ዛሬ ሦስት ተጨማሪ ሰዎች በኮሮና መያዛቸው ተረጋገጠ
3ዲ (3D) ኮሮና ቫይረስ በምስል (© istock.com/Dr_Microbe)
በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የተያዙት ቁጥር 29 ደረሰ
ኢዛ (ረቡዕ መጋቢት ፳፫ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. April 1, 2020)፦ የጤና ሚኒስቴር ዛሬ መጋቢት 23 ቀን 2012 ዓ.ም. እንደገለጸው ከኾነ፣ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ከመረመራቸው 68 ሰዎች ውስጥ ሦስቱ በኮሮና ቫይረስ መያዛቸውን አረጋግጧል። ይህም በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የተያዙትን ቁጥር 29 አድርሶታል።
ሦስቱም ግለሰቦች ኢትዮያውያን ሲሆኑ፣ አንድ ሴትና ሁለት ወንዶቻ ናቸው። ሴትዋ የ33 ዓመት ዕድሜ ያላት ሲሆን፣ ከጉዞ ታሪኳ መረዳት እንደተቻለው ጅቡቲ፣ ብራዚል፣ ሕንድ እና ኮንጎ ብራዛቪል እንደነበረች ታውቋል።
ሁለተኛው ታማሚ የ26 ዓመት ወጣት ሲሆን፣ ከተለያዩ ተጓዥ መንገደኞች ጋር ግንኙነት ያለው እንደነበር ተረጋግጧል። ሦስተኛው ግለሰብ ደግሞ የ32 ዓመት ዕድሜ ያለው ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም ቫይረሱ ከተገኘበት ሰው ጋር ንክኪ እንደነበረው የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
ሦስቱም ግለሰቦች የበሽታው ምልክት ታይቶባቸው ስለነበር፤ በለይቶ ማቆያ ውስጥ ኾነው የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጎላቸው በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ተረጋግጧል። በአሁኑ ሰዓት እነዚህ ግለሰቦች በለይቶ ሕክምና መስጫ ማዕከል የሕክምና እርዳታ እየተደረገላቸው እንደኾነና ከእነርሱ ጋር ግንኙነት የነበራቸውን ሌሎች ሰዎች የመለይት ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ የጤና ሚኒስቴር ሪፖርት ያስረዳል። (ኢዛ)



