ግርማ ካሣ

W/t Birtukan, Paster Haile, Dr. Kiflu, Paster Tesfatsion & Teddy Afro (L to R)

በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እና በፕሬዝዳንት ኢሣያስ አፈወርቂ በግፍ የታሰሩ ሠላማዊ ወገኖቻችን መካከል በጥቂቱ። (ከግራ ወደ ቀኝ) ዳኛ ብርቱካን ሚደቅሳ፣ ፓስተር ኃይሌ ነዕዝጊ፣ ፓስተር ዶ/ር ክፍሉ ገብረመስቀል፣ ፓስተር ተስፋጽዮን ሃጎስ እና አርስቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን።  

በቅርቡ የኢትዮጵያን ሪቪው ዋና አዘጋጅ አቶ ኤሊያስ ክፍሌ በድረ ገጻቸው ላይ አስመራ ሆነው የተነሱትን ፎቶግራፎች ተመለከትኩ። የአስመራ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የነበሩኩ ጊዜ በዚያ ያሳለፍኩትን ዓመታት ፎቶግራፎቹ አስታወሱኝ።

ብዙ ጊዜ በፖስት ካርድ ላይ የምናየው፣ ዘንባባዎች በዳርና በዳር ያሉበት መንገድ የሚያልፈው፣ ፒያሳ ወይንም ኮምፖሽታቶ በሚባለው ሰፈር ነው። በዚያ መንገድ ብዙ ኬክ ቤቶችና ቡና ቤቶች ነበሩ። ትዝ ይለኛል በአምሳ ሣንቲም አንድ ኬክና ምን የመሰለ ካፑቺኖ እናዝ ነበር። በተለይም ሲመሽ ከመብራቶቿ ጋር ከተማዋ በጣም ታምራለች።

ከከተማዋ ውበት ባሻገር የማልረሳውና በውስጤ የተተከለ አንድ ሌላ ነገር ቢኖር የህዝቡ ፈሪሃ እንግዚአብሔር እና ደግነት ነበር።

እስቲ አንዳንድ ያጋጠሙኝ ላጫውታችሁ። አንድ ቀን በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ወዳለው ካፍቴሪያ እራቴን ለመብላት እየሄድክ ሳለ ጓደኞቼ አገኙኝና “አትሄድም እንዴ?” አሉኝ። “የት?” አልኳቸው። “ንግደት” አሉኝ። ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር ያንን ቃል የሰማሁት። ጓደኞቼ ነገሩን ያውቁ ነበርና ምን እንደሆነ በኋላ አስረዱኝ።

ያን ቀን በአስመራ በሰሜን ምዕራብ በኩል ቪላጆ የሚባል ሰፈር፣ የሚካኤል ይሁን የገብርዔል ቤተክርስቲያን አለ። (የቱ እንደሆነ አሁን አላስታወስም)። የዚያ ቤተክርስቲያን ታቦት የሚወጣበት ቀን ነበር። ታዲያ ቤተክርስቲያኗ አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎች ታቦቱ በነገሠሰበት ቀን ደግሰው በአካባባው ያሉትን ሁሉ ይጋብዙ ነበር። ይሄ ሥርዓት ነው እንግዲህ “ንግደት” የሚባለው።

ያኔ መኪና የለንም። በእግራችን ከአንድ ሰላሳ ደቂቃ በኋላ ቪላጆ ደረሰን። አራት ተማሪዎች ነበርን። በሰፈሩ ስንሽከረከር “ኑ ግቡ!” ብሎ የሚጠራን ሰው አጣን። ለካ ኑሮ በጣም ስለተወደደ እንደድሮ በየመንገዱ እየቆሙ “ብሉልን ጠጡልን” ማለት ቆሟል። “መቼም የዩኒቨርሲቲ ካፍቴሪያ ምግባችንን ትተን ባዶ ሆባችንን አንመለስም” ብለን ወደ አንዱ ቤት አመራንና አንኳኳን። “እንኳን አደረሳችሁ!” ስንል፣ አንዲት ያኔ ወደ አርባ ዓመት የሚጠጋት እናት፣ በእጇ አንድ ሕጻን ልጅ ታቅፋ ወጣችና “ግቡ! ግቡ!” አለችኝ በፈገግታ። የቤቱ በር ጠባብ ነበር። ጎንበስ ብለን ገባን። የነበረችዋን ጠረጴዛ ከበብናት። በትልቅ ትሪ እንጀራ ቀረበልን። ከዚያ ሴትየዋ ድስቱን አመጣችና ወጡን እንዳለ እንጀራው ላይ ገለበጠችው። ብዙ ጊዜም አልፈጀብንም ትሪውን ጠረግነው። ከዚያም በትላልቅ ጣሳዎች ጠላ አመጣች። ምን ልበላችሁ ምን የመሰለ መስተንግዶ ተደረገልን።

