ልጅ ተክሌ

“ለኢትዮጵያ ህዝብ ሰቆቃ ለማዋጣታችን ማስረጃ አለ፤ ለኢትዮጵያ ህዝብ መፍትሄ ለማዋጣታችን ግን ማስረጃ የለም!! እርስ በርሳችን በመናከስና መወያየት ባለመቻላችን የጠላታችንን እድሜ እያራዘምን ነው” ከተሰብሳቢዎች አንዱ

 

ማን ተሰባሰበ? ለምንስ ተሰባሰብን?

 

ባለፈው አንድ እሁድ ቀን በ2 ሺህ ዘጠኝ ዓ.ም. በሁለት ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን አነሳሽነት የተሰባሰቡ ወደ ሀምሳ የሚጠጉ ሌሎች ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን በአካባቢያቸው ያሉ ኢትዮጵያዊያን ግለሰቦችና ድርጅቶች፤ በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ለውጥ ማምጣት የቀን ተሌት ህልማቸው ሆኖ ሳለ፤ በጋራ ጠላታቸው ላይ በማተኮር ፈንታ እርስ በርስ መናከሳቸው፤ በእንግሊዝ፣ በአሜሪካና አልፎ አልፎም በካናዳ በሚገኙ ኢትዮጵያዊያን መካከል ወንጀል ነክና ሌሎች ማህበራዊ ቀውሶች መንሰራፋታቸው፤ እንዲሁም በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ምክንያት ያጋጠማቸውን ችግር በሞዜይክ መሰብሰቢያ አዳራሽ ለሶስት ሰዓታት ሲመክሩበት ውለው የሚከተለውን ውይይት አድርገው፤ ለጥቆም የሚለጥቀውን ውሳኔ አስተላልፈዋል። መጀመሪያ ውይይቱን አስከትለንም ዋና ዋና ውሳኔዎችን ቃለ-ጉባዔ ያዣችን እንዳሰፈረው እንዘግባለን።

 

ሃሳብ ሲንሸራሸር፡ ቁጭት ሲሽከረከር

 

የስብሰባው አንዱ አዘጋጅ ምርር ብሎትና አዝኖም፤ ግን ደግሞ በለሰለሰ አንደበት እኛ ኢትዮጵያዊያን መወያየት ባለመቻላችን እንደተጎዳን ገልጾ “ዘወትር መሪዎቻችንን መከተል ብቻ ሳይሆን አልፎ አልፎም መሪዎቻችን እኛን እንዲያደምጡ” ማድረግ እንዳለብን አብራርቶ ሲያበቃ፤ ብዙ ሰዎች ብዙ ገንቢ ሀሳቦችን መሰንዘር ጀመሩ። አንድ ለረጅም ግዜ በካናዳ የኖረና የዚህን ዓለም ህይወት ጠንቅቆ የሚያውቅ ሕይወት ያስተማረው ጥሩ ጎልማሳ እንዲህ ሲል ተናገረ። ብዙ ግዜ አጥፊ ሀሳቦች የቅጽበት ጉዳይ እንደሆኑና ያንን ቅጽበት ማለፍ ከቻልን ችግሩን በሙሉ ማለፍ እንደምንችል፡ የራሳችን የጋራ ማእከል ባለመገንባታችን ምክንያት መንግስት የሚመድበው ገንዘብ እያመለጠን እንደሆነ ከራሱ ተሞክሮ ገለጸ። ሌላው ጥሩ ሰው ቀጠለ። ቅስሙ ስብር ያለ ይመስላል። “ዛሬ ብዙ ኢትዮጵያዊያን ጨልሞባቸዋል”። የዛሬን አያድርገውና ከልመና ይልቅ ኩራት የሚገድላቸው ዘመዶቼን ችግር መስማት ሰልችቶኝ ስልኬን መዝጋት ከጀመርኩ ሰነበትኩ” አለ። “ዛሬ በሀይማኖት ለመለያየት ጊዜ የለንም። በጾታ ለመለያየት ጊዜ የለንም። በቡድን ለመለያየትም ጊዜ የለንም። እያንዳንዱ ደቂቃ የሰቆቃ ጊዜ ነው። ይሄ ሰው ነው “ለኢትዮጵያ ህዝብ ሰቆቃ ለማዋጣታችን ማስረጃ አለ፤ ለኢትዮጵያ ህዝብ መፍትሄ ለማዋጣታችን ግን ማስረጃ የለም” ያለው። ችግር ብቻ ተብትቦ አልቀረም። መፍትሄም ሰነዘረ እንጂ። “እያንዳንዳችን ተልእኮ እንውሰድ። ሀላፊነት።” ጊዜ የለንም። ያሉብን ችግሮች ጊዜ አይሰጡንም። በጣም የሚያናቁረን የሚያለያየን መሰረታዊ ልዩነት አለን? ብሎ ጠየቀና፡ ይህ ሰው ራሱ መለሰው ጥያቄውን። ምንም አጥጋቢ ምክንያት የለንም። “ወዲህ የደርጅት ፍቅር ወዲያ ደግሞ የራስ ክብርና ዝና ነው ያንገላታን፡ የበላን” ሲል አማረረ።

