ሕብረት ሰላሙ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)

ከጥንቶቹ ጀግኖቻችን፤

እንደሚታውቀው ዐፄ ዮሐንስን እጅግ በጣም ከሚያስደንቃቸውና ከሚያስከብራቸው ታሪካቸው ዋነኛው ለውድ ሀገራቸው ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ዳር ድንበር መከበር በቆራጥነት ይከላከሉ የነበረውና ሕይወታቸውንም የሰዉለት መሆኑ ነው። የጀግናው የዐፄ ዮሐንስ ራስ ተቆርጦ ሱዳን ከተወሰደ ልክ 120 ዓመት ሆኖታል። እስካሁን አልተመለሰም!

 

ዐፄ ካሌብማ ይገዙ የነበረው፤ የዛሬውን አያድርገውና ኢትዮጵያ ከሐያላን መንግሥቶች አንዷ በነበረችበት ዘመን በመሆኑ፤ እነየመንንና የዛሬዋን ሳውዲ ዓረቢያን አብዛኛውን ክፍል በቁጥጥራቸው ሥር አድርገው ነበር።

 

ዛሬስ?

 

ዛሬማ! በኢትዮጵያ ላይ የተንሰራፋው በሙስና የተዘፈቀው የውስጥ ጠንቀኛ ጠላት መንግሥት በብዙ አርበኞች ደም ለዘመናት ተጠብቆ የቆየውን አንጡራ የሀገር መሬታችንን፤ እንደ አልባሌ ዕቃ ለሌሎች ሀገሮች እየቸበቸበው ነው። ኤርትራን ከእናት ሀገርዋ አስገንጥሎ ኢትዮጵያን ለጅቡቲና ለሶማሌላንድ ተንበርካኪ አደረጋት። በሱዳን ወሰን በኩል ያለው ሰፊ ለም መሬት ለሱዳን፤ እንዲሁም ሌሎች ሰፋፊ ለም መሬቶች፤ “ለኢንቨስትሜንት” እየተባለ፤ ለሳውዲ ዓረቢያና ለጅቡቲ መንግሥቶች ለግል ጥቅም እየተሸጡላቸው ናቸው።

 

በሱማሌና በኬንያ ወሰኖች በኩል ያሉትም መሬቶች ተመሳሳይ የመሸጥ ተራቸውን እየጠበቁ ይሆን?! ህዝቡን በዘረኛነት ስልት ከፋፍሎት እርስ በርሱ እንዲተናነቅ እያደረገው ነው። ይህ ሁሉ እኩይ ተግባር እየተከናወነ ሳለ፤ አስራ ሁለት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን በረሃብ አለንጋ እየተቀጡ ፍዳቸውን እያዩ ነው። ኢትዮጵያ ዩ.ኤን.ዲ.ፒ. ባወጣው የሰው ልጅ ልማት መስፈርት ከመቶ ሰባ ሰባት ሀገሮች መቶ ሰባኛ ናት!

 

የኤርትራ መገንጠል ሠላምና ልማት በማስገኘት ፈንታ ያስከተለው ውጤት እልቂት፤ የባሰ ድህነትና እጅግ የከፋ ጭቆና ብቻ ነው። ጎረቤት ከሆነችው ከሶማሊያ ጋርም የተከናወነው የደም መቃባት ጠባሳ ብቻ ነው።

 

ዐፄ ዮሐንስና ዐፄ ካሌብ የዛሬዎቹን ጉደኛ የኢትዮጵያ መሪዎች ድርጊት ማየት ቢችሉ ኖሮ የደም እንባ ያለቅሱ እንደ ነበረ አይጠረጠርም!!

 

እኛስ በሕይወት ያለነው፤ ኢትዮጵያውያን ምን እያደረግን ይሆን?!

 

ሰፊ ለም መሬትና ለሌሎች ሀገሮች የተትረፈረፈ ውሃ (ለግብጽ ከሚጎርፈው ውሃ ሰማኒያ ስድስት በመቶው ከኢትዮጵያ ነው) በሀገራችን እያለ፤ በስንኩል አገዛዝ ምክንያት፤ በድህነትና በገዳይ ደዌዎች ስለምንሰቃይ አብዛኞቻችን ለዕለት ኑሮአችን ከማሰብ ሌላ ለሀገራችን ሉዓላዊነት ዘብ መቆም ተስኖን ይሆን? ጥቂቶቻችንስ ለሀገራችን ሉዓላዊነት እየታገልን አንዳንዶቻችንም በወያኔ የጭቆና አንግልት እየተሰቃየን፣ ሕብረት ተስኖን የምንገኝ አይደለንምን? ሌሎቻችንስ የሀገራችንን ጉዳይ እንደ ባዕድ በሩቁ እያየን እጃችንን አጣምረን የምናይ አይደለንምን?!

