ኤፍሬም እሸቴ

እንግሊዛዊ ሆኖ “ሼኪስፒርን የማያውቅ፣ ሥራዎቹንም ያላነበበ፣ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ሀዲስ ዓለማየሁን የማያውቅ ‘ፍቅር እስከ መቃብርን’ም ያላነበበ” ቢኖር እጅግ የሚደንቅ ይሆናል። እንዲያውም ጥያቄው ‘ስንት ጊዜ አነበብከው?’ እንጂ ‘አንብበኸዋል እንዴ?’ አይሆንም የሚል ግምት ነበረኝ። ከዕለታት በአንዱ ቀን በድሮ የትምህርት ቤት መጽሐፎቻችን ውስጥ ስላሉ ታሪካዊ ጽሑፎች ስናወጋ በመካከሉ አብዲሳ አጋን አስታወስን። “ስንተኛ ክፍል መጽሐፍ ውስጥ ነበር ጃል?” እያልን ስንጠያየቅ አጠገባችን የነበረ አዕምሮው ብሩህ የሆነ ልጅ እግር የዩኒቨርሲቲ መምህር “ማነው አብዲሳ አጋ?” የሚል ጥያቄ አቀረበ። በመጀመሪያ እንደ ቀልድም ወሰድነው። ቀጥሎ እንደ መገረምም አደረገን።

 

ከዚያ በኋላ ግን በርግጥ ሐሳብ ውስጥ ከተተን። “እንዴት ነው ነገሩ?” አሰኘን። በዚያ ሁሉ ብሩህ አዕምሮው ውስጥ አብዲሳ አጋን ሳያውቅ ያለፈበት አጋጣሚ ወይ ከእርሱ ስንፍና ነው ወይንስ ከመማሪያ መጽሐፉ ውስጥ አልነበረም? እየተባባልን መልካም ወግ ፈጠርን።

 

ለጥያቄያችን መልስ ሳናገኝ ስለ አብዲሳ አጋ፣ ስለ ዘርዓይ ደረስ፣ ስለ አሉላ አባ ነጋ ገና በልጅነታችን በጀግንነት እንድናውቃቸው በለጋ ልቡናችን ላይ የተቀረፁትን ኢትዮጵያውያን እያስታወስን ብዙ ተጨዋወትን። ያንን ወጣት መምህር “ይህንን አለማወቅህ ያሳዝናል” በሚል ራስን የመካብና “እኛ ነን አዋቂዎቹ” በሚል መንፈስ ሳንጠርበው ያለፍን አይመስለኝም። ከስንቱ የዕውቀት ጎተራ አንድ “አብዲሳ”ን አለማወቁ “ማይም” እንደማያሰኘው ብናውቅም “እኮ እንዴት ያንን ጀግና ላታውቅ ቻልክ” ሳንለው ግን አልቀረንም። ይኸው መነሻ ሆኖኝ “ፍቅር እስከ መቃብር”ንም ሆነ ሀዲስ ዓለማየሁን የማያውቅ ኢትዮጵያዊ ቢኖር እንዳይደንቀኝ ተዘጋጅቻለኹ።

 

“ፍቅር እስከ መቃብር” መጀመሪያ ከታተመበት ከ1958 ዓ.ም ጀምሮ ከሰባት ጊዜያት ላላነሰ ለመታተም የበቃ፣ በኢትዮጵያ የሥነ ጽሑፍ ጥናት ውስጥ ምሁራኑ እጅግ ከፍ ባለ ዓምደ ወርቅ ላይ የሚያስቀምጡት ታላቅ ሥራ ነው። አብዛኛው ዜጋዋ ማንበብና መጻፍ በማይችለው በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም በኢትዮጵያ ራዲዮ የእሑድ ምሽት “ከመጻሕፍት ዓለም” ተደጋግሞ በመተረኩ ትልቅ ዕውቅናን በሚያነበውም በማያነበውም ዘንድ ያተረፈ፣ ፈረንጆቹ “የቤት ውስጥ ቃል”፣ ‘household name’ እንደሚሉት ለመሆን የበቃ መጽሐፍ ነው። ደራሲው ሀዲስ፣ “ተራኪ ወጋየሁ ንጋቱ” ነዋ። ሀዲስ ዓለማየሁ በአንድ ወቅት “እኔ መጽሐፉን ጻፍኩ፣ ወጋየሁ ደግሞ ሕይወትና ሙቀት ያለው ነፍስ” ሰጠው እንዳሉት (ጥቅሱ ከማስታውሰው ነው፤ ቃል በቃል አይደለም)።

