ጋዜጠኛና ደራሲ ተስፋዬ ገብረአብ Tesfaye Gebreabከተስፋዬ ገብረአብ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)

እነሆ! ዛሬ ቅዳሜ ነው።

ዕለቱም ግንቦት 9፣ 2009።

ትናንት ደግሞ ግንቦት 8 ነበር። በአበሻ የዘመን አቆጣጠር ልክ የዛሬ ሃያ ዓመት ግድም ”ጥቂት ጄኔራሎች” ኮሎኔል መንግሥቱ ላይ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ አድርገው ነበር። ሳይሳካላቸው በመክሸፉ ዛሬ በሕይወት የሉም። ማንኛውም አጥንት - አስከሬን ሆነዋል። አምላክ የጄኔራሎቹን ነፍስ ይማር። እኒያ ሰዎች ከነሙሉ ችግራቸው ከኮሎኔል መንግሥቱ የተሻሉ ዜጎች ነበሩ ብዬ አምናለሁ።

 

ቀደም ሲል ደግሞ ጄኔራል መንግሥቱ ነዋይ ጃንሆይን ለማስወገድ በመሞከራቸው የዚያ ዘመን ወጣት ትውልድ ጃንሆይን መንካትና መድፈር እንደሚቻል ትምህርት ማግኘት መቻሉ ይታመናል። ሰሞኑን ደግሞ ታሪክ ራሱን ለመድገም ሞከረ። የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ርዕሰ አጀንዳ ሆኖ ሲያነጋግረን ሰነበተ።

 

እኔም ታዲያ ምንም እንኳ የፖለቲካ ተንታኝ ባልሆንም፣ እንደ ጋዜጠኛነቴ በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየቴን በጨረፍታ ለማኖር ፈቅጄያለሁ። ለነገሩ ይቺን ”ብጫቂ ወረቀት” የመጫር አሳብ የመጣው ከኔው አልነበረም። በፀጥታ ተቀምጬ፣ ”የደራሲው ማስታወሻ” የሚል ሥም የሰጠሁትን ቀጣይ መጽሐፌን እየፃፍኩ ሳለ የethioforum.org ዋና አዘጋጅ ክንፉ አሰፋ መስመር ላይ አገኘኝና፣

 

”የሰሞኑ ግርግር ላይ አስተያየትህን ለምን አትፅፍም?” ሲል ጠየቀኝ።

 

* * *

 

የሰሞኑን የመፈንቅለ መንግሥት ግርግር ጉዳይ ከማንሳቴ በፊት ግን በዚህ ወቅት የማንም የፖለቲካ ድርጅት አባል አለመሆኔን ከወዲሁ መግለፅ ግዴታ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። ቀደም ሲል የወያኔ አባል ለመሆን የበቃሁትም ባልጠበቅሁት ሁኔታ ከተራራ ወደ ሸለቆ እንደ ኳስ እየተጠለዝኩ መሆኑን በ”ጋዜጠኛው ማስታወሻ” አውግቼያችሁዋለሁና እሱን እዚህ አልደግመውም። ይህን ርዕሰ ጉዳይ ማንሳት ያስፈለገበት ምክንያትም በቅርቡ ከግንቦት 7 ጋር በተያያዘ እየታማሁ በመሆኑ ነው።

 

በመሰረቱ በግንቦት 7 አባልነት መታማት የሚያኮራ ነው።

 

የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ የመግባት ሃሳብ ቢኖረኝ ኖሮ ግንቦት 7 ከአማራጮቼ አንዱ በሆነ ነበር። ቅሬታዬን መግለፅ የፈለግሁትም የአብርሃ በላይ ድረገጽ አትሞት የነበረው አንድ ጽሑፍ ግንቦት 7ን ለማጥቃት ሆን ተብሎ በወያኔ ካድሬዎች የተፃፈ ሊሆን ይችላል ብዬ በመገመቴ ነበር። ”የአድአው ጥቁር አፈር” በሚል ርዕስ ኢትዮሚዲያ ድረገጽ ላይ የታተመው ጽሑፍ ከኔ በላይ ግንቦት 7ን የሚያጠቃ ሆኖ ነበር ያገኘሁት።

 

በዚያን ሰሞን የፀሐፊውን ማንነት ለማወቅ ብዙ ጥረት አድርጌ ነበር። ፍንጭ የሚሰጠኝ ግን ጠፋ። ‘ያያ አባቦር’ በሚል የብዕር ሥም ግንቦት 7ን ከኔ ጋር ደርቦ በቃላት መድፍ ሲደበድበኝ የከረመው ፀሐፊ ለካስ የሩቅ ወዳጄ ኦቦ በፈቃዱ ሞረዳ ኖሮአል።

 

በፈቃዱ ሞረዳ በፃፍው መጣጥፍ እኔን ‘ወኔ ቢስ፣ ፈሪ!’ ብሎ የቻለውን ያህል በሚያጥላሉ ቃላት ሲገልፅ፣ ራሱን ደግሞ ‘የግንባር ስጋ’ ወይም ‘ጀግና’ ‘እውነተኛ ጋዜጠኛ’ ሲል ገልፆአል። እዚህ ላይ ማንበቤን በማቆም ጥቂት ተክዤ ቆየሁ። በፈቃዱ ስለራሱ ጀግናነት በአደባባይ እስኪናገር ድረስ ርግጠኛ መሆን ከቻለ በውነቱ በጣም ዕድለኛ ሰው ሆኖ ይሰማኛል። ጀግና መሆን መልካም ነው። ሰዎች በምርጫቸው ፈሪ ሆነው አያውቁም። ለነገሩ የጀግንነትና የፈሪነት መለኪያዎች ከቶ ምን ይሆኑ? ስንት አይነት ጀግንነቶችስ አሉ? እና በፈቃዱ ሞረዳ ራሱን ጀግና ብሎ እኔን ወደ ፈሪዎች ቀበሌ የላከኝ በየትኞቹ መለኪያዎች ይሆን?

