ምርጫው እንዳይካሔድ ተወሰነ

ምርጫው እንዳይካሔድ ተወሰነ

ምርጫው የተራዘመው በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ነው

ኢዛ (ማክሰኞ መጋቢት ፳፪ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. March 31, 2020)፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አገራዊ ምርጫውን በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ማካሔድ እንደማይችል አስታወቀ።

ቦርዱ ዛሬ መጋቢት 22 ቀን 2012 ዓ.ም. እንዳስታወቀው፤ ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ነኀሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ማካሔድ የማይችልበት ምክንያት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ በተፈጠረው ሁኔታ መኾኑን ገልጿል።

የቫይረሱን በመረዳት ቦርዱ ያወጣውን የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ በመሰረዝ፤ በሰሌዳው መሠረት መከናወን ያለባቸው ተግባራት ለጊዜው እንዲቆሙ መወሰኑን አስታውቋል። ይህንኑ አስመልክቶ ምርጫ ቦርድ ያወጣው ሙሉ መግለጫ የሚከተለውን ይመስላል። (ኢዛ)

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የምርጫ 2012 ኦፕሬሽን እቅድ እና የጊዜ ሰሌዳ ላይ የፈጠረውን ችግር ገምግሞ ያሳለፈው ውሳኔ መግለጫ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ2012 ዓ.ም የሚካሔደውን አጠቃላይ ምርጫ ለማስፈጸም የቅድመ ምርጫ ዝግጅት ሥራዎች ሲያከናውን ከቆየ በኋላ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳውን ይፋ አድርጓል።

በዚህ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ መሰረት ምርጫው ነሐሴ 23 ቀን 2012 እንዲካሔድ ተወስኖ ቦርዱ በጊዜ ሰሌዳው የተገለጹ ተግባራትን በተያዘላቸው ጊዜ እያከናወነ ለሕዝብ እያሳወቀ እንደቆየ ይታወሳል። በዚህም መሰረት በያዝነው መጋቢት ወር እና በሚያዚያ 2012 ዓ.ም መጠናቀቅ ያለባቸው በርካታ ሥራዎች አሉ። መከናወን ካለባቸው ሥራዎች ዋና ዋናዎቹ የመራጮች ምዝገባ፤ የምርጫ አስፈፃሚዎች ምልመላ፤ ሥልጠናና ስምሪት፤ የመራጮች ትምህርት፤ ለመራጮች ምዝገባ የሚያስፈልጉ ቁሳቁስ ሥርጭት የመሳሰሉት ናቸው።

እነዚህን ሥራዎች በጊዜ ሰሌዳው መሰረት ለማከናወን ቦርዱ ተገቢ ጥረት እያደረገ በሚገኝበት ወቅት ባለፉት ሳምንታት በአገራችን እና በዓለም ላይ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እንቅስቃሴዎች እንዲቋረጡ አስገድዷል። ከዚሁ የወረርሽኝ ሥጋት የተነሳ በርካታ አገራት ምርጫን ጨምሮ መንግሥታዊ እቅዶቻቸውን ለማቋረጥ ተገደዋል። በአገራችንም መንግሥት ወረርሽኙን ለመከላከል የሰዎች ግንኙነትን የመቀነስ እርምጃዎች እንዲወሰዱ በመወሰኑ የመንግሥት ሰራተኞች አብዛኛውን ሥራ ከቤት ሆነው እንዲሠሩ ተደርጓል። መንግሥት የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት የተለያዩ ጥብቅ እርምጃዎችን እየወሰደ ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪም በክልል መንግሥት መስተዳድሮች ደረጃ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ የውስጥና የአገር አቋራጭ የትራንስፓርት ገደቦች፣ የመሰብሰብ ገደቦችን የመሳሰሉ ጥብቅ ክልከላዎች ይፋ ሆነዋል።

በመንግሥት ከተላለፉ የክልከላ ውሳኔዎች በተጨማሪ ለቦርዱ ድጋፍ የሚያደርጉ ዓለምአቀፍ አጋር ድርጅቶች አብዛኞቹ ሰራተኞቻቸው ከቤት ሆነው እንዲሰሩ ሲደረጉ አንዳንዶቹ ደግሞ ጥቂቶቹን ብቻ በማስቀረት ሰራተኞቻቸው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ አድርገዋል። ከላይ የተጠቀሱት ድምር ሁኔታዎች በሚያዚያ ሊጀመር በታቀደው የመራጮች ምዝገባ እና ተያያዥ የዝግጅት ሥራዎች ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ አሳድሯል። ከዚህ የሚከተሉት ከችግሩ ማሳያ ከሚሆኑት ጥቂቶቹ ናቸው።

