አሳዛኙ ሞት ኮሮና አለብኝ ብላ ራስዋን ያጠፋችው ኢትዮጵያዊ ነፃ ኾነች
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
ወርቅነሽ ዲባባ የ25 ዓመት ወጣት ነበረች
ኢዛ (ማክሰኞ ግንቦት ፳፭ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. June 2, 2020)፦ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አሳዛኝ የሚባሉ አጋጣሚዎች እየተስተናገዱ ነው። በኢትዮጵያ የቫይረሱ መከሰት ከተሰማበት ጊዜ ወዲህ አስገራሚ፣ አስጨናቂና ያልተጠበቁ ተግባራት ሲፈጸሙም ታይተዋል። በአርባ ምንጭ በቫይረሱ የተጠረጠረች የ25 ዓመት ወጣት ራስዋን ያጠፋች ሲሆን፤ በተደረገው ምርመራ ከቫይረሱ ነፃ መኾኗ ታውቋል።
በቫይረሱ የተጠረጠረ ሰው ከማቆያ ቦታ አምልጦ በብዙ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ስለመያዙ የተሰማው ዜና በአስገራሚነቱ የምናስታውሰው ነው። ይህ ያመለጠ ሰው ግን ሲመረመር ነፃ ኾኗል። እንደዚሁ ዜና ሁሉ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የቫይረሱ ተጠቂ ኾኖ ከተመዘገበው ጃፓናዊ ጋር ግንኙነት የነበራቸው የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ኃላፊም ራሳቸውን አግልለው ከቆዩ በኋላ፤ ነፃ መባላቸውም በተለየ የምናየው ዜና ነበር።
ባለፈው ሰሞን ደግሞ በለይቶ ማቆያ በኋላም ቫይረሱ የተገኘባት ነፍሰጡር ኢትዮጵያዊት፤ ልጇን በሰላም ብትገላገልም በሕይወት የቆየችው ከሁለት ቀን ያልበለጠ ጊዜ ነበር። እርሷ አለፈች ልጇ በሕይወት አለ።
ሦስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እንዲህ ያሉ ዜናዎች ሰምተናል። ዛሬ ግን ከወደ አርባ ምንጭ የተሰማው ዜና በእጅጉ የሚያሳዝን ነው ሊባል ይችላል። የከተማው ፖሊስ እንደገለጸው አንዲት በኮሮና ቫይረስ የተጠረጠረች ሴት ራስዋን ማጥፋትዋን ነው። ዜናውን መራር የሚያደርገው ግን በቫይረሱ የተጠረጠረችው ሴት ሕይወቷ ካለፈ በኋላ የተደረገላት ምርመራ ከቫይረሱ ነፃ መኾንዋን የሚያመለክት መኾኑን ነው።
ወርቅነሽ ዲባባ የተባለችው የ25 ዓመት ወጣት ራስዋን ያጠፋችው ባለፈው ዓርብ የሙቀት ልኬት ከተደረገላትና በለይቶ ማቆያ እንድትኾን ከተደረገ በኋላ መኾኑን የአርባ ምንጭ ፖሊስ አስታውቋል።
የምርመራ ውጤቷ እስኪመጣ በለይቶ ማቆያው ልትቆይ የምትችለው ለአንድ ቀን ብቻ ስለመኾኑ ተገልጾላት እንደነበርም፤ በጉዳዩ ላይ የተሠራጨው ዘገባ ያመለክታል።
በተለይ የጀርመን ሬዲዮ የአርባ ምንጭን ፖሊስ እና የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የለይቶ ማቆያ ኃላፊዎችን አናግሮ እንደዘገበው፤ በዩኒቨርሲቲው የለይቶ ማቆያ በተሰጡት አንድ ክፍል ውስጥ ቀኑን ሙሉ በሰላም አሳልፋ እንደነበረ ያመለክታል።
ኾኖም የሕክምና ባለሙያዎች በማግስቱ ቅኝት ሲያደርጉ አንድ ሰው መጉደሉን ሪፖርት ያደርጋሉ። የወርቅነሽ ክፍልም ሲገባ ሞታ ተገኝታለች። የፖሊስ ሪፖርት እንዳረጋገጠውም ወርቅነሽ ራስዋን አጥፍታለች። የጤና ባለሙያዎቹ ምርመራ ደግሞ ወርቅነሽ በፍራቻ ራስዋን ያጠፋችበት ወረርሽኝ ተጠቂ ያለመኾኗን ነው። ከቫይረሱ ነፃ ነበረች። ወርቅነሽ ግን በለበሰችው ሻርፕ ራስዋን ሰቅላ ተገኘች። (ኢዛ)



