ማቴዎስ ዘገየ (ከስዊድን)

ብፁዓን ጳጳሳት
በ፳ኛው በአውሮፓ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ዓመታዊ ስብከተ ወንጌል ጉባዔ ላይ የተገኙ ብፁዓን ጳጳሳት

በዚህ በያዝነው የአውሮፓውያን በጋ ሐምሌ ወር፣ የሰከነ የሕይወት እንቅስቃሴና የረጋ ጸጥታ የሚታይባት፣ ከአውሮፓ ጽዱ ከተሞች አንዷ የሆነችው የስዊድን ዋና ከተማ ስቶክሆልም፤ ፳ኛውን በአውሮፓ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ዓመታዊ ስብከተ ወንጌል ጉባዔን በተሳካ ኹኔታ አስተናገደች።

በመላው አውሮፓ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች በየዓመቱ የሚዘጋጀው ይኸው መንፈሳዊ ጉባዔ ከሐምሌ (ጁላይ) ፲፬ እስከ ፲፮ ቀን ፳፻፲፯ እ.ኤ.አ. ድረስ ከተለያዩ የአውሮፓ ከተሞች የመጡ ምዕመናን፣ እንዲሁም ከአውሮፓ፣ ከአሜሪካና ከካናዳ የመጡ ብፁዓን ጳጳሳት በተገኙበት ነበር በተሳካ ኹኔታ የተካኼደው።

ምዕመናን
በስቶክሆልም በተካሄደው ፳ኛው በአውሮፓ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ዓመታዊ ስብከተ ወንጌል ጉባዔ ላይ ከተለያዩ የአውሮፓ አገራት የተገኙ ምዕመናን

ጉባዔውን በጸሎትና በቡራኬ የከፈቱት የአውሮፓ ምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የኾኑት ብፁዕ አቡነ ኤልያስ ሲሆኑ፣ በወጣው መርሃ ግብር መሰረት አቶ ጌታቸው ዋና በስቶክሆልም የመድኃኒአለም ቤተክርስቲያን ሰበካ ጉባዔ ም/ ሰብሳቢ ስለጉባዔው ይዘት ንግግር አድርገዋል። በመቀጠልም ከአውሮፓና ከተለያዩ አገራት የመጡት የደብር አስተዳዳሪዎች፣ እንዲሁም ከኢትዮጵያ የመጡ መንፈሳዊ መምህር የወንጌል ትምህት ሰተዋል። የተለያዩ መንፈሳዊ ዘማርያንም በግልና በጋራ መዝሙሮችን አቅርበዋል።

መዘምራን
በ፳ኛው በአውሮፓ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ዓመታዊ ስብከተ ወንጌል ጉባዔ ላይ የተገኙ መዘምራን

በተጨማሪም ባአለፉት ኹለት ዓመታት ተኩል በቂ ጥናትና ዝግጅት ተደርጎበት በበጎ ፈቃድ በተሰበሰቡ ወጣት መዘምራን የተዘጋጀው የመዝሙር ሲዲ በብፁህ አቡነ ኤልያስ ቡራኬ የተመረቀ ሲሆን፣ የሽያጩም ገቢ ሙሉ ለሙሉ አዲስ ለሚሰራው የመድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን ማሰሪያ መርጃ እንዲሆን ከመዘምህራኑ በስጦታ ተበርክቷል።

