20210302 adwa

መስፍን ወልደማርያም (ፕ/ር) ጥር 2000

Prof. Mesfin Woldemariamአሜሪካ ጉድ ፈልቶበታል! አሜሪካ በነቡሹም ቢሆን የታወቀ የነፃነት አገር ነው፤ ይህንን እውነት ሊክዱ የሚዳዳቸው ሰዎች በተለይም አምባ-ገነኖች ሞልተዋል። ነጻነት መንታ መልኮችና ባሕርዮች አሉት፤ በአንድ በኩል በጎና ሰላማዊ፣ ሥራንና ሀብትን ፈጣሪ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ እኩይና ቀጣፊ፣ የሌላውን ሀብት ዘራፊና የወንጀል ፈልፋይ ይሆናል። የነጻነት ባሕርይ ያልገባቸውና ነጻነትን የሚፈሩት እኩዩን የነጻነት ባሕርይ ለማፈን ሲሉ በጎውንም ባሕርዩን አብረው ይከረችሙታል። ምድረ አሜሪካ ሁለቱም የነጻነት ባሕርዮች በገሀድ የሚታዩበት ነው። በአሜሪካ ጉልበትና ገንዘብ ማናቸውንም ነገር የሚያነቃንቁ ኃይሎች ናቸው። እነዚህ ኃይሎች ሕጉን ቢያዶለዱሙትም በትክክል ይሠራል። ጉልበትና ገንዘብ ያላቸው ሁሉ የልማት እንቅስቃሴውን ብቻ ሳይሆን የዜና ማሰራጫዎቹን ሁሉ በቁጥጥራቸው ስር አድርገው የፈለጉትን ፖለቲከኛ የሚያነሡትና ወይም የሚጥሉት እነሱ ናቸው። 

 

Obamaዛሬ ደግሞ ቡሽን ለማንሳት የኦባማ መንፈስ በምድረ አሜሪካ ዓየር ላይ እያንዣበበ ነው። እንዲያውም ምድረ አሜሪካን አዳርሶ በመላው ዓለም እየተሰራጨ ነው፤ አዲስ ነገር የማያመልጣቸው ጃፓኖች ብዙ ነገሮችን ኦባማ የሚል መጠሪያ ስም እየሰጡ ነው ይባላል። የኦባማ መንፈስ አሮጊቶችና ሽማግሌዎች ልብ ውስጥ ገብቶአል፤ የኦባማ መንፈስ ወጣቱን አንቀሳቅሶታል፤ የኦባማ መንፈስ የታወቁ የኬኔዲ ቤተሰቦችን ይዟአል፤ የኦባማ መንፈስ የታወቀችውን የቴሌቪዥን ሰውና በጎ አድራጊ ኦፕራን ማርኮአል፤ በምርጫ ለመሳተፍ አስበውም የማያውቁ ሰዎች ሁሉ ዛሬ ለምርጫ ተሰልፈዋል። 

 

ይህ የኦባማ መንፈስ ከየት የመጣ ነው? ከእስያና ከአፍሪካ መንጭቆ በአሜሪካ የነጻነት ምድር ያበበና ያሸተ ነው። በጎ መንፈስ ከማይደርስበት ድርቅ መሬት መንጭቆ በደኀና ጊዜ የአሜሪካ ምድር የተቀበለውና በበጎው የነጻነት ባሕርይ የተኮተኮተ ነው።

 

የኦባማ መንፈስ ተልዕኮ ምንድን ነው? በደርግ ቋንቋ ልጠቀምና ሰፊውን ሕዝብ ቀሰቀሰው፤ ሰፊው ሕዝብ ፋይዳ እንዳለውና በምድረ አሜሪካ ትልቅ ልዩነትን ሊያመጣ እንደሚችል አሳመነው። ደሀዎች፣ አሮጊቶችና ሽማግሌዎች ከአሉበት ብዝበዛ ሊወጡ እንደሚችሉ የመንፈስ ኃይል ሰጣቸው፤ በአሜሪካ አነጋገር የአይጥ ፉክክር በሚባለው ውስጥ ገብተው ሲዳክሩ ሕይወት ፋይዳ የለውም ብለው ለሚንገዳገዱ ወጣቶች ዓላማና ምርኩዝን ሰጣቸው፤ በጉልበተኞችና በሀብታሞች እየተገፉና እየታመሱ ተስፋ የቆረጡትን የኢንዱስትሪ ሠራተኞች አዲስ ተስፋ ነዛባቸው። የአሜሪካ ሀብትና ጉልበት የደሀዎቹና የደካሞቹም እንደሚሆን የኦባማ መንፈስ አበሰረ። እስከዛሬ ለምርጫ ገንዘብ የሚለግሱት ጉልበትና ገንዘብ ያላቸው ነበሩ፤ ዛሬ ለኦባማ ከፍ ያለ ገንዘብ የሚያዋጣው ሰፊው ሕዝብ ነው፤ ስለዚህም ሰፊው ሕዝብ ሲተባበር ከሀብታሞቹ የበለጠ ሀብት፣ ከጉልበተኞቹ የተለጠ ጉልበት እንዳለው እያየ ነው።

 

ለሌላውስ ዓለም የኦባማ መንፈስ ምን ይዞ መጣ ይባላል? አሜሪካ በአራቱም ማዕዘናት ጉልበቱን የሚፈትንበትና የደሀዎችን ሕይወት የሚቀጥፍበት ሁኔታ ያበቃል፤ አሜሪካ የዓለም ሕዘቦች የጠሉበትን የውጭ አመራር - ስግብግብነትንና ጸረ-ዴሞክራሲነትን፣ በጉልበትና በሀብት ብቻ እየተማመኑ ደካሞችን ማጥቃት - ለማስቀረት ነው፤ በምትኩም የሰፊው አሜሪካ ሕዝብን ገርነት፣ ቸርነትና ሰላም ወዳድነት የሚያንጸባርቅ አመራር በመትከል አሜሪካ የሚወደድ እንጂ የሚጠላ አገር እንዳይሆን ለማድረግ ነው። በአሜሪካ ላይ የሚሰነዘረውን የሽብርተኞች ጥቃት በጥላቻና በጦርነት ሳይሆን በመግባባትና በፍቅር ለማሸነፍ መጣር ነው።

 

የኦባማ መንፈስ አብዛኛዎቹ የአሜሪካን ኃይሎች ነቅንቆአል፤ አስቆጥቶአል፤ አስደንግጦአል፤ እሥራኤልንም በስጋት ላይ ጥሎአል፤ ብዙ አምባ-ገነኖችንም እንቅልፍ ነስቶአል። በኦባማ መንፈስ ላይ ከባድ ዘመቻ ሳይደረግ አይቀርም።

 

(እግዚአብሔር አሸናፊ ያድርገው!)


 

(ምንጭ፦ እንቢልታ ጋዜጣ ቅጽ 1 ቁጥር 009)

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!