የሒልተን ሆቴል ም/ሥራ አስኪያጅና የሐዊ ሆቴል ባለቤት ይገኙበታል

(ስም ዝርዝራቸውን ይዘናል)

Ethiopia Zare (ዓርብ ጥቅምት 28 ቀን 2001 ዓ.ም. November 7, 2008)፦ የአዲስ አበባ ሒልተን ሆቴል ም/ሥራ አስኪያጅና የሐዊ ሆቴል ባለቤትን ጨምሮ፣ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ አንዳንድ ግለሰቦች፣ ከኦነግ ጋር በተያያዘ ታሰሩ። ከተጠርጣሪዎቹ ውስጥ አንዳንዶቹ የኦፌዲንና የኦብኮ አባላቶች እንደሚገኙበት ገልጾ፣ በከተማ ውስጥ የተለያየ የሽብር ተግባራትን ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ የተገኙ ናቸው ሲል ፖሊስ መግለጫ አውጥቷል።

 

መንግሥት በከተማ ውስጥ የተለያዩ የሽብር ተግባራትን ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የኦነግ አመራር አባላት ናቸው ያላቸውን ግለሰቦች፣ ካለፈው ኀሙስ ጀምሮ በቁጥጥር ስር ያዋለ ሲሆን፣ ተጠርጣሪዎቹ ፍርድ ቤት ቀርበው የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸዋል።

 

በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል የኦፌዲን ዋና ፀሐፊ አቶ በቀለ ጅራታ፣ የሒልተን ሆቴል ም/ሥራ አስኪያጅ አቶ ከበደ ቦረና እና ወንድማቸው የሚገኙበት ሲሆን፣ በደብረዘይት መንገድ የሚገኘው “ሐዊ” ተብሎ የሚጠራው ሆቴል ባለቤት አቶ እሸቱ ክትል እንደሚገኙበት ታውቋል።

 

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ ከፊንጫ ስኳር ፋብሪካ እና ከግል ኩባንያ ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩ ወደ 15 የሚጠጉ ግለሰቦች መታሰራቸው ተጠቁሟል።

 

የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎትና፣ የፌደራል ፖሊስ የጋራ ፀረ-ሽብር ግብረ ኃይል በጋራ በሰጡት መግለጫ፣ ተጠርጣሪዎቹ በኅቡዕ የከተማ የኦነግ ዋና አመራር ሆነው፣ ኤርትራ ከሚገኘው የኦነግ አመራር ጋር ግንኙነት በመፍጠር፣ ለሽብር ተግባር የሚሆን ገንዘብ በማሰባሰብና የጦር ማሣሪያ በማቀባበል እንዲሁም ለፀረ-ሠላም ተግባራቸው የሚያሰልፏቸውን ግለሰቦች በመመልመል፣ በሕገ-ወጥ ድርጊት ላይ ተሠማርተው የቆዩ ናቸው ብለዋል።

 

ከተጠርጣሪዎቹ ውስጥ አንዳንዶቹም ኦፌዲን እና ኦብኮን በመሳሰሉ ሕጋዊ የፓለቲካ ድርጅት ውስጥ ተጠልለው፣ በዚህ ፀረ-ሠላም ተግባር ላይ ሲንቀሳቀሱ እንደቆዩ በመግለጽ፣ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ በተደረገ ፍተሻ፣ ለሽብር ተግባር የሚጠቁሙባቸው የተለያዩ ዶክመንቶች፣ መመሪያዎችና የጦር መሣሪያዎች እንደተያዘባቸውም በመግለጫው ተጠቁሟል።

 

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኦ.ፌ.ዲ.ን.) ሊቀመንበር አቶ ቡልቻ ደመቅሳ፣ በተጠቀሰው ተግባር ውስጥ የፓርቲያቸው አባላት ተሳታፊ ናቸው ስለመባሉ ተጠይቀው “ይኼ በፍፁም የማይታመን ነው፣ አቶ በቀለ በፍፁም እንዲህ ዓይነት ነገር ውስጥ አይገቡም …” ብለዋል።

 

