The Grand Ethiopian Renaissance Dam

ታላቁ የህዳሴ ግድብ

የተፋሰሱ አገራት ቀጣይና የመጨረሻ የተባለውን ስምምነት በዚህ ወር መጨረሻ በዋሽንግተን ያካሒዳሉ ተብሎ ይጠበቃል

ኢዛ (ረቡዕ ኅዳር ፳፬ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. December 4, 2019)፦ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ ሦስቱ የተፋሰሱ አገሮች እስካሁን ባደረጉት ውይይት ላይ ተመስረተው የመጨረሻ ስምምነት ያደርጉበታል የተባለው የውይይት መድረክ እንደገና በዋሽንግተን ዲሲ እንደሚካሔድ ለማወቅ ተችሏል።

ኅዳር 21 እና 22 ቀን 2012 ዓ.ም. በግብጽ ርዕሰ ከተማ ካይሮ ላይ የተደረገው የኢትዮጵያ፣ የግብጽና የሱዳን የጋራ ውይይት ከተጠናቀቀ በኋላ የተሠራጨው መረጃ እንደሚጠቁመው ከኾነ፤ አገራቱ እስካሁን በተወያዩባቸውና በተግባቡባቸው ጉዳዮች ላይ የመጨረሻ የተባለውን ስምምነት ኅዳር 29 ቀን 2012 ዓ.ም. በዋሽንግተን ያካሒዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከአንድ ወር ተኩል በፊት አሜሪካ ባደረገችው ጥሪ የሦስቱ አገራት የልዑካን ቡድኖች በዋሽንግተን በመገኘት መክረው እንደነበርና ውይይታቸውን እንደቀድሞው በየተራ በሦስቱ አገራት እንዲያከናውኑ ተስማምተው እንደነበር አይዘነጋም።

ከዋሽንግተን መልስ መጀመሪያ በአዲስ አበባ ውይይት ተደርጎ፤ በቀጣይ ደግሞ የካይሮ ተራ በመኾኑ፤ ኅዳር 21 እና 22 ቀን 2012 ዓ.ም. በካይሮ ተካሒዷል።

በካይሮ ስለተደረገው የሦስቱ አገራት ውይይት ግን ከዚህ ቀደም እንደነበሩት ስለውይይቱ ዝርዝር ጉዳይ ያለተነገረበት ነው። ኾኖም እስካሁን የተደረጉ ውይይቶች በዋሽንግተን ውይይቱ ላይ እንደሚገመገም ግብጽ ገልጻለች።

በካይሮው ስብሰባ ላይ የዓለም ባንክና የአሜሪካ ተወካዮች ለሦስተኛ ጊዜ የተገኙበት እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።

ኢትዮጵያ የዓባይን ውኃ ለመጠቀም ሊገታት የሚችል ምንም ዐይነት ተጽእኖዎችን እንደማትቀበል አቋሟን እንዳጸናች ይታወቃል። የግድቡን ሥራ የበለጠ ለማፋጠን እየሠራች መኾኑ ይታወቃል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