አቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደሰ ካሣ

በምዝበራ ተጠርጥረው ክስ የተመሰረተባቸው አቶ ታደሰ ካሣ (ግራ) እና አቶ በረከት ስምኦን (ቀኝ)

ኢዛ (ረቡዕ ሚያዝያ ፱ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም. April 17, 2019)፦ ከዳሽን ቢራ አክሲዮን ማሕበርና ከጥረት ኮርፖሬት ኩባንያዎች ጋር ተያይዞ በምዝበራ/ሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙት አቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደሰ ካሣ ክስ ተመሰረተባቸው። ተከሳሾቹ ጠበቆቻችን የክርክሩን ሒደት ከአዲስ አበባ ኾነው በፕላዝማ ይከታትሉልን ሲሉ ለፍርድ ቤቱ ያቀረቡትን ጥያቄ ችሎቱ ውድቅ አደረገው።

ሚያዝያ 7 ቀን 2011 ዓ.ም. ክሱን የመሰረተው ልዩ አቃቢ ሕግ፤ ከአንድ ሺህ በላይ ገጽ ያለው የክስ ሐተታ በፌደራል ፍርድ ቤት ያቀረበ ሲሆን፤ የተጠረጠሩበትን ወንጀል ሲመረምር የነበረው ደግሞ የአማራ ክልል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን እንደነበር ታውቋል። አቶ በረከት የፌደራል መንግሥት ባለሥልጣን የነበሩ በመሆናቸው፤ ክሱ የተመሰረተው አግባብነት ባለው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት መኾኑ ይታወቃል። በዚህም ምክንያት በአማራ ክልል ይኽንን ክስ ሊያይ የሚችልና የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቻ ኾኖ በተገኘው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ክሱ ቀርቧል።

የክሱ ሰነድ የደረሳቸው ሁለቱ ተከሳሾች የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ሲጠየቁ፤ ክሱ ብዙ ገጽ ያለው በመሆኑ አጠቃላይ የክሱን ይዘት አይተው መልስ መስጠት እንዲችሉ ፍርድ ቤቱ የጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

በተጨማሪም ጠበቆቻቸው ላይ ከፍተኛ ዛቻና ማስፈራራት ስለደረሰባቸው፤ ጠበቆቻቸው ውላቸውን መሰረዛቸውን በመግለጽ፤ ከአዲስ አበባ አዲስ ጠበቃ አቁመው መከራከር እንዲችሉ፤ አዲሶቹ ጠበቆችም ክርክሩን በፕላዝማ ለማየት እንዲፈቀድላቸው፤ ይህ የማይሆን ከሆነም የሕግ አማካሪ ባለሙያ ማግኘት እንዲችሉ ጠይቀዋል።

አቃቤ ሕግ በበኩሉ የፕላዝማ ክርክሩን የተቃወመ ሲሆን፤ ፍርድ ቤቱም ከሳሽና ተከሳሾችን አድምጦ፤ የተከሳሾችን የፕላዝማ ክርክሩን ጥያቄ ውድቅ በማድረግና ጠበቃ እንዲቆምላቸው ተዕዛዝ በመስጠት፤ ክሱን አንብበው የመቃወሚያ ሐሳብ ካላቸው ማሰማት ይችሉ ዘንድ ለሚያዝያ 14 ቀን 2011 ዓ.ም. የጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!