 

መጽሐፉን ከማንበቤ በፊት ትረካውን ነው የሰማኹት። ከእሑድ እስከ እሑድ በጉጉት ተጠብቆ። እኔ ብቻም ሳልሆን መላው ቤተሰብ። ማንበብ የሚችለውም፤ የማይችለውም። ማታ ማታ መሠረተ ትምህርት ለመማር የሚሔደውም፣ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ የገባው የቤተሰባችን አባል በጉጉት የሚያዳምጠው ዝግጅት ነበር። ዳንቴል የምትለብሰው ሬዲዮ ዙሪያ ከብበን። ሬዲዮ በዳንቴል አሸብርቃ።

 

ከዜናው ቀጥሎ ተስረቅራቂው ዋሺንት መንቆርቆር ሲጀምር እና ዋና አዘጋጁ ርዕሱን፣ ደራሲውን፣ ያለፈውን ሳምንት ሊያስተዋውቅ ሲጀምር ቤቱ የጸጥታ ድባብ ይነግስበታል። ምንም እንኳን መጽሐፉ ከተጻፈ ብዙ ዓመታት ያለፉት ቢሆንም ከቤተሰባችን ቀድሞ ያነበበው አልነበረም። “ሳይማር ካስተማረ” ቤተሰብ ለምንመጣ ኢትዮጵያውያን እኛ የየቤተሰቦቻችን የመጀመሪያ የትምህርት ዓለም አስኳላ ቀማሾች መሆናችንም አይደል?

 

በዚያ የወጋየሁ ንጋቱ መግነጢሳዊ ድምጽ ያዳመጥነው መጽሐፍ ምራቅ ውጠን፣ በሰከነ ልቡና ስናነበው ደግሞ ልዩ ጣዕም ይዞ ይመጣል። በቅርቡ አንድ ወዳጄ ያመጣልኝን የድምጽ ቅጂ ስችልና እና ከረዥም ጊዜ በኋላ ያንን ትረካ ድጋሚ ለማዳመጥ ዕድል ሳገኝ ይኼንን ጽሑፍ ለመጻፍ ግድ አለኝ። በተለይም የካሳ ዳምጤን (የጉዱ ካሳን)፣ የአባ ሞገሴን፣ የባሪያይቱን የሀብትሽ ይመርን ታሪክ የሚያትተውን ክፍል ሳዳምጥ አሁንም ዘመኔን እንድቃኝ ያደርገኛል። በተለይም መገስጹ ጉዱ ካሳ።

 

‘ጉዱ ካሳ’ የፍቅር እስከ መቃብር ልቦለድ ምሶሶ ነው። ያውም ትንታግ መገስጽ። በደማቸውና በዘራቸው የሚንቀባረሩትን ፊታውራሪ መሸሻንና መሰሎቻቸውን፣ የእርሳቸውን ፊት ዓይተው የሚያድሩትን አባ ሞገሴን እና በጠቅላላው ሥርዓቱን የሚተችበት ቋንቋ በየዘመኑ ሕያውና ዘመነኛ ያደርገዋል። “የማኅበራችን አቁዋም የተሠራበት ሥራት፣ ልማዱ፣ ወጉ፣ እንደ ሕይወታዊ ሥራት ማኅበር ሳይሆን ሕይወት እንደ ሌለው የድንጋይ ካብ አንዱ ባንዱ ላይ ተደራርቦ የታችኛው የላይኛውን ተሸክሞ እንዲኖር ሆኖ የተሠራ በመሆኑ ከጊዜ ብዛት የታችኛው ማፈንገጡ ስለማይቀርና ይህ ሲሆን ሕንጻው በሙሉ እንዳይፈርስ እንደገና ተሻሽሎ፣ ሰውን ከድንጋይ በተሻለ መልክ የሚያሳይ የሕያዋን አቁዋመ ማኅበር እንዲሠራ ያስፈልጋል” ይላሉ የሀዲስ ዓለማየሁ ገጸ ባሕርይ ጉዱ ካሳ።

 

