ትራንስ ኢትዮጵያ መጋዘኖች ታሽገዋል
ትራንስ ኢትዮጵያ እና ሕወሓት
ሠራተኞች ሥጋት ላይ ናቸው
ኢዛ (ሐሙስ ነኀሴ ፯ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. August 13, 2020)፦ በሕወሓት ከሚመራው ከኤፈርት ኩባንያዎች መካከል አንዱ የኾነው “ትራንስ ኢትዮጵያ” በአዲስ አበባና ከአዲስ አበባ ውጭ ያሉ መጋዘኖች ስለመታሸጋቸው ተሰማ። ሠራተኞች ሥጋት ላይ ናቸውም ተብሏል።
እንደ ኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገለጻ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ በተለየ የተሽከርካሪ ጐማዎችን በመነገድ ቀዳሚ ከሚባሉት አንዱ ነው የተባለው ትራንስ ኢትዮጵያ ለመጋዘን አገልግሎት ከሚጠቀምባቸው ውስጥ እስካሁን ሦስት የሚኾኑት ታሽገዋል።
በእነዚህ መጋዘኖች ውስጥ ተቀምጠው የነበሩ የተሽከርካሪ ጐማዎችን በመጫን ወዳልታወቀ ቦታ ለማጓጓዝ የተደረጉ ሙከራዎች ስለተደረሰባቸው መጋዘኖቹ እንደታሸጉና ተጭነው ሊወሰዱ ነበሩ የተባሉ ጐማዎች እና ሌሎች ንብረቶች እንዲመለሱ መደረጉንም ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ገልጸዋል።
ትራንስ ኢትዮጵያ በኢትዮጵያ ውስጥ በብዛት አገልግሎት ላይ ይውላሉ የተባሉትን እንደ ማጄላይ ያሉ የጐማ ምርቶችን በማስመጣት የሚያከፋፍል ሲሆን፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ከተለመደው የንግድ እንቅስቃሴ ወጣ ብሎ በእጁ ያሉ ጐማዎችን እና ሌሎች ንብረቶችን እያሸሸ ነው ተብሏል።
ድርጅቱ ሥራውን በማቀዛቀዝ በእጁ ያለ የጐማ ምርቶችንና ሌሎች ንብረቶችን በኮንቴይነር ጭምር በመጫን ወደ አልታወቀ ቦታ እየተጓጓዘ ከመኾኑ ጋር ተያይዞ የድርጅቱ መጋዘኖች እንዲታሸጉ ተደርጓል። መጋዘኑና ዋና መሥሪያ ቤቱም ጥበቃ ላይ ሲሆን፤ የድርጅቱ ኃላፊዎችም በሥራ ገበታ ላይ እንደሌሉ ተነግሯል። ይህም በተለይ በአዲስ አበባ ያሉ ሠራተኞችን ሥጋት ላይ በመጣሉ ቀጣይ ዕጣ ፈንታቸው እያሳሰባቸው ነው። (ኢዛ)



