National Movement of Amhara (NAMA)

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)

የሰልፉ መከልከልና መደናቀፍ እያሟገተ ነው

ኢዛ (ማክሰኞ ጥቅምት ፲፯ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. October 27, 2020)፦ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ሕዝብ ላይ እየተፈጸመ ነው ያለውን “የዘር ፍጅት” ለማውገዝ በአዲስ አበባና በአማራ ክልል ሰላማዊ ሰልፎችን ለማካሔድ ያስተላለፈውን ጥሪ በኃላፊነት መምራት የማይችል መኾኑን አሳውቋል። የንቅናቄው ብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ዛሬ ማክሰኞ ጥቅምት 17 ቀን 2013 ዓ.ም. እስከ ምሽቱ 5 ሰዓት ድረስ ውይይት በማድረግ ባወጣው መግለጫ፤ “በመንግሥት አምባገነናዊ ተግባር ሰልፉን አስተባብሮ በተቋማዊ ማዕከላዊነት ለመምራት ባለመቻሉ” ሰልፉ መሰረዙን ገልጿል።

አብን ይህንን መግለጫውን ያስታወቀው ነገ ረቡዕ ጥቅምት 18 ቀን 2013 ዓ.ም. በአማራ ክልል እና ጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሰልፎቹን ለማካሔድ ይችል ዘንድ፤ ዛሬ በዋዜማው ስለሰልፎቹ ዝርዝር ሁኔታዎች በዋና ጽሕፈት ቤቱ የንቅናቄው ከፍተኛ አመራሮች እየመከሩ ባሉበት ሰዓት በአዲስ አበባ ፖሊስ ከበባ በመፈጸም አፈና ተደርጎብኛል ብሏል።

“የታቀደውን ሰልፍ በተቋማዊ ማዕከላዊነት ለመምራት እና ለሰልፉ የተዘጋጁ ሎጅስቲኮችን ለማንቀሳቀስም ኾነ ሰልፉን ለመምራት ሥራ አስፈጻሚው ወደ ክፍለ አገር እንቅስቃሴ ለማድረግ ተቸግሬያለሁ” የሚለው የአብን መረጃ፤ በዚህም የተነሳ አብን የጠራውን ሰልፍ በኃላፊነት መምራት የማችል መኾኑን ገልጿል።

በዚሁ መረጃው ላይ፤ “መንግሥት አማራ ማዘን እንኳን አይችልም በሚል እርቃን የወጣ አምባገነንነት ውስጥ ገብቷል” በማለት መንግሥትን ኮንኗል።

ከእኩለ ሌሊት ጥቂት ደቂቃዎች ቀደም ብሎ አብን ባወጣው መረጃ ላይ፤ አብን ጠርቶት የነበረውን ሰልፍ በመንግሥት አምባገነናዊ ተግባር ሰልፉን አስተባብሮ በተቋማዊ ማዕከላዊነት ለመምራት ባለመቻሉ መሰረዙን በመግለጽ፤ “ስለኾነም የንቅናቄያችን አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች አብን ሰልፉን የሰረዘ መኾኑን አውቃችሁ፤ ሰልፎችን ከማስተባበርና ከመምራት እንድትቆጠቡ እያሳወቅን፤ ቀጣይ የአብን የትግል አካሔዶችን በተመለከተ በቅርቡ የምናሳውቅ ይኾናል።”

አብን ይህንን የዛሬውን አቋሙን ካመላከተበት መረጃ ቀደም ብሎ፤ ትናንት የአማራ ክልላዊ መንግሥት አብን የጠራው ሰላማዊ ሰልፍ እውቅና የሌለው መኾኑን አስታውቆ ነበር። ለዚህም በአማራ ክልል መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ በኩል ሰፊ ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን፤ ሰልፉ እንዳይካሔድ አሳማኝ ናቸው ያላቸውን ነጥቦችን በማመላከት ነበር።

ይሁን እንጂ ይህ ሰልፍ ሊከለከልበት የሚችልበት ምንም ምክንያት አልነበረም በማለት የሰልፉን ክልከላ በመቃወም ብዙዎች ድምፃቸውን እያሰሙ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ በመንግሥት ደረጃ ሰልፉ እውቅና እንደማይሰጠው በመግለጽ ለክልከላው የጠቀሳቸው ምክንያቶች ትክክል ስለመኾኑም የሚገልጹ አሉ። በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ዘርን መሠረት አድርገው የሚፈጸሙ ጥቃቶች መወገዝ ያለባቸው ቢኾንም፤ እንዲህ ያለውን ሰልፍ በዚህ ሰዓት ማካሔዱ አግባብ አለመኾኑን እነዚሁ ወገኖች ያስረዳሉ።

