አቶ መለስ ብሔራዊ መግባባት አጀንዳችን ነው አሉ (ግርማ ካሣ)
ግርማ ካሣ - ሐምሌ 3 ቀን 2001 ዓ.ም. This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
የአሥራ ሰባት ዓመት ወጣት ነው። ጥይት የጎረሰ ሽጉጥ በእጁ ይዟል። እጅግ በጣም ብዙ ህዝብ በተሰበሰበበት አደባባይ፣ ንግግር አድርገው ወደ ጨረሱ አንድ የዕድሜ ባለጸጋ ሰው ቀስ በቀስ ይጠጋል። ሳያስቡት የያዘውን ሽጉጥ ወደ እርሳቸው ደቅኖ ይተኩሳል። ሰውዬው ይወድቃሉ። አካባቢው ተረበሸ። ተናወጠ። አምቡላንስ ተጠርቶ በአፋጣኝ በስፍራው ደረሰ። የወደቁትን አባት በአምቡላንሱ የነበሩ የሕክምና ባለሞያዎች አነሷቸው። የፍጥነት ጉዞ ወደ ሆስፒታል ጀመሩ። ሆስፒታል ሳይደርሱ በመንገድ ላይ የኝህ ሰው ሕይወት አለፈች።
ይህ ወጣት ይጋል አሚር ይባላል። ተኩሶ የገደላቸውም ሰው የቀድሞ የእሥራኤል ጠቅላይ ሚኒስተር ይስኃቅ ራቢን ነበሩ።
ይስኃቅ ራቢን ዕድሜ ዘመናቸውን በሙሉ የጥይትና የመድፍ ድምፅ በመስማት ያሳለፉ ጦረኛ ወታደር ነበሩ። በፈረንጆች አቆጣጠር በ1941 ከታዋቂው ሞሼ ዳያን ጋር የፓልማክ ግብረኃይል አባል ሆነው፣ ያኔ በፍረሳንዮች ቅኝ ግዛት ስር በነበረችው በሊባኖስ የናዚ ጀርመን ደጋፊ የነበረው የፈረንሳይ ቪቺ መንግሥት ወታደሮች ጋር ተዋግተዋል። በዚያ ጦርነት ጊዜ ነበር ሞሼ ዳያን አንድ ዓይናቸውን ያጡት።
ከዚያ በኋላ ከዐረቦች ጋር በተደረጉት ተከታታይ ጦርነቶች ትልቅ ጀግንነትና የውትድርና ብቃት ያሳዩ፣ በእሥራኤል ታሪክ አሉ ይባሉ ከነበሩት ታላቅ የጦር መሪዎች አንዱ ነበሩ። የእሥራኤል የመከላከያ ሚንስትር፣ የጦሩ የኢታ ማጆር ሹም ሆነውም አገልግለዋል።
ይስኃቅ ራቢን “እኔ ሠላም ሳላይ ዕድሜዪን ጨርሻለሁ። ለልጆቻችን ሠላም ማምጣት አለብን” በሚል እምነት፣ ድፍረት የተሞላበት የሠላም እርምጃ ወሰዱ። የእሥራኤል ጠላቶች ከሚባሉ ጋር መነጋገር ጀመሩ።
ይስኃቅ ራቢን ከመገደላቸው ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት የተናገሩት፣ ለእኛ ለኢትዮጵያውያንና ለመሪዎቻችን ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ አስደናቂ አባባል ነበር። “… የሠላም መንገድ ከጦርነት ይሻላል። ይሄን የምለው እንደ አንድ ወታደር ነው። መከላከያ ሚንስትር ሆኜ የእስራኤል ወታደሮች ቤተሰቦች ስቃይ ይሰማኛል። ለነርሱ፣ ለልጆቻችን፣ ለልጅ ልጆቻችን ስንል መንግሥታችን ዘላቂ ሠላም እንዲገኝ ማንኛውንም ቀዳዳ፣ ማንኛውንም ዕድል መጠቀም አለበት። ሠላም አንድ ፀሎት ብቻ አይደለም። ሠላም የፀሎታችን መጀመሪያ ነው …” ነበር ያሉት።