 

ይህ ሰው አላበቃም፤ አልወጣለትም። ቀጠለናም፡ “የኢትዮጵያን ዘመን በሁለት ብንከፍለው የብርሃንና የጨለማ ዘመን ነው። ከዚህ በኋላ ጉዳያችንና መርሀችን መሆን ያለበት ኢትዮጵያን ማስቀደም ነው። አሁን ጨለማ ውስጥ ነን። የሀይማኖትም የጾታም የፖለቲካም ጊዜ አለው። እያንዳንዳችን በያንዳንዳችን መንገድ ላይ የምንቀብረውን ፈንጂ ማቆም አለብን። ግንቦት ሰባት፣ ኢህአፓ፣ ሀሰን፣ ዘውዴ፣ ቅንጅት አንድ የሚያደርገን ኢህአዴግን መጣል ነው። የሚያጣሉን ግን ጥቃቅን ነገሮች ናቸው። የገደሉን እኔ ያልኩት ካልሆን፤ የኔ ድርጅት ስም ካልተነሳ ነው። በዚህ ረገድ በቫንኩቨር አካባቢ ችግሮችን ለመፍታት የምናደርገው እንቅሰቃሴ መልካም ነው። ዛሬ ግን ቃላችንን አድሰን፣ ቃለ ገብተን እንወጣለን፤ ከምንም በላይ ኢትዮጵያን እናስቀድም ብሎ ሀሳቡን ጠቀለለ።

 

ዮሴፍ መጣ። ነቢዩ ዮሴፍን ይመስላል። ረጋ ያለ ንግግሩ ሰርስሮ እስኪገባ ጊዜ እየሰጠ የሚናገር የሚመስል ሸጋ ሰው ነው። ሰዓሊ ነው። ስእል ይስላል። ሃሳብም ይስላል። ይገጥማልም። ገሞራውን አመጣው። ምን ነበር ያ ግጥም? “ያሰብከው (ዓላማ?) አልሆን ብሎ ከሮ ሁኔታው ቢጠጥር፡ ጠጣሩ እንዲላላ የላላውን ወጥር።” ዮሴፍ ራሱ ሲናገር፤ የላላውን የሚወጥር የጠጠረውንም የሚያላላ ይመስላል። ነውም። እንዲህ ሲልም ጠየቀ፤ መሀላችን ያሉ፣ የጠበቁ፣ የላሉስ ነገሮች ምንድናቸው? ትናንሽ ነገሮች ላይ እናተኩር። እንስራ። የምንመኘው ትልቅ ነገር የምንሰራቸው ትንንሽ ነገሮች ስብስብ ነው። ትንንሾቹ ነገሮች አድገው አድገው ወዳላሰብነው ወደተለያዩ ትልልቅ ነገሮች ያድጋሉ። አቦ ሰዓሊ ይግደለን አልን። መስራት ያለብንን ብዙ ነገር በትንሽ ዐረፍተ ነገር ሳለው።

