ለመጀመሪያ ጊዜ ታላላቅ ሠዓሊያን ሥራዎቻቸውን ሊያቀረቡ ነው
Ethiopia Zare (ሐሙስ ነሐሴ 21 ቀን 2001 ዓ.ም. August 27, 2009)፦ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያላቸው የተከበሩ ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌን ጨምሮ ታላላቅ ሠዓሊያን በዘመነ ኢህአዲግ ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድ ላይ ኤግዚቢሽን ሊያቀርቡ ነው።
ከፊታችን ነሐሴ 27 ቀን 2001 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. ከሴፕቴምበር 2) ጀምሮ ለ6 ተከታታይ ቀናት በሸራተን አዲስ ኤግዚቢሽኑ የሚቀርብ ሲሆን፣ በኤግዚብሽኑ ላይ ሥራቸውን ከሚያቀርቡት እውቅ አርቲስቶችም ውስጥ አለፈለገ ሠላም፣ አብዱራህማን ሸሪፍ፣ ወርቁ ማሞ፣ ወርቁ ጎሹ፣ ታደሰ በላይነህ፣ ዘሪሁን የትምጌት፣ እሸቱ ጥሩነህ፣ ዮሐንስ ገዳሙ፣ ደስታ ሐጎስ፣ ታደሰ መስፍን፣ ተሾመ በቀለ፣ ጥበበ ተርፋ፣ ልዑልሰገድ ረታ፣ መዝገቡ ተሰማ፣ ብስራት ሸባባው፣ ደምሴ ጉርሙ ከአንጋፋዎቹ፤ አብያለው አሰፋ፣ ዳንኤል ታዬ፣ ግዛቸው ከበደ፣ ዳዊት አበበ እና ሌሎችም ወጣት አርቲስቶች በመሰባሰብ ነው ሥራቸውን የሚያቀርቡት።
“የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ 2009” በሚል ርዕስ የሚቀርበው የ3 ትውልዶች ጥምረት ያለበት ይኸው ኤግዜብሽን በኢህአዲግ ዘመን ተደርጎ የማያውቅ ታላቁ አውደ ራዕይ እንደሆነ ተነግሯል።
በዘመነ ደርግ 55 አንጋፋ ሠዓሊያን በጋራ በ1980 ዓ.ም.፣ እንዲሁም በመጋቢት 1983 ዓ.ም. 100 ሠዓሊያን በሕይወት ያሉና የሌሉ በብሔራዊ ሙዚየም ሥራዎቻቸውን ማቅረባቸው የሚታወስ ነው።