የጦርነትን፣ የጥላቻና የእልህ ፖለቲካ አደገኛነቱን ያወቁታልና፤ አብረዋቸው የነበሩ ጓደኞቻቸው ሲረግፉ፣ አካለ ስንኩል ሲሆን፣ ንብረት ሲወድም፣ ሰው በሰው ላይ ሲጨክንና አውሬ ሲሆን አይተዋልና፤ እርሳቸው የኖሩበትን በጦርነት የተበከለን አየር ለልጅ ልጆቻቸው ማውረስ አልፈለጉም። እርሳቸው ይመኙትና ይናፍቁት የነበረውን ሠላም፣ እርሳቸው ባያገኙትም እንኳን፣ የልጅ ልጆቻቸው እንዲያገኙ መደረግ ያለበትን ሁሉ ማድረግ እንዳለባቸው ተገነዘቡ። “ለልጅ ልጆቻችን ስንል ሠላም እንዲመጣ የተገኘችዋን ቀዳዳ ሁሉ መጠቀም አለብን” በሚል ጽኑ አምነት፣ በጦርነት ያልሆነ፣ የውስጥና የልብ ጀግንነት ለማሳየት ተንቀሳቀሱ። የእሥራኤል ጠላት ከተባሉት ከነያሲር አራፋት ጋር መነጋገር ጀመሩ።
ብዙ ተቃውሞ መጣባቸው። እነ ኔታንያሁ ተነሱባቸው። ግትር ፖለቲካ የሚያራምዱ፣ በጭንቅላት ሳይሆን በጠመንጃ የሚያምኑ፣ እነርሱ ብቻ ከሌላው እንደተሻሉ አድርገው በመቆጠር በትዕቢት የተወጠሩ፣ ከነርሱ ዘር ውጪ ለሌላው ግድ የማይሰጣቸው ሰዎች በርሳቸው ላይ ማንጎራጎር ጀመሩ።
ይስኃቅ ራቢን ግን ወደ ኋላ አላሉም። “የሠላም ጠላቶች አሉ። ሊጎዱን፣ የሠላሙን መንገድ ሊያጨናግፉን የሚፈልጉ። በድፍረት እናገራለሁ። ከፍልስጤማውያን መካከል የወጣው፣ በፊት ጠላታችን የነበረው የፍልስጤም ነፃ አውጭ ግንባር አሁን የሠላም አጋራች ሆኗል” ሲሉ ከቀድሞ ጠላቶቻቸው መካከል ወዳጆችን እንዳፈሩ ተናገሩ። ከያሲር አራፋት ጋር በአንድ ላይ ለሠላም ቆሙ። ይስኃቅ ራቢን በጦርነት ሊያጠፉት ያልቻሉትን የያሲር አራፋትን ቡድን በሠላም አሸነፉት።
ታዲያ ለዘመናት በጦር ሜዳ ሲዋጉ በጥይት ያልተመቱት እኝህ ታልቅ ሰው፣ በሠላሙ ሜዳ በቴላቪቭ ከተማ ጥይት አገኘቻቸው። ለሠላም፣ ለፍቅር፣ ለወንድማማችነት ሲሉ ወደቁ። እጅግ ታሪካዊ፣ ተወዳጅ የሠላም ሰው!!!
የይስኃቅ ራቢንን ታሪክ ያለምክንያት አላመጣሁትም። አንዳንዶች ተቃዋሚዎችን መጨፍለቅ ጀግንነት ይመስለናል። አንዳንዶች ኃይልን የምንመዝነው በያዝነው ብረትና በዘረጋነው የስለላ አውታር ነው። መነጋገር፣ መወያየት፣ ፍቅርና መግባባት፣ በጦርነትም ሆነ በጉልበት ከሚገኝ ጊዜያዊ መፍትሔ የበለጠ ዘለቄታ ያለው ጥቅም ሊያመጣ እንዲሚችል አናስብም። የሩቁን፣ እኛ ካለፍን በኋላ በልጆቻችንና በልጅ ልጆቻችን ዘመን ሊፈጠር የሚችለውን፣ ለሁላችንም የሚበጀውን አንመለከትም። ጊዜያዊ ጥቅማችንንና ሥልጣናችን ላይ ብቻ በማተኮር ግትር ፖለቲካ እናራምዳለን።
በቅርቡ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ በፓርላም ተገኝተው ከተመራጮች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ አንዲት ቀልቤን የሳበች አባባል አደመጥኩኝ።
ስለ መጪው የሀገሪቷ በጀት ነበር በፓርላማ ውይይት ሲደረግ የነበረው። ለጦር ሠራዊቱና ለፖሊስ ከተመደበው በጀት ተቀንሶ ወደ ሌላ ጠቃሚ ፕሮግራም እንዲውል የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ሕብረት የፓርላማ ተጠሪ፣ አቶ ገበሩ ገብረማርያም ሃሳብ ያቀርባሉ። ፖሊስና ደህንነት አባላትን በማብዛት ብቻ የሀገር ደህንነትን ለማስጠበቅ ከመሞከር ይልቅ የችግሮች ምንጭ የሆኑትን ከሥራቸው በንግግርና በሠላም መፍታት ቢቻል የበለጠ ለሀገር ጠቀሜታ ይኖረዋል በሚል፤ “ስለ ሀገር በምናስብበት ጊዜ፣ ስለ እድገት በምናስብበት ጊዜ የብሔራዊ መግባባትን የመፍጠር ጉዳይ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ ቢታይ ከበጀቱም ጋር ከሁሉም በላይ ጠቃሚ ነው” ሲሉ ሃሳባቸውን ያቀርባሉ።
