ክፍል 5

ግሩም ተ/ኃይማኖት

Sedet

ማንም የዳስሰው አይመስለኝም። የቀይ ባህር እና ህንድ ውቅያኖስ መጋጠሚያ Gulf of aden አሰቃቂ ጉዞ እና የሱማሊያውያኑን ኢሰብአዊ ድርጊት፣ የእኛም በጉዞ ላይ የዘቀጠ ማንነት.የሚካተትበት ትረካ ነው። መሳፈሪያው ቦታ እስክንደርስ እና ለመሳፈር ባህሩ ጋር ስላለው ነገር ያለውን እንዝለለው። አሁን ምናቦትን አውሱኝ እና የትራንስፖርት ሳይከፍሉ እንጓዝ …


በጀልባው ላይ ያለው የመጫን ስርዓት ፣ወደ ጀልባ መጫኛው ቦታ ያለው ጉዞ ሁሉ በጣም ሰቅጣጭ ነው። ሁሉን መዘርዘሩ ከባድ በመሆኑም ጊዜ ስለሚጠይቅም ልዝለለውና ቅዳሜ ቀን ከምሽቱ 5 ሰዓት አካባቢ ነው። በሶስት ጀልባ ተጠቅጥቀን ተጭነናል። መቶ ሀያ ስድስት እኛ ያለንበት፣ መቶ አስራ ሰባት ቀጥሎ ያለው ... የመጨረሻው ከሁለቱ የተረፈውን ዘጠና ሁለት ሰው እንደጫኑ ሶማሊያዊያኑ ተይዘው የየመኗ አጠቅ ከተማ ፍ/ቤት ስንቀርብ ሲናገሩ ለማወቅ ችለናል። ተጭነን ከብዙ ቆይታ በኋላ ጉዞ ተጀመረ። ”ሰላም ያግባን” አሉ ሴቶቹ። እኔም በውስጤ ደገምኩት። አሁን የውሀው ድምጽ እና የ”ናኩዳዎቹ” ድምጽ /የጀልባ ዘዋሪዎች የሚጠሩበት ነው/ ብቻ ነው የሚሰማው። ተሳፋሪው አወራለሁ ቢል በያዙት ዱላ አናቱን ነው የሚሉት። በጀልባዋ ኋላኛ ክፍል ነው የተቀመጥኩት። እፍግፍግ ከማለታችን የተነሳ አንዱ የሌላውን ጠረን በግዱ ይስባል። አነስተኛ እስከ 16 ሰው የምትጭን አሳ ማስገሪያ ጀልባ ነች። ልክ በምስሉ ላይ እንደምትመለከቱት የገጠር አጥር ይመስል ዳር ዳሩ ላይ ዙሪያውን አጣና ተመቷል። ሸራ ላስቲክም አልብሰውታል። ከላይ ክፍት ነው። ”ቀና ብዬ ሳይ እዩት ሰማይ ደፈረሰ …” የሚለውን ዘፈን አስታውሼ ዳግም ቀና አልኩ። አልፎ ... አልፎ ጣል ጣል ያሉትን ኮዋክብቶች ሳይ ጭላንጭል ተስፋ ታየኝ።

 

”ግሩምዬ ተጫውት እንጂ ዝም አልክ” ሰናይት ነች።

 