ጉዱ ካሳዎች የኅብረተሰባቸው ጉድፍ ነቃሾች፣ ዓይናፋርነትን የገደፉ የክፉ ነገር ጸሮች ናቸውና በእጅጉ ይናፈቃሉ። በሚኖሩበት ዘመን ግን ይጠላሉ። በተለይም ያረጁና የገረጀፉ፣ ውስጣቸው የነቀዘ ሥርዓቶች አንደኛውኑ ተገንድሰው ራሳቸውም ጠፍተው ሌላውንም እንዳያጠፉ ጉዱ-ካሳዎች መድኅን ናቸው።

 

“ጉዱ ካሳዎች” እንዲህ በቀላሉ እንዲኖሩ አይቻላቸውም። የራሳቸውን ነጻነት ለማግኘት “ጉድ” መባል እና ያንን “ጉድነታቸውን” ወይም በቀላል አባባል “ዕብድ” መሰኘታቸውን የተቀበሉ መሆን አለባቸው። ሰካራምና ዕብድ የልቡን ይናገራል እንደሚባለው ማኅበረሰባችን እንዲህ ግልጥ በግልጥ የሚናገሩ ሰዎችን መጀመሪያ ይፈራቸዋል፣ ቀጥሎ ከጀርባቸው አንድ ነገር ቢኖራቸው ነው ብሎ ይጠረጥራቸዋል፣ ሁሉንም ሲያጣ ደግሞ “ዕብዶች ቢሆኑ ነው” ብሎ የዕብድነትን ማዕረግ ያስታቅፋቸዋል።

 

ይህ በብዙዎች ዕብዶች መካከል ጤነኝነቱን ፈልጎ ያገኘው “ጉድ” (በሀዲስ ዓለማየሁ ፈጠራ “ጉዱ ካሳ”) የመጽሐፍ ቅዱሱን ሎጥን ያስታውሰኛል። ድፍን አገር በእግዚአብሔር ላይ አምጾ ኃጢአቱን እንደ ጽድቅ ሲቆጥር ብቻውን ጻድቅ ሆኖ (ከእነርሱ በመለየቱ ዕብድ መስሎ፣ እንደ ዕብድ ተቆጥሮ) የኖረው ሎጥ በዓለማዊ የሥነ ጽሑፍ ቋንቋ ቢገለጽ “የዘመኑ ጉዱ ካሳ ነበር” ማለት ነው። ቅዱስ ጴጥሮስም ስለ እርሱ ሲናገር (2ኛ የጴጥሮስ መልእክት 2፥7-8) “ጻድቅ ሎጥም በመካከላቸው ሲኖር እያየና እየሰማ ዕለት ዕለት በዓመፀኛ ሥራቸው ጻድቅ ነፍሱን አስጨንቆ ነበር” ይላል። በወቅቱ እንደ ዕብድ ቢቆጠር እና “ጻድቅ ነፍሱን ቢያስጨንቅም” የኋላ ኋላ ግን ጻድቅነቱ ማለት እውነተኛነቱ ተመስክሮለታል። ጉዱ ካሳዎችም እንዲሁ።

 

ሎጥ ጻድቅ ነፍሱን እንዳስጨነቀ እነዚህ የየዘመናቸው ሎጦችም ነፍሳቸውን ብቻ ሳይሆን ሥጋቸውንም በብዙ መከራ ለማስጨነቅ ይገደዳሉ። ከኤርትራ የበረሃ እስር ማሰቃያ ወኅኒዎች እስከ አዲስ አበባ ማዕከላዊ እሥር ቤቶች ብዙ ሎጦች እና ጉዱ ካሳዎች መከራቸውን አይተዋል። ከቻይና መንግሥታዊ ነፍሰ ገዳዮች ጀምሮ የሜክሲኮ አደንዛዥ ዕጽ አመላላሽ ነጋዴዎች እስከሚያሰማሯቸው ሽፍቶች ድረስ ብዙ እውነተኛ ሰዎች ሕይወታቸው ተቀጥፏል። ነገር ግን ታሪክ ዘወትር ይዘክራቸዋል። በጠራራ ፀሐይ ኩራዝ አብርተው ሰው ሲፈልጉ መቆየታቸው ውሎ አድሮ ትርጉም ያገኝላቸዋል።

 

