የልጆቼ የጎህዬና የሱመያ፣ የሩቴና የኦማር “ጩኸት”
አብዩ በለው
ዓርብ ሴፕቴምበር 10 ቀን 2010 እ.ኤ.አ. ከሌሊቱ ለሰባት ሰዓት አስር ጉዳይ (12:50 AM) በኢሜል ለማገኛቸው የትየለሌ ወዳጆቼ ለ2003 ዓ.ም. የአዲስ አመት መልካም ምኞት መግለጫ የላኩላቸው መልዕክቴ የሚከተለው ነበር።
“መልካም አዲስ ዓመት ይሁንላችሁ! እንኳዋን ከዘመን ዘመን በጤና አሸጋገራችሁ! እኔ ግን ከሃሌ ጋር እንዲህ ብያለሁ። ብርቱን ጥዬ አልሻገርም!”
ዛሬ ፍልቅልቋ ሃሌ ከመራራው የ“እናት ናፍቆት” ሰቆቃ ወጥታ አሜሪካን ሃገር በእናቷ እቅፍ ውስጥ ትገኛለች። ስለሃሌ እግዚአብሔርን ሁሌ አመሰግነዋለሁ። ሌላው ሁሉ ቢቀር በልደት ቀኗ የእናት ናፍቆት ሰቀቀኗን አስቀርቷልና።
እነሆ ዛሬ የተመስገን ደሳለኝ “የሀገር ጩኸትና የታሳሪ ልጆች … አውደ-ዓመት” መጣጥፍ እንደተለመደው “ተሜን” አንብቤ ወደ አልጋዬ መሄድ አልተቻለኝም። እነ ናፍቆት፣ ኦማር፣ ፍትህና፣ ጎህ … በአንድ ወገን እነ ሱመያ፣ ሩህና፣ ኢናስ፣ … በሌላ ወገን በወላጆቻቸው ናፍቆትና ስስት ሌት ከቀን እየጮሁ እንዴት ይተኛል? እንዴትስ ሌሊቱ በሰላም ይነጋል? የትኛው ህሊና ያርፍ ይሆን?
እስክንድርም ሆነ አንዷለም ወይም ውብሸት አሊያም አቡበክርና አህመዲን ይልቁንም ካሚልና የሱፍ ዛሬ በግፈኛው የህወሓት እስር ከመማቀቃቸው እጅግ አብዝቶ የሚያደማቸው እነዛ የሚያሳሱ እምቦቀቅላ ፍሬዎቻቸው ፍፁም ንፁኃን ሆነው እያለ የህወሓት የግፉ በትር ለእነርሱም ተርፎ እንዲያ በናፍቆት ሲጨነቁና ሲዋትቱ ማየቱ ይመስለኛል። እንኳንስ ጣፋጯ ሱመያ በናፍቆት ስታለቅስ ይቅርና አልበላም አልጠጣም ስትል ምንኛ እንደምታስጨንቅና እንደምታሳቅቅ ለማወቅ ሰው መሆን ይበቃል። ወላጅ ሲኾን ደግሞ …
ታላቁ መጽሐፍ “አንዱ ስለሁሉም …” እንዲል የእነ ጎህዬና የሩቴ “ጩኸት” ተመሳሳይ አንድምታ ያለው ይመስለኛል። ለምንስ? ቢሉ፦
አንድም እንደ ህፃን - ወላጆቻቸው ንፁሃን ሆነው እያለ አንዴ ነፍጠኛ፣ ሌላ ጊዜ ኦነግ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ቅንጅት፣ አሁን ደግሞ አሸባሪ እየተባሉ በ“ዓይንህ ቀለም አላማረኝም” ስይጥንና በወያኔ ሲዖሎች ውስጥ ለዘመናት ተቆልፎባቸው የወላጅ እቅፍና ፍቅር እጦት ለሚያናውዛቸው የኢትዮጵያችን “የራሔል ልጆች” ተገብተው ሲጮኹላቸው በማየቴ፣
አንድም እንደ ህዝብ - ሰሚ ስላጣው የኢትዮጵያውያን የፍትህ፣ የነፃነት፣ የዲሞክራሲና፣ የእኩልነት እጦት ስለ እኛ ተገብተው እንዲጮኹልን ወላጆቻቸው ስለፈረዱባቸውና በእውነትም ሳይገባቸውና ሳይገባቸው ስለእኛ ሲጮሁልን በማየቴ፣