 

በፈቃዱ ከ1981 ጀምሮ እንደሚያውቀኝም ጽፎአል።

 

እውነቱን ነው።

 

ግጥሞቹን በጣም ስለምወዳቸው ራሴ ነኝ ፈልጌ የተዋወቅሁት። እኔ ከዚያ በፊት በሥነ-ግጥሞቹ አውቀው ነበር። እሱም እንደኔው ሐረር ላይ ያቺኑ የፉገራ ፖለቲካ ተምሮ ነበርና እኛ ስንመረቅ በፈቃዱ የኢሠፓ ጋዜጠኛና ካድሬ ሆኖ መጣ። አዲሳባን እንጂ ጦርነትን አያውቃትም። ሐረር ላይ ግማሽ ሰዓት ያህል ሥነጽሑፍ ነክ ወሬ ተጨዋውተን ተለያየን። በዚሁ አበቃ። በፈቃዱ ሞረዳ ወደ አዲሳባ፣ እኔ ወደ አሰቃቂው ጦርነት ተለያየን። መልዓከ ሞት ደግሞ ሬሣ በዝቶበት ነው መሰለኝ፣

 

”አንተን ለጊዜው አንፈልግህም” ብሎ ሳይወስደኝ ቀረ።

 

ደርግ ወድቆ አዲሳባ ስንገባ ከበፈቃዱ ጋር በድጋሚ ተገናኘን። አሁን ደግሞ ሁለታችንም ስደተኞች ነን። ከስደቱ በሁዋላ ወያኔን በጋራ እንታገለዋለን ብዬ ስጠብቅ በፈቃዱ ሞረዳ ፊቱን ወደኔ አዙሮ በባዙቃ ይደበድበኝ ያዘ። አብርሃ በላይም፣ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ የበፈቃዱ ሞረዳን ጽሑፍ ከድረገጹ ነቅሎ ጣለው። እንዳልኳችሁ ግን ”የግንቦት 7 አምባሣደር” ሆኜ አስመራ ልጓዝ እንደተዘጋጀሁ የሚገልፀውን የፈጠራ ጽሑፍ የፃፈው በፈቃዱ ሞረዳ ሊሆን ይችላል ብዬ አልገመትኩም ነበር።

 

ያን ሰሞን ታዲያ ለቀጣዩ መጽሐፌ ከበፈቃዱ ሞረዳ ውብ ግጥሞች፣ ”ጀጎል” የተባለችውን ልጠቀምባት በማሰብ፣ ”... ’ጀጎል’ የተባለች ግጥምህን ላክልኝ” የሚል ኢ-ሜይል ፃፍኩለት። በጀጎል ፈንታ በኔ ላይ ያለውን ጥላቻ የሚተርከውን ጽሑፍ በፒ.ዲ.ኤፍ. አስሮ ላከልኝ። ”የአደአው ጥቁር አፈር” መድፈኛ እሱ ራሱ እንደሆነም ነገረኝ።

 

በእውነቱ ወያኔዎች በዚህ ነው የሚበልጡን። የራሳቸውን ሰው በመደብደብ ኃይል አያባክኑም። በፈቃዱ ሞረዳ እኔን በመደብደብ ወያኔን ብቻ ነው ማስደሰት የቻለው። በርግጥ በፈቃዱ ወደ ኦነግ ስለመግባቱ ያልተረጋገጠ ጭምጭምታ ወሬ ሰምቻለሁ። ወሬው እውነት ከሆነ ለገጣሚው ያያ አባ ቦር መልካም ትግል እመኝለታለሁ ...

 

በዚያን ዕለት ምሽት ወደ ፕሪቶሪያ ደቡብ ነዳሁ። የከተማችን ደቡባዊ አቅጣጫ ኮረብታማ ነው። ገና ሙሉ በሙሉ አልመሸም ነበር። ባቡሮች የጉልበት ሠራተኞችን እየጫኑ፣ ፕሪቶሪያን እያቋጡ፣ በውበቱ ከቶውንም ተወዳዳሪ ወደሌለው ወደ ኩዋዙሉ ናታል ክፍለሀገር ይከንፋሉ። ኮረብቶቹ በጣም ውብ ሲሆኑ ጃኪ ቻን የተባለው የፊልም አክተር ”ሑ አማ አይ” (Who am I) የተባለውን ፊልም ለመሥራት እኒያን ኮረብቶች ተጠቅሞባቸዋል። እዚያ ኮረብታ ላይ ወጣሁና ቁጭ አልሁ። ቁጭ አልኩ ብቻዬን።

 

በወርቃማው ዘመን ስለ ተፈጠሩት የሩስያ ደራስያን አሰብኩና ቅናት ሰቅዞ ያዘኝ። በአንድ ወቅት ሃያስያን ወደ ቶልስቶይ ቀርበው ስለ ቼኾቭ ጠይቀውት ነበር።

 

ሳያመነታ እንዲህ መለሰ፣

 

”ወደድኩም ጠላሁም አንቶን ቼኾቭ እንደሚበልጠኝ አመኜያልሁ!!”

