በጉቦ ቅሌት የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት መዝገብ ቤት ኃላፊ ታሰሩ

Ethiopia Zare (ኀሙስ ነኀሴ 15 ቀን 2000 ዓ.ም. August 21, 2008)፦ የ50 ዕድሜ ባለፀጋ የሆኑትና ለ30 ዓመታት በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያገለገሉት፣ የፍ/ቤቱ የአስተዳደር ክፍል የመዝገብ ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ታዬ ተኮላ ከአ.አ.ዩ. ተማሪ ላይ 200 ብር ጉቦ ሲቀበሉ እጅ ከፍንጅ ተያዙ። ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረቡ። የታሪኩ ድራማ እንደሚከተለው ይገኛል ...

 

አቶ አብዲ ሱልጣን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማታው ክፍለጊዜ የሕግ ተማሪ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር መንገድ የፍተሻ ሠራተኛ ነው። የዩኒቨርሲቲው የሕግ ዲፓርትመንት ተማሪ አብዲን ለልምምድ ጊዜ (አፓረንትሺፕ) ወደ ፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይመድበዋል።

 

ሰኞ ነኀሴ 12 ቀን 2000 ዓ.ም. ተማሪ አብዲ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የአስተዳደር መዝገብ ቤት ሲሄድ ኃላፊውን አቶ ታዬ ተኮላን ያገኛቸውና ለልምምድ መምጣቱንና ማመልከት እንደሚፈልግ ይገልጽላቸዋል።

 

አቶ ታዬም ስድስት የሕግ ተማሪዎች በፌደራሉ ፍ/ቤት ልምምድ ላይ ስለሆኑ ለተማሪ አብዲ የሚሆን ቦታ እንደሌለ ይገልጹለታል። አክለውም ምናልባት ቦታ ከተገኘ ስልክ ሊደውሉለት እንደሚችሉ ይነግሩትና ስልኩን ይቀበላሉ።

 

በማግስቱ ማክሰኞ ነኀሴ 13 ቀን አቶ ታዬ ለተማሪ አብዲ ስልክ ይደውሉለታል። ዩኒቨርሲቲው ፍርድ ቤት የመደበበትን የሚገልጸውን ወረቀት ይዞ ከመጣ ሳይለማመድ እንደተለማመደ አድርገው ማስረጃ እንደሚሠሩለት ይገልጹለታል። ለዚህም ውለታቸው የምሳ የሆን ገንዘብ እንዲሰጣቸው ይጠይቁታል።

 

ተማሪ አብዲም ”አሁን ገንዘብ ስላልያዝኩ ነገ እንገናኝ” ብሎ ይመልስላቸውና ሜክሲኮ ቅድስተ ማርያም ኮሌጅ ፊት ለፊት ካሉት ካፍቴሪያዎች በማግስቱ ይቀጥራቸዋል። ጉዳዩንም ለልደታ ፖሊስ ጣቢያ ሄዶ በማስረዳት ያስመዘግባል።

 

ረቡዕ ነኀሴ 14 ቀን ተማሪ አብዲ በልደታ ፖሊስ የተመዘገቡና ቁጥራቸው ኤምሲ132175 እና ኤጂ2605070 የሆኑ ሁለት ባለመቶ ብር ኖቶች ይዞ፣ ሁለት ሲቪል የለበሱ ፖሊሶች እና አንድ የደህንነት ሠራተኛ አስከትሎ አቶ ታዬን ወደቀጠረበት ሥፍራ ያመራል።

 

በቀጠሮው ሥፍራ አቶ ታዬና ተማሪ አብዲ ሲገናኙ የተመዘገቡትን ሁለት ባለመቶ ብር ኖቶች አቶ ታዬ ይቀበላሉ። አቶ ታዬ ወዲያው በቁጥጥር ስር ይውሉና ልደታ ፖሊስ ጣቢያ ተወስደው ይታሰራሉ።

 

ዛሬ ኀሙስ ነኀሴ 15 ቀን 2000 ዓ.ም. የልደታ ፖሊስ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት አቶ ታዬን አቅርቧቸው የጊዜ ቀጠሮ ጠይቆባቸዋል። በሕጉ መሠረት የልደታ ፖሊስ ከፌዴራሉ የሥነምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን የውክልና ደብዳቤ ካላቀረበ የጊዜ ቀጠሮ መጠየቅ እንደማይችል ተገልጾለት ተጠርጣሪ የሆኑትን አቶ ታዬ ተኮላን ለጊዜው ወደ ልደታ ፖሊስ ጣቢያ ውስዶ አስሯቸዋል።

 

አቶ ታዬ ተኮላ ምንም እንኳን የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስተዳደር (የሠራተኞች) መዝገብ ቤት ኃላፊ ቢሆኑም የድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) ችሎት በቋሚነትና ካለማቋረጥ ከሚከታተሉ ሰዎች አንዱ ናቸው።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!