አስመራን ሳስብ፣ የአስመራ ነዋሪዎችን ሳስብ ያቺን ሴት አስባለሁ። ለእግዚአብሔር ፍቅር ስትል፣ እንግዳን በደስታ የምትቀበል ችግረኛ ናት፤ ነገር ግን ከፊቷ ውስጣዊ ሠላም ያላትና ሰውን የምትወድ ትልቅ ሴት ነበረች። ያኔ በትግሪኛ አይደለም ያናገርናት። “የኔ ዘር ናቸው” ብላ አልነበረም ያስተናገደችን። ነገር ግን ትልቅ ሴት በመሆኗ እንጂ።

የማያልፍ ነገር የለምና የዩኒቨርሲቲ ትምህርታችንን አጠናቀን የምረቃችን ቀን ደረሰ። ባጽዕ (ምፅዋ) በህዝባዊ ሓርነት ኤርትራ ግንባር ሥር ከወደቀ በኋላ በምፅዋና በአስመራ መሃከል ከሚገኝ አንድ የከፍታ ቦታ፣ “ግራፒ” እንለው የነበረ ከሩቅ የሚተኮስ መድፍ በየጊዜው አስመራ ከተማ ላይ ያርፍ ነበር። በዚህ ምክንያት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አስመራ መብረሩን አቁሞ ነበር። (የጦር አውሮፕላን ግን ማረፉን አላቆመም)።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስለማይበርም ቤተሰቦቻችን ለምረቃችን ከአዲስ አበባ ሊመጡ አልቻሉም። ስለዚህ የምረቃ ሥነሥርዓታችን ብዙ አልጓጓንለትም ነበር።

የምረቃችን ሥነ-ሥርዓት ቀን በወንዶች ሽንት ቤት ውስጥ ትልቅ ፈንጂ ፈነዳ። ያን ሰዓት ትልቅ ድንጋጤ በዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ ለጥቂት ደቂቃዎች ተፈጠረ። ወዲያው ሻዕቢያ የደስታ መግለጫ መልዕክት ማስተላለፉ ነው ብለን ቀልደን አለፍን። ከሩቅ በሚተኮስ መድፍ በግራፒ ተምሮ በፈንጂ መመረቅ ይሉታል ይሄ ነው።

ያ ቀን ከፈንጂ ፍንዳታው ሌላ የማልረሳው፣ በጣም ልቤን የነካና ከኤርትራ ህዝብ ጋር ዘላቂ ፍቅር እንዲኖረኝ ያደረገ አስደናቂ ነገር ሆነ። ቤተሰቦቼ ከአዲስ አበባ ስላልመጡ የምረቃ ልብሴን አውልቄ ወደ ዶርሚተሪ ለማምራት እየተዘጋጀሁ ሳለ ድንገት፣ አንዲት ሴትዮ አበባ ይዘው ብቅ አሉ። ‘ትዬ ዘይዳ ነበሩ። ትንሽ ቆይቶ ደግሞ አንዲት አሮጊት ሴትዮ ሌላ እቅፍ አበባ ይዘው መጡ። አደይ ፀሐይቱ ነበሩ። ሁለቱም አይተዋወቁም። በአራት ዓመት የአስመራ ቆይታዬ የተወዳጀኋቸው እናቶች ናችው። ‘ትዬ ዘይዳ እና አደይ ፀሐይቱ ከመምጣታቸው በፊት ብቻዬን የሆንኩ መስሎኝ ነበር። ግን ከአንድም ሁለት እናቶች እንደ እናቴ ሆነው አበባ ይዘው በምረቃዬ ተገኙ።

እነዚህ ሁለት እናቶች እኔን ምረቃ አስመልክተው ዶሮ አርደው ቤታቸው ድግስ አዘጋጅተው ነበር። ሁለቱም ወደ ቤታቸው እንድመጣ ፈለጉ። ግራ ገባኝ። በኋላ አንዳቸው ጋር ምሳ ሰዓት፤ ሌላኛዋ ጋር ደግሞ ሲመሽ ሂጄ ከጓደኞቼ ጋር የተዘጋጀልኝን ድግስ ተካፈልኩ።