 

አንዱ የስብሰባ አዘጋጅ ተመለሰ፤ ችግሮችን እንመርምር፤ የድርጅት ፍቅር

 

መሰረታዊ ችግር ያለው ከራሳችን ነው አለ። ሃላፊነት መውሰድና የችግሮችን ስረ-መሰረት መመርመር አለብን። ይሄን ሰው በያካባቢው የሚሰማው ማህበራዊ ችግር አውኮታል። ሊባኖስ ውስጥ 27 ራሳቸውን የገደሉ ኢትዮጵያዊያን ይታዩታል። ወደ የመን ለማቋረጥ ቀይ ባህር ውስጥ የሚሰጥሙ አበሾች ይመጡበታል። ደቡብ አፈሪካ ለመግባት መንገድ ላይ ከአውሬ የሚፋለሙ ወጣቶች ያስጨንቁታል። “ይህቺን ሀገር መጠበቅ መነሳት አለብን” ይላል። ያለንን እውቀት ለኢትዮጵያዊ ጉዳይ የምናበረክተው መቼ ነው? እያንዳንዳችን በቀን ለ3-4 ሰዓት ያህል ለቲቪ እናባክናለን። ባለፈው ሰሞን ኢትዮጵያዊያን ተራቡ በተባለ ጊዜ ከኛ ያልተወለዱ የካናዳ የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪዎች የ3 ቀን ጾም፤ ሂሳብ ለሚሳናችሁ ቀን ቀኑን ብቻ ስትቆጥሩት፣ የሰላሳ ስድስት ሰዓት ጾም አድርገው 9000 ዶላር ልከዋል። ወደ ኢትዮጵያ። ማኩረፍ መገለማመጥ አያስፈልግም። መከባበር መተባበር እንጂ። ነገ የምንሞት ሰዎች የሚያኮራ ታሪክ ሰርተን ማለፍ የሚያስችለን ሙሉ ሰውነት አለን። መከባበር። ራሳችንን መመርመር። ችግሩ ከኛ ከራሳችን ነው። ሀላፊነት መውሰድ መጀመር አለብን። ይህ ሰው ይመክራል። ይናገራልም።

 

ሌላው ደግ ሰው መጣ። መፍትሄ ነው መፈለግ ያለብን ብሎ ጀመረ። የድርጅቶች መከፋፈል ነው እኛንም የከፋፈለን። የተለያዩት ድርጅቶች ተገናኝተው ተጠራርተው ችግሩን ካልፈቱት በስተቀር እንዴት እንደምንሰባሰብ አይታየኝም። ይሄ የቡድንተኝነት ነገር አለ። “እኔ የምጠላው ሰው ካለ አልመጣም አይነት ነገር”። እዚያው ባላጋራዎቻችንም ውስጥ ሁኖ ስለመታገልም አንስቷል ይሄ ሰው። እነዚህ ሰዎች አደገኞች ናቸው። ኢህአዴግን ማለቱ ነው። በሀያ ዓመቴ ኢትዮጵያ ስሄድ፡ “ምንድነው አገሩ ይሞቃል። አዲስ አበባ እንደዚህ አልነበረም?” ስላቸው፡ “እነዚህ ሰዎች ናቸው ሙቀቱን የሚጨምሩትና የሚቀንሱት፤ ሲናደዱ ይጨምሩታል፣ ሲደሰቱ ይቀንሱታል። ዝም ስንል ራሱ ለምን ዝም አላችሁ ብለው ይንጡናል። በግድ ተናገሩ።” ብሎ አንድ ዘመዱ እንዳጫወተው ነገረን። ሰዎቹ አደገኞች ናቸው። እነዚያው የላይኞቹን ማለቱ ነው። ረቂቅ ናቸው። በእንግሊዘኛ “ብሪሊያንት” ናቸው አለ። ጉባዔውን እንደወረደ ነው የምናትተው። እና እዚህ ቁጭ ብለን መፍትሄ ማምጣት አንችልም። ድርጅቶቹ ተቀምጠው ልዩነታቸውን ያስወግዱ። እኔ የብርቱካን ነኝ፣ እኔ የዚያ የምንል ከሆነ ዋጋ የለውም። እንደ ቀላል አንየው ችግሩን። ዲሞክራሲ ሲኖር ውይይቶቻችንን እልባት እናገኝላቸዋለን። አንድ ሰው ሲናገር ፐርሰናሊቲውን እንወስዳለን። መቻቻል መተላለፍ አለብን። ሰውን ማለፍ ጥፋተኝነት እንዲሰማው ሊያደርግ ይችላል። መጋፈጡ ለክርክር ሲጋብዝ። ይሄንን ባህል ማሳደግና ማዳበር አለብን። ድርጅቶች ተለያያተው በተናጠል ብንጠራራ ዋጋ የለውም። ብንጠናከ፤ አንድ የወል ብንሆን መልካም ነው።