 

የነዐፄ ዮሐንስ ጀብድ

 

በዐፄ ዮሐንስ፣ በነራስ አሉላና ሌሎች ጀግኖች የተመራው የኢትዮጵያ ህዝብ ከኢጣልያኖች፤ ከግብጾችና ከደርቡሾች የተቃጣበትን ጥቃት መመለስ እንደቻለ እነተክለጻድቅ መኩሪያ፣ ስቬን ሩበንሰን፣ ባሕሩ ዘውዴና ሌሎችም ብዙ የታሪክ ፀሐፊዎች በሰፊው ዘግበውታል። ግብጾችን በጉንደትና በጉርዓ፣ ኢጣሊያኖችን በዶጋሊ ጦርነቶች ድባቅ እንደመቱዋቸው የታወቀ ነው።

 

“የኢትዮጵያ ታሪክ ከንግሥተ ሳባ እስከ ታላቁ የአድዋ ድል” በተሰኘው የብላቴን ጌታ ሕሩይ ወልደሥላሴ መጽሐፍ (ገጽ 184 - 187)፤ ስለ ዐፄ ዮሐንስ የመጨረሻ ጀብድ እንደሚከተለው ተጽፏል፤

 

“ዐፄ ዮሐንስም … ደርቡሽ ወደ ኢትዮጵያ ወሰን ሊመጣ ይሰናዳል ማለትን ሰምተው ነበርና እርሱ ሳይወጣ እርሳቸው ወደ መተማ ወርደው ለመዋጋት ሲሉ ፊታቸውን ወደ መተማ አዞሩ። …

 

“ከዚህም በኋላ ዐፄ ዮሐንስ ከጎጃም ተነስተው በአገው ምድር አልፈው ወደ ደምቢያ ወርደው ንጉሥ ተክለ ኃይማኖትና ደርቡሾች ወደ ተዋጉበት ሣር ውሃ ወደሚባለው ሥፍራ ሲደርሱ በጦርነት ውስጥ የሞቱትን የህዝበ ክርስቲያን አጥንት ብዛቱን አይተው አጅግ አዘኑ። ልባቸውም እንደ እሳት ተቃጠለ።

 

“… ከዚያም ወደ መተማ ገሠገሡ። አሳባቸውም በፊት መተማን አጥፍተው ቢመቻቸው ወደ ትልቁ ከተማ ወደ ኡምዱርማን ለመሄድ ነበር። ከዐፄ ዮሐንስም ጋራ የዘመቱት መኩዋንንቶች ትልቁ ራስ አርኣያ፣ ቢትወደድ ገብረመስቀል፣ ራስ ሚካኤል፣ ራስ ኃይለማርያም፣ ራስ አሉላ፣ ራስ መንገሻ፣ ራስ ሀጎስ ነበሩ። የዘመተውም ሠራዊት ሁሉ ቁጥሩ 150 ሺህ ነበር። ከዚሁም ከ150 ሺህ ውስጥ ሃያው ሺህ ፈረስኛ ነው። …

 

“ከዚያም ዐፄ ዮሐንስ የየካቲት ወር ሲያልቅ መተማ ደረሱ። ለጦሩ አበጋዝ ለዘኬም “መጣሁብህ ተዘጋጅተህ ቆየኝ። እንደ ሌባ በድንገት መጣብኝ እንዳትለኝ፤ መምጣቴም የክርስቲያንን ደም ለመበቀል ነው” ብለው ላኩበት።

 

“በመጋቢት 1 ቀን 1881 ዓ.ም. ቅዳሜ ጦርነት ተጋጠሙ። … በብርቱ ጦርነት ከተዋጉ በሁዋላ ግን የከተማውን ቅጥር ባንድ ወገን ጥሰውት ገቡ። በከተማው ውስጥ ያለ ሰው ሁሉ እየሸሸ እንዲወጣ ብለው ቤቱንና ቅጥሩን አቃጠሉት። ባንድ ወገንም ዘልቀው ግምጃ ቤቱን ያዙት።

 

“የአቡ አንጋንም አጽም ለማቃጠል ቤቱን ሁሉ ይቀሰቅሱ ጀመር። ይህንንም ያሰቡበት ምክንያት አቡ አንጋ ጎንደርን አጥፍቶ ሊቃውንቱን ሁሉ በእሳት አቃጥሉዋቸው ነበርና የዚያን ብድር ለመመለስ ነበር። ነገር ግን ዐፄ ዮሐንስ ምንም አጠንክረው ቢዋጉ ድል ማድረጋቸው ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ አይሆንምና ድል ለማድረግ ጥቂት ሲቀራቸው ዐፄ ዮሐንስም በጠመንጃ ቆሰሉና ወሬው ያንጊዜውን በየሠልፉ ውስጥ ተሰማ። መኩዋንንቱም ወታደሩም ከቅጥሩ ውስጥ እየወጡ መሸሽ ጀመሩ።