አስመራን ሳስብ፣ የአስመራን ህዝብ ሳስብ ትዬ ዘይዳ እና አደይ ፀሐይቱን አስባለሁ። እነዚህ እናቶች በስጋ እናቶቼ አይደሉም። እንደነርሱ ትግሬ አይደለሁም። እንደነርሱ የኤርትራ ተወላጅ አይደለሁም። የእነዚህን እናቶች የዋህነት፣ ፍቅርና ያላቸውን ፈሪሃ እግዚአብሔር ከተግባራቸው እናያለን። የእነዚህ እናቶች ደጎችና ለዘር ቦታ የማይሰጡ መሆናቸውን አይቻለሁ፤ እናንተም ይህን ማየት እንደምትችሉ አምናለሁ። እነዚህ እናቶች ባይወልዱኝም እናቶቼ ናቸው! እግዚአብሔር ባሉበት ቦታ ያክብራቸው! - አሜን!!!

የመጨረሻ ዓመት ተማሪ እያለን በአንድ ሃይ ስኩል (ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት)፣ ለሦስት ወር ማስተማር ነበረብን። ባርካ ተብሎ በሚታወቅ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመደብኩ። የተመደብኩበት ክፍል አስተማሪ ክፍሉ በጣም ረባሽ ክፍል እንደሆነ አስጠነቀቀኝ። በጣም ፈራሁ። ነገር ግን ማስተማሩን ስጀምር የተካሁት አስተማሪ ከነገረኝ የተቃረነ ሁኔታ ነው ያየሁት። ተማሪዎቹ በጣም የሚያዳምጡ፣ በአክብሮት ከተያዙ ብዙ ሊሠሩ የሚችሉ ሆነው ነበር ያገኘኋቸው። አስተማሪያቸውም ብሆን ጓደኞቼም ሆነው ነበር የተለያየነው። ያኔ ከተማዋ ችግር ላይ ነበረች። እንደዚያም ሆኖ ግን ከፊታቸው፣ ከሁኔታቸው ያየሁት ፍቅርንና ደስታን ነበር።

አስመራን ሳስበ፣ የአስመራን ህዝብ ሳስብ ያኔ ወርቃማ ዩኒፎርም ለብሰው የማስተምራቸውን ያዳምጡ የነበሩትን፣ ሳስረዳቸው ፊቴን ያዩ የነበሩትን የባርካ ተማሪዎችን አስታውሳለሁ።

እርግጥ ነው ብዙ የሚያሳዝኑ ነገሮች በአስመራ አይቻለሁ። እርግጥ ነው ከተማዋ ያኔ መለስተኛ ጦር ግንባር ነበረች። እርግጥ ነው በየጊዜው ሳይታሰብ በሻዕቢያ የሚተኮስ መድፍ ባልተጠበቀ ቦታ ያርፍ ስለነበረ ብዙ ሰዎች አልቀዋል። እርግጥ ነው በደርግ ወታደሮች የተሠሩ ብዙ ግፎች ነበሩ።

ነገር ግን እንደዚያም ሆኖ የህዝቡ ፍቅር አሸንፎኝ ነው የጦር መሣሪያ በተሸከመ የጦር አውሮፕላን፣ መሣሪያ ላይ ተቀምጬ ከተማዋን የለቀቅሁት። አሁንም ለአስመራ ትልቅ ፍቅር አለኝ። አሁንም አስመራን ከአዲስ አበባ ቀጥሎ እንደከተማዬ ነው የማያት። አሁንም ያንን ህዝብ እንደ ህዝቤ ነው የማየው። አሁንም ኤርትራውያንን ከተቀረው ኢትዮጵያዊ እንደተለዩ ተደርጎ ሲታይ አያስደስተኝም።

በዚህ ምክንያት ነው የኤርትራን መገንጠል አጥብቄ የተቃወምኩት። አሁንም የምቃወመው። ለዚህ ነው ከመረብ ደቡብ ይኖሩ የነበሩ ወደ ኤርትራ፣ ከመረብ ሰሜን ይኖሩ የነበሩ ደግሞ ከኤርትራ በግፍ እንዲባረሩ መደረጉ ትልቅ ታሪካዊ ስህተት ነው የምለው። ለዚህ ነው የባድመ ጦርነት የወንድማማቾች የርስ በርስ ጦርነት እንጂ ከውጭ ኃይላት ጋር የተደረገ ጦርነት አይደለም የምለው።

