እውነት እውነት እላችኋለሁ - አታንስም!!

አባኪያ  

ብርቱካን፤ እነሆ ሌላ ታሪካዊ ቅጽበት መጣ። ታስሮ የሟሟ የለም። ቴዲም አልሟሟ። ዶ/ር ታዬም። ታምራትም እንዲሁ። አሁን ያ ታዬ እዚያው እንደታሰረ ቢቀር ይሻለው ነበር እዚህ ከሚርመጠመጥ። ሆነ ሀኦነነ፤ ብርቱካን ሆይ፤ ብትታሰሪ በቅሌት አይደለም። ወይም በስርቆት። ለመብትሽና ለኢትዮጵያዊያን መብት ባደረግሽው በምታደርጊው ተጋድሎ እንጂ።

 

የዛሬ ሁለት ሺህ አንድ ዓመት አካባቢም እንዲህ ያለ ተመሳሳይ ጥያቄ በእስራኤለ ውስጥ ተነስቶ ነበር። ዛሬም ሰኔና ሰኞ ተገናኝተዋል። እነሆ ብርቱካን ሚደቅሳ የዛሬ ሁለት ሺህ አንድ ዓመት አካባቢ ትንሽቷ፣ አልባሌዋ፣ የተናቀችው ቤተልሄም የተጋፈጠችው ጥያቄ ከፊቷ ተደቀነባት። ቃል በቃል አላስታውሰውም። በከፊል ግን እንዲህ ነው። ክርስቶስ የሚወለድ ሰሞን፤ በእውኑ አንቺ የኤፍራታዋ ቤተልሄም ከሌሎች የይሁዳ ነገዶች ታንሻለሽን? ነገር ግን የእስራኤል ንጉስ የሚሆን ካነቺ ይወለዳል አይነት ነገር። ቤተልሄምም አላነሰችም። እንዲያውም ልቃ ተገኘች እንጂ። የክርስቲያኖች ንጉስ፤ የክርስትናቸው ማእዘን የሆነው ክርስቶስ ተወለደባት። ብርቱካን ያ የንግስትነት ቅጽበት አምልጧት ነበር። አሁን ተመልሶ መጥቷል። ሰሞኑን ቴዲ አፍሮንና ሌሎች የህሊና እስረኞችን ልናስብ ላይ ታች እያልን ነው። ቴዲ አፍሮ የብርቱካንን ያህል ስለኢትዮጵያዊያን ተሟግቶ አይደለም። እንዲያውም የተወሰነውን ኢትዮጵያዊ አጀንዳ እኛ ጫንበት እንጂ። ሀሳቡም እቅዱም የነበረው አይመስለኝም። እንዲያ ከሆነ፤ በእውኑ ብርቱካን ከቴዲ አፍሮ፣ ከአጼ ቴዎድሮስስ ቢሆን ታንሳለችን? እስካሁን ታንሳለች። አጼ ቴዎድሮስ ግን የሰሩት የሰሩትን ብቻ ነው። ከዚህ በኋላ ሊጨምሩ የሚችሉት አንድም ነገር የላቸው። እነሆ ብርቱካን ከነሱ ሁሉ የምትበልጥበትና ከነኦውንግ ሳን ሱ ኪ፣ ከነማርቲን ሉተር ኪንግ፣ ከነማንዴላ፣ ከነጋንዲ ተርታ የምትሰለፍበት ቅጽበት መጥቷል።

 