 

* * *

 

የሆነው ሆኖ በፈቃዱ ሞረዳ ስለ ግንቦት 7 የገመተውን እንርሳውና እንደ አንድ የሥነጽሑፍ ሰው በሰሞኑ አጀንዳ ላይ የግል ዕይታዬን ላውጋችሁ …

 

ከትናንት በስቲያ ግንቦት 7 ነበር ዕለቱ።

 

መለስና በረከት የኮሎኔል መንግሥቱ ርኩስ መንፈሥ ምን ሹክ እንዳላቸው ባይታወቅም፣ እንደ መርዶ ነጋሪ በጠዋት ተነስተው፣ ”ግንቦት 7 ወንበራችንን ሊሰርቅ ሲል ለጥቂት ያዝነው!!” ሲሉ በጩኸት ነገሩን።

 

አያያዘናም በረከት፣

 

”ለግንቦት 20 ሲያስቡን፣ ግንቦት 7 ላይ አስቀረናቸው” አለን።

 

በርግጥ በረከት እንደዚህ ሲል አልሰማሁትም። አይልም ግን አይባልም።

 

እንደዋዛ ከጀመርኩት ወግ ወዲያ ማዶ ታዲያ አያሌ መራራ አጀንዳዎች አሉ። በአስር ሺዎች የሚገመቱ ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ እስረኞች በየማጎሪያው የከፋውን ስቃይ እየተቀበሉ ይገኛሉ። ቴዲ አፍሮ አንዱ ነው። ብርቱካን ሚደቅሳ - ሁለት። ገመቹ አባቢያ - ሦስት። ገመቹን የሚያውቀው አለ? ምናልባት የምናውቀው ጥቂቶች ሳንሆን አንቀርም። የኦነግ ታጋይ ነበር። ወያኔ አስሮታል። ከናይሮቢ አፍነው ወሰዱትና አሁን የት እንዳለ አይታወቅም።

 

የስንቱ ሥም ተዘርዝሮ ይቻላል?

 

በርግጥ የሹርሹራ ጓደኛ ስለሆነው ገመቹ በቀጣዩ መጽሐፌ በስፋት አወጋችሁዋለሁ። ”ሹርሹራ ደግሞ ማነው?” ትሉ ይሆናል። ለማንኛውም ሹርሹራ በሕይወት የለም። የወለጋ ምድር ላይ በክብር አርፎአል። እንግዲህ በየማጎሪያው ከተወረወሩት ወገኖቻችን መካከል እነ ጄኔራል ተፈራ ማሞ የዚህ ማስታወሻ መነሻና ማዕከል ናቸውና ወደዚያው ልዝለቅ …

 

* * *

 

ወያኔ አብላጫ ቁጥር ባላቸው ብሔሮች መካከል እንዴት አክሮባት እየሠራ መዝለቅ እንዳለበት የቤት ሥራውን የሠራው ደርግ ከመውደቁ በፊት እንጂ ትናንት አልነበረም። ቀድሞውንም በተዳከመ የግንኙነት ማዕቀፍ ውስጥ የነበረው የኢትዮጵያ ህዝብ ጣራው ተደርምሶበት፣ የሚያገናኙት የጋራ የስሜት ክሮች እየተበጣጠሱ አንዱ ለሌላው ጠላት በሚሆኑበት ጎዳና ላይ ሲደነቃቀፍ ዘመናት ባጅተዋል።

 

ጄኔራል ከማል ገልቹ ከ150 በላይ የታጠቁ የሠራዊት አባላትን አስከትሎ የኤርትራን ድንበር ሲያቋርጥ ”የወያኔ ሠራዊት ፍፃሜ ተቃረበ!” ተብሎ ነበር። የጄኔራሉን መኮብለል ተከትሎ በረከት ሰምዖን በሰጠው ቃለምልልስ ”ተገላገልን!” ሲል ነበር የገለፀው። ወያኔ ራሱን የሚያጠናክርበት በር ተከፈተለት። ከ20 ሺህ ያላነሱ ኦሮሞ ወታደሮች ከየጦር ክፍሉ ተመንጥረው ትግራይ ውስጥ ታሰሩ። በመቶዎች የሚገመቱ ኦሮሞ መኮንኖች ደግሞ ደሴ አካባቢ ወደሚገኝ ወታደራዊ እስር ቤት ተላኩ። መኮንኖቹን የተረከበቻቸው የእስር ቤቱ ኃላፊ፣ ኮሎኔል ብራ የተባለች ነባር የህወሓት አባል ስትሆን፣ የአሉላ ክፍለ ጦር ኮሚሳር ከነበረችበት ጊዜ አንስቶ በጨካኝነቷ ትታወቃለች። ኮሎኔል ብራ የሀገር መከላከያ ከፍተኛ መኮንኖችን እርቃናቸውን አስቁማ ታስገርፋለች። እንደ ወይራ በጠነከረ የጎማ ዱላ ተደብድበው፣ ፓራላይዝድ ሆነው ዛሬም ድረስ ማገገሚያ ጣቢያ የተቆለፈባቸው አንድ ሁለት መኮንኖችን አውቃለሁ።

 

መኮንኖቹ በግርፊያው ወቅት የተጠየቁት አንድ አጭር ጥያቄ ብቻ ነበር፣

 

”ከኦሮሞ ጄኔራሎች መካከል ከኦነግ ጋር ግንኙነት ያለው ማነው?”