በአዲስ አበባና በአስመራ ዲሞክራቲክ መንግሥት ቢኖር በፍቅር፣ በውይይት፣ ለሁሉም በሚጠቀም መልኩ የኤርትራ ችግር ይፈታል የሚል ሙሉ እምነት አለኝ። ኤርትራም ከኢትዮጵያ ጋር ትዋሃዳለች። በሳባ ስቴዲየም ቺፖሊኒና ጊዮርጊስ ይጫወታሉ። በአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን ፊት ለፊት ከአስመራ የመጡ እንደ ተስፋጋብር አይነት ብስክሌተኞች የብስክሌት ጥበባቸውን ያሳዩናል።

ስለዚህ ትኩረት በኤርትራውያንና በተቀረነው መሃከል ያለውን ያለፉት አሳዛኝ አስራ ሰባት ዓመታት የፈጠሯቸው ጠባሳዎች ላይ መሆን የለበትም።

ትኩረቱ፣ በአዲስ አበባና በአስመራ ህዝብን የሚያከብሩ፣ ለሕግ የበላይነት የሚገዙ መንግሥታት እንዲዘረጉ ማድረጉ ላይ መሆን አለበት። አቶ መለስ ዜናዊና ድርጅታቸው ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን፣ ቴዲ አፍሮን፣ … የመሳሰሉ የሕሊና እስረኞችን በመፍታት፣ የህዝብን ጥያቄ እንዲያከብሩ፣ አቶ ኢሳያይስ አፈወርቂ ደግሞ የቀድሞ የአስመራ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሣይንስ ዲን የነበሩት ዶ/ር ክፍሉ ገብረመስቀልን፣ ፓስተር ኃይሌ ነእዝጊን፣ ፓስተር ተስፋጽዮን ሃጎስን፣ … የመሳሰሉ በእምነታቸው ምክንያት የታሰሩትን በመፍታት፣ ከግትርና ከእልህ ፖለቲካ ወጥተው ለህዝብ ጥያቄ ቅድሚያ እንዲሰጡ ማድረጉ ላይ ትልቅ ግፊት መደረግ አለበት እላለሁ።

“ከአቶ ኢሣያስ ጋር መነጋገር ያስፈልጋል” የሚሉ ወገኖችን አልቃወምም። ሻዕቢያም ሆነ ኢህአዲግ አንድ ናቸው። ሁለቱም በእናት ሀገራቸው ላይ ትልቅ ጥፋት እያደረጉ ያሉ ኢትዮጵያውያን ናቸው። (እነርሱ አይደለንም ሊሉ ይችላሉ፤ ነገር ግን - “ኢትዮጵያዊ መልኩን፣ ነበር ጅንጉርጉርነቱን ይቀይራልን?” እንደተባለ ኢትዮጵያዊነት ፓስፖርት በመለወጥ ወይንም በመጣል የሚጠፋ ቀላል ነገር አይደለም። ኢትዮጵያዊነት የውስጥ የሆነ ማንም የፖለቲካ ሥርዓት የማይለወጠው ማንነታችን ነው።)

“ኢህአዲግን እናነጋግር” እንደምንለው ሁሉ ከሻዕቢያ ጋር መነጋገሩን እደግፋለሁ። በአንዳንድ ድረ ገጾች እንደምናነበው አስመራ በርሮ መሄድ ወንጀል አይደለም። ከኤርትራውያን ጋር መወያየት የኢትዮጵያን አንድነት መጉዳት አይደለም። ከኤርትራ መሪዎች ጋር ውይይት የሚያደርጉትን ከመቃወም ይልቅ፣ በኢትዮጵያ ዲሞክራሲ እንዲኖር እንታገላለን እስካሉ ድረስ፣ በኤርትራ ያለውን አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ረገጣ ትልቅ ቦታ እንዲሰጡት ማሳሰቡ ይበጃል እንጂ።

ያ ካልሆነ ግን ኤርትራ ያሉ ወገኖቻችን በላያቸው የግፍ ቀንበር ተጭኖባቸው አቶ ኢሣያስ አፈወርቂ ለተቀረው ኢትዮጵያዊ መፍትሔ ይሆናሉ ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው።


ግርማ ካሣ
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