• በኢትዮጵያ አየር መንገድ መጋዘን የሚገኙ የምርጫ ቁሳቁሶችን የማሸግ ሥራ በሁለት ሳምንት ዘግይቷል፤
• የቀሪ ሕትመት ውጤቶች ግዥ በቫይረሱ ምክንያት በተፈጠረ የአቅርቦት ሰንሰለት መደናቀፍ ምክንያት ተጓቷል፤
• ለምርጫ አስፈፃሚዎች ሥልጠና ቁጥራቸው 1000 /አንድ ሺ/ በላይ የሚሆን አሰልጣኞችን ክክልሎች ወደ አዲስ አበባ በማምጣት የአሰልጣኞች ሥልጠና መስጠት አልተቻለም፤
• ለ 150,000 የምርጫ አስፈፃሚዎች በየክልሎቹ መሰጠት ያለበትን ሥልጠና መጀመር አልተቻለም፤
• ቦርዱ የሚሰጠው የመራጮች ትምህርት ኮቪድ 19 ቫይረስን አስመልክቶ በሚወጡ የማኅበረሰብ ጤና መልእክቶች ሊዋጡ የሚችሉበት እድል ከፍተኛ ሆኖ ተገኝቷል።

የቫይረሱ ሥጋት በቀጣዩ አገራዊ ምርጫ በአጠቃላይ በተለይም በአፋጣኝ መፈጸም ባለባቸው የመራጮች ምዝገባ፤ የምርጫ አስፈፃሚዎች ሥልጠና፤ የመራጮች ትምህርት ተግባራት አፈፃፀም ላይ ሊኖረው የሚችለውን ተፅእኖ አስመልክቶ ቦርዱ ከሕግ አውጪው አካል፤ በጉዳዩ ላይ ከሚሰሩ የጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ የማህበረሰብ ጤና ባለሞያዎች፣ ከዓለምአቀፍ አጋሮች እና ከፖለቲካ ፓርቲዎች እና ጋር ተመካክሯል።

ከፓለቲካ ፓርቲዎች ጋር በተደረገው ውይይት አብዛኞቹ ፓርቲዎች የችግሩን ግዝፈት እና በምርጫ ላይ የሚኖረውን ተጽእኖ ተገንዝበው ቦርዱ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር ተመካክሮ አማራጭ የአፈጻጸም አቅድ ሊኖረው እነደሚገባ መክረዋል።ይሁን እና በዚህ አግባብ የሚወሰደው እርምጃ ችግሩ ከሚጠይቀው በላይ የሆነ መዘናጋት እንዳያመጣ ቦርዱ በወረርሽኙ አፈጻጸማቸው የማይስተጓጎል ሥራዎችን እንዲያጠናቅቅ አሳስበዋል።

ቦርዱ ለውሳኔው መሰረት የሚሆነው የዳሰሳ ጥናት በአማካሪ ባለሙያዎቹ ተሰርቶ እንዲቀርብለትም አድርጓል። የተፈጠረው አጠቃላይ ሁኔታ ከታቀደው የምርጫ ምዝገባና ቀጣይ እርምጃዎች ላይ ሊያሳድር የሚችለውን ተፅዕኖ ባግባቡ ለመዳሰስ ያስችለው ዘንድ በዳሰሳ ጥናቱ ላይ ተመስርቶ ቦርዱ ሁለት የቢሆን ሁኔታ ግምቶች (scenarios) ተመልክቷል።

የመጀመሪያው የቢሆን ሁኔታ ግምት መሰረት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመግታት በኢትዮጵያ መንግሥት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ለአራት ሳምንት ብቻ ማለትም እስከ ሚያዚያ 7 ሊቆይ ይችላል በሚል ግምት ላይ የተመሰረተ ነው። ክልከላው የአራት ሳምንት ብቻ የሚቆይ ከሆነ አሁን ባለው የጊዜ ሰሌዳ ዋና የሆነውን የመራጮች ምዝገባ ቢያንስ በአራት ሳምንት የሚገፋው ሲሆን፣ ምዝገባው ቢከናወን የማህበረሰቡ ተሳትፎ፣ የምርጫው ተአማኒነት ማግኘትን እና የኦፕሬሽን ድጋፍ የሚያደርጉ ተቋማት ድጋፍን ሙሉ ለሙሉ ማግኘትን በጣም አስቸጋሪ መሆኑን ያሳያል።

