የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ ግዴታ መኾኑን የሚደነግግ መመሪያ ጸደቀ
የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ)
መመሪያው ከዛሬ ጀምሮ በሥራ ላይ ውሏል
ኢዛ (ረቡዕ ግንቦት ፲፱ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. May 27, 2020)፦ በኢትዮጵያ በተለይም በአዲስ አበባ በኮሮና ቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ከቤት ውጭ በማንኛውም ቦታዎች የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ ግዴታ መኾኑን የሚደነግግ መመሪያ ጸደቀ። መመሪያው ከዛሬ ጀምሮ በሥራ ላይ ውሏል።
ይህንን ያሳወቁት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፤ ቸልተኝነት ዋጋ እያስከፈለ በመኾኑ፤ ሕጉን ማጥበቅ አስፈላጊ መኾኑን በመጥቀስ፤ ከቤት ውጭ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ) ማድረግ ግዴታ መኾኑን የሚደነግግ ሕግ መጽደቁን አሳውቀዋል።
ወ/ሮ አዳነች መረጃውን ባሳወቁበት ወቅት፤ ከሌላው መማር ብልህነት ነው በማለት በኮሮና ቫይረስ ብራዚል ውስጥ የነበረው መዘናጋትና ቸልተኝነት፣ የተላለፉትን ደንብና መመሪያዎችን አለማክበር፤ ዛሬ ብራዚልን ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈለ ነው ብለዋል።
“እኛም ሕጎችን ማጥበቅ ግድ ብሎናል” ያሉት ወይዘሮ አዳነች፤ ስለዚህ ከዛሬ ረቡዕ ግንቦት 19 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ማስክ ከቤት ውጭ ሁሉም ቦታዎች ማድረግ ግዴታ የሚጥል መመሪያ አጽድቀናል በማለት ገልጸዋል። (ኢዛ)