 

“… ቀጥለውም … ለርሱ (ለራስ መንገሻ) ተገዙ ብለው የኑዛዜ ቃል ተናገሩና በማግሥቱ አረፉ። ያፄ ዮሐንስን ሬሣ በሣጥን ውስጥ አግብተው ይዘው ወደ አትባራ ወንዝ ፊታቸውን መልሰው ሸሹ።

 

“… ደርቡሾችም በጦርነት ውስጥ የሞቱትን የኢትዮጵያ መኩዋንንት ሁሉ ራሳቸውን እየቆረጡ ኦምዱርማን ድረስ ለከሊፋ አብደላ ላኩለት። …

 

“በመጋቢት ሦስት ቀን የዐፄ ዮሐንስን ሬሣ ይዘው የሚጉዋዙትም መኩዋንንቶች በአትባራ ወንዝ ዳር ሠፍረው ደረሰባቸውና አደጋ ጥሎ ተዋጋቸው። … ከዚህ በሁዋላ ደርቡሾቹ በድንኩዋን ውስጥ አንድ ትልቅ ሣጥን አገኙ። ሣጥኑም በሰም ተመርጎ ነበር። በመጀመሪያ ገንዘብ ያለበት መስሎዋቸው ነበር። ቢከፍቱት ግን የሰው ሬሣ ሆኖ አገኙት። ወዲያው ከምርኮኞቹ አንዱን ሰው አቅርበው ቢጠይቁት የዐፄ ዮሐንስ ሬሣ ነው አላቸው።

 

“… ደርቡሾችም የዐፄ ዮሐንስ ሬሣ መሆኑን ከተረዱ በሁዋላ ራሳቸውን ቆርጠው ለከሊፋ አብዱላሂ ወደ ኡምዱርማን ሰደዱለት። ከሊፋ አብዱላሂም ያንን ባየ ጊዜ የደስታ ነጋሪት እንዲመታ፣ መለከት እንዲነፋ አድርጎ የከተማው ሰው ሁሉ ይህንን በመስማት ደስ አለው። ከሦስት ቀን በሁዋላ የዐፄ ዮሐንስን ራስ በእንጨት ላይ ሰክቶ በግመል ጀርባ ላይ አድርጎ ገበያ ለገበያ መንደር ለመንደር እያዞረ ለትልቅ ለትንሹ ለሴት ለወንዱ ሲያሳያቸው ዋለ ይባላል።”

 

የጀግናው የዐፄ ዮሐንስ ራስ ተቆርጦ ሱዳን ከተወሰደ ልክ 120 ዓመት ሆኖታል። አሁንም ተወርውሮ ያለው ካርቱም ከተማ በሚገኝ የሱዳን ሙዚየም ውስጥ ነው ይባላል። ለሀገር የመቆርቆር ስሜት ያለው መንግሥት ቢኖር፤ የዐፄ ዮሐንስን ራስ አስመልሶ ከሌላው ሰውነታቸው ጋር በክብር እንዲቀበር ማድረግ አይገባውም ነበር። ዐፄ ዮሐንስና ሌሎችም ስፍር ቁጥር የሌላቸው ኢትዮጵያውያን የተሰዉለትን የሀገራችንን መሬት ክህደት በተጠናወተው ስልት ለሱዳን ከማስረከብ ይልቅ።

 

ዐፄ ካሌብና ታላቂቱ ኢትዮጵያ

 

በአክሱሞች ዘመን፤ በተለይም በዐፄ ካሌብ ዘመነ መንግሥት (485-515)፤ ኢትዮጵያ የማትደፈር ታላቅ ሀገር ነበረች። ግዛትዋም በአፍሪካ ቀንድ ብቻ ሳይሆን የመንንና አብዛኛውን ዛሬ ሳውዲ ዓረቢያ የሚሰኘውን ሀገር ትቆጣጠር ነበር። ዶ/ር ሥርግው ሐብለ ሥላሴ በጻፈው “Ancient and Medieval Ethiopian History to 1270” በተሰኘው መጽሐፉ፤ ገጽ 128-137፤ ዐፄ ካሌብ በ230 መርከቦች በመጠቀም፤ ከ70,000 - 120,000 የሚገመት ጦር ዛእፈርና ናግራን በተሰኙ (ዛሬ ሳውዲ ዓረቢያ ውስጥ የሚገኙ) ከተሞች ሁለት ጊዜ አዝምተው በኢትዮጵያውያንና በሌሎች ዜጎች ላይ ጥቃት ፈጽሞ የነበረውን ተቀናቃኝ አሸንፈው ወኪላቸውን አብርሃ የተሰኘውን (በሁዋላ በዝሆን ታጅቦ መካን የወረረው) ሰንዓ፤ የመን አመቻችተው ወደ አክሱም ተመልሰዋል። ይህንንም ዘመቻ ለማከናወን ሲነሳሱ እርዳታቸውን በጽሑፍ አድርገው የጠየቁዋቸው፤ በጊዜው የሮማ የቄሣር ገዢ የነበሩት ቀዳማዊ ጀስቲን የተሰኙት ነበሩ።

 

ዛሬስ?!

