በኢትዮጵያ በአንድ ቀን ከ1000 በላይ የኮሮና ተጠቂዎች ተገኙ
በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ የሁኔታ መግለጫ (ሐሙስ ነኀሴ 7 ቀን 2012 ዓ.ም.)
የሟቾች ቁጥር 479 ደረሰ፤ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ 23,038 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል
ኢዛ (ሐሙስ ነኀሴ ፯ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. August 13, 2020)፦ በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ መከሰቱ ከተሰማበት ጊዜ ወዲህ በከፍተኛ ቁጥር ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች በዛሬው ዕለት ሪፖርት ተደረገ።
ከወትሮው ለየት ብሎ የዕለታዊ ሪፖርቱ ከምሽት በኋላ የተገለጸ ሲሆን፤ በሪፖርቱ መሠረተ በ24 ሰዓታት ውስጥ 1,086 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸውን ነው። ይህም በኢትዮጵያ በ24 ሰዓታት ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተጠቂዎች የተገኙበት ኾኖ ተመዝግቧል።
እንደ ጤና ሚኒስቴር መረጃ 1,086 ተጠቂዎች የተገኙት፤ 14,688 ሰዎች የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጎላቸው ነው።
በዛሬው መረጃ መሠረት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር 26 ሺህ 204 መድረሱ ተረጋግጧል። በአንጻሩ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 11 ሺህ 428 መድረሱ ታውቋል።
በቫይረሱ ተጠቅተው ስለሞቱ ሰዎች ቁጥር የሚያመለክተው መረጃ፤ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ 16 ሰዎች ሞተዋል። ይኽም በቫይረሱ ተጠቅተው የሞቱ ሰዎችን ቁጥር ወደ 479 አሳድጎታል።
ከሰሞኑ እየወጡ ካሉ መረጃዎች መረዳት እንደተቻለው፤ በተለይ በትግራይ ክልል የኮሮና ሥርጭት እየሰፋ ከመምጣቱም በላይ፤ በክልሉ እስካሁን 35 የጤና ባለሙያዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን፤ አንድ የሕክምና ዶክተር ሕይወቱ ማለፉ ታውቋል።
ልክ የዛሬ ሁለት ወር ግንቦት 6 ቀን 2012 ዓ.ም. በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙት ጠቅላላ ቁጥር 3,166 የነበረ ሲሆን፤ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ተጨማሪ 23,038 ሰዎች በመገኘታቸው የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ዛሬ 26,204 ደርሷል። በተመሳሳይ የዛሬ ሁለት ወር የሟቾች ቁጥር 55 የነበረ ሲሆን፤ ተጨማሪ 424 ሰዎች በመሞታቸው በዛሬው ዕለት የጠቅላላ ሟቾች ቁጥር 479 ኾኗል። በአንጻራዊነት 495 ሰዎች የዛሬ ሁለት ወር አገግመው የነበረ ሲኾን፤ ተጨማሪ 10,933 ሰዎች በማገገማቸው ጠቅላላ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር ዛሬ 11,428 ደርሷል።
በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር 23,038 መኾኑ፤ እንዲሁም ያገገሙት ሰዎች ቁጥር 11,428 ከመኾኑ አንጻር ከሚያገግሙት ሰዎች በበለጠ ሁኔታ በቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር እየጨመረ መሔዱን ለመረዳት ይቻላል። ለዚህ ዘገባ ሲባል የኢትዮጵያ ዛሬ ዘጋቢ ለንጽጽር የተጠቀመው ከጁን 13 ቀን እስከ ኦገስት 13 ቀን 2020 እ.ኤ.አ ሲሆን፤ ጠቅላላ የቀናቱ ቁጥር 60 መኾኑን ልብ ይሏል። (ኢዛ)