 

ሴቶችም ነበሩበት፤ አፍአዊና ተግባራዊ “ዲሞክራሲ”

 

ሌላ ወጣት መጣ። በተጠናከረ ሲቪል በሆነ ሁኔታ የምንወያይበት መድረክ ያስፈልጋል። እኔ የድርጅት ፍቅር የለብኝም። ግን አንዳንድ ጊዜ ስር የሰደደ ችግር አለ። ስራ ለመስራት መደራጀት ያስፈልጋል። ከምንም በላይ ግን እያንዳንዳችን የየራሳችንን የፖለቲካ መብት ማስከበር አለብን። መወያየት፣ መነጋገር ያስፈልጋል። ረጋ ብሎ ሃሳብን ማብላላት በመቻቻል መወያያት ያስፈልጋል። ይሄንን መድረኩን የወንዶች ብቻ ማን አደረገው? እነሆ፡ አንድ እህት መጣች። ትንታግ የሆነች ሴት ናት። ጊዜ የለንም የሚለውን የአቶ ዘውዱን ሃሳብ በአጽንኦት ደገመችው። አስራ አምስት አመት ተዳርቄ አስራ ስደስተኛ መዳረቅ አልፈልግም። እንደውም ሁለት ቀነሰችላቸው። ርግጥ ነው መከፋፈል ማንንም አልጠቀመም። ግን ደግሞ ተንኮለኞች አሉ። ስለዚህ የሚሰራውን አይቼ የሚጠቅመውን መርጬ እጓዛለሁ። ለኢትዮጵያ የማይጠቅም ከሆነ ወደተሻለው ቦታ እሄዳለሁ። እየተሸነጋገልን፣ እየተደባበቅን፣ እያስመሰልን መኖር ይብቃ። እነሆ የመጋለጥ ቀን ዛሬ ነው ብላ ሃሳቧን ደመደመች።

 