 

ድብደባው ሲበዛባችው የአባዱላን ሥም ጠሩ።

 

ኮሎኔል ብራ ወቀጣው እንዲቆም አዘዘችና ያገኘችውን ”ምርጥ የምርመራ ውጤት” ለአለቆቿ አቀረበች። አለቆቿ ግን አባዱላ ዝንተ ዓለም እንደማይከዳ ያውቁ ነበር።

 

ጄኔራል ከማል ሠራዊቱ ውስጥ በኅቡዕ ካደራጀው የኦነግ ደጋፊዎች መካከል ሲሶውን እንኳ ይዞ አለመውጣቱን ገልዖ ነበር። ይህ ለወያኔ እልል በቅምጤ ሆነለት። በዚያ ሰበብ ምንጠራውን ለማካሄድ በቂ ምክንያት አገኙ። ከጠረጋው በሁዋላ በጎደለ ለመሙላት በተደረገው የሥልጣን ሽግሽግ ወያኔ ከአማራ የሠራዊቱ አባላት ድጋፍ ለማግኘት ጥቂት ሞካክሮአል። በዚያን ጊዜ አፍንጫ ሲመታ ዓይን ሳያለቀስ ቀረ።

 

ይህን ዘዴ ወያኔ ደጋግሞ ይጠቀምበታል።

 

ቅንጅት አዲሳባ ላይ በምርጫ ሲያሸንፍ በአንድ አዳር ፊንፊኔ የኦሮሚያ ዋና ከተማ ሆና አደረች። በዚሁ ሰሞንም ኢህአዲግ አዳማ ከተማ ላይ ባዘጋጀው አንድ ግብዣ ላይ የኢህአዲግ አባላት በትግርኛና በኦሮምኛ ብቻ ጨፈሩ። አባዱላም የሚያምነው ታቦት ስላልነበረው በጠመንጃ ሥም እየማለ ታሪካዊ ንግግር አደረገ። ግብዣው ላይ የነበሩ እንደሚተርኩት አባዱላ እንባው ባይኑ ቸፈፍ ብሎ፣

 

”ፊንፊኔ ወደ እናት ክልሏ እንደምትመለስ ህልም ነበረኝ!!” ሲል እንደ ማርቲን ሉተር ኪንግ ድምፁን ቢለቀው ዝቋላና ካካ ተራሮች ደግሞ ያንን በገደል ማሚቷቸው በኩል አገማሸሩት።

 

አባዱላ እንባውና ህልሙን አጣጥሞ ሳያበቃ መለስ ዜናዊ ጠርቶ፣

 

”ህልምህን ህፃናት የማይደርሱበት ቦታ አስቀምጠው። ለጊዜው ግን አዳማ ትቆያላችሁ” አለው።

 

ወያኔ ሁለቱ አብላጫ ቁጥር ያላቸውን ብሔሮች በተመሳሳይ ጊዜ አጥቅቷቸው አያውቅም። አንዱን ሲያጠቃ የሌላው ድጋፍ ስለሚያስፈልገው የፈረቃ ቁማር ይቆምራል። የህወሓት አባላትም ምንጊዜም ፍርድ ሰጪ ዳኛ ሆነው መካከል ላይ ይገኛሉ። የኮሜዲያን ክበበው ገዳ ”ገብረመድህን” የተባለው ገፀባህርይ ለዚህ አባባሌ እንደ መልካም ማሳያ ሊጠቀስ የሚችል ነው።

 

የሰሞኑ፣ ”የመፈንቅለ መንግሥት ድራማ” ለአየር ከበቃ በሁዋላ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ በቃለመጠይቁ ሲገልፅ እንደነበረው ከጄኔራል ከማል ኩብለላ በሁዋላ በሠራዊቱ ውስጥ በተካሄደው ጠረጋ የአገዛዙ ሥርዓት ዘረኛ አካሄድ ላይ ጥያቄ ያሳደሩ ምርጥ የሠራዊቱ አባላት በአብዛኛው እየታፈኑ ተሰውረዋል።

 

ወያኔን እንቅልፍ የሚከለክሉ የሠራዊቱ አባላት አንድ ባንድ እየተመነጠሩ ጥጋቸውን ይዘዋል። ኃይሌ ጥላሁን ሊጠቀሱ ከሚችሉት መካከል ነው። በሰሞኑ ”የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ” ጣት ከሾለባቸው መካከልም ኃይሌ ዋናው መሆኑን ውስጥ አዋቂዎች ያወጋሉ። ዳሩ ግን ወያኔ በዚህ ጊዜ በቀጥታ ጄኔራል ኃይሌን ሊነካው እንደማይፈልግ የምናውቅ ከጥቂት በላይ ነን። በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ጄኔራል ኃይሌን የተመለከቱ ጥቂት አስገራሚ ወጎች ነበሩ። በዚያን ወቅት የህወሓት ጦር ኮማንደሮች በከባድ መሣሪያ ግዢ ሰበብ በሚሊዮናት ዶላር ኮሚሽን እየበሉ የመሆናቸው ወሬ አየሩን በክሎት ነበር። ጄኔራል ኃይሌ ደግሞ እዚሁ ግዢ አካባቢ የተመደበ ባለሥልጣን ነበር። እና ድምፁን ከፍ አድርጎ በስብሰባ ላይ እንዲህ ሲል ተናገረ፣

 

”እኔ እዚህ ተቀመጬ የሀገሪቱን ገንዘብ አትበሉም! ስትዘርፉ እያየሁ ዝም አልላችሁም!”

