ቅዱስ ሲኖዶስ በተለያዩ ጉዳዮች አቋም የወሰደበትን መግለጫ አወጣ
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ (ከላይ)፣ ከስር ያሉት አራቱ ሲኖዶሱ ክህነታቸውን የያዘባቸውና የታገዱት ግለሰቦች
መግለጫው በ22 አካባቢ ስለጠፋው ሕይወት፣ ስለኦሮሞያ ቤተ ክህነት ማቋቋም፣ ስለአሜሪካኑ ጽላት፣ ስለመገናኛ ብዙኀንና ስለጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስቷል
ኢዛ (ረቡዕ የካቲት ፲፩ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. February 19, 2020)፦ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ 22 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የተፈጸመውን ድርጊት ያወገዘ፣ ከቤተክርስቲያኑ ሕግና ደንብ ውጭ የኦሮሚያ ቤተ ክህነት እናቋቁማለን በማለት የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችን ማገዱን፣ እንዲሁም በሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ውሳኔ የደረሰበትን መግለጫ አወጣ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ላለፉት ሦስት ቀናት ያካሔደውን አስቸኳይ ስብሰባ መጠናቀቅን ተከትሎ ያወጣው መግለጫ ስድስት ዋና ዋና በተባሉ ጉዳዮች ላይ ያነጣጠረ ነው።
በ22 አካባቢ ተከስቶ ስለነበረው ግጭትና የሰዎች ሕይወት መጥፋት፣ እንዲሁም ስለመሬት ጥያቄ
በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ 22 አካባቢ ጥር 24 ቀን 2012 ዓ.ም. ለ25 አጥቢያ በውድቅት ሌሊት በምእመናን ላይ በተደረገ ተኩስ የሁለት ሰዎች ሕይወት ከመጥፋቱም በላይ አስለቃሽ የመርዝ ጋዝ ጭስ በመተኮስ፣ በጥይትና በዱላ በርካቶች መቁሰላቸው አይዘነጋም። ሲኖዶሱ ከዚህም ሌላ ጽላት መወሰዱን፣ ንዋያተ ቅድሳት መዘረፋቸውን፣ ቤተ ክርስቲያኗ መፍረሷን አስመልክቶ “ክፉና ጭካኔ የተመላበት ድርጊት” በማለት አውግዞታል።
“በቤተ ክርስቲያናችን ላይ እንዲህ ዐይነት ክፉ ድርጊት የፈጸሙ አካላት ላይ መንግሥት ጥብቅ ምርመራ በማድረግ ወንጀለኞቹ ለፍርድ እንዲቀርቡና ውጤቱ ለምእመናኖቻችን በሚዲያ እንዲገለጽ እንጠይቃለን።” ሲል መግለጫው መንግሥትን ይጠይቃል።
ለዚህ ሁሉ ምክንያት መነሻ የኾነውን የቦታ ጥያቄ አስመልክቶ፤ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከአራት ዓመታት በፊት ጀምሮ ቦታው ለአካባቢው ምእመናን ማምለኪያ ይኾን ዘንድ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በመነጋገርና በመጻጻፍ መቆየቷን ሲኖዶሱ ገልጿል። በመኾኑም ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ ተገንብቶ ምእመናኑ አምልኳቸውን ይፈጽሙ ዘንድ መንግሥትን ጠይቋል። አያይዞም “ደም የማፍሰስና ሕይወትን የማጥፋት ተልዕኮ አልበቃ ብሎ፤ በየምክንያቱ የታሰሩ ካህናት፣ ምእመናንና ወጣቶችም ጭምር በእስር ላይ መኾናቸው ስለሚታወቅ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስራት እንዲፈቱ እንዲደረግ ቅዱስ ሲኖዶስ አጥብቆ ይጠይቃል።” በማለት የታሰሩት ይፈቱ ዘንድ ለመንግሥት ጥያቄውን አቅርቧል።
ከኦሮሞያ ቤተ ክህነት ጉዳይና ከአሜሪካው ጽላት ጉዳዮች ጋር የተያያዙትን ሰዎች ስለማገድ
ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንንን፣ አባ ገ/ማርያም ነጋሳን፣ መምህር ኃ/ሚካኤል ታደሰንና ቄስ በዳሳ ቶላን ሲኖዶሱ በስም ጠቅሶ፤ “በሕገወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሱ እንዲሁም በቅዱስ ሲኖዶስ ተባርኮ ጽላት ተሠጥቶናል በሚል፤ በምድረ አሜሪካ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም ቤተ ክርስቲያን አቋቁመናል የሚሉት፤ ከድርጊታቸው ተቆጥበው በንስሐ እስኪመለሱ ድረስ ከቤተ ክርስቲያናችን የተሠጣቸው ክህነት ከዛሬ የካቲት 11 ቀን 2012 ዓ.ም. ተይዟል” በማለት አስታውቋል።
ከዚህም ሌላ እነዚህ ግለሰቦች በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም ምንም ዐይነት እንቅስቃሴም ኾነ መንፈሳዊ አገልግሎት እንዳይሠጡ በሲኖዶሱ መታገዳቸውን መግለጫው ይጠቅሳል።
ዐረብ ኤምሬቶችና ዱባይ ለቤተ ክርስቲያንዋ የተፈቀደው ቦታ አስመልክቶ
በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች፣ በዱባይ በስደት ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቤተ ክርስቲያን ለመሥራት የቦታ ጥያቄ ለአገሪቱ መንግሥት (የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች) ሲቀርብለት የቆየ ቢሆንም፤ እስካሁን ምላሽ ሳያገኝ ቆይቶ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ባደረጉት ጥረት ሰሞኑን ቤተ ክርስቲያን መገንቢያ ቦታ መገኙቱን አይዘነጋም።
ቅዱስ ሲኖዶሱ በዐረብ ኤምሬቶች ቤተ ክርስቲያ መገንቢያ ቦታ መገኘቱን አስመልክቶ፤ “የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በእጅጉ ከመደሰቱም በላይ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ወደዚህ አገራዊ መንበረ ሥልጣን ከተጠሩበት ጊዜ ጀምሮ የቤተ ክርስቲያናችንን ጉዳይ ጉዳያቸው አድርገው እየፈጸሙት ያለ አኩሪ መንፈሳዊ ተግባር ሁኖ ስላገኘው፤ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የከበረ ምስጋናውን አቅርቧል።” በማለት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ምስጋና አቅርቧል።
የቤተ ክርስቲያኒቱን ስም እያጠፉ ነው በማለት ሲኖዶሱ የከሰሳቸው የመገናኛ ብዙኀን
ኦኤምኤን (OMN)፣ ኤልቲቪ (LTV) እና ኦቢኤስ (OBS) የተባሉት ቴሌቭዥን ጣቢያዎች በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ ማካሔዳቸውን በመግለጽ፤ “ታሪክን እያበላሹ የተሳሳተ መረጃ ለሕዝብ እያስተላለፉ ናቸው” በማለት መግለጫው ይከሳል።
ቅዱስ ሲኖዶሱ በዚሁ መግለጫው፤ “ከ60 ሚሊዮን ያላነሰ ተከታይ ያላትን ቤተ ክርስቲያን ክብሯንና ልዕልናዋን ዝቅ ባደረገ መልኩ የሚያስተላልፉት የተሳሳተ መረጃ፤ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ብቻ ሳይሆን አገራዊ ቀውስ ለማምጣት እየተደረገ ያለ ጥረት በመኾኑ፤ የሚመለከተው የመንግሥት አካል አስፈላጊውን ማጣራት በማድረግ፤ የጣቢያዎቹ ኃላፊዎች ከብዙኃን መገናኛ ሕግና ደንብ አኳያ በሕግ እንዲጠየቁ፤ ለወደፊቱም ከእንዲህ ዐይነት ሕገወጥ ድርጊት እንዲታቀቡ መንግሥትም በዚሁ ላይ አስፈላጊውን ውሳኔ እንዲያሳልፍልን” በማለት ጠይቋል። የቅዱስ ሲኖዶሱን ሙሉውን መግለጫ እዚህ በመጫን ማንበብ ይችላሉ። (ኢዛ)



