ሕወሕት ታጣቂዎቹን የኤርትራ መከላከያ መለዮ በማልበስ “ኤርትራ ወራናለች” እያለ ነው

የኢንዶክትሪኔሽን ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል መሐመድ ተሰማ
መለዮውን ያመረተው በአልመዳ ጨርቃ ጨርቅ ነው
ኢዛ (ረቡዕ ኅዳር ፪ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. November 11, 2020)፦ ሕወሓት የኤርትራ መከላከያ ሠራዊትን መለዮ በአልመዳ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ በማምረትና ላደራጃቸው ታጣቂዎች በማልበስ፤ “ኤርትራ ወራናለች” በማለት ሕዝቡን እያደናገረ መኾኑን የመከላከያ ሠራዊት የኢንዶክትሪኔሽን ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል መሐመድ ተሰማ ዛሬ አስታወቁ።
ጄኔራል መሐመድ ተሰማ አክለው እንደገለጹት ከኾነ፤ መከላከያ ሠራዊቱ ሑመራና አካባቢውን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥሩ ሥር አውሏል። ከዚህም ሌላ በአሁኑ ሰዓት መከላከያ ሠራዊቱ ከሑመራ እስከ ሽራሮ ያለውን ቦታ በማጥቃት ላይ እንደሚገኝና የተለያዩ ቦታዎችንም በቁጥጥሩ ሥር እያዋለ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በእነዚህ ሠራዊቱ በቁጥጥር ሥር ባዋለቸው አካባቢዎች ላይ ለሚኖሩና ለተጎቹ ወገኖች ድጋፍ ማድረግ የሚፈልጉ ወገኖችና ድርጅቶች ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የመንግሥታ አካላት በማነጋገር እርዳታና ድጋፍ ማድረግ እንደሚችሉ ሜ/ጄኔራል መሐመድ ተሰማ ጠቁመዋል። (ኢዛ)