 

ጄኔራል ኃይሌ ከነታምራትና በረከት ጋር ኢህዲንን ከመሰረቱት ነባር ታጋዮች አንዱ ሲሆን፣ አዲስ አበባ እስክትያዝም በኢህአዲግ ደረጃ ትግሉን የመራ ሰው ነው። በስብሰባ ላይ የህወሓት ኮማንደሮችን እንዲያ ከተናገረ በሁዋላ ግን የኃይሌ ጉዳይ ያለቀለት ሆነ። ”ጡረታ!” አሉና አገለሉት። ጉዳዩ ተራ የዕድሜና የአስተዳደር ጉዳይ ቢሆን ኖሮ፣ ሳሞራ የኑስ ቀድሞት ጡረታ ሊወጣ በተገባ ነበር። እነደሰማሁት ጡረታ ከወጣም በሁዋላ ኃይሌ አላረፈም። ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ፣

 

”እንተዋወቃለን!” እያለ ይናገራል አሉ።

 

እነ ሳሞራም ”የትም አይደርስ” በሚል ችላ ብለውት ሰንብተዋል።

 

እንግዲህ በዚህ መረጃ ዙሪያ አንዳንድ ፍንጮችን ማሽተት የሚገድ አይሆንም። ዛሬ በመፈንቅለ መንግሥት ወይም በሽብርተኛነት ሥም ተይዘው የታሰሩት ከፍተኛና ጄኔራል መኮንኖች ከኃይሌ ጥላሁን ጋር ያላቸውን የጠበቀ ግንኙነት ወያኔም ሆነ የቅርብ የብአዲን አባላት አሳምረው ያውቁታል።

 

የመፈንቅለ መንግሥቱን ወሬ እንደሰማሁ የሚፃፉትን ዜናዎችና ዜና ትንታኔዎች ለማንበብ ሞክሬ ነበር። ወያኔ ጉዳዩን ከመፈንቅለ መንግሥት ወደ ሽብርተኛነት ሊለውጠው ለምን እንደፈለገ ገልፅ ነበር። ”ሽብርተኛነት” ክስ ለመመስረት የሚያመች ሲሆን፣ ባንፃሩ ”መፈንቅለ መንግሥት” የሚለው ግንቦት 7 የተባለውን ድርጅት ዝና ይበልጥ ከፍ ሊያደርገው ይችላል የሚል ስጋት አሳድሮባቸዋል። ”ከሠራዊቱ እየተመነጠሩ ያሉት አማራ መኮንኖች የግንቦት 7 አባላት ናቸው ወይስ አይደሉም?” የሚለው ጥያቄም አከራካሪ አይደለም። ቢሆኑም ብርሃኑና አንዳርጋቸው፣ ”አባላቶቻችን ናቸው!” ብለው ይነግሩን ዘንድ አንጠብቅም። ይህ ለታሪክ የሚቆይ ይሆናል። እንደምንሰማው ግን ከግንቦት 7 ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያልመሰረቱ፣ በዓላማው ዙሪያ በራስ አነሳሽነት የተደራጁ ወጣቶች የክፍለ ሀገር ከተሞችን እያጥለቀለቁ ይገኛሉ። በየአካባቢው ”ወንድም ጋሻ!” የመሆን የአርበኛነት ስሜት ተቀስቅሷል። ብርቱካን ሚደቅሳ እንደገለፀችው፣ አንድ ዓላማ በህዝብ ተቀባይነት ካገኘ የሚያደራጀውን አካል ሳይጠብቅ እንደ መንፈሥ ይሰራጫል። ቀደም ሲል ለቅንጅት ዓላማዎች ሕይወታቸውን የሰጡት አብዛኞቹ ወጣቶች በአባልነት የተመዘገቡ እንዳልነበሩ እናስታውሳለን። የወያኔ ዘረኛ አገዛዝ ሰለባ የሆነውን ሰፊ ህዝብ እንተወውና በዚህ ቀውጢ ወቅት ተፈራ ዋልዋ ራሱ የግንቦት 7 ደጋፊ ሆኖ ቢገኝ አይደንቀኝም።

 

ከመነሻው ብአዲኖች ውስጣቸው ጥሩ አለመሆኑን የውስጥ መረጃዎች አሉኝ። ከኢህአዲግ አራት አባል ድርጅቶች መካከል ክፉኛ ሞራሉ ተነክቶ በቀውስ ላይ የሚገኘው ብአዲን ነው።

 

ኦህዲድን በቀላል ቋንቋ ላስቀምጥላችሁ!

 

አመራሩ ንፁህ ወያኔ ሲሆን፣ አባላቶቹ ደግሞ በአብዛኛው የሥራ ዕድል ለማግኘት ድርጅቱን የተቀላቀሉ በአመለካከት ወደ ኦነግ የሚቀርቡ ናቸው።

 

”ደቡብ ህዝቦች” በሚል ሥም አባይ ፀሐዬ ያቋቋመው ድርጅት ”አለ ይባላል በሣይንስ ግን አልተረጋገጠም” እየተባለ የሚቀለድበት፣ ዶክተር ካሱ ይላላ እንደፈለገ የሚያንገላታው ከሞቱት በላይ ያለ እቁብተኛ ነው።

 

ወደ ብአዲን ስንመጣ ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ወድቀዋል። መለስ ዜናዊ እንደሚለውም ቀዩን የፈንጂ መስመር ረግጠዋል።

 

አመራሩን በጨረፍታ ላስጎብኛችሁ …

 

