Prof. Mesfin Woldemariam

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም

በርካቶች ኀዘናቸውን እየገለጹ ይገኛሉ

ኢዛ (ረቡዕ መስከረም ፳ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. September 30, 2020)፦ እውቁ ምሁርና የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በ91 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

ዛሬ ማለዳ ሕልፈተ ዜናቸውን የተመለከተው ዜና ከተሰማ በኋላ ኢትዮጵያውያን ኀዘናቸውን እየገለጹ ናቸው። አብዛኛው የመገናኛ ብዙኀንም በዚህ ዜና እረፍት ጊዜ ሰጥተው እየዘገቡ ሲሆን፣ ፕሮፌሰሩ ይታወቁበት የነበሩ ሥራዎችን እያስታወሱም ነው።

የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምን ዜና እረፍት ተከትሎ ዜጐች በተለያየ መንገድ ኀዘናቸውን እየገለጹ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይም በፕሮፌሰር መስፍን ሞት የተሰማቸውን ኀዘን ከገለጹት መካከል ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር መስፍንን ሲገልጹ “የሐሳብ ልዕልና ምልክት፣ የሰላማዊ ትግል አርኣያ ላመኑበት ነገር እስከመጨረሻው ሞጋች፣ ላመኑበት እውነት ብቻ የሚቆሙ” ብለዋቸዋል።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት በበኩላቸው ፕሮፌሰር መስፍንን ትልቅ የእውቀት አባት ስለመኾናቸው ጠቅሰው፤ ቁርጠኛ የሰላማዊ ታጋይ፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋች እና ላመኑበት ጉዳይ ማንኛውንም መሥዋእትነት ለመክፈል ወደኋላ የማይሉ የጽናትና የአዲሱ ትውልድ አርኣያ መኾናቸውን ገልጸዋል።

ከፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በረጅሙ የሕይወት ዘመናቸው እርሳቸው ባመኑበትና ለአገራቸው ይበጃል ብለው ባሰቡበት መንገድ ሲሠሩ እንደነበር በመጥቀስ ኀዘኑን የገለጸው ደግሞ አብን ነው።

በብዙዎች ዘንድ በድፍረታቸው እንዲሁም የተሰማቸውን የመሸማቀቅ በመግለጽ የሚታወቁት ፕሮፌሰር መስፍን ዛሬ ማለዳ ሕልፈተ ሕይወታቸው ሲሰማ ታዋቂ ሰዎች፣ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችና ሌሎችም የሕብረተሰብ ክፍሎች ቀዳሚ አስተያየታቸው የፕሮፌሰር መስፍን ደፋርነት የሚያመለክቱ ነበሩ።

ከዩኒቨርሲቲ መምህርነታቸው ጀምሮ በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ትልቅ አበርክቶ የነበራቸው ፕሮፌሰር መስፍን፤ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል ውስጥ አሻራም ያሳረፉ ናቸው። እንደ ምሳሌ የሚጠቀሰው ቅንጅት የተባለው ፓርቲ እንዲወለድ የእርሳቸው ድርሻ የጎላ ነበር።

ከሰብአዊ መብት ጋር ተያይዞም በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የኾነውን የሰብአዊ መብት ተቋም (ኢሰመጉ) በመፍጠርና በመምራት በዚህም ተቋም የዜጎችን የሰብአዊ መብት ጥሰት በማጋለጥ ያበረከቱትም አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። ፕሮፌሰሩ ደራሲም መምህርም ኾነው በረዥሙ ዕድሜያቸው ብዙ ሠርተዋል። እስከ ሕልፈተ ሕይወታቸው ድረስ ከሕመማቸው እየታገሉ ስለ አገር፣ ስለ ኢትዮጵያዊነትና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ያለማቋረጥ ስሜታቸውን ሲገልጹ ነበር።

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም የአንድ ልጅ አባት ናቸው። ፕሮፌሰር መስፍን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ የለውጡን ሒደት የሚያወድሱ ጽሑፎቻቸውን በፌስ ቡክ ገጻቸው ከማስፈር ባለፈ፤ ያዩትንም ህፀፅ በተመሳሳይ ሲያሰፍሩም ነበር። በሕመም ላይ እያሉም ጭምር በመስከረም 2013 ከገባ በኋላ አልጋቸው ላይ ኾነው ከጻፉአቸው የመጨረሻ ሁለት ጽሑፎች የሚከተሉት ነበሩ። (ኢዛ)

ደብረ ማርቆስ - አርኣያ

(መስፍን ወልደማርያም፣ መስከረም 2013 ዓ.ም.)

ደብረ ማርቆስን ያየሁት በ1944 ክረምት ላይ ነበረ፤ ገና በጎረምሳነቴ በእቴጌ መነን ትምህርት ቤት አንድ ዓመት አስተምሬ በክረምቱ መሔጃ አልነበረኝም፤ አንድ ጓደኛዬ የደብረ ማርቆስ ልጅ ነበረና ጋበዘኝ። ለእኔ አዲስ አበባ ተወልጄ ላደግሁትና ከአዲስ አበባ ወጥቼ ለማላውቀው በጭነት መኪና ላይ ተጭኜ ድልድይ ያልነበረበትን የዓባይ ወንዝ ተሻግሬ የጎጃምን ትንሽ መንደር ማየቴ ትልቅ ነገር ነበር። ያኔ ቋንቋቸውም ልዩ ነበር፤ መግባባት ችግር ነበረ፤ ስለዚህ ከአዲስ አበባ ውጭ ደብረ ማርቆስ የመጀመሪያ “ውጭ አገሬ” ነበር፤ ተገድጄ በመጀመሪያ ደረቅ ጠጅ የጠጣሁትም እዚያው ነበረ።