የጉዱ ካሳን ያህል የሚደንቁኝ ደግሞ የየዘመኑ “አባ ሞገሴዎች” ናቸው። የሰው ፊት ዓይተው የሚያድሩ፣ የገዢዎቻቸውን ሐሳብ ለማጽደቅ፣ ሰማያዊ ትርጉም ለመስጠት፣ አቦ አቦ ለማለት ብቻ የሚተጉ እምነት ለበስ አጎንባሾች። የክፉ ነገር አጽዳቂዎች። እንደዚህ ዓይነት ሰዎች በየቤተ እምነቱ ነበሩ፤ አሁንም አሉ። በየቤተ እምነቱ ብቻ ሳይሆን በየትምህርት ተቋማቱ አሉ፤ በሊቅነት፣ በፕሮፌሰርነት፣ በዶክተርነት፣ በታዋቂ ጋዜጠኝነት፣ ደራሲነት፣ ዘፋኝነት፣ በአገር ሽማግሌነት፣ በአዋቂነት ወንበር የተቀመጡ የየሥርዓታቸው አፎች፣ አንደበቶች፣ ምላሶች። George Ayittey/ ጆርጅ አዪቴይ “ሰበነክ ምሑራን፤ Intellectual Prostitutes” ያላቸው “ንጉሥ ፈጣሪዎች”። ከሚያነግሷቸው ባልተናነሰ የክፋታቸው አጋሮች።

 

እንደዚህ ዓይነት አዋቂ ሰዎች ባላቸው ችሎታ በአገር ላይ ትልቅ የአድርባይነት አዚም በማስፈን ትውልድ ሊገድሉ ይችላሉ። ሰበነክ-ደራሲዎቹ የሚደርሱትን፣ ሰበነክ-ዘፋኞቹ እያንጎራጎሩ፣ ሰበነክ-ምሑራኑ ማጣቀሻ ታሪካዊ ዳራ እየቆፈሩ፣ ሰበነክ-የእምነት መሪዎቹ መለኮታዊ ገጽ እየሳሉ ተርታውን ሕዝብ በተለይም ሕጻናቱን፣ ወጣቶቹን እና ሕጻናተ አዕምሮዎቹን በጸጥታ እና በዝምታ እንዲኖሩ በማድረግ ለጌቶቻቸው ወታደር እንኳን ሊፈጽመው የማይቻለውን “ጸጥ ረጭ” የማድረግ ተጋድሎ ይፈጽማሉ። እንዲህ ዓይነቶቹ “ሰበነክ-ሊቃውንት” በየዘመኑ ነበሩ። ነገር ግን ለዕውቀታቸው የማይገባ ኅሊና-ቢስ ተግባራትን ፈጽመው አልፈዋልና በየሙያቸው ባላቸው ዕውቀት እና ችሎታ አንቱ የተባሉ ቢሆኑም በሕዝባቸው ላይ ያውም ዘመን ከሚያመጣቸው ዲክቴተሮች ጋር በማበር የሚፈጽሙት ወንጀል በሌላው ሙያዊ አገልግሎታቸው በጎነት የሚካካስ ሳይሆን ይቀራል።

 

ወደ መነሻዬ ተመልሼ ለማጠቃለል ልሞክር። ስለ አብዲሳ አጋ አላውቅም ያለውን ወጣት መምህር “የታሪክ ዕውቀት እጥረት” የሚባል በሽታ እንዳለበት በወዳጃዊ ተግሳጽ ሸንቁጠነው፣ ስለዚህ ጀግና ለማንበብ ቃል ገብቶ ተለያየን። ምናልባት አንድ ቀን “የታሪክ ዕውቀት እጥረት” ማለት ምን ማለት እንደሆነ እና ውጤቱም እንዴት እንደሚከፋ ይጽፍልን ይሆናል። ለአገር ብዙ ተግባር የሠሩ ሰዎችን ማወቁ ቢያንስ ቢያንስ “ሰበነክ-ምሑር” ከመሆን ያድነዋል።

ይሰውረን!!!


ኤፍሬም እሸቴ /

www.adebabay.com/

 

© ይህ ጽሑፍ በሮዝ አሳታሚ ኃ. የተወሰነ የግ.ማ በሚታተመው አዲስ ጉዳይ መጽሔት” ላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ላይ ማተም አይገባም።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