በኢትዮጵያ በ27ኛው ቀን የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር 55 ደርሷል
በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ የሁኔታ መግለጫ (መጋቢት 30 ቀን 2012 ዓ.ም.፤ በጤና ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተዘጋጀ)
በአማካኝ በቀን ሁለት በቫይረሱ የተያዘ ሰው ሪፖርት እየተደረገ ነው
ኢዛ (ረቡዕ መጋቢት ፴ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. April 8, 2020)፦ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የኮሮና ቫይረስ የተጠቃ ሰው ሪፖርት ከተደረገበት ከመጋቢት 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ባላፉት 27 ቀናት በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር 55 ደርሷል።
ጤና ሚኒስቴር ዛሬ መጋቢት 30 ቀን ይፋ እንዳደረገው፤ በዛሬው ዕለት አዳዲስ ሦስት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች በመገኘታቸው፤ ትናንት 52 የነበረውን ቁጥር ወደ 55 አሳድጎታል።
በጤና ሚኒስቴር መረጃ ባለፉት 24 ሰዓታት 225 ሰዎች የላቦራቶሪ ምርመራ ተደጎላቸው ሦስቱ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ ሁለቱ የውጭ ጉዞ የነበራቸው ናቸው ተብሏል። አንደኛው የውጭ ጉዞ የሌለው ግለሰብ የ36 ዓመት ዕድሜ ያለውና በአማራ ክልል አዊ ዞን አዲስ ቅዳም ነዋሪ ነው። ሁለቱ ደግሞ ከዱባይ ተመልሰው በለይቶ ማቆያ የነበሩ የ29 ዓመት ዕድሜ ያላቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ናቸው።
ዛሬ ላይ 55 የደረሰው በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር የተገኘው፤ ለ2496 ሰዎች የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጎ ነው። (ኢዛ)



