የትራንስፖርት አገልግሎት መ/ቤት ከታክሲ ባለንብረቶችና አሽከርካሪዎች ጋር እየተወያየ ነው
ሾፌሮችና ተራ አስከባሪዎች አደጋ ላይ ናቸው
Ethiopia Zare (ሰኞ ነሐሴ 11 ቀን 2001 ዓ.ም. August 17, 2009)፦ በዋና ከተማ አዲስ አበባ ነዋሪውን ህዝብ እየገጠመው ያለውን ችግር ለማስወገድ በሚል የትራንስፖርትና መገናኛ መ/ቤት ከታክሲ ባለንብረቶችና አሽከርካሪዎች ጋር ውይይት ማካሄዱን የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገለጹ።
ይኽው ውይይት የሚቀጥል መሆኑን ከታክሲ ባለንብረቶችና አሽከርካሪዎች ያገኘነው መረጃ አመልክቷል። ሐሙስ ነሐሴ 7 ቀን 2001 ዓ.ም. በትራንስፖርትና መገናኛ መ/ቤት አምቼ ኩባንያ አጠገብ ከባለሥልጣኖች ጋር መወያየታቸውን የገለፁልት ምንጮች፤ “መንግሥት የታክሲ ስምሪትን ከ1975 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ወታደራዊው ሥርዓት ውድቀት ድረስ ሲሠራበት ወደነበረው የቀጠና ስምሪት ለመለወጥ ውሳኔ ላይ መድረሱን ለመረዳት ችለናል።
ከቅርብ ጊዜ በኋላ ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ በሚጠበቀው አዲስ የቀጠና ድልድል መሠረት የአዲስ አበባ ከተማ ታክሲዎች በአንድ የመዲናይቱ ክፍለ ከተማ ውስጥ በአምስት ልዩ ልዩ የጉዞ መስመሮችና በሦስት ምድብ ቀጣናዎች ይደለደላሉ። በዚህም መሠረት ከዚህ ቀደም በየሁለት ኪሎ ሜትሩ እና በየመንደሩ ቆመው ለአሽከርካሪዎችና ለተሣፋሪዎች አስቸጋሪ ሆነው ነበር የተባሉት ተራ አስከባሪዎች ከሥራ ውጪ ይሆናሉ። አገልግሎት የሚሰጡትም ታክሲዎች የስምሪት ቀጠና መለያ ታፔላን ለጥፈው በየመሥመራቸው ይንቀሳቀሳሉ። ታክሲዎቹ በመነሻና በመድረሻ ጣቢያቸው ከሚገኙ የቁጥጥር ኬላዎች የንቅናቄ ፈቃድ ደረሰኝ እየተቀበሉ ተሳፋሪዎቻቸውን የሚጭኑ ሲሆን፣ ተራቸው ካልደረሰ በቀር ከመነሻም ሆነ ከመድረሻ ጣቢያቸው እንዲነቃነቁ አይፈቀድላቸውም።
የትራንስፖርትና መገናኝ መሥሪያ ቤቱ የታክሲ ስምሪት ዕቅድ ተግባራዊ ሲሆን፣ አሽከርካሪዎች የምድብ ቀጠና ሠራተኞች መሆናቸውን የሚያረጋግጥ መለያ ባጅ በደረታቸው ለመለጠፍ ወይም ለማንጠልጠል ይገደዳሉ። የታክሲ ባለንብረቶችና አሽከርካሪዎች ልዩ የኮንትራት ሥራ በሚያገኙበትም ጊዜ በየቀጠናው ከተሰየሙ የስምሪት ተቆጣጣሪዎች ፈቃድ መጠየቅ ይኖርባቸዋል።
ከባለንብረቶችና ከአሽከርካሪዎች ጋር የተደረገው የሰሞኑ ውይይት ይሄንኑ ዕቅድና መመሪያ ለማሳወቅ ሲሆን፣ የታክሲ ባለንብረቶችና አሽከርካዎች ግን የቀጠና ስምሪቱን ያልወደዱትና በነፃ ተዘዋውረው የመሥራት መብታቸውን የገደበ በመሆኑ አምረው እንደሚቃወሙት ተናግረዋል። ይሁን እንጂ በአዲስ አበባ ትራንስፖርት ተጠቃሚው ኅብረተሰብ በባለታክሲዎች መስመር የማቆራረጥ ድርጊት መከፋቱ እውነት ነው።