”እሺ” ሌላ ምን እላለሁ? የምን መጫዎት አመጣችብኝ? እንኳን ልጫወት እያቅለሸለሸኝ ነው። ገና ጀልባ ላይ እንደወጣን ባደሉን ስስ ፌስታል የመጀመሪያውን ዙር አስተናግጄበታልሁ። ቀሪም አለ መሰለኝ ይጓጉጠኛል። ሰውነታችን ላይ የቀረው የባህር ውሀ፣ አሁንም ባህሩ የሚለቀው የሚተነፍግ ግማት፣ እንደ እኔ ወደላይ ያላቸው ሽታ፣ ሲመቱ ... ደንግጠው ወደታች ያላቸው ... ካላቸውም ጋዝ የለቀቁ ለአየሩ ብክለት አስተዋፅዖ አድርገዋል። የባህሩ ውሀ የነካው ጫማ ሽታ፣ የብብት ሽታ፣ የሚጨሰው ሲጋራ እና ሀሺሽ ሽታ … ሀሺሹን እንኳን ድፍረት እንዲሰጠኝ ብዬ አጠገቤ ካለ ሱማሌ ተቀብዬ ሳብ ... ሳብ አድርጌው ነበር። ምን ያደርጋል እኔ ላይ ሲሆን አይሰራም መሰለኝ ፍርሃቴ አለቀቀኝም። ብቻ ሽታዎች ሁሉ ህብረት ፈጥረው ሽንት ቤት ጉድጓድ ውስጥ የተቀመጥኩ መስሎኛል። ጨጓራዬ በምላጭ ይሁን በመላጊያ አላወኩም እየተፈቀፈቀ ነው። ወደላይ ብሎ ፌስታል የሚሞላው በጨመረ ቁጥር ድጋሚ ዙር ለራሴ ፍራሁ።ለነገሩ ባዶ ስለሆነ መሰለኝ የሚፈቀፍቀኝ።

 

በሁሉም ልብ ውስጥ ፍርሃት ነግሶ የሚጋልብ መሰለኝ። እኔ በውስጤ ስለባህሩ የሰማሁትን አስታውሼ ያለ የሌለ ጸሎት ይዣለሁ። እንደዚያን ቀን ጸሎዬ የማውቀ አይመስኝም። ለምን እንደሆን አላውቅም ልጄ ደጋግሞ በሀሳብ ታየኝ። ድክ ድክ ሲል አይቼ ያልጠገብኩት፣ ሲኮላተፍ ጣፋጭ አንደበቱን ሰምቼ ያላጣጣምኩት ልጄን ዳግም የማገኘው የማገኘው አልመስል አለኝ። እናቴ በምስኪንኛ አይታኝ ”ልጄ የኢትዮጵያ አምላክ ይጠብቅህ” ያለችኝ መሰለኝ። ለነገሩ የቁርጡ ቀን ክ/ሀገር ሄጄ ሸሸግ ብዬ ላሳልፍ ነው ስላት ነበር እንዲህ ያለችኝ። አስታውሳለሁ በዛን ሰዓት ”ኢትዮጵያ አምላክ አላት እንዴ? ካላት ምነው ዘላለሟን ዘነጋት። ሁሌ ለአምባገነን መፈንጫ ያደረጋት ... የኢትዮጵያ አምላክ አባባል ነው። ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሄር ትዘረጋለች ይባላል። በእውነታው ከሆነ ግን ወደ ፈረንጆቹ ነው የዘረጋችው” የሚል እሳቤ ውስጤ ስንቅር ብሎ ነበር።

 

ሌሊት ሰባት ሰዓት አካባቢ ”ግሩም ተኛህ እንዴ?” ሠናይት ነች። ሁላችንም ኩርምት..ኩርምት ብለን ነው የተቀመጥነው። በህይወቴ እንዲህ አይነት የስቃይ አቀማመጥ ኩርምት ብዬ አላውቅም። ግዴለሽነት ይሁን ሀሳብ መጣል ካሁኑ እንቅልፍ የጣላቸው ሰዎች አሉ። ለእነሰናይት መልስ ስላልሰጠኋቸው እኔም የተኛሁ መሰላቸው።

 

”ውይ ለእናቴ ጉሩሙ ተኛ” አለች አልማዝ ረገጥ አድርጋ በምትሰባብረው አማርኛዋ። አሁንም መልስ አልሰጠሁም። ”አንቺ ለወንድሜ ነው የሚመስል ሳየው ሆዴ ረበሽነሽ አለ።”

 

”አይ! ... እረፊ ያን የመኪና ረዳት ወንድሜን ትመስላለህ ብለሽ ልቡን ያቆምሽበት ዘዴ አይሰራም።”

 