ሌላው ወዳጃችን መጣ። ከማድነቅ ነው የሚጀምረው። ባለፈው በዚህ በቫንኩቨር የተካሄደው የስነጽሁፍ ምሽት ድንቅ ነው። ከዚያ ቀደም ብሎ ሴቶቹ ያስተባበሩት የብርቱካንን ቤተሰቦች ገንዘብ መርጃ ዝግጅት ወርቅ ነው። ይሄ ስብሰባ ራሱ መልካም መፍትሄና ወደመፍትሄው አንድ ርምጃ ነው። እኛን ካስቸገረን ነገር እንጀምር አለ። ፖለቲካ። በሱ ቋንቋ የፖለቲካ ጉዳይ ነው እኛን የበወዘን። ግን ይሄ የመነጨው ባንድ በኩል ፖለቲካ የቡድን ስራ መሆኑን እያመንን በሌላ በኩል ግን ፖለቲካ በሃሳብ ከሚጣጣሙን ጋር ብቻ ሳይሆን ከማይጣጣሙንም ጋር መሆኑን ከመዘንጋት ነው። ሌላ ምሳሌ በያንዳንዱ በምንሰራው ፖለቲካዊ ስራ ውስጥ በምንሰይማቸው ድርጅቶች፤ በምናቋቁማቸው ቡድኖች ውስጥ፡ “ዲሞክራሲያዊ” የሚል ቃል ሻጥ እናደርጋለን። ያ ማለት ሁላችንም በአፍአዊ ደረጃ ዲሞክራሲ መፍትሄ በመሆኑ እናምናለን ማለት ነው። ግን ደግሞ ተግባራዊ የሆነ ዲሞክራሲን በውስጣችን ያለማስረጽ ችግር አለብን። የአመለካከት ልዩነቶች ይኖራሉ። ያ ግን አንድ ከመቶ ነው። እንደሰው አንድ የሚያደርገንን 99 ከመቶ ባህርይ ችላ ብለን ያ አንድ ከመቶ ችግራችን ዘጠና ዘጠኝ ከመቶውን መልካምነታችንን ይዞት ይጠፋል። ወያኔን እንጠላለን። ግን በያንዳንዳችን ውስጥ ትንሽ ትንሽ ወያኔነት አለ። በሌላ አነጋገር ወያኔነት የአመለካከት ችግር ከሆነ ከወያኔ ጋር አንድ የሚያደርገን ልዩነትን ያለመቀበል፣ የአመለካከትና የባህርይ ችግር አለ ማለት ነው። ስለዚህ ራሳችንን መመርመር አለብን። የህዝባችንን ችግር እንፈታለን ብለን ከማለታችን በፊት ራሳችንን መመርመር አለብን። የራሳችን ጥቃቅን ችግሮችና ልዩነቶች ይኖራሉ። በእነሱ ምክንያት ግን ቤት አይፈርስም። ከጥርጣሬና ከፍርሀት ወጥተን በራሳችን ላይ የባህርይ ለውጥ ለማምጣት መታገል አለብን። የባህርይ ለውጥ ይሰመርበት።

 

እንደልቡ መጣ። እዚህም እንደልቡ ነው እሱ። ሌላ አንበሳ ነው። ይሄኛው ከወያኔዎች ጋር የሚደረግ መተሻሸት አይመቸውም። ሁላችንም ወያኔዎች የሚያደርጉትን እናውቃለን። ለምሳሌ ከቤተክርስቲያን መከፋፈል ጋር በተያያዘ፡ ቤ/ክኑ ለሁለት ተከፍሏል። እዚህ ቫንኩቨር ያለውን ቤ/ክ ማለቱ ነው። “አባ ጳውሎስ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን አሳልፈው ሰጥተዋል። ከሳቸው ጋር መተሻሸት ከወያኔ ጋር መተሻሸት ነው” የሚል ነው መልእክቱ። ምክንያት፡ “የሀይማኖት አባት ጨቋኝ ስርአትን መደገፍ የለበትም” ነው የሚለው። የፖለቲካ ድርጅቶች አባል ስለመሆን፡ “ያ ምንም ችግር የለውም። ችግሩ ያንን ድርጅት አልወደውም እዚያ ድርጅት ጋር አልሄድም ነው። የኢህአፓን ድርጅት አለመደገፍ መብት ነው። ግን ኢህአፓ ወያኔን ቢቃወም ሁላችንም ከጎናቸው መቆም አለብን። እኛ ጋር ያለው ችግር ግን የዚህ የዚያ ድርጅት አባል ነኝ ስለዚህ የሌላኛውን አይኑን አልይ የማለት ችግር ነው። ፖለቲካ ድርጅት መሳሪያ ብቻ ነው። እኛ የምንገለገልበት መሳሪያ። እኛ ግን እንነሳና ለፖለቲካ ድርጅት የበላይነት ስንታገል እንኖራለን። ይሄ ያ መገልገያችን ሊሆን ለሚገባው ፖለቲካ መገልገያ መሳሪያ መሆን ነው። ለዚያውም ሰንካላ መሳሪያ። ይሄም ይሰመርበት። አቋማችን ነውና።”

 

ምስኪኑ ጋሽ ከቤ፡ እንግዳው ኃይሌ

 