በሕብረቱ ተወካይ ለቀረበው ሃሳብ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ሲመለሱ “ብሔራዊ መግባባት መፈጠር አለበት የሚባለው በራሱ ምክንያት የምንደግፈው አጀንዳ ነው። የፀጥታ አስከባሪ አቅማችንን በማሽመድመድ የሚፈጠር ብሔራዊ መግባባት ግን የለም። ሀገሪቱን ለውጭ ጥቃት አጋልጦ የሚፈጠር የፖለቲካ ትርፍ የለም” አሉ።
እርግጥ ነው ሀገሪቱን ለውጭ ጥቃት ማጋለጥ ፀረ-ኢትዮጵያዊነት ነው። ሀገሪቷ በዓባይ ወንዝ አጠቃቀም ምክንያት ከግብጽ ሊነሳ የሚችልን ጥቃት፣ አልሻባብ የተባለው በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰው ጨካኝ ቡድን ሊያመጣ የሚችለውን የተወሳሰበ የሽብር አደጋ በአንድነትና በጋራ እንደ ኢትዮጵያዊ መመከት መቻል አለብን። በአዲስ አበባ ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት እኛ የምንወደው አለመሆኑ በሀገራችን ላይ የመጣውን አደጋ እንዳናይ ዓይኖቻችንን ሊሸፍነው አይገባም።
ከሰባ ዓመታት በፊት በቻይና፣ በማኦ ዜዱንግ የሚመራው የኮምዩኒስት ፓርቲና በኋላ ታይዋንን በመሰረቱት በቺያንግ ካ ሼክ የሚመራው የናሽናሊስት ፓርቲ እርስ በርስ ይዋጉ ነበር። ጃፓን ቻይናን በምትወርበት ጊዜ ግን፣ እርስ በርስ ሲዋጉ የነበሩት ወገኖች በአንድነትና በጋራ የውጭ ወራሪን መመከት ጀመሩ። እኛም ከቻይናውያን ተምረን የውስጥ ችግሮቻችንን ከውጭ ችግሮቻችን መለየት መቻል አለብን እላለሁ።
ስለሆነም የአየር ኃይላችንን፣ የምድር ጦራችንን የበለጠ ማጠናከርና ማደራጀት ተገቢና እጅግ አስፈላጊ ነው። የሀገር አንድነት፣ የሀገር ደህንነት ማንም ይግዛ ማንም ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው።
ከበጀት ጭመራውም ባለፈም መልኩ፣ ሠራዊቱ የኢትዮጵያን ህዝብ ያንጸባረቀ፣ ከፖለቲካ ነፃ የሆነ፣ የግለሰቦችን ጥቅም ሳይሆን የሀገርን ጥቅም የሚያስጠብቅ ሠራዊት እንዲሆን በተሻለ መንገድ መዋቀር ይኖርበታል። ኢትዮጵያ ጠንካራ፣ ሁላችንም የምንኮራበትና የምንተማመንበት የመከላከያ ሠራዊት ያስፈልጋታል።
እዚህ ላይ የውጭ ጥቃት በምልበት ጊዜ ኤርትራን እንደማልጨመር እንዲታወቅልኝ እፈልጋለሁ። ኤርትራውያን ወንድሞቻችንና ወገኖቻችን ናቸው። ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል ናት ብዬ ነው የማምነው። በሠላም በፍቅር እንደገና አንድ እንሆናለን የሚል ትልቅ እምነት አለኝ። ከኤርትራ ጋር የሚደረግም ጦርነት የወንድማማቾ የርስ በርስ ጦርነት እንጂ ከውጭ ኃይሎች ጋር የሚደረግ ጦርነት አይደለም።
