የሰማእታት ቀን

ዛሬ የካቲት 12 ቀን 2012 ዓ.ም. 83ኛው የሰማእታት ቀን በአዲስ አበባ ሲከበር

አብርሃም ደቦጭና ሞገስ አስገዶም የፋሺስት ጣሊያን የጦር መሪ ጄኔራል ላይ ቦንቦች የወረወሩባት ዕለት ነች

ኢዛ (ሐሙስ የካቲት ፲፪ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. February 20, 2020)፦ በ1929 ዓ.ም. ልክ በዛሬዋ ዕለት (የካቲት 12 ቀን)፤ የፋሺስት ጣሊያን የጦር መሪ ጄኔራል ሩዶልፍ ግራዚያኒ በቤተመንግሥት የአዲስ አበባን ሕዝብ ጠርቶ ንግግር ሲያደርግ፤ ኢትዮጵያ በመወረሯ ሲቃጠሉ የነበሩ ሁለት ጀግና ወጣቶች የእጅ ቦንብ በመወርወር የመግደል ሙከራ ያደረጉባት ቀን ናት። የአገራቸው ጉዳይ ያንገበገባቸው ወጣቶቹ፤ አብርሃም ደቦጭና ሞገስ አስገዶም ናቸው። ይኽ ከኾነ ዛሬ 83ኛ ዓመቱ ነው። ዕለቱም “የሰማእታት ቀን” እየተባለ ይከበራ።

ጄኔራሉ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. በገነተ ልዑል ቤተመንግሥት እንዲገኝለትና በዕለቱም ድሆችንም እመጸውታለሁ በማለት ለከተማው ነዋሪ ጥሪ አስተላለፈ። የአዲስ አበባ ነዋሪም ተገኘለትና ጄኔራሉ መደስኮር ጀመረ። ወጣቶቹ አብርሃም ደቦጭና ሞገስ አስገዶም አጋጣሚውን በመጠቀም ጄኔራል ሩዶልፍ ግራዚያኒን ለመግደው የእጅ ቦንቦችን ወረወሩ፤ ጄኔራሉንም አቆሰሉት። በቦንቡ ጥቃት አንድ የጣሊያን አብራሪ ሞተ።

ፋሽስት ጣሊያን በስፍራው የተገኙትን በሚዘገንን ሁኔታ በግፍ መጨፈጨፈ ጀመረ፤ በዚያ አላበቃም፤ መላው አዲስ አበባን አዳረሰ፤ ጨፈጨፈ። ገደለ። አረደ። በጠብመዣ፣ በሽጉጥ፣ … ሌላው ቀርቶ በአካፋና መሰሎቹ አልቀሩትም ጭፍጨፋውን ለማካሔድ። አብርሃምና ሞገስን አዲስ አበባ ውስጥ ማግኘት ያልቻለው ፋሺስት፤ ይገኙበታል ብሎ የጠረጠረበት የደብረ ሊባኖስ ድረስ በመሔድ ጭፍጨፋውን ቀጠለ። ከ30 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያንን ተሰዉ።

ፋሽስት ጣሊያን በወቅቱ አባቶቹና አያቶቹ ከ40 ዓመት በፊት (የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም.) በአጼ ምኒልክ አድዋ ላይ የቀመሱትን የሽንፈትና ውርደት ቂም ይዞ፤ ለ40 ዓመታት ሲሰናዳ ቆይቶ ነበር መስከረም 1928 ዓ.ም. ኢትዮጵያን የወረረው። ከ400 ሺህ ጦር በላይ አሰልፎ፣ በዘመናዊ የጦር መሣሪያዎችን ጨምሮ፣ ታንኮችና አውሮፕላኖችን ጭምር ታጥቆና ተደራጅቶ ነበር ወረራውን ያካሔደው። ኢትዮጵያውያን መወረራቸውን ሲያውቁ እጃቸው ላይ የነበሩትን ቆመህ ጠብቀኝ (አንድ ጥይት ብቻ ጎራሽ ጠብመንዣ)፣ ጦር፣ ጋሻና ዱላ ከኢትዮጵያዊ ወኔ ጋር ቀላቅለው፤ አገራቸውን ከወራሪ ሊያድኑ ተሰለፉ። ጦርነት ገጠሙ። አይበገሬነታቸውን አሳዩ።

ዛሬ 83ኛው የሰማእታት ቀን በተለይ በአዲስ አበባ የተከበረው፤ ስድስት ኪሎ በሚገኘው የሰማእታት መታሰቢያ ሐውልት አደባባይ ሲሆን፤ በሥነሥርዓቱ ላይ የዛሬ 83 ዓመት በፋሺስት ጣሊያን ለተጨፈጨፉትና መሥዋዕት ለኾኑት ከ30 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን የሕሊና ጸሎት ተደርጎላቸዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