ዳንኤል ግርማ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አቶ ሠለሞን አየለአንድነትም እንደ መአህድ - ብርቱካንም እንደ አሥራትበሚል ርዕስ መአህድንና አንድነትን እያነፃፀሩ፤ በመአህድ የሆነው ሁሉ ዛሬ በአንድነት እየተፈፀመ መሆኑን ያሳዩበትን ጽሑፍ ኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ላይ አነበብኩ። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ የማይመጣ ሁሌም በትናንት ዜማ የሚያቀነቅን፣ ፖለቲከኛ ነን ባዮችም ከትናንት ስለመማራቸው እያወሩ፤ በተግባር ግን ያንኑ የሚደግሙ በመሆናቸው አያሌ የለውጥ ጊዜያት እንደዘበት አምልጠውናል። የዛሬው ሁኔታቸውም ለነገ ተስፋ የሚሰጥ ሆኖ አይታይም። 

 

"... የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በኢትዮጵያ ለለውጥ እንታገላለን ብለው የሚነሱ ኃይሎች በሥልጣን ላይ ያለውንና እንለውጠዋለን ብለው የሚታገሉት ኃይል ከሚያደርስባቸው በደል በላይ እርስ በእርሳቸው የሚያደርጉት መጠፋፋት ሚዛን ይደፋበታል። ..." 

ከዛሬ አሥር ዓመት በፊት የተፈፀመ ድርጊት በተመሳሳይ ሁኔታ ሲደገም ማየት የእርግማን ካልሆነ ምን ሊባል ይችላል። አቶ ሠለሞን ሁለቱን ፓርቲዎች እያነፃፀሩ ፕ/ር አሥራትንና ወ/ት ብርቱካንን እያመሳሰሉ ያቀረቡት ጽሑፍ መልዕክቱ ለአንድነት አመራሮችና አባላት ብቻ አይደለም። የጽሑፉ አቅራቢ እማኝነታቸውን ቸረው በአብነት ከአቀረቡት የትናንት በስቲያውን መአህድ እና የዛሬውን አንድነት በንጽጽር አለፍ ብሎ የፖለቲካ ሂደቱ ቢፈተሽ የትናንቱ ድክመት ዛሬ እየተደገመ፤ የዛሬው ጥፋት ነገ እየተሰለሰ ስለመሆኑ በቀጥታም በተዘዋዋሪም ተገልጿል፤ ተነግሯል። ቁም ነገሩ መጻፉ ወይንም መነገሩ አይደለም። የተፃፈው ተነቦ፣ የተነገረው ተደምጦ ትምህርት ሊወሰድና መሻሻል ሊታይ ካልቻለ ጩኸቱ የቁራ ጩኸት ይሆናል። ለመናገርና ለመፃፍማ አጥፊቶቹን የሚቀድማቸው የለም።

 

የአንድነት መሪዎች ከትናንት ተምረናል ብለው ደጋግመው ተናግረዋል። በመብራት ኃይል አዳራሽ በጠሩት ህዝባዊ ስብሰባ ሌሎችን አንጓለን ጠርተን ወጥተናል ሲሉ ተደምጠዋል። ሊቀመንበር ብርቱካን ሚደቅሳ ከታሰረች በኋላ ግን እውነተኛ ማንነታቸው ለአደባባይ ሲበቃ ቀናት አልፈጀባቸውም። የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በኢትዮጵያ ለለውጥ እንታገላለን ብለው የሚነሱ ኃይሎች በሥልጣን ላይ ያለውንና እንለውጠዋለን ብለው የሚታገሉት ኃይል ከሚያደርስባቸው በደል በላይ እርስ በእርሳቸው የሚያደርጉት መጠፋፋት ሚዛን ይደፋበታል።

 

ሁሉም ከላይ መሆንን ይፈልጋሉ። ለዚህም ይሻኮታሉ። ተሳክቶለት ከላይ የሆነው በዙሪያው የሚያሰባስበው አቤት!፣ ወዴት፣ ብሎ የሚላክ፤ የሚሰጠወውን ”አሜን!” ብሎ የሚቀበል፤ የሚታዘዘውን ተሽቆጥቁጦ የሚፈጽም እንጂ፤ ”ለምን?” ብሎ የሚጠይቅ፣ ”እንዴት?” ብሎም የሚከራከር፣ አማራጭ ሃሳብ ይዞም የሚሞግት ማየት አይፈቅድም።