አዲሱ ለገሰ ከጤንነቱ መበላሸት ሁኔታ ጋር ተደማምሮ ሥልጣን ላይ መቆየት እንደማይፈልግ ማመልከት የጀመረው ከሚሊኒየሙ ዋዜማ ጀምሮ ነበር። ተፈራ ዋልዋ፣ ”የታገልነው ለዚህ አልነበረም!” እና ”መምራት አቅቶናል!” የተባሉ ሁለት ነጠላ ዘፈኖችን ውስጥ ውስጡን ማንጎራጎር መጀመሩን በምሰማበት መንገድ ሰምቻለሁ። ህላዌ ዮሴፍ ቀድሞውንም ”ከኢህአፓ መንፈሥ አልተላቀቁም!” እየተባሉ ከሚታወቁት አንዱ ነበር። ህላዌ ”ኢትዮጵያዊነት!” የሚል መንፈሣቸው ጠንካራ ከነበሩ የቀድሞ የኢህአፓ ትንታጎች አንዱ ነበር። የሽግግር መንግሥቱ ሥራ ከጀመረ በሁዋላ መለስ ዜናዊ፣

 

”ህላዌ ዮሴፍ ሆይ! አንተ አማራ ብቻ ነበርክ፣ አማራ ብቻ ሆነህም ትኖራለህ!! ስለሌላው አያገባህም!” ብሎት ሲያበቃ አረንጓዴዋን ቀንሶ በቀይና ቢጫ ቀለማት ያማረች ክራቫት አሰረለት። ከኢህዲን ላይ የተቀነሰችው አረንጓዴ ቀለም ሁመራ መሆኗም በሹክሹክታ ተናፈሰ። ጄኔራል ኃይሌ ጥላሁን ቀደም ብዬ እንደገለፅኩት ለይቶለታል። መኮንኖች ክበብ ብቅ ሲል፣ ”እነዚህ የቀን ሌቦች፣ ተጫወቱብን!” ማለቱን ቀጥሎአል።

 

ከምርጫ 97 አንድ ወር ቀደም ብሎ መኮንኖች ክበብ ላይ በተደረገ አንድ ግብዣ ላይ ስብኃት ነጋ፣

 

”ነፍጠኛው ወደ ሥልጣን ይመጣል ብሎ የሚያልም ካለ የዋህ ነው!” ብሎ ሲናገር ህላዌ ዮሴፍ የሚጠጣው ትን ብሎት ወደ መፀዳጃ ቤት መሄዱ ተሰምቶአል።

 

ብአዲን ማለት እንግዲህ እነዚሁ ናችው። ያልተጠቀሱ ቢኖሩ ታደሰ ጥንቅሹና በረከት ስምዖን ናችው። ታደሰ ብአዲን ውስጥ የህወሓት ትክል መሆኑ ነው የሚነገርለት። በረከት ያው በረከት ነው። በወያኔ ዘረኛ ፖለቲካ ውስጥ ገብቶ የወገኖቹን የስቃይ ጊዜ ከሚያራዝም፣ አንዴ ጎንደር ሌላ ጊዜ ቡግና ከሚንከራተት፣ ”አማራ ነኝ!” እያለ በምድረበዳ ከሚጮህ፣ የጎንደር ልጅነቱን አክብሮ፣ በኢትዮጵያዊነቱ ቢፀና እንዴት ባማረበት?

 

የሆነው ሆኖ ከመነሻው ብአዲኖች ውስጣቸው ጥሩ አለመሆኑን ገልጫለሁ። ከአባላቶቻቸውና ከህዝቡ የሚመጣውን ግፊት ከቶውንም ሊቋቋሙት ተቸግረዋል። ብአዲኖች በህወሓት ላይ የቆየ ቅሬታ እንዳላቸውም ”የጋዜጠኛው ማስታወሻ” ላይ መግለፄ አይዘነጋም። ብርሃኑ ነጋ ጠቁሞት እንዳለፈውም ሠራዊቱ ውስጥ ቁጣ አለ። የሰሞነኛው ግርግር ከግንቦት 7 ባሻገር የብአዲን ውስጣዊ ሁኔታ ላይ እንዳተኩር ያደረገኝም ብአዲን የወያኔን ዘረኛ ፖሊሲ እያስፈፀመ መቀጠል ከማይችልበት ደረጃ ላይ መድረሱ ይበልጥ ግልፅ እየሆነ በመምጣቱ ነው። ከበረከትና ከታደሰ ጥንቅሹ ባሻገር ያሉት የብአዲን የአመራር አባላት የጄኔራል ኃይሌ ጥላሁንን ቁጣ ቢጋሩ አይደንቀኝም።

 

”የጋዜጠኛው ማስታወሻ” የተባለውን መጽሐፍ በረከትና ተፈራ ዋልዋ እንዳነበቡት ሰምቻለሁ። በረከት ጠረጴዛ እየደበደበ፣ ”ውሸታም!! የውሸት ክምር!!” አለ ተባለ። ተፈራ ግን፣ ”የሚያውቀውን ፅፎአል” ማለቱን ሰማሁ። እኔን የሳበኝ ሁለቱ የጥንት ጓደኛሞች የሁለት ዓለም ሰው መሆን የመጀመራቸው ፍንጭ ነው።

 

ተፈራ ዓይኑን መግለጥ ጀምሮ ይሆን?