ወደ ፖሊስና የደህንነት አባላት ስንመጣ ግን የተለየ ሃሳብ ነው ያለኝ። ለነርሱ በስፋት የሚጨመር በጀት በምን መልኩ ከውጭ ሀገር ከሚመጣ ጥቃት ጋር ጠቅላይ ሚንስትሩ እንዳገናኙት አልገባኝም። አቶ ገብሩ ገብረማርያም እንዳሉት ፖሊስና ሰላዮች ከማብዛት ብሔራዊ መግባባት ላይ ማተኮሩ የበለጠ ይበጃል እላለሁ።
በፓርላማው በነበረው ክርክር ወቅት ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ድርጅታቸው ብሔራዊ መግባባት ሊኖር እንደሚገባ ሲናገሩ፤ “ብሔራዊ መግባባት መፈጠር አለበት የሚባለው በራሱ ምክንያት የምንደግፈው አጀንዳ ነው” ነበር ያሉት።
እንግዲህ ከላይ ለማሳየት የሞከርኩት የይስኃቅ ራቢን ምሳሌነት እዚህ ላይ ነው የሚመጣው። እንደ ይስኃቅ ራቢን አሁን በሥልጣን ላይ ያሉት የኢህአዲግ ባለሥልጣናት ከወጣትነታቸው ጀምሮ ጦርነትን ያዩ፣ በጦርነት የኖሩ ሰዎች ናቸው። በታሪክ ስለሚኖራቸው ቦታ፣ ስለ ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው ማሰብ አለባቸው እላለሁኝ።
ፀረ-ሽብርተኝነትን ለመቋቋም ተብሎ የወጣው አዋጅ፣ አባቶቻችን በአድዋ፣ በካራማራ፣ በአዶሉስ፣ በጉራ፣ … ደማቸውን ያፈሰሱለትን አረንጓኤ - ቢጫ - ቀይ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ፤ ሰማያዊ ኮከብ ካልተደረገበት የሚያስቀጣው ሕግ፣ በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ላይ የተወሰደው ኢ-ሰብዓዊና ኢፍትሃዊ የጭካኔ እርምጃ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ በተቃዋሚውች ላይ በየወረዳውና በየክልሉ የሚደርሰው ወከባ፣ … ኢህአዲግን ከህዝብ ጋር የሚያጣሉ፣ ጥላቻን እንዲሰፋ የሚያደርጉ፣ ዜጎች የበለጠ ወደ ከረረ አቋም እንዲሄዱ የሚገፋፉ እንጂ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ እንደ አጀንዳ እንደግፈዋለን ያሉትን የመግባባትንና የእርቅን መንፈሥ የሚያመጡ አይደለም።
ስለሆነም ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊን የምለው ነገር ቢኖር፤ “ድርጅትዎ በብሔራዊ መግባባት የሚያምን ከሆነ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተናገሩትን በሥራ ይተርጉሙት” የሚል ነው።
ጦርነት ያላወጁትን፣ በሠላምና በሕጋዊ መልኩ የሚታገሉትን፣ ከኢህአዲግ ጋር አብረው ለመሥራት የተዘጋጁትን፣ አገዛዙን እንደ”ጠላት” በሚቆጥሩ ሰዎች ፊት “ወያኔ ጠላት አይደለም” ብለው የተሟገቱትን ማጥቃት፣ መግደል፣ ማሰር፣ ማፈን እንዴት ተደርጎ ነው እርቅና ብሔራዊ መግባባትን ማምጣት የሚችለው? የሠላምና የፍትህ ሴት የሆኑትን ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን ከስድስት ወራት በላይ በጨለማ ቤት ማሰር፣ ነገሮችን የበለጠ ያካርራል እንጂ እንዴት ተደርጎ ነው ሀገርን የሚጠቅመው?
