ኢህአዲግ ከተቃዋሚዎች ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን ገለጸ
Ethiopia Zare (ቅዳሜ ነሐሴ 23 ቀን 2001 ዓ.ም. August 29, 2009)፦ በመጪው ሰኞ ነሐሴ 25 ቀን 2001 ዓ.ም. የኢትዮጵያው ገዢ ፓርቲ (ህወሓት/ኢህአዲግ) በሀገር ውስጥ አሉ ከሚባሉት “ዋንኛ” የሚባሉ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች ጋር ውይይት እንደሚያካሂድ ተገለጸ።
በ2002 ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው ምርጫ አጀንዳ እና ከዚህም ጋር ጉድኝት ይኖረዋል ከሚሉት “የፓርቲዎች የሥነ-ምግባር መርሆ” ላይ ውይይት ለማካሄድ የተነሳው ገዥው ፓርቲ በምክር ቤት ጸሐፊው በአቶ ሙክታር ከድር ፊርማ “የእንወያይ” ደብዳቤ ለተቀናቃኞቹ መላኩ ታውቋል።
የምዕራባውያን ሀገራት ግፊት እና ዲፕሎማሲያዊ ጫና እየበረታ መምጣቱን የገለጹት የዜናው ምንጮች፤ አገዛዙ ተቃዋሚዎችን ከጨዋታው ሜዳ ውጭ ለማድረግ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ላይ ቢሆንም የዲፕሎማቶች ጥረትና ጫና እየበረታ መምጣቱን ገልጸዋል።
ምንጮች ኢህአዲግ ከሚንቃቸውና ከሚጠየፋቸው ተቀናቃኞቹ ጋር ለመደራደር ብዙዎቹ አውሮፓውያን መሆናቸው በሚታወቀው “የኢትዮጵያ ወዳጆች ቡድን” በኩል መጎትጎቱን ጠቁመው፤ ከጉትጎታው በኋላ ገዥው ፓርቲ መልካም ፈቃዱን ያሳየ ቢሆንም፤ “ድርድሩን ለማካሄድ ምን ያህል ቁርጠኛ መሆኑን ለመናገር አልደፈሩም።
በወይይቱ “መድረክ” ተብሎ የተቋቋመው አዲስ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የታዋቂ ግለሰቦች ስብስብ ተሳትፎ ሊያደርግ እንደሚችል የተገመተ ሲሆን፣ በጋራ ድርድሩ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።