 

በርግጥም ሚስቱን እስከ ማሰር ሊደፍሩት የበቁበትን ምክንያት እንደ ተራ ስህተት የሚታይ ሊሆን አይችልም። ተፈራና አዲሱ ያሻውን ያህል የሥልጣን ጥመኞች ቢሆኑም፣ የመከላከያ አባላቶቻቸውና የቀድሞ የትግል ጓዶቻቸው እንደ አይጥ እየተለቀሙ ወደ ኮሎኔል ብራ ሲላኩ ድርጊቱን በደስታ ሊያስተናግዱት ከቶ አይችሉም። ለዘመናት ውስጥ ውስጡን ሲብላላ የባጀው የብአዲንና የህወሓት ሽኩቻ ካለፉት ጊዜያት በላቀ ደረጃ ወደ ግጭት አምርቶአል።

 

ህወሓት ብአዲንን ለማዳከም ይህን ጊዜ ለምን እንደመረጠ መረዳትም ከባድ አይደለም።

 

ምርጫ 2010 እየቀረበ ነው።

 

የማጭበርበሪያ ሜዳው ከወዲሁ መደልደል እንዳለበት ግልፅ ነው። ”ኢትዮጵያዊነት” የሚል ባንዲራ የሚያስቀድሙ ኃይሎችና የትጥቅ ትግል ያወጁ፣ ኦነግ፣ አርበኞች፣ የኦጋዴን ነፃ አውጪ የመሳሰሉ አማፅያን ”የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላቶች!” ተብለው ተፈርጀዋል። ወያኔ ”የግንቦት 7” እና ”የአንድነት” ፓርቲዎችን ሁለትነት አለማመኑም ግልፅ ነው። በቀጣዩ ምርጫ ወያኔ እንደለመደው ሊያጭበረብርና ጠመንጃ ሊጠቀም ሲሞክር የግንቦት 7 ትንታጎች መብረቅ እንዳያወርዱበት ሰግቶአል። ብአዲን ለግንቦት 7 የመፈልፈያ ጫካ ሊሆን እንደሚችልም ወያኔ ከምርጫ 97 በቂ ትምህርት አግኝቶአል። እና ግንቦት 7 ወጣት ወታደሮቹን ይዞ የማይቀርለትን ፍልሚያ የሚጋፈጥ ከሆነ በርግጥም ማዕከሉ መከላከያ ነው የሚሆን። የሰሞኑ የመፈንቅለ መንግሥት ድራማ እንዲህ ሰፊና አሻገሮ የተመለከተ ስለመሆኑ ከቶ ምን ጥያቄ አለውና?

 

የብአዲን አመራር በበረከት ሰንሰለት ተጠፍሮ የታሰረ ተስፋ የቆረጠ አካል እንደመሆኑ በህወሓት የሚታዘዘውን የጎጥ አስተሳሰብ ተፈፃሚ የማድረግ ብቃቱን አጥቶአል። ይህ ማለት ግን ህወሓት አልቆለታል ማለት አይደለም። ”ኢትዮጵያዊነት” የሚል ባንዲራ ያስቀደሙ ኃይሎች ሲበረቱበት አባዱላ ገመዳን ጠርቶ አንድ የቤት ሥራ እንደሚሰጠው ከወዲሁ የሚጠበቅ ነው። አሁንም አፍንጫ ሲመታ ዓይን ካላለቀሰ ወያኔ ሊሳካለት ይችላል።

 

ወገኖቼ ሆይ!

 

ምን ቀረ?

 

ቀሪው ግልፅ ነው …

 

በቀጣዩ ምርጫ መለስ ዜናዊ ሥልጣኑን እንደሚለቅ ነግሮናል። መለስ ቃሉ አይታመንም። አሳ የላሰው ድንጋይ ነው። በአሁኑ ንግግሩ ”አሁንስ በቃኝ! እለቅላችሁዋለሁ!!” ማለቱን ግን እኔ በበኩሌ አምኜዋለሁ። መለስ በርግጥም ሥልጣኑን ሊለቅ ወስኖአል። አማራጭም የለውም። ሁኔታዎችንና ዕድሜውን አስልቶ የቤት ሥራውን ሠርቶ አብቅቶአል። ሆኖም ብቻውን እንደማይለቅም አስባለሁ። የፖሊት ቢሮ አባላቱን ሁሉ በትልቅ ዘንቢል ሸክፎ ዘወር ይል ዘንድ እንጠብቃለን። ይሁን እነጂ የዚህች ሀገር መከራ እዚህ ላይ ያበቃል ብላችሁ አትጠበቁ። የሚወራው እውነት ከሆነ አስመራ የተማረው ባለመነጽሩ ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም መለስን ተክቶ ኢህአዲግን ሊመራ እጅጌውን ሰብስቦአል። የቅንጅት መሪዎች ከመፈታታቸው ቀደም ብሎ ስዬ አብርሃ ከእስር የተለቀቀበት የሥምምነት ምስጢርም ያልተነካ ወሬ ነው። ህወሓት አንድ አስገራሚ ጠባይ አለው። ጥንካሬ ሲሰማው ርስበራስ ይባላሉ። ጠላት ሲበረታባቸው ደግሞ ልዩነታቸውን መሳቢያ ውስጥ አስቀመጠው ባንድ ሰልፍ ለውጊያ ይዘጋጃሉ። የስዬ አብርሃ በድንገት የመፈታትና የተቃዋሚ ንቅናቄ ውስጥ መገኘት የህወሓት ራስን የማዳን ስትራቴጂ አካል ስለመሆኑ የሚጠራጠር ካለም የዋህ ፖለቲከኛ መሆን ይኖርበታል።

