ሁለት ታዳጊዎችን ጨምሮ ስምንት በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ሰዎች ተገኙ
በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ የሁኔታ መግለጫ (ማክሰኞ ሚያዝያ 6 ቀን 2012 ዓ.ም.፤ በጤና ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተዘጋጀ)
በቫይረሱ የተያዙት ቁጥር 82 ደረሰ
ኢዛ (ማክሰኞ ሚያዝያ ፮ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. April 14, 2020)፦ በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጠ ሰዎች ቁጥር 82 መድረሱን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ እንዳስታወቀው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 82 የደረሰው ባላፉት 24 ሰዓታት ከተመረመሩት 447 ሰዎች ስምንቱ አዳዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች በመገኘታቸው ነው።
ዛሬ ማክሰኞ ሚያዝያ 6 ቀን 2012 ዓ.ም. በተደረገው ሪፖርት ከስምንቱ በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች መካከል የ14 እና 16 ዓመት ሴት ታዳጊዎች ይገኙበታል።
ከስምንቱ ውስጥ የ14 እና የ16 ዓመት ታዳጊዎችን ጨምሮ አምስቱ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ኤርትራዊ፣ እንግሊዛዊና ሱማሊያዊ ናቸው።
ሦስቱ ኢትዮጵያውያን ከቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት የነበራቸው ናቸው። አንድ የ40 ዓመት ጎልማሳ ደግሞ የውጭ አገር የጉዞ ታሪክ የሌለው ሲሆን፣ በቫይረሱ የተያዘው ከሥራው ባሕርይ ጋር በተያያዘ ነው ተብሏል። ቀሪዎቹ አራቱ ደግሞ የውጭ ጉዞ ታሪክ የነበራቸው ናቸው።
እስከዛሬ ባለው መረጃ 4557 የላቦራቶሪ ምርመራ የተደረገ ሲሆን፣ 63 በለይቶ ማቆያ ሕክምና እየተደረገላቸው ነው። 14ቱ ደግሞ ያገገሙ መኾናቸው ታውቋል። ሁለቱ በቫይረሱ የተያዙ ጃፓናውያን ወደ አገራቸው የተመለሱ ሲሆን፤ ሦስቱ መሞታቸው ይታወቃል። (ኢዛ)



