በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ጤና ኮሌጅ በማዕረግ ተመራቂዋ ወጣት ላይ የተፈጸመው አሰቃቂ ግድያ
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን
የተለያየ የሰውነት ክፍሏን በአሰቃቂ ሁኔታ በስለት ተወግታ ነው የተገደለችው
ኢዛ (ረቡዕ ግንቦት ፲፱ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. May 27, 2020)፦ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የጤና ኮሌጅ የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪ ወጣት በቤተ ሙከራ ውስጥ በስለት ተወግታ ሕይወቷ እንዳለፈ ገለጸ።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ዛሬ ግንቦት 19 ቀን 2012 ዓ.ም. እንዳስታወቀው የጤና ኮሌጁ የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪ የኾነችው ሃይማኖት በዳዳ ሰኞ ግንቦት 17 ቀን 2012 ዓ.ም. በኮሌጁ አስተዳደር ሕንፃ ላይ በሚገኘው ቤተሙከራ ክፍል ለምርምር በገባችበት ወቅት ስለመገደሏ ይጠቅሳል።
የግድያው ሁኔታም የተለያየ የሰውነት ክፍሏን በአሰቃቂ ሁኔታ በስለት ተወግታ እንደኾነና የወጣቷ አስክሬንም ትናንት ግንቦት 18 ቀን 2012 ዓ.ም. መገኘቱንም የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልጿል። እንደ ፖሊስ የዛሬው መግለጫ የሟች ሞባይልና ሌሎች ዕቃዎችም ስለመወሰዳቸው በምርመራ ማረጋገጡንም አስታውቋል።
መግለጫው እስከመጣበት ጊዜ ድረስም ፖሊስ አራት ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር በማድረግ ምርመራ መጀመሩንም አስታውቋል።
ሟች የመጀመሪያ ዲግሪዋን ከቴፒ ዩኒቨርሲቲ በማዕረግ ተመርቃ፤ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ስታገለግል የቆየችና በኋላም ለሁለተኛ ዲግሪዋ ወደ ጥቁር አንበሳ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተልካ፤ ትምህርቷን ስትከታተል እንደቆየችም መረጃው ያስረዳል።
ፖሊስ የዚህን ወንጀል ፈፃሚ ለመያዝ ምርመራውን አጠናክሬ እያካሔድኩ ነውም ብሏል። (ኢዛ)