በሌላ በኩል ኦ.ፌ.ዲ.ን. ጉዳዩን በማስመልከት ባወጣው መግለጫ “ድርጅቱን ሽባ ለማድረግ እስከ ዛሬ የተካሄደው መጠነ ሠፊ ጥቃት እየከፋ ቢሄድም፣ ያጋጠሙትን ችግሮች ተቋቁሞ፣ ጠቅላላ ጉባዔ ለማድረግ ጥሪ ባስተላለፈበት ሰዓት፣ የድርጅቱ ዋና ፀሐፊና በተቃዋሚ ፓርቲዎች የዲሞክራሲ ምክክር መድረክ፣ የድርጅት ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ በቀለ ጅራታ መታሰራቸው አግባብ አይደለም” ይላል።

 

በአቶ በቀለ ላይ የተካሄደው እስራት ”በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንዲሉ፣ በአንድ በኩል ድርጅቱ ፕሮግራም ይዞ ለማካሄድ ካሰበው ድርጅታዊ ጠቅላላ ጉባዔ ለማሰናከል ሲሆን፣ በሌላ በኩልም የተቃዋሚዎች መሰባሰብ እጅግ ያሳሰበው ገዥው ፓርቲ የጀመሩትን የዲሞክራሲያዊ ምክክር መድረክን ለማዳከም ታስቦ የተቃጣ ነው” ብሎ ድርጅቱ እንደሚያምን በመግለጫው ላይ ሠፍሯል።

 

የ.ኦ.ፌ.ዲ.ን. መግለጫ በማጠቃለያው፣ በሀገሪቱ የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ ጉልህ ሚና የሚጫወቱ ድርጅቶችም ኾኑ ግለሰቦችን ከማዋከብ ገዥው ፖርቲ እንዲቆጠብ አሳስቦ፤ የታሠሩት የአመራር አባሉ እንዲፈቱ ጠይቋል።

 

በሽብር ተግባራት ላይ ተሳትፈዋል የተባሉት የኦብኮ (የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ) አባላትን በሚመለከት፣ የፓርቲው ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና እንደገለፁት፣ ከዚህ በፊት ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ፓርቲያቸው ውስጥ የኦነግ አባላት አሉ እንዳሏቸው ገልፀው፣ ”ደግመን ደጋግመን የተጠርጣሪዎቹን ዝርዝር ስጡን፣ ክትትል እናደርጋለን አልናቸው አልሰጡንም” ብለዋል።

 

አያይዘውም ”ብዙም ሳይቆይ 10 የፓርላማ አባላት በዚሁ ተግባር ተጠርጣሪዎች ናቸው ተባለ፣ ወዲያው ደግሞ ሦስቱ ሄደው ተቀላቀሉ ተባለ፣ ኦነግና እነዚሁ አባላት ተመልሰው መጥተው በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን መግለጫ ሲሰጡ ተመለከትን፣ እኛም ግራ ገብቶናል …” ብለዋል።

 

አባላቶቻቸው ሲታሰሩና ሲፈቱ የነበረ በመሆኑ፣ የአሁኑ እስር እንዳላስገረማቸው የገለጹት ዶ/ር መረራ፣ በዚህ ተግባር ተጠርጥሮ ታስሯል የተባለውን የኦብኮ አባል የተባለ ግለሰብ፣ ካዩት ወደ ሦስት ዓመት እንደሆናቸው ተናግረዋል።

 

እስካሁን አባሎቻቸው እንደሚታሰሩና እንደሚፈቱ የገለፁት ዶ/ር መረራ፣ እሳቸው እንደተረዱት በተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ ተጽዕኖ ለመፍጠር እንጂ ወንጀል እየተገኘ አይመስለኝም ብለዋል።

 

አያይዘውም ከኦነግ አመራር አባላት ጋር ስምምነት ለመፍጠር፣ በሽምግልና የተያዘ ጉዳይ እንዳለ መስማታቸውን ገልፀው ”እስርና ዕርቅ እንዴት አብሮ እንደሚሄድ ግልጽ ሊሆንልኝ አልቻለም፤ ወይም ደግሞ ሽማግሌዎቹ የማያውቁት ነገር ውስጥ ገብተዋል” ሲሉ ዶ/ር መረራ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

 

ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ጥቅምት 12 ቀን 2000 ዓ.ም. ፓርላማ ሲከፈት፣ ፕሬዝዳንቱ ያቀረቡትን ንግግር አስመልክቶ ለቀረበው ሃሳብ (ሞሽን) ማብራርያ በሰጡበት ወቅት፣ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ”ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው በኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲና የሰው ልጅ መብት ይከበራል …” በሚል የጠቀሱትን ንግግር ተቃውመው፣ እሳቸው ባላቸው መረጃ 204 የሚጠጉ ኦሮሞዎች መታሰራቸውን በመጠቆም ”በርግጥ ሰው ወንጀል ሠርቶ ሊታሰር ይችላል፣ እንዴት ይህ ሁሉ የኦሮሞ ህዝብ ይታሠራል?” ሲሉ ላቀረቡት ጥያቄ ጠ/ሚኒስትሩ በሰጧቸው ምላሽ የታሰረ ኦሮሞ አለመኖሩን፣ አቶ ቡልቻ በጠቀሱት ቁጥር ዙሪያ የታሰሩት ኦነጎች መሆናቸውን ገልጸውላቸው ነበር።

 

አያይዘውም አንዳንድ በፓርላማ መቀመጫ ያላቸው የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና በአመራር ደረጃ ያሉ ተመራጮች፣ የኦነግ ሽፋን መሆናቸው ያለ አንዳች ጥርጥር እንደሚታወቅ በመግለጽ የትኛው ፓርቲ፣ የትኛው ግለሰብ ለኦነግ ሽፋን እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጸው ነበር። በአንድ በኩል ሕጋዊ ለመምሰል መሞከር፣ በሌላ በኩል ደግሞ የፀረ-መንግሥት እንቅስቃሴ ተጠቃሚ ለመሆን የሚደረግ ሙከራ የሚያዛልቅ እንዳልሆነ አቶ መለስ አስጠንቅቀው ነበር።

 

ይህንኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ማስጠንቀቂያ በማስታወስ ”የአባላችሁ እስር ያኔ ከተሰጠው ማስጠንቀቂያ ጋር ይገናኛል?” በሚል ለአቶ ቡልቻ ላቀረብንላቸው ጥያቄ ”አይመስለኝም አሁን ከታሰሩት ውስጥ የፓርላማ አባላት የሉበትም፣ ያኔ ያስጠነቀቁት የፓርላማ አባላቱን ነው” ብለዋል።

 

በፕሮፌሠር ኤፍሬም ይስሓቅና በአምባሣደር ብርሃኑ ዲንቃ የሚመራ ሁለት የሽማግሌዎች ቡድን፣ የኦነግ አባላትን ከመንግሥት ጋር ለማስማማት ሥራ የጀመሩ ሲሆን፣ ለዚህም የቀድሞው የኦነግ አመራር አቶ አባቢያ አባጆቢር አዲስ አበባ ገብተዋል።

 

የታሰሩትን ተጠርጣሪዎች በሚመለከት፣ የፌደራል ፓሊስ ጉዳዩ በምርመራ ላይ ስለሆነ ዝርዝሩን ከመግለጽ ተቆጥቧል።

 

የታሰሩት ሥም ዝርዝር

 

1, አቶ በቀለ ጅራታ - የኦ.ፌ.ዲ.ን. ዋና ፀሐፊ፣

2, አቶ ከበደ ቦረና - የሒልተን ሆቴል ምክትል ሥራ አስኪያጅ፣

3, አቶ እሸቱ ክትል - የሐዊ ሆቴል ባለቤት፣

4, ወ/ሮ አበራሽ ያደታ - የኦዳ ኩባንያ ሠራተኛ፣

5, አቶ ቀናዋ ዋቅጅራ - በኦሮሚያ ክልል ባኮ ከተማ መምህር ሲሆኑ፣ ከሥራ ታግደዋል፣

6, አቶ ጫጪሳ አቢሳ - የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ ሠራተኛ፣

7, አቶ ድርቢሳ ለገሰ - የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ ሠራተኛ፣

8, አቶ እመሩ ጉርሚሳ - (ለሦስት ዓመታት ታስረው የነበሩና ከተለቀቁ 3 ወራቸው ነው)፣

9, አቶ በቀለ ገለታ፣

10, አቶ ክበብው ታዬ - ነጋዴ፣

11, አቶ ደረጀ ቦረና - ነጋዴ (የሒልተኑ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ወንድም)፣

12, አቶ ባንቲ ቡላ - በምዕራብ ወለጋ የመንጂ ነዋሪ፣

13, አቶ ቀጀላ አብደታ - በምዕራብ ወለጋ የመንጂ ነዋሪ፣

14, አቶ አሰፋ ተፈራ - የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኦሮሚያ ቋንቋ መምህር እና

15, አቶ ሮባ ገደፋ - የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሠራተኛ ናቸው።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!