Former PM Tesfaye Dinkaኢትዮጵያ ዛሬ (ዓርብ ኅዳር ፴ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም. Dec. 9, 2016)፦ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ብሎም ከ1981 እስከ 1983 ዓ.ም. በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ኢትዮጵያን ያገለገሉት አቶ ተስፋዬ ዲንቃ ያዴሳ ኅዳር ፳፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም. በ፸፯ ዓመታቸው አረፉ።

አቶ ተስፋዬ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ (ኢሠፓ) ፖሊት ቢሮ አባል የነበሩ ሲሆን፣ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ በኢኮኖሚ ሚኒስቴር እና በተለያዩ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በሚኒስትርነት አገልግለዋል። አቶ ተስፋዬ በደርግ የመጨረሻ ወራት ለአንድ ወር ከዘጠኝ ቀናት (፴፱ ቀናት) ከሚያዝያ ፲፰ እስከ ግንቦት ፱ ቀን ፲፱፻፹፫ ዓ.ም. የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ነበሩ።

በዓለም አቀፍ መሥሪያ ቤቶች ውስጥም ከማገልገላቸውም በላይ፤ እ.ኤ.አ. 1990 በዓለም ባንክ ውስጥ ሠርተው እንደነበር ይታወሳል። ለረዥም ዓመታት በዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ፣ ቨርጂንያ ነዋሪ የነበሩ ሲሆን፣ በአፍሪካ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ በሚሠራውና ”ግሎባል ኮአሊሽን ፎር አፍሪካ” (ዓለም አቀፉ የአፍሪካ ጥምረት) ለተሰኘው ድርጅት በከፍተኛ አማካሪነት ሲሠሩ ቆይተዋል።

አቶ ተስፋዬ ዲንቃ የተወለዱት አምቦ ከተማ ሲሆን፣ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን አምቦ ጨርሰው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በአዲስ አበባ የጄነራል ዊንጌት ት/ቤት ነበር። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ቤሩት በሚገኘው የአሜሪካን ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል። የማስትሬት ዲግሪያቸውን ደግሞ በአሜሪካ ኒው ዮርክ በሚገኘው ሲራከስ ዩኒቨርሲቲ በኢንደስትሪያል ኢንጂነሪንግ ለማግኘት ችለዋል።

በደርግ መጨረሻ ሰዓት፣ ኸርማን ኮኽን በአወያይነት በመሩትና በአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር (State Department) አስተባባሪነት፤ ደርግ በሎንዶን ከወያኔ፣ ሻዕቢያ እና ከኦነግ ጋር ባደረገው ድርድር፤ የደርገን ልዑካን ቡድን መርተው በድርድሩ ላይ ከተገኙት የወቅቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ውስጥ አቶ ተስፋዬ ዲንቃ አንዱ እንደነበሩ አይዘነጋም።

በድርድሩ ላይ ከደርግ ወገን አቶ ተስፋዬ ዲንቃ፣ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የነበሩት አቶ ቢልልኝ ማንደፍሮ እና ዶክተር ግርማ ወልደሥላሴ የተገኙ ሲሆን፣ በሌላኛው ወገን ለድርድሩ የቀረቡት ሟቹ ጠ/ሚ አቶ መለስ ዜናዊ (ከወያኔ)፣ የአሁኑ ፕ/ት ኢሳያስ አፈወርቂ (ከሻዕቢያ)፣ አቶ ሌንጮ ለታ (ከኦነግ) ነበሩ። በወቅቱ ኸርማን ኮኽን የወያኔ/ኢሕአዲግ ጦር አዲስ አበባን በአስቸኳይ እንዲቆጣጠር ሲሉ፤ አቶ ተስፋዬ ተቃውሞ አሰምተው እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ።

አቶ ተስፋዬ ዲንቃ ባለትዳር፣ የአራት ልጀች አባት እና የአራት ልጆች አያት ነበሩ።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