 

ባጭሩ ቀጣዩ የኃይል አሰላለፍ በአንድ ወገን መለስና ቡድኑን የሚተካው ኃይል፣ በሌላ ወገን ደግሞ በስዬና በገብሩ የሚመራው ኃይል ይሆናሉ። ከዚህ ባሻገር ያሉ ኃይሎች እጣ ፈንታ ገብሩና ስዬን መቀላቀል አለያም መጥፋት ይሆናል። ሥልጣን ከሁለቱ ኃይሎች እጅ እስካልወጣች ድረስም የህወሓት ዓላማዎች እንደተጠበቁ ይቆያሉ። ከዚህ ባሻገር መለስ ለግሉ የሚመኛቸው ጥቂት ነገሮች አይጠፉም። የሞ ኢብራሂም ሽልማት ቀዳሚው ይሆናል። ለገንዘቡ ሳይሆን ለክብሩ።

 

ይህ የወያኔ ሂሳብ ይሳካ ይሆን? ለማንኛውም ትግሉ ቀጥሎአል! …

 

* * *

 

እነሆ! ዛሬ ቅዳሜ ነው …

 

ዕለቱም ግንቦት 9፣ 2009።

 

ፕሪቶሪያ ቁጭ ብዬ እኔም ይቺን እጫጭራለሁ። የደቡብ አፍሪቃ ክረምት ከነጓዙ ገብቶአል። ዛሬ ጠዋት ከቤት ስወጣ ቆፈኑና ዝናቡ ፕሪቶሪያ ላይ እንደጉድ እየወረደባት ነበር። ያፍሪቃ መሪዎች አብዛኞቹ ፕሪቶሪያ ገብተዋል። ጃኮብ ዙማ መንበረ ሥልጣኑን የሚረከብበት ዕለት ዛሬ ነው። የኛው አዛውንት ጋሽ ግርማም ገብተዋል። መኖሪያ ቤቴ ከቤተመንግሥቱ ብዙም አይርቅ። እንደምንም እየተሹለከለክሁ ወደ ሰኒሳይድ አቅጣጫ ነዳሁ። አብዛኞቹ አበሾች እዚያ ቀበሌ ይኖራሉ። ሰኒሳይድ ውብ ናት። ሰኒፓርክ የተባለ አንድ ትልቅ የገበያ አዳራሽ አለ። እዚያ ገባሁና በረንዳው ላይ ቁጭ አልኩ።

 

ሰኒሳይድ በደስታ አብዳለች።

 

የዙሉ ጎሣ አባላት የቆዳ ልብስ ለብሰው ባህላዊ ጭፈራቸውን ያስነኩታል። እኔም ደስ አለኝ። ይህቺን መጣጥፍም መጫጫር ጀመርኩ። ስጫጭር ቆየሁና ቀና ስል ለካስ አጠገቤ ካለ ጠረጴዛ ላይ አንዲት ነጭ ደቡብ አፍሪቃዊት ብቻዋን ቁጭ ብላለች፣

 

”ጋዜጠኛ ነህ እንዴ?” ስትል ጠየቀቺኝ።

 

ለማሳጠር ያህል፣

 

”ነኝ አዎ!” አልኩ።

 

”በምርጫው ሥራ በዝቶባችሁ ከረመ?”

 

”እኔ እንኳ ደስተኛ አይደለሁም” አልኳት ”… ምንም ሥራ የለም። ምርጫው ቢጭበረበርና ግርግር ቢኖር ሥራ ይኖረን ነበር ...”

 

ቀልዱ ገብቶአት ሳቀች። እናም፣

 

”እናንተ ሥራ ብታጡ ይሻላል” አለች።

 

በርግጥም ደቡብ አፍሪቃውያን ዛሬ ተደስተዋል። በጣም ተደስተዋል። ምርጫው በሠላም አለቀ። አልተጭበረበረም። እና ፕሪቶሪያ ደስ ብሎአታል። እንኳን ደስ ያላት።

 

አዲሳባስ ለዚህ አይነቱ የደስታ ዕለት የምትበቃው መቼ ይሆን?

 

ተስፋዬ ገብረአብ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)


 

ከኢትዮጵያ ዛሬ ይህንን ጽሑፍ ጋዜጠኛና ደራሲ ተስፋዬ ገብረአብ የጻፈውና በኢትዮ ሚዲያ ፎረም ላይ የተነበበ ሲሆን፣ ተስፋዬ በዚህ ጽሑፉ ውስጥ ሁለት በ”ናፍቆት ኢትዮጵያ” መጽሔት ላይ የተነበቡ ጽሑፎችን ጠቅሷል። ምላሽም ሰጥቶባቸዋል። የመጀመሪያው ጽሑፍ ያያ አባቦር ”የአደአው ጥቁር አፈር ጋዜጠኛ ወይስ የፓርቲ ካድሬ?” በሚል በመጽሔቱ ላይ ያስነበቡት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የ”ጦማር” ጋዜጣ ባለቤትና ዋና አዘጋጅ የነበረውና አሁን በስደት በሰሜን አሜሪካ የሚገኘው ጋዜጠኛ በፈቃዱ ሞረዳ ”እኔም ማስታወሻ አለኝ” በሚል ርዕስ የጻፈው ጽሑፍ ነው። ለአንባብያን ግንዛቤ ይረዳ ዘንድ ሦስቱንም ጽሑፎች አቅርበናቸዋል። መልካም ንባብ!

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