የመዝሙር ሲዲ
በወጣት መዘምራን የተዘጋጀውና በብፁህ አቡነ ኤልያስ ቡራኬ የተመረቀው የመዝሙር ሲዲ

እስከዛሬ በየአገራቱ ከተደረጉት ጉባዔዎች መካከል ያኹኑን ልዩ አድርጎታል ተብሎ ከተነገረለት ዝግጅት አንዱ፣ ከአሜሪካን እንዲመጡ የተጋበዙት መንፈሳዊ መምህራን ስዊድን ተወልደው ላደጉና ወጣት ኢትዮጵያውያን ልጆች ስለሚከተሉት የኦርቶዶክስ እምነት፣ ሥርዓትና ደንብ እነሱ በሚረዱት መልክና ቋንቋ መንፈሳዊ ትምህርት መሰጠቱ ነበር። ይህ ትምህርት ወጣቶቹ ስለኃይማኖታቸው በተገቢው ኹኔታ እንዲያውቁ የረዳ ሲሆን፣ ትምህርቱ እጅግ የተደሰቱበት እንደነበር ታውቋል። ወጣቶቹ በሃሳባቸው ሲጉላሉ የነበሩ ጥያቄዎችንም ጠይቀው መልስና ማብራሪያ አግኝተዋል። ከጥያቄዎቻቸው መካከል "በኦርቶዶክስ ኃይማኖት ውስጥ የሴት ቄሶች ለምን አይኖሩም?" የሚለው አንዱ የነበረ ሲሆን፤ ለዚሁም በኃይማኖቱ ደንብ መሰረት መልስ ተሰጥቷቸዋል።

ብፁዓን ጳጳሳት
በስብከተ ወንጌሉ ጉባዔ ላይ የተገኙ ብፁዓን ጳጳሳት ትምህርት ሲሰጡ

የጉባዔው መዝጊያ በሆነው የመጨረሻው ቀን በሰንበተ እሁድ በመድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን ከተለያዩ አህጉራት በመጡ ጳጳሳት በተካሄደው የቅዳሴ ሥርዓት ላይ በፊት በቋሚ ሲኖዶስ ምላዐተ ጉባዔ በተወሰነው መሰረት ብፁዕ አቡነ ኤልያስ የአውሮፓ ምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የበላይ ጠባቂ ረዳት እንዲሆኑ ለመልአከ ብሥራት ቆሞስ አባ ሀብተ እየሱስ ለገሠ የኤጴስ ቆጶስ ማዕረገ ሹመት ተሰጥቷል።

ማዕረገ ሹመት ሲሰጥ
ብፁዕ አቡነ ኤልያስ ለመልአከ ብሥራት ቆሞስ አባ ሀብተ እየሱስ ለገሠ የኤጴስ ቆጶስ ማዕረገ ሹመት ሲሰጡ

ይኸው ከተለያዩ የአውሮፓ ከተሞች ቁጥራቸው እጅግ በበዛ መዕምናን እና አባቶች ሲካሄድ የቆየው ጉባዔ እንደመክፈቻው ሁሉ መዝጊያውም እጅግ የተዋጣና የደመቀ ሲሆን፣ የተለያዩ የአቋም መግለቻዎችም አውጥቷል። ለዚህ ስዊድን ላዘጋጀችው ጉባዔ መሳካት ለደከሙ ለቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪዎች፣ መዕምናንና ጥሪውንም ተቀብለው ለመጡ ሊቀ ጳጳሳትና የደብር ኃላፊዎች ለካህናትና ለመዘምራን የቤተ ክርስቲያንዋ አስተዳዳሪ መልአከ ፀሐይ አበበ ገላው ምርቃትና ምስጋና አቅርበዋል።

ብፁዓን ጳጳሳት
በ፳ኛው በአውሮፓ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ዓመታዊ ስብከተ ወንጌል ጉባዔ ላይ የተገኙ ብፁዓን ጳጳሳት

በመጨረሻም ለቀጣዩ ዓመት ልዑል እግዚአብሔር በጤና፣ በሰላምና በፍቅር ጠብቆ እንዲያደርሰን በመመኘት፤ ጉባዔው በብፁዕ አቡነ ኤልያስጸሎተ ቡራኬ ተጠናቋል።

ምዕመናን
በስቶክሆልም በተካሄደው ፳ኛው በአውሮፓ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ዓመታዊ ስብከተ ወንጌል ጉባዔ ላይ ከተለያዩ የአውሮፓ አገራት የተገኙ ምዕመናን

ሰላም ለሁላችሁም ትሁን!!

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!