 

ዛሬማ! የኢትዮጵያ የውስጥ ጠላት፣ የሀገሪቱን መሬት ለዓረቦች እያስረከበ ነው። የኑሮ ፍዳ እያስገደዳቸው ኢትዮጵያውያን ሥራና ጥቅም ፍለጋ ወደ ዓረብ ሀገሮች እየፈለሱ ነው። ወደ የመን ለመሄድ በጥቃቅን መርከቦች ሲጉዋዙ እየሰመጡ ሕይወታቸው ያለፈው ብዙዎች ናቸው።

 

መፍትሔው ምን ይሆን?

 

አማራጭ ያልሆነ አንድ ነገር ቢኖር፤ የሀገራችን ሉዓላዊነት መደፈሩን እያየን ዝም ማለት ነው። ጭቆናና ድህነት ቢያዳክመንም፤ ወኔያችንን አላኮላሸውም። ስለዚህ፤

 

(ሀ) የሀገርህ ሉዓላዊነት የተደፈረብህ የኢትዮጵያ ህዝብ፤ በቃኝ ብለህ ተነስተህ ለመብትህ መታገል አለብህ።

 

(ለ) የኢትዮጵያ የመከላከያና የፖሊስ ሠራዊቶች አባሎች ሁሉ፤ የራሳችሁ ሀገርና ህዝብ ሲጠቃ ማየት ለሕሊናችሁና ለልጅ ልጆቻችሁ ጥቅም እጅግ ጠንቀኛ መሆኑን በመገንዘብ ታሪካዊ ጀግንነታችሁን ለውድ ሀገራችሁ ለኢትዮጵያ ለዘለቄታው በሚጠቅም ሁኔታ አሁኑኑ ማሳየት አለባችሁ። በሙስና የተዘፈቀ፣ ለሀገር ሉዓላዊነት ደንታ በሌለው መንግሥት የጭቆና መሣሪያ መጠቀሚያ መሆናችሁ እናንተንም ሊያስነውራችሁ ይገባል።

 

(ሐ) ለኢትዮጵያ ህዝብ የሥልጣን ባለቤትነት በመታገል ላይ ያላችሁ የፖለቲካና የሰብዓዊ መብት ተፋላሚዎች የሚጎድላችሁ አንድ ከባድ ጉዳይ ቢኖር ሕብረት ማጣታችሁ በመሆኑ፤ “ድር ቢያብር …” ስለሆነ ሀገራችንን እያሽመደመደ ያለውን አውሬ መንግሥት በአንድነት እንድንታንብረክኩት ያስፈልጋል።

 

(መ) የአፍሪካ ቀንድ ሀገሮች ሠላምና ልማት ማግኘት የሚችሉት፤ ዲሞክራሲ ሥርዓት የሰፈነበት የተቀናጀ ሕብረት ሲኖራቸው ብቻ ነው።

 

(ሠ) ኢትዮጵያ ከዓረብ ሀገሮች ጋር ሊኖራት የሚገባው ግንኙነት ሚዛናዊነት ባለው ጥቅም ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት። ኢትዮጵያ የሰው ኃይል እንዲሁም የውሀና የእርሻ ሀብት ልትሸጥላቸው ስትችል በዓረቦቹ በኩል ደግሞ ነዳጅ ማቅረብ ይችላሉ። በተጨማሪም፤ በሳውዲ ዓረቢያ በኩል የሚፈለገው ሚዛናዊነት ኢትዮጵያ ውስጥ መስጊዶች ማቁዋቁውም እንደ ተፈቀደላት ሁሉ ኢትዮጵያም ሳውዲ ዓረቢያ ውስጥ ቤተክርስቲያን እንድትሠራ መፍቀድ አለባት።

 

(መ) መንፈሣዊም ሆነ ማኅበራዊ፤ ባህላዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ፤ ሠላምም ቢሆን እርቅ፤ ሌላም … ሌላም ተልዕኮ ቢኖረን ሊሳካ የሚችለው የሀገር ሉዓላዊነት ሲኖር በመሆኑ እንደ የጥንት አባቶቻችንና እናቶቻችን ተባብረን በርትተን ስንታገል ነው።

 

ቸሩ የኢትዮጵያ አምላክ ሀገራችንን እንድንጠብቅ ያበርታን! - አሜን!!!


 

ሕብረት ሰላሙ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