ተናዶ የኃይል እርምጃ መወሰድ፣ በበቀል መነሳሳት፣ ሰውን ማዋረድ፣ ሰውን መስደብ፣ ሰውን መክሰስ በጣም ቀላል ነው። በዓይናችን ላይ ትልቅ ምሰሶ እያለ የሌላውን ጉዳፍ ማየት፣ የተገነባውን ማፍረስ፣ ሀገርን ከድህነት ወደ ድህነት ማወረድ፣ ጠላቶችን ማፍራት፣ ህዝብን ከህዝብ መከፋፈል፣ ወንድምን ከወንድም ማጣላት አስቸጋሪ አይደለም።
ይስኃቅ ራቢን እንዳደረጉት ጠላት የነበሩትን ወዳጅ ማድረግ፣ የፈረሰውን መገንባት፣ ሀገርን ከድህነት ማውጣት፣ ችግሮችን በውይይት መፍታት፣ የተጣሉትን ማስታረቅ፣ የተበተኑትን መሰብሰብ፣ ትችትና ወቀሳን በትህትና ተቀብሎ ስድብና አሉባልታን ደግሞ ንቆ ነገሮችን በትዕግስት ማሳለፍ ግን እጅግ በጣም ከባድ ነገር ነው።
ስለሆነም አቶ መለስ ዜናዊንና ጓደኞቻቸውን፣ አሁንም የቀናውን መንገድ እንዲይዙና በፓርላማ እንደሰማነው ሁሉ በተግባር ለእርቅና ለብሔራዊ መግባባት መዘጋጀታቸውን ለማሳየት ተጨባጭ ሥራዎችን ለመሥራት እንዲነሱ ጥሪ አቀርባለሁ።
ከነዚህም ከተጨባጭ ሥራዎች መካከልም በቀዳሚነት፣ በዋናነትና በአስቸኳይ ትልቅ ሥራ ሊሠራበትና እልባት ማግኘት ያለበት ጉዳይ ቢኖር የወ/ት ብርቱካን እስር ጉዳይ ነው።
ወ/ት ብርቱካን ቃሌ በሚለው ጽሑፋቸው ይቅርታ መጠየቃቸውን በግልጽ አስቀምጠዋል። “በሽማግሌዎች የእርቅ ማግባቢያ መንፈሥ መሰረት በፖለቲካ የተቀሳቀሰውን ክስ ፖለቲካዊ እልባት ለመስጠት በማሰብ ለእርቅ ስል ከሌሎች የፓርቲው (ቅንጅት) መሪዎች ጋር ተስማምቼ ሰኔ 11 ቀን 1999 ዓ.ም. በተጻፈው ሰነድ በሽማግሌዎች አማካኝነት ይቅርታ ጠይቄአለሁ። ይህ ብፈልግም ልለውጠው የማልችለው ሐቅ ነው” ነበር ያሉት።
ስለሆነም አቶ መለስ ዜናዊ ለቢቢሲ ሃርድቶክ ጋዜጠኛ ለመግለጽ እንደሞከሩት ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ያጭበረበሩት ወይንም ያታለሉት አንድ ነገር የለም። “የይቅርታ ውሳኔ ለይቅር ተባዩ ከደረሰና ተቀባይነት ካገኝ በኋላ የይቅርታ ውሳኔ በማጭበርበር ወይም በማታለል የተገኘ መሆኑ ከተረጋገጠ የይቅርታ ውሳኔው ዋጋ አይኖረውም” የሚለውና በጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ የሚጠቀሰው የይቅርታ ሥነ ሥርዓት አዋጅ ቁጠር 395፣ አንቀጽ 16፣ ንዑስ አንቀጽም 2፣ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን በጭራሽ አይመለከትም። “ይቅርታ አልጠየኩም” ሳይሉ፣ የማይገናኝ ይህንን የሕግ አንቀጽ እንደ ሌጦ በመተርጎም፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ደጋፊዎች ያሏቸውንም እኝህን የሠላም ሴት በግፍ ማሰር አሳዛኝና አሳፋሪ እንጂ በምንም አይነት መልኩ ሀገራዊ መግባባትን የሚፈጠር አይደለም።
ኢህአዲጎች፣ ተቃዋሚዎች ሁላችንም ብሔራዊ መግባባትን በእውነት ከፈለግን፣ በሁላችንም ዘንድ የልብ መሻት ካለ እንቆቅልሾቻችንን መፍታት ይቻላል። ስለዚህ በትጋትና በቅንነት ወደ አንድነትና ወደ እርቅ ሁላችንም ልባችንን እናነሳሳ። ኢህአዲግ በአስቸኳይ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በመፍታትና የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ለብሔራዊ መግባባት ያለውን ቁርጠኝነት በግልጽ ያሳይ። እንደ ይስኃቅ ራቢን ደፋርና ሠላምን የሚያበራክቱ እርምጃዎችን ይወሰድ።