አቶ ከበደ ዕድል ደረሰው። ጋሽ ከቤ ምስኪን ነው። ሰው ታሰረ ከተባለ የዚያን ሰው ፎቶ ታቅፎ ለአሜሪካን ባለስልጣናት ለካናዳ ሹማምንት እሪ ሲል ይኖራል። “ዳር ዳር አንሂድ” አለ። “ወያኔ እየሳቀና እየተጫወተ ነው የሚገድለን።” ሳቅ፡ ፈገግ እያለ ነው የሚናገረው። “ይሄ ሀገር፡” ካናዳን ማለቱ ነው “ዲሞክራሲ ያለበት ሀገር ነው። የሰላም አየር እንተነፍሳለን። የማንንም ድርጅት ሳንቃወም ስራችንን መስራት እንችላለን። ተከባብረን፡ በመፍትሄ፡ “አሉ”ን ትተን በማስረጃ መንቀሳቀስ አለብን።” ቀደም ሲል እስብሰባው መጀመሪያ ላይ ሃሳብ የሰጠው ጎልማሳ መፍትሄ ብሎ ጠቆመ። መልእክቱ ለፖለቲካ ድርጅቶችና አባላቶቻቸው ነው በተለይ። “እዚህ ሳንደጋገፍ እዚያ የኢትዮጵያን ህዝብ እንደግፋለን ብንል አይሰራም። ውሸታሞች ነን።” አቶ ግርማቸውም ለጠቀ። ድሮ ዩ ኤን እህል ከሁመራ ገዝቶ ወደ ውጭ ይሰጥ ነበር። ቀደም ሲል ኢትዮጵያ ካናዳን ስለመርዳቷ ከሰማነው ታሪክ ጋር ተመሳሰለብን። የዛሬ ሰማኒያ ዓመት አካባቢ ካናዲያዊያን በድርቅ ምክንያት የዘር እህላቸውን በበሉ ጊዜ ኢትዮጵያ የዘር ስንዴ ረድታለች ከሚለው ጋር። አሁን ኢትዮጵያ ሰው ተራበ ሲባል እጅግ ያስደነግጣል። ሌላ ሰው ተከተለና፡ “በመከካከችን የሃሳብ ተቃውሞ ቢነሳ መቃወም ወይም ብዙ መጋፈጥ እንደሌለብን ያም ተቃውሞ ማንሳቱ ገንቢ እንደሆነ” ተናገረ።

 

በእንግድነት በአካባቢያችን የሚገኘውና ውይይቱን ሲያዳምጥና ሲያላምጥ የዋለው ኃይሌ ቀጠለ። “አስተውሎና አይቶ መምጣት ይለያያል። አስተውለን መምጣት አለብን። ሰዎች ስለአንድ ነገር የተለያየ አመለካከት ይኖራቸዋል። አንዱ ወዲህ አንዱ ወዲያ ሊል ይችላል። ስኪርፒቶ ግን ስኪርፒቶ ነው። በሰዎች አመለካከት ምክንያት አይለወጥም። በሰለጠነው ዓለም ፖለቲካ መዝናኛ ነው። ደስ እያላቸው እየተዝናኑበት ነው የሚያስኬዱት። እኛ ጋር ግን ፖለቲካ መባያ፣ መጣያ ነው። ሲናደዱ ነው የምናየው። ፖለቲካ የሃሳብ ነጻነት ይጠይቃል። ያ ሰው ይናገራል። ለሃሳብ መለያየት መልሱ ሌላ ሃሳብ ነው። ምናልባት እንደው ጥቁር ውሻ ውለዱ የሚለው የምኒሊክ ርግማን ደርሶብን ይሆን? የሚያናክሰን ምንም ምክንያት የለም። ቀለማችን፣ ቋንቋችን፣ መልካችን፣ ጸጉራችን፤ ደማችን አንድ … ነው። ምንድነው የሚያጣላን? የስብሰባው ሰብሳቢዎች ስብሰባውን ሰብሰብ አድርገው ከመበተናቸው በፊት የተናገረው ኃይሌ መፍትሄውን እንዲህ አለ። “አስተዋይ ፖለቲከኞች ያስፈልጉናል።” “የታሉ?” አብረን እንፈልጋቸው። አስተዋይ ፖለቲከኞች ወደፍቅር ይወስዱናል። አስተዋይ ፖለቲከኞች ወደስራ ይወስዱናል። አስተዋይ ፖለቲከኞች የራሳቸው ስሜት አይገዛቸውም። አስተዋይ ፖለቲከኞች ግልፍ አይላቸውም። አስተዋይ ፖለቲከኞች አስተዋይ ናቸው። የነገር ክፍፍል ሳይሆን የስራ ክፍፍል ይመጣል። የሃሳብ ልዩነት መኖር አለበት። ማንም የማንም ፎቶኮፒ መሆን አይችልም። ያንን መመኘት የተፈጥሮን ህግ መቃረን ነው። እኔ ብቻዬን ሻኛዬን አሳብጬ ለመኖር ከሆነ ምንም ዋጋ የለውም። ሆደ ሰፊ እንሁን። የፖለቲካ ድርጅቶችም የተለያየ ሃሳብ ሊኖራቸው ይችላል። በርግጥ የአቶ አደፍርስ የመጨረሻ ሃሳብና ማሳሰቢያ ነበር። እነሆ ይሄ ውብ ስብሰባ በሚከተለው ውሳኔ ተጠናቀቀ።