”ውይ ... ውይ ሰኒ ግፍ ላትናገሪ ለንደዚህ አላሰብኩም። ብቻ ሳየው ለወንድሜ መሰለይ በቃ! ላንቺ ላሰብሽውን አላሰብኩም” ሰባብራ ብታውራውም ከወፍራም ድምጽዋ ጋር ያምራል።

 

”አይመስለኝም።”

 

”ላጭወረውረው አይደለም። ያኮ ሹፌሩን ላሰኘው ጊዜ ሊመጣኝ ... ሊጎትተኝ ሲል መረጥኩ። አመጡት አለ ጉጉው የማወቅ ፍላጎቴ ... ሰማኋቸውም።

 

ከዚ በላይ የሚያወሩት ያሳፈራል። ተገደው ሳይሆን ፈልገው ያደረጉት አስመስለው ያወራሉ። በስቃይ፣ በመገደድ ቦታ እርካታን በተመለከተ ሲያወሩ አፈርኩ። ያኛው ጎበዝ ነው ያኛው ሰነፍ ሲሉ ለምን አላፍር? የነቃሁ መስዬ ላስቆማቸው እያሰብኩ ሳለ አንዱ ከእንቅልፉ ባኖ ብድግ አለ።ሶማሌው ”ፈሪሶ ያ-አባሀወስ” ብሎ በቡጢ አጎነው። መደዳ የተቀመጥነው እግራችን ላይ ወደቀ። ጥሩ አጋጣሚ ሆነልኝ ተነሳሁ።

 

”ምነው አመመህ እንዴ? በጊዜ ተኛህ” አለች ሰናይት። አለመተኛቴን እና ስሰማቸው እንደነበር እንዲያውም ያሳመመኝ የእነሱ መረን ቃላት እንደሆነ ብነግራት ምን ሊሰማት እንደሚችል እያሰብኩ ”በጣም ደከመኝ” አልኳት።

 

ከዚህ በኋላ እየተጨዋወትን በመሀል በመሀል ዝምታም እየሰፈነ ጉዞው ቀጠለ። የባህሩ ውሀ የጀልባው እሽክርክሪት ሲቀዝፈው የሚያወጣው ድምጽ እና የሞተሩ ሰቅጣጭ ድምጽ ብቻ ይሰማል። የጀልባው ሞተር ተለውጦ የn3 /ኤንትሬ/ ከባድ መኪና ሞተር ነው የገጠሙለት። ልክ ገጠር ያለ በናፍታ የሚሰራ ወፍጮ አይነት ድምጽ አለው። ለሞተሩ ከፀሀይና ዝናብ ከለላ ሰርተውለታል። በሶስተኛው ፎቶ ላይ እንደሚታየው ... ከላዩም ጋርደውት እንደመኝታ ይጠቀሙበታል። አንድ በርሜል ናፍታ መጠባበቂያ ይዘዋል። በመሀል እያቆሙ ይሞላሉ። አንዱን እዛ ላይ ውጣ እያለ ይታገለዋል። ቢወጣ ምን ያደርገዋል እያልኩ ስጠይቅ አይለቀውም ለምን መሰለህ መኝታ ላይ ውጣ የሚለው … አሀ!!! ገባኝ። ይሄ ሁሉ ሰው እያለ ለማድረግ ማሰባቸው የሚገርም ይመስላል። ግን ሀሺሽ እያጨሱ ስለሆነ … ታዲያ ምነው ለእኔ የተለየ ነገር አልተሰማኝ?

 

ቀና ብዬ ሳይ ሰማዩ በባለሞያ የተንቆጠቆጠ ውብ ጥበብ የፈሰሰበት ይመስላል። ጨረቃዋ የሙዝ ቅርጽ ይዛ ”አለሁ” የምትል ትመስላለች። ከዋክብቱ አጅበዋት ”አሁን ደመቅሽ …” የሚሉ፣ የሚጨፍሩ መሰለኝ። እኛ ተፋፍገን 16 ሰው የምትጭን አሳ ማስገሪያ ጀልባ ላይ 126 ሰው ሆነን አንዱ አንዱ ላይ ተደራርቧል። ጨረቃ ተንሰራፍታ በኮኮብ ታጅባ ታሰቀናለች።

