Ethiopia Zare (ሐሙስ ነሐሴ 14 ቀን 2001 ዓ.ም. August 20, 2009)፦ አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሰኞ ዕለት ነሐሴ 11 ቀን 2001 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ ላይ እንዳለው የናዝሬቱ ህዝባዊ ስብሰባ የተበጠበጠው “የክልሉ ቋንቋ፣ ወግና ባህል ባለመከበሩ” ሳይሆን የተደራጁና ሆን ብለው ረብሻ የመፍጠር ዓላማ ባላቸው በኦህዲድ የተደራጁ ኃይሎች ነው።

 

በአንድነት ፓርቲ አባባል መሠረት “የኦሮሞ ህዝብ የሌሎች ወገኖቹን ድምፅ በቋንቋቸው ጭምር የማድመጥ የተከበረና ተወዳጅ ባህል ያለው ቢሆንም” የኦህዲድ (የኦሮሞ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት) ኹከት ፈጣሪ ስብስቦች “በቋንቋችን የሚካሄድ ስብሰባ ካልሆነ በቀር በነፍጠኞች ልሳን የሚካሄደውን ማናቸውም ዓይነት ጉባዔ የመሣተፍ ፍላጐት የለንም፤ ይህ ስብሰባ በክልላችን በኦሮሚያ እንዲካሄድ አንፈቅድም …” በማለት በናዝሬት አዳማ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ሰኔ 10 ቀን 2001 ዓ.ም. ተጀምሮ የነበረውን ህዝባዊ ስብሰባ በመበጥበጥ እንዲታወክ አድርገዋል።

 

የኦህዲድ ኢህአዲግ ካድሬዎች እና “የኦሮሞ ህዝብ ነፃነትና መብት ተቆርቋሪ ነን” የሚሉ ግለሰቦች “ነፍጠኛ በምድራችን ላይ አይንቀሳቀስም፣ ለነፍጠኞች አሳልፎ የሸጠንን ነጋሶን ማየት አንፈልግም፣ ሴት ልጅ በመድረክ ላይ ወጥታ ንግግር ማድረጓ የኦሮሞን ባህልና ህዝብ መናቅ ነው፣ ነፍጠኞች በአማርኛ ቋንቋ አንሰማችሁም! ውጡልን! …” በማለት በጩኸትና በፉጨት ጭምር ተጀምሮ የነበረውን ህዝባዊ ስብሰባ አውከዋል።

 

በዕለቱ በሥፍራው የክብር እንግዳ ሆነው ተገኝተው የነበሩትን የቀድሞውን የሀገሪቱን ፕሬዝዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳን፣ የቀድሞውን የመከላከያ ሚኒስትር አቶ ስዬ አብርሃን፣ እንደዚሁም ፕሮፌሠር በየነ ጴጥሮስን በኃይለ ቃል ተናግረዋል፣ ዘልፈዋል፣ ፀያፍ ስድብ ተሳድበዋል፣ ለመማታትና ለማስፍራራትም ቃጥተዋል የኦህዲድ ልጆች በአዳማ።

 

ከዚህ ድርጊት በኋላ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በሰጡት ምጥን ያለ አስተያየት በተፈጠረው አስነዋሪ ድርጊት በእጅጉ መናደዳቸውንና ከልብ ማዘናቸውን ገልጸው፤ “አንድ ስብሰባ ሲከፈት በአካባቢው ህዝብ ባህልና ወግ መሠረት ቢሆን የተሻለ እንደሚሆን እምነቱ አለኝ። ነገር ግን አማርኛ የሀገሪቱ የሥራ ቋንቋ መሆኑ እስከታወቀና በናዝሬትም ቋንቋውን የማይሰማ ሰው እንደሌለ ግልጽ ሆኖ ሳለ፤ ያን ያህል ከኦሮሞ ህዝብ የማይጠበቅ ሥነ-ምግባር ከኦህዲድ ሰዎች በኩል መመልከቱ በሀገሪቱ ሕገ-መንግሥት መጣሱን አስገንዝቦኛል …” ብለዋል።

 

ስብሰባው የተስተጓጐለበት አንድነት ፓርቲ በመግለጫው “የፖለቲካው ሜዳ መጥበብ ሳይሆን ተዳፍኗል” ሲል፤ ስብሰባውን ፈቅጃለሁ፤ ከዚህ ያለፈ ምን ማድረግ ነበረብኝ? በማለት ራሱን የሚጠይቀው የናዝሬት ከተማ ም/ቤት ከንቲባ አቶ ሲሳይ ነጋሽ በበኩላቸው፤ “የኦህዲድ አባላት ረብሸዋል መባሉ ሐሰት ነው። አንድነቶች በአዳማ ድጋፍ አልነበራቸውም። የተበጣበጡትም የራሳቸው ደጋፊዎች ናቸው” የሚል መልስ ሰጥተዋል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