 

የመጨረሻው መጀመሪያ፡ የቫንኩቨር ውሳኔ

 

የሃሳብ ልዩነት በየትኛውም ማህበረሰብ ውስጥ ይኖራልና የሃሳብ ልዩነትን መቀበል።

 

ከታች ወደላይ እንዲሁም ወደፊትና ወደኋላ ወደጎንም ጭምር ውይይት ቢኖር መልካም ነው። የውይይት ባህል መዳበር አለበት። ስለዚህም በአካባቢያችን፡ በየአካባቢያችሁም የውይይትንና የዲሞክራሲን ባህል እንድናዳብር ጥሪ እናደርጋለን።

 

አንድ የአካባቢያችን የፖለቲካ ድርጅቶች መሪዎች ወይንም ተወካዮች የተገኙበት ውይይት ቢደረግ መልካም ነው። መግለጫም ማውጣትም አለብን።

 

ሽማግሌም ያስፈልገናል። የሽማግሌዎች ቡድን ማቋቋም ያስፈልጋል። ለጊዜውም ባይሸመግሉም ሽማግሌዎች መረጠናል።

 

የጸና ማህበራዊና ፖለቲካዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ችግር እንዳለብን ማመንና ያንንም ችግር ለመቅረፍ መተባበር አስፈልጋል።

 

ትንንሾቹን ነገሮች የመስራት ባህል ማዳበር በየግልም ሀላፊነት መውሰድ።

 

የአመለካከት ልዩነቶችን መቀበል ከመቻል ባሻገር ስብሰባ ላይ የምንመጣ ሰዎችም በጓደኝነት ሳይሆን በዓላማ እንዲሆን፤ በሁሉም ስብሰባዎች ላይ መገኘትም ወላዋይነት ሳይሆን፤ ምርጫ እንደሆነ ያም ሁሉንም የማስተናገድ ባህል መዳበር እንዳለበት ወስነናል።

 

ከምንም በፊት ኢትዮጵያ ትቅደም ማለት እንዳለብንና ኢትዮጵያን የማስቀደም ባህል ማዳበር እንዳለብን ለዚህም በጋራ መስራት እንዳለብን ወስነናል።

 

ሀሰንና ልጅ ተክሌ ይሄንን ስብሰባ አስተባብረውና አስተናብረው ታዳሚውም ዳግም ደጋግሞ ለመገናኘት ቃል ገብቶ በድል አጠናቆ ተበትኗል።


 

ይሄ መግለጫ ልጅ ተክሌ እንደዘገበው፤ ሌላው የስብሰባው አስተባባሪም እንዳጸደቀው፣ ሰኔ በገባ በመጀመሪያው ሣምንት ታትሟል። ቫንኩቨር - ካናዳ

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