 

ከሌሊቱ 10 ሰዓት ተኩል አካባቢ ከፊት የነበረችው ጀልባ ቆማ ጠበቀችን። የእኟም ቆመች። ምን እንደሚያወሩ እንጃ ያወራሉ። መደማመጥ ባልሰፈነበት ሁኔታ በጩኸት ያወራሉ። ጀልባዎቹን አጠጋጉና እኛ ያለንበት ላይ ያሉት ግማሾቹ ዘለው ወደ ዛኛው ጀልባ ሄዱ። መፍቻ ይቀባበላሉ። ብረት አቅልጠቀው መጥረቢያ የሚሰሩ እስኪመስል ይቀጠቅጣሉ። ብልሽት እንዳለ ተረዳሁ። ”ኦ! ... አምላኬ አውጣን!!! ...” አልኩ። በእርግጥም ከዚህ አስቀያሚ ሁኔታ በሰላም መውጣትን የመሰለ ምን ፀጋ አለ? በባህር ደጋግመው የሚመላለሱትን አስብኩና ከምንም በላይ ጤነኛ አልመስል አሉኝ።

 

ሲነጋጋ ገመድ አውጥተው የተበላሸውን እኛ ያለንበት ጀልባ ላይ አሰሩ እና መጎተት ጀመሩ። ”እነዚህ ሰዎች እብድ ናቸው ሁለቱም ቢበላሽ ጥግ አስይዤ ላቁም የሚባልበት መሬት ላይ ያሉ መሰላቸው እንዴ? ተያይዘን መስመጣችን መሆኑን አያውቁም?” አለ ከፊቴ ያለ ልጅ። የውስጤን ነው የተነፈሰው እድሜ ይስጠው። ተያይዘን እንዳንሰምጥ ፍርሃቴ ቀላል አልነበረም። ጨረቃዋ መንጋቱን አላወቀችም መሰለኝ ብርሃኗ ደብዝዞ ትታያለች። ”ሲምቦሊክ ነው” አልኩ ለራሴ። የእሷን አለመግባት ከእኛ አለመስመጥ ጋር ላቆራኘው ፈልጌ። ፍጥነት ቀንሰው ወደ ተኩል ሰዓት ከተጓዝን በኋላ ገመዱን ፈቱት። ውስጤን የሸበበኝ ፍርሃትም ለቀቀኝ። ፍርሃቴ ቢለቀኝም ጭንቀት የሚፈጥር ነገር ገጠመኝ። ገመዱ የተፈታለት ጀልባ ተሰርቶ ችግሩ ተፈቶ አይደለም።

 

”ለመከራ ተፈጥረን በመከራ የምናልፍ አሳዛኝ ዜጎች ...” ብዙ ብዙ ... አሰብኩ።

 

