በኢትዮጵያ በአንድ ቀን በኮሮና ቫይረስ ሦስት ሰዎች ሞቱ
በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ የሁኔታ መግለጫ (እሁድ ግንቦት 23 ቀን 2012 ዓ.ም.፤ በጤና ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተዘጋጀ)
109 አዲስ ተጠቂዎች ተገኝተዋል
የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር 1,172 ደርሷል
ኢዛ (እሁድ ግንቦት ፳፫ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. May 31, 2020)፦ በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በአንድ ቀን ሦስት ሰዎች ሲሞቱ፤ 109 የሚኾኑ አዲስ ተጠቂዎች ተገኙ።
ዛሬ ይፋ በተደረገው የጤና ሚኒስቴር ሪፖርት ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ የሞቱት ሦስት ሰዎች የ29፣ የ55 እና የ75 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ናቸው።
በኢትዮጵያ በአንድ ቀን ሦስት ሞት የተመዘገበበት የመጀመሪያው ቀን ሲሆን፤ አጠቃላይ በቫይረሱ የሞቱትን ሰዎች ቁጥር 11 አድርሶታል።
በዛሬው የጤና ሚኒስቴር ሪፖርት 109 አዳዲስ የቫይረሱ ተጠቂዎች የተገኙት ለ2,836 ሰዎች የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጎ ነው። ከ109ኙ ተጠቂዎች ውስጥ 94ቱ የውጭ ጉዞ ታሪክ እና ከበሽታው ጋር የታወቀ ግንኙነት የሌላቸው ናቸው። 13ቱ በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር የታወቀ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን፤ ሁለቱ ግን የውጭ የጉዞ ታሪክ ያላቸው ናቸው ተብሏል። በሪፖርቱ መሠረት ዛሬ ከተገኙት አዳዲስ ተጠቂዎች 99ኙ ከአዲስ አበባ ናቸው።
በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር አንድ ሺህ ተሻግሮ 1,172 ደርሷል። (ኢዛ)



