱን መጠበቅና ለውጡን ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ ማስኬድ የሕዝቡ ኃላፊነት ነው። ስለሆነም፤

  • ሕዝቡ መንግሥት የአገሪቱን ፀጥታ እንዲያስከብር ጠንክሮ መጠየቅ፣ መታገልና ማስገደድ፤
  • ሕዝቡ በየአካባቢው በመደራጀት የአካባቢውን ፀጥታ መጠበቅና ግጭቶች እንዳይነሱ መከላከል፣ ከአጎራባች ሕዝብ ጋር መልካም ግንኙነት መቀጠል፣ ለጋራ ደህንነት መተባበር፤
  • በፖለቲካ አስተሳሰብ፣ በሃይማኖት፣ በባህልና በዘር ልዩነት የሚራገቡ ቅስቀሳዎችን ማስወገድ፤ ይህንን ልዩነት የሚሰብኩትን እንዲያቆሙ ማስገደድ፤
  • በተፈጠረው ቀውስ የተፈናቀሉትን ማቋቋም፣ ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ፤
  • የአገሪቱ ኤኮኖሚ አደጋ ላይ ስለሆነ ምርት እንዲጠናከር፣ ገበያ እንዲስፋፋ፣ የሕዝብ ግንኙነት እንዲሳለጥ ማድረግ። የምርት ተቋማት ላይ የሚደረግን ጥቃት መከላከል፤
  • በባህላችንም፣ በእምነታችንም ያልነበረውን እየተለመደ የመጣውን ጭካኔ ማውገዝና መከላከል ያስፈልጋል።

መንግሥት ኦነግን እሽሩሩ የሚልበት አንቀልባ እስኪበጠስ በትዕግሥት ስንጠብቅ አገራችንን እናጣታለን። ዛሬ መንግሥት የምንለው ኃይል የጠራ አቋም ወይንም አቅም ያለው አይመስልም። አቋሙም ሆነ አቅሙ የሕዝቡን ፍላጎት ማካተት የሚችለው ሕዝባዊ ትግሉ ሲቀጥል ነው። አሁን “ፖለቲከኛ” ነኝ የሚለው አማተርም ሆነ ሕዝቡ የለውጥ ኃይል ከሚባለው አካል ብዙ ይጠብቃል። ጨርሶ ስሕተት ነው። እነዚህ ሰዎች በሕዝብ ትግል ተገድደው አገልጋይነቱም ሰልችቷቸው ትግሉን ተቀላቀሉ እንጂ፤ በተፈጥሮአቸው የለውጥ ኃይል አይደሉም። በሕዝብ ሙቀትና ጭብጨባ የጀመሩት እስክስታ ከውስጣቸው የመነጨ አለመሆኑን ተግባራቸው እያሳየን ነው። ዋናውን ሥራቸውን ትተው አሁንም ድቢ እየመታን እንድናጅባቸው እንጂ ስሕተታቸውን እንድንነግራቸው ፍላጎት እያሳዩ አይደለም። ቀዝቀዝ ስናደርግ ሲቆጡና ሲደናገራቸው፣ እልፎ እልፎም የከፈሉትን መሥዋዕትነት ሊሰብኩን ይዳዳቸዋል። ልጆቻቸው በስናይፐር ከተገደሉባቸው ወላጆች ወይንም ጥፍራቸው በፒንሳ፣ ብልታቸው በሃይላንደር ከተጎተቱት በላይ መሥዋዕት ከፍለናል ሊሉን ምንም አልቀራቸውም። ውሾን ያነሳ ውሾ ይሁን እንደሚባለው የትናንቱን ረስተን ወደፊት እንሂድ ያለን ሕዝብ የዛሬ ጥፋታቸውን እንዲያርሙ ሊነገራቸው ሲሞከር ትናንት የሠሩትን “ገድል” ሊሰብኩን ይዳዳቸዋል። ሕወሓትም የአስራ ሰባት ዓመት ገድልና የስልሳ ሺህ መሥዋዕት ለሃያ ሰባት ዓመት ሰብኮ አልጨረሰውም። አላሳመነንም። ከሕዝብ የተደበቀ መሥዋዕት ሆነ ወንጀል የለም። አንበሳ ጦጣን “ነይ ውረጅ አልበላሽም” ሲላት፤ “አልበላሽምን ምን አመጣው?” ብላለች። “ትናንት ይህን አድርገናል” የሚል የውለታ ጥያቄ የዛሬን ስሕተት አይሸፍንም።

አብይ ሆይ! ያለምንም ዋስትና ከሰንሰለት የለቀቅከው ኦነግ፤ ዛሬ ሕዝብና አገር እያደማ ነው። አንተንና ጓዶችህን ለመብላት እንደማይመለስ ልቦናህ ያውቀዋል። የጊዜ ጉዳይ ነው። ትናንት በአንቀልባ እሹሩሩ የተባለው ኦነግ ዛሬ በመግዘፉ አንቀልባውን በጥሶ አዛዩን ሊያጠቃ ምንም አልቀረውም። አዝሎት ያመጣውን ያጠፋ እነደሆነ እንጂ፤ ኢትዮጵያና ሕዝቧ ራሳቸውን ለመጠበቅ ይገደዳሉ።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