ባህሩ በደንብ ይታየኛል። ከኋላ ጀልባ ዘዋሪዎቹ ጋር ነው የተቀመጥኩት። ሲጎተት የነበረው ጀልባ ግማሽ አካል እየሰመጠ ነው። ሁሉም ውሃው ላይ ነፍሱን ለማዳን ይፍጨረጨራል። ግን እንዴት? ወዴት ሄደው ራሳቸውን ያትርፉ? ማን ጎበዝ ነው ከስምንት ሰዓት በላይ በጀልባ የተጓዝነውን በዋና የሚመለስ? የህይወት ማዳን ጣር፣ሰቆቃ ያዘለው ያድኑን ጩኸት ድምጽ፣ ጣራቸው ... ሁሉነገር በጣም ያሳዝናል። በጣም በጣም ያሳዝናሉ። የእነሱ ጀልባ ዘዋሪዎች ሶስቱም በዋና እኛ ያለንበት ላይ ወጡ። ከዚህ በኋላ ውስጤ በፍርሃት ይርገደገድ ጀመር። እጣ ፋንታቸው ምን ይሆን? ጥርጥር የለውም። እኛ ያለንበት ጀልባ ላይ ከአስር የማይበልጡ ሶማያዊያን ናቸው ያሉት። እዛኛውም ላይ ያሉት ከአስር አይበልጡም። ግፋ ቢል ሰማኒያ የሚሆኑት ኢትዮጵያዊያን ይሆናሉ። አስቡት ይህን ያህል ወገኔን የያዘ ጀልባ ሲሰምጥ እያየሁ ምን ሊሰማኝ እንደሚችል አስቡት። ጅብሪል የት ይሆን? ሁለት እግሩን የሚያመው እና በሰው ታዝሎ የሚሄደው ልጅስ?ልጆች ይዛ እርግዝና ደርባ ያየኋትስ? ሁሉን ሳስበው ሰቀጠጠኝ። ያለንበት ጀልባ ጉዞውን ቀጥሏል። ለእይታ እየራቁ ... እየራቁ ከአይናችን ተሰወሩ። ሁላችንም እያለቀስን ራቅናቸው። ብርቃቸውም በልቤ ግን እያሰብኳቸው ነው። እንኳን ያኔ አሁንም ያን ትዕይንት ሳስታውስ ይሰቀጥጠኛል። አይኖቼ በእንባ ጭጋግ ይሞላሉ። ስንቴ አቋርጨ ስንቴ እንባዬን ጠርጌ እንደጻፍኩት ፈጣሪ ነው የሚያውቀው።

 

በዚህ ሁሉ ጊዜ ስናይትና ጓደኛዋ አለም ዘጠኝ ብለው እንቅልፋቸውን ያጣጥማሉ። ጉልበቴን ተንተርሶ የተኛው ሶማሊያዊ ለእንቅልፉ ማጀቢያ ሳውንድ ትራኩን ያሰማል /ያንኮራፋል/። መታደል ነው እኔ ደግሞ ትንሽ ጭንቀት ወይ ሀሳብ ካለብኝ በአይኔም ዞር አይል። አሁን እሁድ ነው። ላለለት በሀገሩ ላለ ሰው ቤተክርስቲያን ሄዶ ማስቀደሻ፣ ላደለው ቁርስ መብያ ሰዓት ነው። ቶሎ ቶሎ ገርገጭ የማደርጋት ውሀ ፕሮሰሷን ጨርሳ መውጣት ፈለገች። ”እንዴት ይሆን መንገዱን የማመቻችላት?” ስል አሰብኩ። ሌሊት ላይ ውሀ ባመጣንበት ጀሪካን ሞልተው ወደ ባህሩ ሲያሽቀነጥሩ ማየቴ ትዝ አለኝ። እኔም ባዶ ላስቲክ ነበረኝ እና ተንፈስ አልኩባት። ተንቀሳቃሽ ሽንት ቤት መሆኗ ነው። ”ሰላም ሁኚ ሰሽንቴ ለህንድ ውቅያኖስ ቆሪጥ ግብር ነሽ እኔን እንዳይወስድ ያው አንቺን ...” ብዬ ቱርርርር ... አደረኳት። አንድ ጥያቄ ግን ውስጤ ተጠነሰሰ። ”ሴቶቹስ እንዴት እንዴት ይሆናሉ?” ጉዞው ቀጥሏል። የእኔም ሀሳብ እና ጭንቀት እንደዛው በየአቅጣጫው በሚመለከተኝ በማይመለከተኝ ይኳትናል። ዛሬ ሁሉን ጥቃቅን ጭንቀቶች ማስታወስ ይከብደኛል። መክበድ ብቻ ሳይሆን ቦታም ይገድበኛል።

 

ቀን ወደ ስድስት ሰዓት ፀሀዩ ንዳድ ሆኖ ሳለ ከታች መቀመጫዮ አካባቢ ባስ ያለ ሙቀት ተሰማኝ። ትንሽ ቆይቶ ቀዘቀዘኝ። በትክክል ልብሴን ያለፈ ርጥበት ተሰማኝ።

 

”ሰናይት ከየት ነው ውሀ ነገር ተደፍቷል ረጠበኝ።” ሳቋን ለቀቀችው። በጥያቄዬ በመሳቋ ተናደድኩ።

 

