እኔ እንዳዳመጥኩት
ጌቱ ኃይሉ
መቼም ሰው ይናገራል። እኔ ደግሞ ጆሮ ፈጥሮብኛልና እሰማለሁ። የምሰማውና የማዳምጠው ግን ይለያያል።
ባለፈው ሰሞን ቁጥር 00 ሰውዬ ሲናገሩ ሰማሁ፣ “የዛሬ አሥር ዓመት ከ80 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን ሥራ እናስይዛለን” ብለው ሲናገሩ ሰማሁ።
እና አዳመጥኩ፣ “የዛሬ አሥር ዓመት ከ80 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን ሥራ እናስይዛለን፣ ምክንያቱም አሁን እየቀጠርናቸው ያለነው ቻይናውያን፣ ሕንዳውያን፣ ብራዚላውያን፣ ወዘተርፈዋውያን ... የዛሬ አሥር ዓመት ኢትዮጵያውያን ይሆናሉ፣ በቁጥርም ከ80 ሚሊዮን በላይ ይሆናሉ።” ብዬ አዳመጥኩ።
ያገሬ ሕዝብ ደግሞ የቀን ሥራ እንኳን ሳይቀር እየተቀማ ለቻይና ሲሰጥበት፣ ተግቶ ይጸልያል። “የባሰ አታምጣ” እያለ። እኔ ደግሞ አዳምጣለሁ፣
“የባሰ አታምጣ”ን መሥማት ደከመኝ!
“የተሻለ አምጣ” የሚል ናፈቀኝ” ብዬ።
ሌላ ጊዜ ደግሞ ሌላው ቁጥር 00 ተናገሩ። እኔም አዳመጥኩ። በጫወታዬ ላይ ቁጥር ከ00 በላይ መቁጠርም ሞክራለሁ። ግን የሚናገሩት ተመሳሳይ ስለሆነ መለየት ቸግሮኝ ነው አንድ አይነት ቁጥር የሰጠኋቸው። እና ሌላው ቁጥር 00 ተናገሩ። “እኛ ስለእድገታችን ስንተነብይ ቁጥሩን ለጥጠን ተናግረናል። አሁንም ቢሆን ለጥጠን እንናገራለን።” ሲሉ ተሰማ።
እኔም ደግሞ “አዎን! ለጥጠን እንናገራለን። ቃም፣ ቃም አርገን መርቀን ስንል በጎ፣ ከፍ፣ ከፍ ያለ ቁጥር ብንመኝ ምናለበት? ቢሳካ ባይሳካ ምን ችግር አለው? ማን ይጠይቀናል?” ብዬ አዳመጥኩ።
ሌላ ጊዜ ደግሞ ሌላው ቁጥር 00 ተናገሩ፣ “ቻይናዎች አውሮፕላኑ የነሱ እንደሆነ እንዲሰማቸው እንፈልጋለን። የነሱን ዜጋም የቀጠርነው ለዚህ ነው።”
እኔም “ከቻይናው ባንክ በወለድ የተበደርነውን መክፈል ባለመቻላችን በሰሊጥ፣ በኑግና በሌሎችም ጥሬ ምርቶች ከፍለን፣ ከፍለን፣ ከፍለን፣ ... እዳው አላለቀም። እንግዲህ የኢትዮጵያ አየር መንገድን እየሸራረፍን፣ ለምሳሌ የነሱን ዜጋ በመቅጠር አይነት ለመክፈል አስበን ነው” ብዬ ለማዳመጥ እየከጀልኩ ነው።
ጌቱ ኃይሉ የጸኃዮቹ (https://www.facebook.com/book.tsehayochu)መጽሐፍ ደራሲ ነው።