በግብጽ የሆሳዕናን በዓል እያከበሩ የነበሩ አርባ ሦስት ሰዎች በሽብርተኞች ቦምብ ተገደሉ
አንድ መቶ ሰዎች ቆሰሉ
ጥቃቱ የተፈጸመው በታንታ እና በአሌክሳንድሪያ ከተሞች ነው
ኃላፊነቱን አይሲስ ወስዷል

ኢዛ (እሁድ ሚያዝያ ፩ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም. April 9, 2017)፦ ክርስቲያኖች የሆሳዕና በዓልን እያከበሩ ባሉበት በዛሬው ዕለት፣ በግብጽ ሁለት ከተሞች አርባ ሦስት ሰዎች በሽብርተኞች ሲሞቱ አንድ መቶ አስራ ዘጠኝ ሰዎች ቆሰሉ። የሽብር ጥቃቱን ኃላፊነት አይሲስ መውሰዱ ታውቋል።
የመጀመሪያው ጥቃት የተፈጸመው በታንታ ከተማ በሚገኘው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ውስጥ በፈነዳ ቦንብ የሃያ ሰባት (፳፯) ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ፣ ሰባ ስምንት (፸፰) ሰዎች መቁሰላቸው ታውቋል።
ሁለተኛ ጥቃት የተፈጸመው ከሰዓታት በኋላ በአሌክሳንድሪያ ከተማ በሚገኘው ቅዱስ ማርቆስ ካቴድራል በመባል በሚጠራው ታሪካዊው የክርስትና ቤተክርስቲያን ሲሆን፣ ጥቃቱን የፈጸመው በራሱ ላይ ቦንብ የታጠቀ አጥፍቶ ጠፊ ነበር።
በአሌክሳንድሪያው ቅዱስ ማርቆስ ካቴድራል ቤተክርስቲያን በደረሰው የሽብር ጥቃት ሕይወታቸውን ያጡት ሰዎች ቁጥር አስራ ስድስት (፲፮) ሲሆን፣ የቆሰሉት ደግሞ አርባ አንድ (፵፩) ሰዎች መሆናቸውን የግብጽ መገናኛ ብዙኀን ዘግበዋል።
የአሌክሳንድሪያው ፓትርያርክ ዳግማዊ ቴዎድሮስ የሆሳዕናን በዓል በቅዱስ ማርቆስ ካቴድራል ውስጥ ሲመሩ የነበሩ ቢሆንም፤ ከጥቃቱ መትረፋቸው ታውቋል። አጥፍቶ ጠፊው ፓትርያርኩን የመግደል ዕቅድ ይኑረው አይኑረው ግን እስካሁን የተረጋገጠ ነገር የለም።