ዳር ይዞ፤ ያዘው፣ ግደለው፣ በለው፣ ፍጨው፣ ከካው፣ እንደማለት የሚቀል ነገር የለም። ፈረሱ እምቢኝ ብሎ ያስቸገረውን ሰው አንዱ እንዲህ አድርገው፤ አንዱ ደግሞ እንደዚያ እያሉ ሲያስቸግሩት፣ ቢቸግረው፣ ግራ ቢገባው፣ አይ መሬት ያለ ሰው እንዳለው ነገር መሆኑ ነው። ግን ደግሞ ብርቱካን የምትሰራውን የምታውቅ፣ በራሷ የምትመራ፣ ጎበዝ ሴት ነች። ጎበዝ መሪ። እኔም ሆንኩ ሌሎች ሰዎች ምንም ስላልን ብቻ ዝም ብላ የምትነዳ ህጻን አይደለችም። ጊዜዋን ጠብቃ የበሰለች፡ የምትበስል ብርቱካን እንጂ። በዚሁ ሰሞን ሲያትል ከሚገኝ አፍቃሬ ብርቱካን ጓደኛዬ ጋር ብርቱካንን ስለመርዳትና ስለማጠናከር እየተነጋገርን ነበር። በዚያ ዙሪያ ብዙ መጣጥፎችን ለመጣፍ እየተነጋገርን፤ ኢህአዴጎች እናስርሻለን ብለው እያስፈራሯት እንደሆነና ብትታሰር ለሷም ክብር ለሁላችንም ደግሞ የማታገያ ጉዳይ ሊሆን እንደሚችል እያወጋን ምክክራችንን ሳናበቃ እነሆ ኢትዮጵያ ዛሬ ድረ-ገጽ፡ ከወደ አዲስ አበባ፡ ብርቱካን ሚደቅሳ “በአውሮፓ ሀገራት አድርገሽው የነበረውን ንግግር የሚያስተባብል እርማት ካላደረግሽ፤ ይቅርታ ተደርጎልሽ የነበረው ተነስቶ እስር ቤት ትገቢያለሽ" የሚል የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣት ዘገበ። በቴሌቪዥንና በሬዲዮም ይሄው ሆኗል አሉ ዘመቻው።

 

ብርቱካን፤ እነሆ ሌላ ታሪካዊ ቅጽበት መጣ። ታስሮ የሟሟ የለም። ቴዲም አልሟሟ። ዶ/ር ታዬም። ታምራትም እንዲሁ። አሁን ያ ታዬ እዚያው እንደታሰረ ቢቀር ይሻለው ነበር እዚህ ከሚርመጠመጥ። ሆነ ሀኦነነ፤ ብርቱካን ሆይ፤ ብትታሰሪ በቅሌት አይደለም። ወይም በስርቆት። ለመብትሽና ለኢትዮጵያዊያን መብት ባደረግሽው በምታደርጊው ተጋድሎ እንጂ። ቀድሞውንም መታሰራችሁ ያለአግባብ ነበር። አፈታታችሁም መቼም ይሁን ብለን እንጂ የሚያኮራና የሚያንቀባርር አልነበረም። መቼም ዋጥነው እንጂ አንገታችንን አስደፍቶናል። ቴዲ አንድ ሰው ገደልክ ተብሎ ነው የታሰረው። የሚመጣውን አናውቅም። ገደለም አልገደለም፤ አልገደልኩም ብሎ እነሆ ወደ እስር ቤት ተወርውሮ አሳሩን ይቆጥራል። አንቺና ወዳጆችሽ ግን ዘር ነው አጠፋችሁ የተባላችሁት። ብሄር በብሄር ላይ አነሳሳች፣፤ መንግስት ለመገልበጥ አሴራችሁ፣ ህገ መንግስታዊ ስርአት ለመናድ ተነሰሳችሁ፤ ቀሰቀሳችሁም። እነሆ ተፈረደባችሁ። ታሰራችሁ። ሁላችንም እንደምንገምተውም በሽምግልና ብዛት ተለቀቃችሁ። ስለሽምግልናው ይዘትና ዝርዝር ጉዳዮች ባናውቅም፤ እናንተ ከተፈታችሁ ጊዜ ጀምሮ በአፈታታችሁ ዙሪያ የተድበሰበሰ ነገር ብቻ እየሰማን፤ እኛም ብዙ ሳያመን ብንኖርም፤ ኢህአዴግ ግን ከመፈታታችሁ ዋዜማ ጀምሮ በቴሌቪዥንና በሬዲዮ ሀጢያታችሁንና ሽንፈታችሁን እያበዛ ከመናገር ወደኋላ አላለም። እናንተ ቃላችሁን ጠበቃችሁ። እነሱ ግን ቃላቸውን አጠፉ።

 