ቫይረሱ በቁጥጥር ስር ካልዋለም የመራጮች ምዝገባን ማካሄድ የማኅበረሰብ ደኅንነትን አደጋ ውስጥ የሚጥል ከመሆኑም በተጨማሪ ከማህበረሰብ የጤና ደህንነት ከመጠበቅ አንጻር ጥቂት እንኳን ክልከላዎች የሚኖሩ ከሆነ ይህንን እቅድ ወደ ተግባር መለወጥ አስቸጋሪ ያደርገዋል።

በተጨማሪም በያዝነው ሳምንት መንግሥት ተጨማሪ እርምጃ እየወሰደ መቀጠሉ፣ እንዲሁም ቦርዱ ከጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሙያዎች ጋር ባደረገው ውይይት እስከ ሚያዚያ መጨረሻም ሁኔታው የመሻሻል ዕድል እንደሌለ የተገለጸለት በመሆኑ፣ በዚህ የቢሆን ሁኔታ ግምት በታየው መልኩ የመራጮች ምዝገባን በተያዘለት ጊዜ ማከናወን እንደማይቻል ቦርዱ መረዳት ችሏል።

የዳሰሳ ጥናቱ ሁለተኛ የቢሆን ሁኔታ ግምት የሚያሳየው ወረርሽኙን ለመቆጣጠር መንግሥት የሚወስዳቸው እርምጃዎች ከሚያዚያ 7 ቀን 2012 ዓ.ም በኋላ ላልተወሰነ ጊዜ ሊቆዩ ይችላሉ፤ በመሆኑም በመንግሥት የሚደረግ ማንኛውም ከአራት ሳምነት የበለጠ ክልከላ ቢኖር ምርጫውን በተያዘለት ሕገመንግሥታዊ የጊዜ ሰሌዳ ማከናወን እንዳይቻል ያደርገዋል፤ ስለዚህም ወረርሽኙን መቆጣጠር በሚቻል ጊዜ ቦርዱ እቅዶቹ ላይ የተለያዩ ማሻሻያ ሊደርግ ይገባል የሚል ነው።

በመሆኑም ቦርዱ እነዚህን የቢሆን ሁኔታ ግምቶች መርምሮ እንዲሁም ከባለድርሻ አካላት ጋር ካደረጋቸው ምክከሮች ያገኘውን ግብአት ታሳቢ በማድረግ የሚከተለውን ወስኗል።

1. በተፈጠረው ሁኔታ የተነሳ ቦርዱ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ምርጫውን ማካሔድ የማይቻለው መሆኑን በመረዳት ያወጣውን የጊዜ ሰሌዳ በመሰረዝ በሰሌዳው መሰረት መከናወን ያለባቸው ተግባራት ለጊዜው እንዲቆሙ ወስኗል፤

2. ቦርዱ የወረርሽኙ ሥጋት ተወግዶ ሁኔታዎች ሲመቻቹ እንደገና ግምገማ በማድረግ አዲስ የምርጫ ኦፕሬሽን እቅድና ሰሌዳ በማውጣት እንቅስቀሴውን የሚያስጀምር ይሆናል፤

3. ቦርዱ ባደረጋቸው ምክክሮችና የዳሰሳ ጥናት ላይ በግልጽ የተለዩ፣ በኮቪድ 19 የማይስተጓጎሉ፣ የቦርዱን የምርጫ አፈጻጸም ዝግጁነት የሚጨምሩ፣ ሁኔታው ተቀይሮ ተቋሙ ወደ መደበኛ ተግባሩ ሲመለስ በተገቢው ሁኔታ ምርጫን ለማስፈጸም የሚያሥችል ሁኔታን የሚፈጥሩ ተግባራትን እያከናወነ መቆየት እንዳለበት ወስኗል።

4. በሕገ መንግሥቱ በተቀመጠው መሠረት በሥራ ላይ የሚገኘው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥልጣን ጊዜው ከሚያበቃበት አንድ ወር አስቀድሞ ቦርዱ አጠቃላይ ምርጫውን ማድረግ የማይችል መሆኑን ም/ቤቱ ተገንዝቦ፣ ከዚህ አንጻር የሚሠጠው ውሳኔ ቢኖር ለመነሻነት ያገለግለው ዘንድ ይህ ውሳኔ እንዲሁም ቦርዱ ያደረገው የዳሰሳ ጥናት ሰነድ ለሕዝብ ተወካዮች እንዲተላለፍለት ወስኗል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
መጋቢት 22 ቀን 2012 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