በመንግሥት ደረጃ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል በንጹኀን ላይ የተፈጸመው ግድያ፣ መፈናቀልና የንብረት ውድመት ያስከተሉ አካላት ላይ እርምጃ በመወሰድ ላይ በመኾኑ፤ በአብን የተጠራው ሰልፍ ጊዜ ሊሰጠው ይገባ ነበር የሚሉም አሉ። በተለይ እንዲህ ያሉ ሰልፎች ቢካሔዱ ሌሎች ችግሮችን ሊያስከትል የሚችል በመኾኑ፤ የሰልፉ መቅረት ጠቀሜታ እንዳለው የሚሞግቱም አሉ።

ሰልፉን ለሌላ ዓላማ በማዋል ለሌሎች ችግሮች በር መክፈት በመኾኑ እጅጉንም ከአማራ ውጭ ያሉ የአማራ ተወላጆችን ደኅንነት ሥጋት ላይ የሚጥል ሁኔታ ሊፈጥር የሚችል መኾኑን የሚጠቅሱ ደግሞ፤ ዜጎች ድምፃቸውን በአደባባይ የመግለጽ መብት ቢኾንም፤ የሰላማዊ ሰልፉ መደረግን ጥቅምና ጉዳቱን ማመዛዘን ተገቢ ስለመኾኑ ያወሳሉ።

መንግሥት አብን ሰላማዊ ሰልፍ ለመጥራት ያበቃውን ተግባር ያልፈጸመ መኾኑ የሚታወቅ ቢኾንም፤ ነገር ግን የጥቃቱን መደጋገም እየተመለከተ መንግሥት ተገቢውን እርምጃ አለመውሰዱ ግን፤ አሁንም መንግሥት ሕግን ለማስከበር ጊዜ እየወሰደ (እያረፈደ) ነው የሚለውን አመለካከት ደግሞ ብዙዎች እያንጸባረቁ ነው።

በዚህ ሰልፍ ጥሪና መከልከል ዙሪያ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የተለያዩ አመለካከቶች እየተንሸራሸሩ ሲሆን፤ በተለይ ሰልፉ እንዳይካሔድ ከአማራ ክልል መንግሥት የተጠቀሱ ምክንያቶች አሳማኝ ያለመኾናቸውንና ድርጊቱ መብትን መጋፋት ነው የሚለው እየተሰማ ነው። በሌላ መንገድ ደግሞ ሰላማዊ ሰልፉን ፈቅዶ በሰልፎቹ ላይ ሊነሱ የሚችሉ ችግሮች ቢኖሩ ኃላፊነቱን ሰልፉን የጠራው አካል እንዲወስድ ማድረግ ይቻል እንደነበር የሚያመለክተውም ሐሳብ የዚህ አካል ነው።

በዚህ አወዛጋቢ ሁኔታ ውስጥ ደግሞ ሌላው ጥያቄ እየተነሳ ያለው ጉዳይ፤ በተለይ ሰሞኑን በጉራ ፈርዳ የተፈጸመውን ጥቃት በተገቢው መንገድ አለመወገዙም ትክክል እንዳልነበር እየተጠቆመ ይገኛል። በጥቅል ሲታይ ግን ከዚህ ሰልፍ መካሔድ እና አለመካሔድ እያስነሳ ያለው ጥያቄ ለመንግሥት ትልቅ የቤት ሥራ ሊኾን ይችላል የሚል እምነት ያላቸው ወገኖች፤ እንደ ሕወሓት ያሉ ቡድኖች ደግሞ፤ ከዚህ ሰልፍ ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን ውጥረት መጠቀሚያ ለማድረግ እየጣሩ ስለመኾኑ መረሳት የለበትም ይላሉ።

በርካቶች ይህንን ተደጋጋሚ ዘር ተኮር ግድያና ጥቃት መንግሥት ማስቆምም ኾነ መቆጣጠር አለመቻሉን አጥብቀው እየኮነኑ ሲሆን፤ የሕግ የበላይነት እንዲከበር፣ የዜጎች በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል በነፃነት የመኖር፣ ሠርቶ የማደር ሰብአዊ መብታቸው እንዲከበር እየጠየቁ ይገኛሉ። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