እውነት ይሁን አይሁን እርግጠኛ አይደለሁም፤ ተኝቼ ቲቪው ሲያወራ የሰማሁት ነገር በጣም አስደሰተኝ። የደብረ ማርቆስ ነዋሪ እየተባበረ መንገድ ይሠራል፤ ለተለያዩ የሕዝብ አገልግሎት የሚውሉ ቤቶችን ይሠራል፤ የመንግሥት ወይም የበጎ አድራጎት ድርጅትን እጅ ወይም ምጽዋት ሳይጠብቅ ነዋሪው ያለውን እንደ ችሎታው እያዋጣ ለችግሩ መፍትሔ ይፈጥራል። ይህ በእውን ይሁን በሕልሜ ያላረጋገጥኩት ነገር፤ በኢትዮጵያ በሙሉ የሚፈጸም ቢኾን ብዙዎቹ የኢትዮጵያ ችግሮች ይፈቱ ነበር፤ እውን አርኣያ ያድርገው።

 

የዐቢይ አሕመድ የይቅርታ መርኅ

(መስፍን ወልደ ማርያም፣ መስከረም 2013 ዓ.ም)

በመስከረም 2 ተወልደ በየነ በኢጣልያ ኤምባሲ የሙጢኝ ስላሉት የደርግ አባሎች ሲናገር ሰማሁና የይቅርታው መርኅ ትዝ አለኝ። ጓደኞቻቸው ቃሊቲ ገብተው ፍርድ ቤት ቀርበው በመጨረሻ ቅጣታቸውን ጨርሰው ተፈቱ።

በኤምባሲ ውስጥ የሙጢኝ ያሉት አልተቀጡም? አንደኛ የቅጣት ወጉ አልተፈጸመም፤ ሁለተኛ እልሃችንንና ቂማችንን ለመወጣት ካልፈለግን በቀር በኢጣልያ ኤምባሲ ግቢ ውስጥ ተዘግቶበት መኖር ከቃሊቲ (እኔም አውቀዋለሁ!) የበለጠ እንጂ የተሻለ አይደለም። ወዳጅ-ዘመድ የማይጠይቅበት ሁኔታ ውስጥ ለብዙ ዓመታት መቆየት እንደ ከባድ እስር የሚቆጠር ይመስለኛል። ታዲያ የምሕረቱ ወሬ የት ገባ! ሌላ ቢቀር መነጋገር ያልተቻለው ለምንድን ነው?

ከኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ዝግጅት ክፍል፤

የኢትዮጵያ ዛሬ ዝግጅት ክፍል ለቤተሰቦቻቸው፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው፣ እንዲሁም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መጽናናት ይመኛል። ፈጣሪ የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምን ነፍስ በገነት ያኑራት!

ወለላዬ (ገጣሚ ማትያስ ከተማ) “ማዕረግ እንስጣቸው” በሚል ርዕስ ለፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም 86ኛ ዓመት መታሰቢያ የጻፈው ግጥም የእኔ ሽበት በሚለው መጽሐፉ ያካተተው ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ላይ ሚያዝያ 19 ቀን 2008 ዓ.ም. (ኤፕሪል 27፣ 2016 እ.ኤ.አ.) ታትሞ ነበር። እነኾ ግጥሙ!

ማዕረግ እንስጣቸው (ወለላዬ)

(ግጥሙን በፒ.ዲ.ኤፍ. አስነብበኝ!)

ሰው በሕይወት ሳለ መቼም ማድነቅ አንወድ

ማሻሻል አለብን ይሄን ነገር የግድ

እኚህ ጠንካራ ሰው ፕሮፌሰር መስፍን

ለራሳቸው ቢኾን የለፉት እስካሁን

ሀብት ከሥልጣን ጋር በእጃቸው ጨብጠው

በታዩ ነበረ ከሁሉ ሰው በልጠው

ነገር ግን እኚህ ሰው ለአገር ሲለፉ

ምንም ሳይኖራቸው ዕድሜአቸውን ገፉ

ኾኖም እንደሳቸው ከሕሊናው አድሮ

መኖር ክብር አለው እየበሉ ሽሮ

ጥንትም ኾነ አሁን በተሳሳተ አገር

መቼም ድኖ አያውቅም አዋቂ ከችግር

ገዢን የማይፈሩት በዕድሜ ዘመናቸው

እኮ ለምንድነው ብለውም ቢሏችሁ

ሕሊናው የጸዳ ያልፈጸመ በደል

እስከዛሬ ድረስ መቼ ፈርቶ ያውቃል

ብላችሁ መልሱ ይሔን ተናገሩ

ሌላ ምንም አይደል አትጠራጠሩ

እኚህን ታላቅ ሰው እንያዛቸው በወግ

በዕድሜ ዘመናቸው ክብርን አንንፈግ

የሳቸው ብቸኛ ሕዝብ ነው ሿሚያቸው

ማዕረጋቸው ላይ ማዕረግ እንስጣቸው

******

ለፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም 86ኛ የልደት በዓል መታሰቢያ የተጻፈ

ለፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም 86ኛ የልደት በዓል መታሰቢያ የተጻፈ
ማዕረግ እንስጣቸው (ወለላዬ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