መቼም ከተፈታችሁ በኋላ ያለውን ሁላችንም ስለምናውቀው፤ ብዙም አላነሳው። አንድ ነር ብቻ ግን ባነሳ መልካም ነው። ርስ በርሳችሁ ስትጣሉ፤ በመካከላችሁ የተፈጠረውን ጸብና ውዝግብ ባዩ ጊዜ፤ ሁላችሁም ከምትፈቱ ይልቅ እዚያው እስር ቤት እንድትቆዩ ይሻል እንደነበር የተመኙ ሁላ ነበሩ። የናንተ መታሰር አስደስቷቸው ሳይሆን ስለናንተ ያላቸው ክብር እስራታችሁን አስመኝቷቸው። ይባስ ብሎ በምንም ይሁን በምን ከለቀቀ፣ ከፈታ፣ በኋላ የመናገርና የመደራጀት ሀሳብሽንም የመግለጽ መብትሽን ሽሮ እነሆ የተናገርሽውን ዋጭ ያለበለዚያ እስር ቤት እንመልስሻለን። ይሄ የድፍረት ጫፍ ነው። ይሄ የትእቢት ጣሪያ ነው። ይሄ የሚመጣውንም የሚናገርና የሚገልጽ ምልክት ነው። እነሆ በሄድሽበት ሁሉ የምትይውን እናደምጣለን። ለኛ የማይመች፣ የማይጥም፣ የማይስማማ ነገር በተናገርሽ ቁጥር እየተከታተልን እናስውጥሻለን አይነት ነገር ነው። ለዚህ ነው፡ ቴዎድሮስ ዘፋኙ፣ ወጣቱ ያልዋጠውን ወንጀል፤ ብርቱካን ፖለቲካኛዋ፣ ብቱካን የወደፊት አገር መሪዋ፣ ብርቱካን የቅንጅቷ፣ ብርቱካን አርበኛችን የምትውጠው ያልነው።

 

በእውኑ ብርቱካን ከቴዎድሮስ ታንሳለችን? በእውኑ ብርቱካን ለልጇ ያልሰራችውን ሰራሁ ማለት ታስለምዳታለችን? ታወርሳታለችን? ብርቱካንም ትሁን ጓደኞቿ የማንንም ዘር ለማጥፋት አልተነሱም። በዘር ማጥፋት ወንጀል መከሰስ ካለበት መከሰስ ያለበት ራሱ ኢህአዴግ ነው። የዘርና ብሄር ፖለቲካ ወደአገራችን ያስተዋወቀ፤ ዘረኛ መንግስት። ራሱ ባመጣው ጣጣ ሳትጠለፍ እነሆ ዘርንና ብሄርን ተራምዳ ኢትዮጵያዊነትን የምታራምደውን ብርቱካንን በዘር ማጥፋት ከሶ አዎን አጥፍቻለሁ አስባላት። እንደገና ደግሞ አሁንም ድገሚው፡ ያለበለዚያ ትገቢያታለሽ። አሁንም በፊትም ብርቱካን እስረኛ ነች። ኢህአዴግ ከዚህ በላይ ሊያመጣ የሚችለው እስርም እንግልትም የለም። እንደውም ካሁኑ ሁኔታዋ የእስር ቤት ውሎዋ እኛን ሊያታግል፤ እኛን ሊያስተባብር ይችላል። በርግጥ በዚህ ቃል አልገባም። ማለቴ ብርቱካን ካመነችበት እንጂ እኛን በተለይ እዚህ ባህር ማዶ ያለንን ሰዎች ተማምና እንኩዋን እስር ቤት ፖሊስ ጣቢያም ትግባ አልልም። ግን ከቆመችለት ዓላማ አንጻር፣ አሁን ነጻ መስላ ከምትመላለስ ይልቅ፤ ብትታሰር የበለጠ ዋጋ አላት ብዬ አምናለሁ። ብርቱካን አሁንም እስረኛ ነች። ይሄ ቅጽበት ለብርቱካን ወሳኝ ነው። ዛሬ አውሮፓ መጥታ የተናገረችውን ከካደች፤ ዛሬ አሜሪካ መጥታ ያለችንን ከለወጠች፤ ነገ መጥታ የምትነግረንን የማያምኑ ብዙዎች ናቸው። ለኛ ስትል መንገዷን ትለውጥ ማለታችን አይደለም። ለኛም ለራሷም ስትል በመንገዷ ትሂድ እንጂ። የብርቱካን መንገድ ደግሞ እውነት ነው። እውነቱን ከተናገረች እንኩዋን እስር ቤት ሲኦልም እንጨምርሻለን ቢሏት መፍራትና የተናገረችውን መካድ የለባትም። በእውኑ ብርቱካን ከቴዲ አፍሮ ታንሳለችን? ከአጼ ቴዎድሮስስ ቢሆን?

 

አባኪያ ነኝ

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