 

ይህን ጥሶ ለመውጣት የሚሞክር ከተገኘ የቅጣት አርጩሜ ይጠብቀዋል። ለዚህም ነው የተለያዩ የፍረጃ ቃል ከፖለቲከኞች አንደበት ዘወትር የማይጠፋው። ሃሳብን በሃሳብ ከማሸነፍና የሚቀርብ ጥያቄን በተጨባጭ ማስረጃ ከመመለስ ይልቅ፤ ”ይህን የሚያስቡት ፓርቲውን ለማዳከም የሚጥሩ ናቸው”፣ ”እንዲህ አይነት ጥያቄ የሠርጎ-ገቦች ነው”፣ ... ወዘተ የሚለው አገላለጽ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለዘመናት አብሮ የዘለቀ፤ መቼ እንደሚቆምም የማይታወቅ፤ መድኃኒት ያልተገኘለት ክፉ በሽታ ነው።

 

አቶ ሠለሞን ያነሱትና አንድነትና መአህድን አነፃጽረው ያሳዩበት ደረጃው ይለያይ ካልሆነ በስተቀር በሁሉም ፓርቲዎች ውስጥ ያለ ጉዳይ ነው። ”መንግሥት ለጻፈውና ላፀደቀው ሕገ-መንግሥት አይገዛም፣ ሕጉን ለማጥቂያነት ይጠቀምበታል፣ ...” በማለት ሲጮሁ የሚደመጡት ተቃዋሚዎች፤ ራሳቸው የመተዳደሪያ ደንባቸውን ይጥሱታል። የጠሉትን ለመጉጃነት ይጠቀሙበታል፣ ሲፈልጉም አዛብተው ይተረጉሙታል፣ አጣመው ይተገብሩታል። ሲላቸውም ”በደንብ ታጥረን የትም መድረስ አንችልም፤ የፖለቲካ ውሳኔ እንወስናለን” በማለት ባደባባይ በድፍረት ይናገራሉ። ይህ ደግሞ ”በፖለቲካ ትግሉ ቁም ነገሩ አሸናፊ ሆኖ መገኘት በመሆኑ የፖለቲካ ሰው ይህንን ውጤት ለማግኘት በማንኛውም ዘዴ (ውሸት፣ ጭካኔ፣ ... ወዘተ) መጠቀም አለበት” የሚለው የማኪያቬሊ አስተሳሰብ ውጤት ነው። የአንድነት ፓርቲ ዋና ፀሐፊ አቶ አስራት ጣሴ አውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ላይ የተናገሩት ለዚህ በቅርብ ጊዜ ማስረጃነት ይጠቀሳል።

 

በሥልጣን ላይ ያለው ገዢ ፓርቲ ወገኖችን ”ሥልጣን ወይም ሞት ያሉ ናቸው። ሥልጣናቸውን ለማስጠበቅ የማይፈጽሙት ነገር የለም” በማለት ለመክሰስ የሚደፍሩት ተቃዋሚዎች ”ኃላፊነታችሁን አልተወጣችሁም፣ ፓርቲውን እየመራችሁት አይደለም፣ ከጊዜው ጋር መራመድ አልቻላችሁም፣ ደንብ አላከበራችሁም፣ ...” ወዘተ የሚል ጥያቄ ሲነሳባቸው ጥያቄው የእነርሱን ሥልጣን ለመቀናቀን የተነሳ አድርገው በመውሰድ የሥነ-ሥርዓት መመሪያ በማዘጋጀት፣ ኮሚቴ በማቋቋም፣ ታዛዦቻቸውን በዙሪያቸው በማሰለፍና በጠያቂዎቹ ላይ አሉባልታ በመንዛት ሥራ ይጠመዳሉ። ከፓርቲው ሊቀመንበር መታሰር በኋላ ከአንድነት ፓርቲ አካባቢ የሚሰሙት ወሬዎች ይህንን የሚያሳዩ ናቸው።

 

