በምዕራብ ሸዋ ገበሬው ለማዳበሪያ ግዢ የእርሻ በሬዎችን ለመሸጥ ተገደደ
Ethiopia Zare (ሐሙስ ነሐሴ 14 ቀን 2001 ዓ.ም. August 20, 2009)፦ በምዕራብ ሸዋ አንቦ አቅራቢያ በሚገኘው ዳንዲ ወረዳ የሚገኙ ገበሬዎች ከአዝመራው ጊዜ ቀደም ብሎ ማዳበሪያ ባለማግኘታቸው በሬዎቻቸውን ለመሸጥ መገደዳቸውን የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ጠቆሙ።
የዞኑ እና የወረዳው ሹማምንቶችና የግብርና ባለሙያዎች ከማዳበሪያ አቅራቢ ነጋዴዎች ጋር በመመሳጠር ገበሬው ከዘር ወቅት በፊት ማዳበሪያ እንዳያገኝ ከማድረጋቸው የተነሳ፤ ከሥፍራው የተገኘው መረጃ እንዳመለከተው በአዝመራ ጊዜ የማዳበሪያ ችግር የገጠመው የዳንዲ ወረዳ ገበሬ በከፍተኛ ዋጋ የገዛቸውን የእርሻ በሬዎች በርካሽ ዋጋ በመሸጥ ከገበያ የጠፋውን ማዳበሪያ ካለበት ሥፍራ በውድ ለመሸመት ተገድዷል። አንዳንድ የዳንዲ ወረዳ ገበሬዎች “እስከ አንድ ሺህ ሁለት መቶ ብር የገዛናቸውን በሬዎች ማዳበሪያ ለማግኘት ስንል በርካሽ ዋጋ ለመሸጥ ተገደናል” ብለዋል።
በአቅራቢያቸው ማዳበሪያ ለማግኘት ባለመቻላቸው ማዳበሪያ ፍለጋ ብዙ ርቀት ተጉዘናል የሚሉት ገበሬዎች፤ “መንግሥት ግን ገበሬው ባለበት በተገቢው ጊዜ ማዳበሪያ አቅርበናል፣ በዚህም ገበሬው ተጠቃሚ ሆኗል … በማለት የሐሰት ዜና እየተሠራጨብን ነው …” በማለት ቅሬታቸውን ገልጸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በዚያው በምዕራብ ሸዋ “እልፈታ” የተባለ ወረዳ ውስጥ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ተጐጂ ለሆኑ በሺህ የሚቆጠሩ ዜጐች የማዕከላዊው መንግሥትም ሆነ “ጨፌ ኦሮሚያ” ተብሎ የሚጠራው የክልሉ መንግሥት ም/ቤት ትኩረት እንዳልሰጠው የኦሮሞ ህዝብ ኮንግረስ ፓርቲ አባላት ለምንጮቻችን የገለጹ ሲሆን፤ እነሱ እንዳሉት የወረዳው ህዝብ በድርቅ ምክንያት ለረሃብ ተጋልጧል።