”ምን ያስቅሻል” ድጋሚ ሳቀችብኝ። ሳቀችልኝ የሚያስብል አባባል አይደለም የሳቀችው።አሁን የእሷን ሳቅ ተከትሎ አልማዝም ሳቀች።የሆነ ያሳቃቸው ነገር እንዳለ ገመትኩ።ነገሩን ስላላወኩ ግን መሳቅ አልቻልኩም። ከፊቴ የተቀመጡት ሶማሌዎች አጠገብ የተቀመጠ አንድ የሀረር ልጅ ሴቶቹ ሽንታቸውን ሸንተው እንደሆነ ነገረኝ።

 

ጠዋት ላይ አልታወቀገህም ነበር

 

”አልታወቀኝም ሸንተሸ ነበር ሰኒ”

 

”ታዲያስ!” በጣም ብርድ ሆኖ ስለነበር ይሆናል ያልታወቀኝ። የሚል ሰበብ ለራሴ ሸለምኩ።እንዴት እንዳልታወቀኝ ግራ ገባኝ።

 

”አሁንስ ማነው” ድምጽዋን ወዳጠፋችው ጓደኛዋ በጣትዋ ጠቆመችኝ። አልማዝ ሚጢጢዬ ሀፍረት ቢጤ ሽው አለቻት። እጥፍጥፍ ብዬ የተቀመጥኩበት ግራ ከመደንዘዙ ጋር መቀመጫዮን ሸንቱ ስላቃጠለኝ ሰውነቴን ላፍታታ ቆም አልኩ። ከየት ጋር እንደመጣ ያላየሁት ሶማሊያዊ የጀልባ ዘዋሪ /ናኩዳ ይሏቸዋል/ በያዘው ዱላ አናቴን ነረተኝ። ዞሮብኝ ልጆቹ ላይ ወደኩ። ጀልባዋን የሚዘውሩት ሁሉም ሽጉጥ፣ ጩቤ፣ ዱላ የታጠቁ ናቸው። ሀሺሽ ያጨሳሉ። ሰዉን እንደፈለጉ አድርገው ይመታሉ። አንስተው ወደባህር ይከታሉ። የእኔ ለምን ትማታለህ ብሎ መፍጨርጨር ምንም እንደማያመጣ አውቄያለሁ። ዝም አልኩ። እንባዬ መጣ። ራሴ ላይ የመታኝ ማዞር ብቻ ሳይሆን ደሜ ተንዠቀዠቀ። ከሙቀት ጋር አልቆም አለ። አንዱ ሶማሌ የሰናይትን ሻርፕ ተቀበለና ጫፉን ይዞ ወደ ባህሩ ወርውሮ ነከረው። በኋላም አናቴ ላይ እንድይዘው ሰጠኝ። ውሀው ጨዋማ ስለሆነ አቃጠለኝ። እልህም ውስጤን ይንጠው ጀመር። ወንድ ሆነው ወንድ የማይሆኑበትን የስደት ህይወት ላይ መሆኔን ሳስብ ... ከሀገሬ ስነሳም ህወቴን አድናለሁ ብዬ ነውና የባሰ ህይወቴን እንዳላጣ ዝምታን መረጥኩ። ገድለው ወደባህር ቢወረውሩኝ ማን ይጠይቃቸዋል የሚጠይቃቸውም ቢኖር እኔ ጠያቂ ሳይሆን ህይወቴን ነው የምፈልጋ።

 

ዝምታዬም ቢሆን ያመጣው ነገር የለም። አንደኛው የያዘውን ሀሺሺ እያቦነነ፣ ዱላውን እየነቀነቀ ወደ እኔ መጣ።

 

ከዚህ በፊት በዚህ ዙሪያ ያሰባሰብኩትን የቪዲዮ እና ፎቶ መረጃ በቪዲዮ መልክ አዘጋጅቼ ዩቱብ እና ፌስ ቡክ ላይ ለቅቄው ነበር ያላገኛችሁት ከሁለቱ መርጣችሁ ማየት ትችላላችሁ።

 

 

(ይቀጥላል)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