በመንግሥት ሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎችን በግልም ሆነ መንግሥታዊ ሥልጣን የያዘውን ፓርቲ እንደተቋም ”የልዩነት ሃሳብን የማስተናገድ ፍላጎት የላቸውም፣ የፖለቲካ አመለካከት ልዩነትን በጠላትነት ያያሉ፣ ለመቻቻል ፖለቲካ ቦታ አይሰጡም፣ ...” ወዘተ በማለት በድፍረት የሚከሱት ፖለቲከኞች፤ እነርሱ በሚመሩት ፓርቲ ውስጥ ከእነርሱ ሃሳብ የተለየ ሃሳብ ሲነሳ አፍራሽ፣ ሠርጎ-ገብ፣ ባዕድ አካል፣ ... ወዘተ በማለት ለመፈረጅ ይጣደፋሉ። አቻችሎ ለመምራትና የልዩነት ሃሳብን በውይይት ለመፍታት ከመጣር ይልቅ መከፋፈል እየፈጠሩ እና ልዩነትን እያሰፉ አባላቱ የጎሪጥ እንዲተያዩ ያደርጋሉ።

 

ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ታፍኗል፣ የፕሬስ ነፃነት አይከበርም ሲሉ የሚደመጡት ፖለቲከኞች ከፓርቲያቸው ውስጥ ሃሳባቸውን ደፍረው ጋዜጣ ላይ የሚጽፉ ብቅ ሲሉ የእገዳ እርምጃ ለመውሰድ ትዕግሥት እንደማይኖራቸው በየጊዜው በፓርቲዎች ውስጥ የምናየው ተግባር ነው። የሀገሪቱ ጠ/ሚኒስትር ሥራቸው በጋዜጣ በሚተችበት በአሁኑ ወቅት በጋዜጣ ለምን ሥማችን ተነሳ? ለምንስ ሥራችን ተተቸ? ብለው ለእርምጃ የሚጣደፉት ሰዎች ቤተ-መንግሥት ቢገቡ ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ መገመት የሚከብድ አይሆንም።

 

የኢትዮጵያ የተቃውሞ ፖለቲካ በአንድ ቦይ የሚፈስ፣ ከትናንት በስቲያውም ሆነ ከትናንቱ የተለየ ነገር የማይስተዋልበት፣ ፖለቲከኛ ነን ባዮቹም ሌሎች ከሠሩት ስህተት ቀርቶ ከራሳቸው የትናንት ጥፋት እንኳን የማይማሩ፣ ፖለቲካ ጥበብ መሆኑን ያልተገነዘቡና ዛሬም በትናንት አስተሳሰባቸው የሚጓዙ ለመሆናቸው ሰሞነኛው የአንድነት እና የመአህድ ትርምስ በቂ ማሳያ ነው።

 

እነዚህን ለአለፉት አሥርት ዓመታት በተቃውሞው ጎራ ሲስተዋሉ የነበሩ ድርጊቶችን ዛሬም የሚፈጽሙት ፖለቲከኞች የሚሠሩት ሁሉ ከያዙት ኃላፊነት ጋር የማይመጥን፣ ከዕድሜያቸው ጋር የማይጣጣም፣ ካላቸው የረዥም ጊዜ ልምድና ከሥማቸው ቀድሞ ከሚጠራው የማዕረግ ሥም ጋርም የማይሄድ ነው። ይህ ትግሉን ሳይሆን ግለሰቦቹን ማዕከል ያደረገ አሠራር ወደ አምባገነንነት እያመራ ያለ ተግባር ነውና በጊዜ ሊታረም ካልቻለ አደጋው የከፋ ነው። የአምባገነንነት መገለጫው ድርጊት እንጂ ቦታና ወንበር አይደለም። ለሕግ አልገዛም ማለት ዋንኛው የአምባገነንነት መገለጫ ነው። አውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ላይ የአንድነት ዋና ፀሐፊ የተናገሩትም ይህንኑ ነው።

 

ህዝቡ ከምርጫ 97 ብዙ ተምሯል። ይህንንም በብዙ መንገዶች እየገለፀ ነው። በዝምታ ጭምር። ሊረዳው ለቻለ ዝምታም መልዕክት አለው። በሁሉም ወገን ያሉ ፖለቲከኞች ግን ከረዥሙ የኢትዮጵያ ታሪክ ቀርቶ ከትናንቱ ምርጫ 97 እንኳን የተማሩ አልሆኑም። ”ዛሬም እዛው ነሽ ወይ?” የሚዘፈንላቸው ፖለቲከኞች።

 

”በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ዜጎች በሚናገሩት ግልፅ የሆነ የሃሳብ ልውውጥ አማካኝነት ሐሰት እየኮሰመነችና እውነት ደግሞ እያበበች ጐልታ የምትታይበት መድረክ ይፈጠራል!!!”

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