ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች
እንኳን ለ1442ኛው የረመዳን ወር በሰላም አደረሳችሁ! ረመዳን ሙባረክ!
ኢትዮጵያ ዛሬ

አቶ ሙስጠፌ መሐመድ ዑመር፣ ፕሮፌሰር ዶ/ር ሲሳይ መንግሥቴ፣ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና እና አቶ ሚሊዮን አብርሃ

(ከግራ ወደቀኝ) አቶ ሙስጠፌ መሐመድ ዑመር፣ ፕሮፌሰር ዶ/ር ሲሳይ መንግሥቴ፣ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና እና አቶ ሚሊዮን አብርሃ

“ግንቦት 20 ለሶማሌ ሕዝብ ካስገኘለት ጥቅም ይልቅ፤ ጉዳቱ ያመዝናል” አቶ ሙስጠፌ መሐመድ፣ የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር

ኢዛ (ሐሙስ ግንቦት ፳ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. May 28, 2020)፦ ግንቦት 20 ቀን ለማሰብ ትናንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድና የትግራይ ክልላዊ መንግሥት (ሕወሓት) ከሰጡት መግለጫ ባሻገር፤ የተለያዩ ክልሎችና ታዋቂ ሰዎች የተሰጡ መግለጫዎች የተለያዩ ምልክታዎች የታዩባቸው ሲሆን፤ ከቀድሞ የውዳሴ ጋጋታ ወጣ ያሉም ኾነው ተገኝተዋል። የኢትዮጵያ ዛሬ ድረገጽ ዝግጅት ክፍልም እነዚሁን የተለያዩ ምልከታዎች ለመዳሰስ ሞክሯል።

በዛሬ ዕለት (ግንቦት 20 ቀን 2012 ዓ.ም.) 29ኛ ዓመት የሞላውንና በአገር አቀፍ ደረጃ በበዓልነት እንዲከበር በገዥው ፓርቲ ተወስኖ የነበረውን የግንቦት 20 በማስመልከት መግለጫ ከሰጡት ውስጥ የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የኾኑት አቶ ሙስጠፌ መሐመድ ዑመር አንዱ ናቸው። አቶ ሙስጠፌ ይህንን ቀን፤ “ግንቦት 20 ለሶማሌ ሕዝብ ካስገኘለት ጥቅም ይልቅ፤ ጉዳቱ ያመዝናል” በማለት ነበር የገለጹት።

የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ፤ በሶማሌ ሕዝብ ላይ በታሪኩ ተፈጽሞበት የማይውቀ ግፍ፣ ግድያ፣ መንገላታት አድርሶበታል በማለት ገልጸው፤ በተደራጀ መልኩ ሕዝባችንን የማዋረድ ሥራ ተሠርቷል በማለት ተናግርዋል።

ግንቦት 20 ለሶማሌ ክልል ሕዝብ በቋንቋው ከመማርና ራሱን በራሱ ከማስተዳደር መብት ካስገኘለት ጥቅም ይልቅ፤ ከፍተኛ የኾነ የሰብአዊ መብት ጥሰትና የጸጥታ ችግር በመፍጠር መጥፎ አሻራ ማሳረሩን በመጥቀስ ግንቦት 20ን አስታውሰዋል።

የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ደግሞ በአንድ ቡድን የሥልጣን ስስት በአገሪቱ ባለፉት 27 ዓመታት በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባለመገንባቱ፤ ለግንቦት 20 ድል የተከፈለው መሥዋእትነት ሊመክን ስለመቻሉ ገልጸዋል።

በዛሬው ዕለት ለተለያዩ የመገናኛ ብዙኀን ስለግንቦት 20 ሐሳባቸውን ካጋሩት መካከል ረዳት ፕሮፌሰር ዶ/ር ሲሳይ መንግሥቴ አንዱ ናቸው። እንደ ፕ/ር ዶ/ር ሲሳይ ገለጻ፤ ግንቦት 20 ብሔራዊ በዓል ተደርጎ መከበር የለበትም የሚል እምነት አላቸው።

ግንቦት ሃያ በአሁኑ ወቅት የሚታዩ አለመግባባቶችና ግጭቶች ባለፉት ዓመታት ሲደረግ የነበረው የመከፋፈል ፖለቲካዊ ውጤት ነው ብለው ያምናሉ።

የፕ/ር ዶ/ር ሲሳይን ሐሳብ የተጋሩት የብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካን ርዕዮተ ዓለም ቢሮ ኃላፊ የኾኑት አቶ ሚሊዮን አብርሃ፤ ግንቦት ሃያ ሁሉም ኢትዮጵያውያንን ከአምባገነን ሥርዓት ለማላቀቅ ዋጋ ከፍለው ለድል የበቁበት ዕለት ቢኾንም፤ ለሁለት አሥርት ዓመታት ሲከበር ከአንድነት ይልቅ አሸናፊና ተሸናፊነትን በሚሰብክ መልኩ መኾኑን ኮንነዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!