ይልቁንም የእነ ናፍቆትም ሆነ የእነ ሩቴ ሰቆቃ ልዩ የሚሆንብኝ ዛሬ ወላጆቻቸው ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲያድጉ “ባይፈርዱባቸው” ኖሮ እንደ አብዛኛዎቻችን ልጆች ሁሉ ቢያንስ በዚህቺው በፈረደባት “ሃገረ-አሜሪካ” በሰላም መኖርና ከወላጆቻቸው ጋር በቅንጦት የመማር ሙሉ እድሉ የነበራቸውና ዛሬም መብቱ በእጃቸው መሆኑ ሲታሰበኝ ጭምር ነው።
እጅግ ይልቁንም - እርግጥ ነው አብዛኛዎቻችን (ሁሉም ማለት በሚያስደፍር ሁኔታ) ከሃገር ከወጣንና በስደት መኖር በጀመርን ማግስት እንደ ተሞሸርንና ልጆችም እንደወላለድን ይታወቃል። ህዝባችንም በአርምሞ ያያል (ምስጋና ለፌስ ቡክ)። ታዲያ እኒህ ልጆቻችን በአብዛኛው የተወለዱት ቢያንስ እንደ ሰው በክብር በሚያድጉበት ሃገርና እንደ “ዜጋ” በሚሳሳላቸው የሰለጠነው ዓለም ህዝብ እቅፍ ውስጥ ሲሆን፤ እኛ የእነ አንዷለምና የእነ እስክንድር … ጓዶች በእነርሱ የእስር ዋጋና በብልጣብልጥ ስደተኝነት ለልጆቻችን እንደ ዘመኑ አባባል “አወዳደቃቸውን” እንዳሳመርንላቸው? በተሰማኝ ጊዜ ነው።
ከዛም ምን አለበት ታላቁ ደራሲ አቤ ጉበኛ ዛሬ በህይወት ቢኖሩልንና በወያኔ የግፍ አለንጋ የሚሰቃዩትን የአምላክ ንፁሃን ህፃናት በነፃነት፣ በፍቅርና፣ በሰላም እንዲኖሩና እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በወላጆቻቸው እቅፋና በፍቅራችን ልናሳድጋቸው የማንችል ከሆነ ከቶውንም ወደዚህ የሰቆቃ ህይወት እንዳናመጣቸው የሚመክርና የሚዘክር በ“አልወለድም” ፋንታ “አልወልድም”ን ቢከትቡልን እላለሁ። ማን ያውቃል እኛን “ስለደላን” ብቻ ወላልደን ከዓላማ ማፈግፈግና የነፃነት ትግሉን ከማኮላሸት እንድን ይሆናል።
በመጨረሻም ስለ ውድ ወገናቸው ክብር፣ ነፃነትና፣ አንድነት ሲሉ ዘወትር የሚሳሱላቸውን እነዚያን ፍቅር የሆኑ ልጆቻቸውን ወላጅ አልባ፣ ደካማና፣ ጎስቋላ አድርገው እራሳቸውን ለወያኔ የማሰቃያ ካምፕ አሳልፈው የሰጡት የጀግኖቻችንን የአብራክ ክፋዮች ሰቆቃና እንግልት በምድራችን እስኪያከትምና ይልቁንም ነፃነት፣ እኩልነት፡ ፍትህና፣ ሰላም በኢትዮጵያ ሃገራችን እስኪሰፍን ድረስ በትግሉ እንፀና ዘንድ የእነ ናፍቆት፣ ኦማር፣ ፍትህና፣ ጎህ … የእነ ሱመያ፣ ሩህና፣ ኢናስ … ጩኸት ሁላችንንም ግድ ሊለንና ዛሬም ከነፃነት ትግሉ ጎን እንድንሰለፍ ሊያስገድደን ይገባል እላለሁ። ለዛሬ አበቃሁ።
ልጆቼ ናፍቆት፣ ኢናስ፣ ፍትህ … ሁሌም እወዳችኋለሁ!
እግዚአብሔር አምላክ በሞገሱና በፍቅሩ ያሳድግልኝ። አሜን!
አብዩ በለው
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ጥር 2005 ዓ.ም. ኮሎምበስ/ኦሃዮ



